ለሰላምና ዴሞክራሲ መሠረቱ ብሄራዊ መግባባትና የሁሉም ባለድርሻዎች ተሳትፎ ነው

ኅዳር 8፣ 2010 (November 17, 2017)

በሀገራችን በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የተፈጠሩ ሁኔታዎችን በትክክል መጠቀም ባለመቻሉ ከአምባገነን አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር አልተቻለም። ከአንድ አምባገነን ወደሌላ አምባገነን አገዛዝ ስንሸጋገር ቆይተን እነሆ አሁን ከምንገኝበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። በመሆኑም አምባገነንነት ሰፍኖ የሕዝባችን ስቃይና መከራ እንደቀጠለ ነው።

የቅርብ ጊዜ እውንታን ስንመረምር በኮሎኔል መንግሥቱ ይመራ የነበረው አገዛዝ ከሥልጣን በተወገደ ጊዜ ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ባለብዙ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር እጅግ ሰፊ አጋጣሚ እንደነበራት ነው። ሆኖም  በወቅቱ  ሥልጣኑን  አዲስ  አባባና አሥመራ ላይ የተቆጣጠሩት ህወሓት፣ ኦነግና ሻአቢያ ሌሎች የተደራጁ ኢትዮጵያውያንን በሰበብ በአስባቡ በሽግግሩ ሂደት ውስጥ እንዳይሳተፉና ሕዝብ የሚተዳዳርበትን ሕገ-መንግሥት በመቅረጽ ደረጃ ድርሻ እንዳይኖራቸው አድርገው ብዙሃኑን ባገለለ መልክ ለብቻቸው በፈጠሩት አገዛዝ ሕዝብን ለቀጣይ ስቃይ፣ ለመብት ረገጣና ለከፍተኛ ግፍ ዳረጉት።

ህወሓት-መራሹ አገዛዝ ለኢትዮጵያውያን ቃል የገባው የዴሞክራሲ መብት  መከበር፣ የፍትኅ መስፈን፣ እኩልነት፣ በነፃ የመደራጀት መብት መከበር፣ ሰላምና ብልጽግና፤ የራስን መንግሥት የመምረጥ መብት…ወዘተ፣ ከ26 ዓመታት በኋላ ዛሬም መጨበጥ የማይቻል የህልም እንጀራ ሆነው ቀርተዋል። አገዛዙ ከዴሞክራሲ አቀንቃኝነት ርቆ በዓለም ውስጥ ቀንደኛ ከሆኑት ፀረ-ነፃ ፕሬስ አገዛዞች ውስጥ አንዱ ሆኗል።

ይህ የሆነው አገዛዙ ገና ከመሠረቱ የአምባገነንነት መሠረት ይዞ በመነሳቱና አግላይ ሆኖ ስለተመሠረተ ነው። ሕዝባችን በሰጥቶ-መቀበልና በብሄራዊ መግባባት ሂደት የሚተዳደርበትን ሕገ-መንግሥት ለመቅረጽ ከመጣር ይልቅ የህወሓትን ድርጅታዊ አጀንዳ በሕገ-መንግሥት ስም እንዲጸድቅ ስለተደረገ ሕዝብ ገና ከጅምሩ የኔ  ብሎ አልተቀበለውም። የዛሬ 26 ዓመት የተፈጠረው ስህተት የሕዝባችንን ስቃይ  ማባባሰ  ብቻ ሳይሆን የሀገራችንንም ህልውና አጠያያቂ ደረጃ ላይ አድርሷል።

ከ26 ዓመታት የግፍ አገዛዝ  በኋላ  እነሆ  ሕዝቡ  ጭቆና  በቃኝ  ብሎ  ለሥርዓት  ለውጥ  አምርሮ እየታገለ ሲሆን አገዛዙም ክንዱ እየዛለ ነው።  የሕወሓት/ኢህአዴግ  አገዛዝ  በብዙ  ሕዝብ እጅግ የተጠላ አገዛዝ ነው። በመሆኑም ዛሬ በመላ ሀገሪቱ የከፋ ተቃውሞ ወጥሮ  ይዞታል። ህወሓት-መራሹ አገዛዝ አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል እንደማይችል ግልጽ

 

ሆኗል። አሁን ያለው ጥያቄ የአገዛዝ መወገድ አለመወገድ ሳይሆን መቼ? የሚለውና ወደ ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት  እንድንሸጋገር  የሚረዳ  መሠረት  እንጥል   ይሆን?   የሚሉት  ጥያቄዎች በብዙዎች ኣእምሮ ውስጥ ይመላለሳሉ።

በሸንጎ አመለካከት ከህወሓት-መራሹ አምባገነን አገዛዝ ወደ ሕገ-መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት  ለመሸጋገር  ሀገራችን  የሽግግር   ሥርዓት   ያስፈልጋታል።   ይህ የሽግግር ሂደትም  ካሁን  በፊት  ከተሠሩት  ስህተቶች  ትምህርት  መውሰድ  እንጂ  ያንኑ  ስህተት መድገም የለበትም፡፡  በመሆኑም  አግላይነት  ቦታ  ሊኖረው  አይገባም።  የሽግግሩ  ሂደት  ሁሉንም  ባለድርሻዎች  አሳታፊና  የተለያዩ  አመለካከቶች  ያላቸው   ኢትዮጵያውያን  ሁሉ  የሚወከሉበት  ሊሆን  ይገባል።  የሽግግር  ሂደቱ  በባለድርሻዎች  ስምምነት  ላይ  ተመርኩዞ ነፃና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ በአጭር ጊዜ  ውስጥ  የሚካሄድበት፣  የሕዝብን  ፈቃድ ያገኘ ድርጅትም የመንግሥት ሥልጣን የሚይዝበት ሂደት ሊሆን ይገባዋል።

በተደጋጋሚ እንደገለጥነው የሸግግር ሂደቱን እውን ለማድረግ ተመራጭ የሚሆነው ሁሉንም ባለድርሻዎች አሳታፊ የሆነ ድርድር በማካሄድ ነው። ይሁን እንጂ ህወሓት-መራሹ አገዛዝ በተቃዋሚነት ከተሰለፉ ድርጅቶች ውስጥ  “መረጋጋትን  ሊያሰገኙ  ይችላሉ“  ብሎ ከገመታቸው ድርጅቶች ጋር በቅርቡ የፖለቲካ ድርድር  ማካሄዱ  በስፋት  ተወርቷል።  ይህ  አካሄድ ከ26 ዓመት በፊት ሀገራችንን ወደ መገነጣጠልና ወደባሰ ምስቅልቅል ውስጥ ያሰገባ   የጎሳ ፖለቲካን በሕዝባችንና በመላ ሀገሪቱ ላይ በጉልበት  እንዲጫን  ያደረገውን  አገዛዝ  ምሥረታ ያስታውሰናል።

ኢትዮጵያ ከ26 ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ስህተት መፈጸም አትችልም፣ ሕዝባችን በድጋሚ በአግላይነት ላይ የተመሠረተ ሌላ አምባገንን አገዛዝን ማስተናገድ አይችልም። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ብሄራዊ መግባባትና የሁሉን አቀፍ ሥርዓት ምሥረታ ነው። ስለሆነም የሕዝባችንን ትግል ወደኋላ የሚወስድን የአግላይነት አደጋ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊያወግዙት ይገባል።

ሀገራችን የገባችበትን ምስቅልቅል ፖለቲካ እፍኝ በማይሞሉ ድርጅቶች ምክክር የሚፈታ አይደለም። ማንኛውም ድርጅት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የበላይነት የለውምና። ስለዚህ በጋራ ሀገራችን ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ አማራጩ ሁሉንም አሳታፊ የሆነን የሽግግር ሂደት እውን ማድረግ  ነው። ለዚህም  ተቃዋሚዎች  ሁሉ በአንድነት መቆምና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ የሚካሄደውን የሕዝብ ትግል በመደገፍና በማጠናከር በድርድርም ሆነ በሽግግር ጊዜ አሳታፊ የሆነ  ሥርዓት  መከተል  እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሸንጎ በአንክሮ እየገለጸ የድርሻውን ለማበርከትም ዝግጁነቱን ያረጋግጣል።

ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነት ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.