አቶ በረከት ስምዖን ከጀርባ ሆነው ብአዴንን እየመሩ እንደሚገኙ ታወቀ

ስልጣን እንደለቀቁ የተነገረላቸው አቶ በረከት ስምዖን ከጀርባ ሆነው ብአዴንን እየመሩ እንደሚገኙ ታወቀ፡፡ የአቶ አባዱላ ገመዳን የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ ማስገባት ተከትሎ በተወሰኑ ቀናት ልዩነት ስልጣን እንደሚለቁ አስነግረው የነበሩት አቶ በረከት፣ የስልጣን መልቀቂያቸው ተቀባይነት ማግኘቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር ተገልጾ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ከወር በፊት ፓርላማ በተገኙበት ወቅት፣ የአፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ጥያቄ በይደር ተይዞ፣ የአቶ በረከት ጥያቄ ግን ተቀባይነት ማግኘቱን ገልጸው ነበር፡፡

አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንዳመለከቱት ግን፣ የብአዴን ከፍተኛ አመራር የሆኑት (እንደ መንግስት አገላለጽ ስልጣን የለቀቁት) አቶ በረከት ስምዖን፣ በፓርቲያቸው ውስጥ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ ሰውዬው በአደባባይ ስልጣን መልቀቃቸው ይነገር እንጂ፣ ብአዴንን እያሾሩ ከሚገኙት ሁለት ግለሰቦች አንዱ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህ ቀደም ሰልጣን መልቀቃቸው የተነገረላቸው የብአዴን ነባር አመራር አቶ አዲሱ ለገሰ አንደኛው የብአዴን አንቀሳቃሽ ሲሆኑ፣ በቅርብ ጊዜ ስልጣን ለቅቂያለሁ ብለው ያስነገሩት አቶ በረከት ደግሞ ሌላኛው የፓርቲው አንቀሳቃሽ መሆናቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡

የኢህአዴግ ባለስልጣናት ለረዥም ጊዜ ስልጣን ላይ ይቆያሉ ተብሎ የሚሰነዘረውን ትችት ለማርገብ ሲባል ብቻ፣ ከኦህዴድ እና ከብአዴን አንዳንድ ሰዎች የስልጣን መልቀቂያ እንዲያስገቡ መደረጉን የሚገልጹ ወገኖች፣ የአቶ አባዱላም ሆነ የአቶ በረከት ስምዖን የስልጣን መልቀቂ ጥያቄ የፖለቲካ ጨዋታ እንጂ የምር አለመሆኑንም እነዚሁ ወገኖች ያክላሉ፡፡ አቶ በረከት በአሁን ሰዓት የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) በቀጣይ የሚመራበትን ፖለቲካዊ መርህ እያረቀቁ እንደሚገኙ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በእሳቸው አማከይነት እየተረቀቀ ያለው ሰነድ፣ በብአዴን ውስጥ ጥልቅ ተሃድሶ ለማድረግ ይረዳል ተብሎ እንደታመነበትም ከመረጃዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ መረጃዎች እንደገለጹት ከሆነ፣ አቶ በረከት ስምዖን ፊት ለፊት ከሚታይ ስልጣን ዞር ይበሉ እንጂ፣ በተለይ ከብአዴን ጀርባ አለመራቃቸው ተረጋግጧል፡፡

BBN Daily Ethiopian News November 21, 2017

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.