ሮዴዢያ፤ ዚምባብዌ …? – በሳምሶን ደሳለኝ

በሳምሶን ደሳለኝ/ ሰንደቅ፡

 

የሰሞኑ የዚምባብዌ ፖለቲካዊ ቀውስ የጀመረው ሮበርት ሙጋቤ በባለቤታቸው ግፊት ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩትን ኤመርሰን ምናንጋግዋ ‘ታማኝ አይደሉም’ ብለው ከሥስልጣን ካባረሯቸው በኋላ ነበር። የኤመርሰን ምናንጋግዋን መባረር ይፋ ያደረጉት የኢንፎርሜንሽን ሚኒስትሩ ሳይመን ካሃያ ሞዮ ምናንጋግዋ “ታማኝ” አይደሉም ሲሉም ተደምጠዋል።

በገዢው ፓርቲ “አዞው” በሚል ስም የሚታወቁት ምናንጋግዋ፣ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ “ዛኑ ፒኤፍ ፓርቲ አንተና ሚስትህ እንደፈለጋችሁ የምታደርጉት የግል ንብረታችሁ አይደለም” ሲሉ ሙጋቤን ተችተውም ነበር። የቀድሞው የደህንነት ሹም የነበሩት ምናንጋግዋ ፕሬዝዳንት ሙጋቤን የመተካት ተስፋ የተጣለባቸው መሪ ነበሩ።

ምናንጋግዋ ከሥልጣን በመነሳታቸው የሮበርት ሙጋቤ ባለቤት የሆኑት ግሬስ ሙጋቤ ባለቤታቸውን በመተካት ቀጣይ የዚምባብዌ መሪ እንደሚሆኑ በበርካቶች ዘንድ ተገምቶም ነበር። ከዚህ በፊት ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ምክትል ፕሬዝዳንቱን ከስልጣናቸው እንዲያነሱ ሮበርት ሙጋቤን በተደጋጋሚ ይወተውቱ እንደነበርም ይነገራል።

ከሳምንት በፊት ግሬስ ሙጋቤ በሃራሬ ለተሰበሰቡ ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ”እባቡ በሃይል ጭንቅላቱን መመታት አለበት። በፓርቲው ውስጥ መከፋፈል እና አለመግባባትን የሚፈጥሩትን ማስወገድ አለብን። ወደ ቀጣዩ የፓርቲያችን ስብሰባ በአንድ መንፈስ ነው መሄድ ያለበን” ሲሉ በምናንጋግዋ ላይ ሲዝቱ ተሰሙ። ግሬስ ሙጋቤ ይህን ባሉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኤመርሰን ምናንጋግዋ ለህይወቴ ሰግቻለው ብለው ሃገር ጥለው ሸሹ።

ሙጋቤ ምክትላቸውን ካባረሩ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር የሀገሪቱ ጦር በፓርቲው ውስጥ እየተደረገ ባለው ጉዳይ ጣልቃ ልገባ እችላለሁ ሲል ማስጠንቀቂያ የሰጠው። ከ90 የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ነበር የዚምባብዌ ጦር ኃይል ጄነራል ኮንስታንቲኖ ቺዌንጋ ገዢውን ፓርቲ ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ ጦሩ ጣልቃ እንደሚገባ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ያስጠነቀቁት።

ቀጥለውም የዚምባብዌ ጦር ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነውን ዜድ ቢ ሲን ተቆጠጠረ። ጦሩ በሰጠው መግለጫ “ይህ መፈንቅለ-መንግሥት አይደለም፤ በፕሬዝዳንት ሙጋቤ ዙሪያ የሚገኙ ወንጀለኞች ላይ እርምጃ የመውሰድ ተልዕኮ እንጂ። ጦሩ የመንግሥትን ስልጣን ለመቆጣጠር አልተንቀሳቀሰም” ሲል በመግለጫው ጠቅሶ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ እና ቤተሰቦቻቸው ደህንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን አረጋገጠ።

የአፍሪካ ሕብረትም ሆነ የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማሕበረሰብ (ሳድክ) መፈንቅለ-መንግሥት አካሂደው ስልጣን ለያዙ አካላት ዕውቅና አይሰጡም። የደቡብ አፍሪካው መሪ ጃኮብ ዙማ ሳድክን በመወከል በዚምባብዌ የሚካሄድ ማንኛውንም ዓይነት ሕገ-ወጥ የሥልጣን ሽሽግግር በማሕበረሰቡ ተቀባይነት የለውም ሲሉ ተሰምተዋል። በደቡብ አፍሪካ የዚምባብዌ ልዑክ የሆኑት አይዛክ ሞዮ መፈንቅለ መንግሥት አለመኖሩን ጠቁመው መንግሥት በተለመደ መልኩ ሥራውን እያከናወነ ነው ብለዋል።

እስካሁን የጦሩን እንቅስቃሴ ማን እየመራው እንደሆነ የታወቀ ነገር ባይኖርም ጦሩ በሚሰጠው ተደጋጋሚ መግለጫ እያደረገ ያለው ‘መፈንቅለ-መንግሥት’ እንዳልሆነና ተልዕኮውን ሲያጠናቅቅ ነገሮች ወደቀድሞው እንደሚመለሱ ማሳወቁን አላቋረጠም።

ባለፉት ሁለት ቀናት የዛኑፒኤፍ ፓርቲ ያልተጠበቀ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ ሮበርት ገብሬኤል ሙጋቤን ከፓርቲው ሊቀመንበርነት አንስቷል፡፡ እንዲሁም ግሬስ ሙጋቤን ከፓርቲው አባሯቸዋል፡፡ ለዛሬ በምልሰት የፕሬዝደነት ሮበርት ሙጋቤ እና የሮዴዢያ አያን ስሚዝ ታሪካዊ ሒደቶችን እናስቃኛለን፡፡

*** *** ***

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የአሁኑ የዚምባብዌ ፕሬዝደንት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ እ.ኤ.አ. ፌብርዋሪ 21 ቀን 1924 በሃራሬ የተወለዱት። የዘጠና ሶስት ዓመቱ ሮበርት ሙጋቤ አንድ ነጥብ ስምንት ሜትር ይረዝማሉ፡፡ እምነታቸው የሮማ ካቶሊክ ሲሆን፣ ርዕዮተ ዓለማቸው ደግሞ ማርክሲስት ነው፡፡ አባታው ገብርኤል ማቲቢሊ ሲሆኑ፣ እናታቸው ቦና ይባላሉ፡፡ የቀድሞ ባለቤታቸው ሳሊ ሃይፍሮን (1987-1992) ሲባሉ አሁን በጋብቻ የተጣመሯቸው ግሬስ ሙጋቤ (1996-) ይባላሉ፡፡ የአምስት ልጆች አባት ሲሆኑ፤ እስከ ጁን 20 ቀን 2017 ያላቸው ተቀማጭ 10 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መሆኑ ተዘግቧል፡፡

ሮበርት ሙጋቤ ለአባታቸው ገብርኤል ማቲቢሊ ሶስተኛ ልጅ ናቸው፡፡ ታላቅ ወንድማቸው በ1934 አርፏል፡፡ አባትየውም ቤተሰቡን በትኖ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ርቆ ሄዷል፡፡ በሮማን ካቶሊክ ውስጥ ሙጋቤ፣ ስለእየሱስ ክርስቶስ በሚገባ ተምረዋል፡፡ ኩታማ በሚባል ኮሌጅ ገብተው ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ አስተማሪም ለመሆን በቅተዋል፡፡ በዚህ ሳይወሰኑ በደቡብ አፍሪካ ፎርት ሃሬ ገብተው ተምረዋል፡፡ ሙጋቤ በአርት ካገኙት ዲግሪ በተጨማሪ ከስድስት ዲግሪ በላይ ተምረው አግኝተዋል፡፡ ከተመረቁ በኋላም ቻሊምባና መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ከ1955-1958 አስተምረዋል፡፡ በዚህ ወቅት በማርክሲስት አስተሳሰብ እና በጋናው ኩዋሜ ኒከሩማ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሥር ወድቀው እንደነበር ማጣቀሻዎች ያሳያሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ1958 ሙጋቤ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ለመስራት ወደ ጋና አቀኑ፡፡ ቀድሞውኑ በኩዋሜ ኑክሩማና አስተሳስብ የተጠለፉት ሙጋቤ፣ በጋና ቆይታቸው አርነት በጣም ራባቸው፡፡ ከቀኝ ገዢዎች ነፃ የወጣችውን ጋናን ሲመለከቱ፣ በውስጣቸው በርካታ ነገር አጫረባቸው፡፡ በ1960 ወደ ምዕራባዊ ሮዴዢያ ተመልሰዋል። ወደ ሀገራቸው ሲገቡ ባዩት ነገር እጅግ ደነገጡ፤ ተቆጩም፡፡ አዲሱ የኢያን ስሚዝ የሮዲዢያ አገዛዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ነጮችን በዚምባብዌ ኢኮኖሚውን እና ፖለቲካውን ተቆጣጥረው ጥቁር ዜጐች የበይ ተመልካች ሆነው ሲመለከቱ ደግሞ የአርነት ደውል በሕሊናቸው ዳግም አስተጋባ፡፡ ለነጩም ለጥቁሩም የተመቻቸ ዚምባብዌን ለመፍጠር ትግል ውስጥ ገቡ፡፡

ሙጋቤ የአርነት ታጋይ ናቸው፡፡ በተለይ ዚምባብዌ ሮዴሺያ ተብላ በምትጠራበት ጊዜ ከእንግሊዝ ቀኝ ግዛት ለማላቀቅ በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል በወጣትነታቸው ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በወቅቱ የማርክሲዝም አስተሳሰብ ከፍተኛ አፍቃሪና ተከታይ ነበሩ፡፡ በነበራቸው ንቁ ተሳትፎ ናሽናል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ፀሐፊ ሆኑ፡፡ በፓርቲው ውስጥ ከፍተኛ መሰረት በመዘርጋትና ተቀባይነታቸውን ከፍ በማድረግ ሶሻሊስት ናሽናሊስ ሙቨመንት ወይም ዛኑ (ZANU) የተባለ ፓርቲ በመመስረት እንግሊዝን ከዚምባቡዌ ጠርጎ ለማስወጣት አጀንዳ ቀርጸው ተንቀሳቅሰዋል፡፡

የሮበርት ገብሬኤል ሙጋቤ ሥርነቀል እንቅስቃሴ በእንግሊዞች ባለመወደዱ በ1964 እርስ ቤት ወረወሯቸው፡፡ ለ10 ዓመታትም ታሰሩ ሙጋቤ በእስር ቤት ሆነውም የውጭ ወራሪዎችን ሕዝብ እንዲታገላቸው እና ዚምባብዌን ነፃ ሀገር ማድረግ እንዳለባቸው ከመናገር አልተቆጠቡም፡፡ ሕዝቡም እንዲበረታ የሚችሉትን ድጋፍ ሁሉ ያደርጉ ነበር፡፡ እንዲሁም በዚህ የእስር ጊዜያቸው ከሳወዝ አፈሪካ ዩኒቨርሲቲ ና ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ለንደን በርቀት ትምህርቶች ተምረው ሁለት የህግ ዲግሪዎች አገኙ።

ሙጋቤ በአርነት እንቅስቃሴ ውስጥ National Democratic Party (1960-1961), Zimbabwe African People’s Union (1961-1963), Zimbabwe African National Union (1963-1987), Zimbabwe African National Union-Patriotic Front (1987-Present) እነዚህን የፖለቲካ ፓርቲዎች በመፍጠርና በማዋሃድ ከፍተኛ ትግል በማድረግ የነፃነት ጉዟቸውን በአስተማማኝ ደረጃ በመምራትና ለድል እንዲበቁ ዋጋ የከፈሉ ምርጥ ጥቁር አፍሪካዊ ታጋይ ናቸው፡፡

የነጮች አገዛዝ ለምን እንዲያከትም ተደረገ

እ.ኤ.አ. 1965 ሮዴዢያ፣ በአይን ስሚዝ መሪነት ከዩናይትድ ኪንግደም ነፃ ሀገር መሆኗን አወጀች፡፡ ዚምባብዌ በወቅቱ ግማሽ ሚሊዮን በሚጠጉ ነጮች ትተዳደር የነበር ሲሆን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ የበላይነትም በነጮቹ እጅ የተያዘ ነበር፡፡ ይህን የነጮች የበላይነት ተከትሎ በመጀመሪያ በዩናይትድ ኪንግደም ቀጥሎ በተባበሩት መንግስታት ማዕቀብ በዚምባቡዌ ላይ ተጥሏል፡፡ ይህንን የነጮች የበላይነት በመቃወም በ1972 ለሰባት ዓመታት ያህል የዘለቀ ጦርነት በጥቁር ብሔርተኞች እና በሮዴዢያ የፀጥታ ኃይሎች መካከል ተደርጓል፡፡

በ1970ዎቹ ማዕቀብ እና የፖለቲካ ጫናዎች በሮዴዢያ አገዛዝ ላይ የበረታ ነበር፡፡ በ1976 በተደረገው የፖለቲካ ድርድር አብዛኛው ሕዝብ ውክልና ወደ ሚያገኝበት የመንግስት ሥርዓት እንዲለወጥ ከስምምነት ተደረሰ፡፡ ይህንን ድርድር ተከትሎ በ1979 ሁሉንም ዘር ያካተተ ምርጫ ተደረገ፡፡ በምርጫው ግን ዛኑ (ZANU) እና ዛፑ (ZAPU) ፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይሳተፉ ታገዱ፡፡ ይህንን በዛኑ እና በዛፑ የተጣለውን እገዳ በመቃወም ዩናይትድ ኪንግድም እና አሜሪካ ባደረጉት ከፍተኛ ጫና አዲስ ምርጫ በ1980 ዳግም ተደረገ፡፡ ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ በምርጫው አሸናፊ ሆነው ተመረጡ፡፡ ሮዴዢያም ወደ ዚምባቡዌ በሚል ስም መጠሪያ ተለወጠ፡፡

የምዕራብ ሮዴዢያ ኤክስኪዊቲቨ ካውንስል፣ 1933

በ1891 ነበር፣ ሮዴዢያ የሚባለው አካባቢ ብሪቲሽ ሳውዝ አፍሪካ ካምባኒ በሚል አስተዳደር ውስጥ የተጠቃለለው፡፡ ይህንን ተከትሎ በርካታ ነጮች ወደ አካባቢው በመምጣት ሰፍረዋል፡፡ እነዚህ ነጮች ከደቡብ አፍሪካ ሕብረት ጋር ከመቀላቀል፣ ደቡብ ሮዴዢያ በሚል ስያሜ ለብቻቸው አስተዳደር ፈጠሩ፡፡ ትንሽ ከቆዩ በኋላም ራሳቸውን ማስተዳደር የሚያስችላቸውን ሥርዓት ዘረጉ፡፡ ማለት፣ የዩናይትድ ኪንግድም ጫና በቀነሰ መልኩ አስተዳደራቸውን ዘረጉ፡፡ በ1936 እና በ1941 የሮዴዢያን የእርሻ መሬቶች ለነጮች እና ለጥቁሮች ተከፋፈለ፡፡ ለም መሬቶችን ነጮቹ ሲወስዱ፣ ሌላውን ለጥቁሮቹ አስተላለፉ፡፡ ምዕራብ ሮዴዢያ ከሰሜን ሮዴዢያ (ዛምቢያ) እና ኔሳላንድ (ማላዊ) ጋር ውህደት በመፈጸም በብረቲሽ ኮመንዌልዝ ቅኝ ግዛት ሥር በመጠለል ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ሀገሮች በመሆን፣ ሮዴዢያ፣ ተብለው ተጠሩ፡፡ ሮዴዢያ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ተላቃ ራሷን የቻለች ሀገር ለመሆኑን ፍላጎት ብታሳይም፣ በወቅቱ የእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች የአብዛኛው ሕዝብ ውክልና ወዳለው አስተዳደር ካልተለወጠ አዲስ አስተዳደር እንዲመሰረት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ፡፡ ሶቨየት ሕብረት፣ የአይን ስሚዝን ዘረኛ መንግስት በመቃወም አቋሟን አንጸባርቃለች፡፡ ብሬዥኔቭ ለዘረኛው አያን ስሚዝ አገዛዝ እንግሊዝ የኢኮኖሚ ድጋፍ እና የመሣሪያ አቅርቦት ታደርጋለች ሲሉ በወቅቱ ከሰዋል፡፡

 

አያን ዳግላስ ስሚዝ (1919-2007) የሮዴዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር

የእንግሊዝ የ1965 ፖሊሲ በሳሊስበሪ (የዛሬዋ ሃራሬ) የከተመውን የአይን ስሚዝን አገዛዝ አልተቀበለም፡፡ የጦር መሣሪያ ድጋፍ፣ ወደ እንግሊዝ የሚላኩ እቃዎች ላይ ማዕቀብ፣ የትምባሆ ግዢን ላይ እገዳ ጥለዋል፡፡ ከቀጥተኛ ጦርነት በአገዛዙ ላይ ከመክፈት በኢኮኖሚ ጫና አገዛዙን ለመጣል የተደረገ ሙከራ ነበር፡፡ ሆኖም በማእቀቡ ፖርቹጋል (ሞዛምቢክ እና አንጎላ) እና ደቡብ አፍሪካ አልደገፉትም፡፡ እንዲሁም እገዳው በወቅቱ የተጣለ ቢሆንም ጃፓና ምዕራብ ጀርመን እና ቤልጂየም ከሮዴዢያ ጋር የንግድ ልውውጥ ያደርጉ ነበር፡፡ ስለዚህም የአያን ስሚዝ መንግስትን ጫና ውስጥ ለማስቀመጥ አልተቻለም፡፡

ማዕቀቡ ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳያመጣ በመቅረቱ በኖቬምበር 1964 በሮዴዢያ ነፃ ሀገር በመሆን ጥያቄ ላይ ሕዝበ ውሳኔ ተደረገ፡፡ ሃምሳ ስድስት በመቶ ነፃ ሀገር እንድትሆን ድምጽ ሰጡ፡፡ በኖቬምበር 11 ቀን 1965 የአያን ስሚዝ አገዛዝ ነፃ ሀገር መሆናቸው በይፋ አወጁ፡፡ ሮዴዢያም ነፃ ሀገር ሆነች፡፡ ዓለም ዓቀፉ ሕብረትሰብ ግን እውቅና አልሰጣቸውም፡፡ እንደውም የአማፃያን መንግስት አድርጎ ነው የተቀበላቸው፡፡ ሆኖም ለአምስት አመታት በነፃ መንግስት ደረጃ ተዳድረዋል፡፡

 

የሮዴዢያ ዲሞግራፊ

በ1970 በነበረው የሕዝብ ቆጠራ ስታስቲክስ፣ 228ሺ 296 አውሮፓውያን፣ 15ሺ 154 ኦሪጅናቸው የተቀላቀሉ፣ 8ሺ 965 ኤዢያዎች በሮዴዢያ ነበሩ፡፡ የጥቁር አፍሪካዊያን ቁጥር 4 ሚሊዮን 846ሺ 930 ሲሆን ሃያ አንድ በመቶ እጥፍ ከነጮቹ ይበልጡ ነበር፡፡ ሰላሳ በመቶ የሚሆኑት ነጮች ጥምር ዜግነት የነበራቸው ናቸው፡፡ በ1960ዎቹ መረጃዎች እንደሚያሳዩት 42ሺ ነጮች ግዛቱን ለቀው ተሰደዋል፡፡ አብዛኞቹ የብሪቲሽ ዝርያ ያላቸው ነበሩ፡፡

የሮዴዢያ የጫካ ጦርነት

የዚምባቡዌ አፍሪካ ናሽናል ዩኑየን እና የዚምባቡዌ አፍሪካንስ ፒፕልስ ዩኒየን ለነፃነት ከሚታገሉ ግንባር ቀደም ሃይሎች ነበሩ፡፡ ትግላቸው የጀመረው በ1960ዎቹ አካባቢ ሲሆን ኢላማ ያደረጉት ሮዴዢያን ነው፡፡ ሮበርት ሙጋቤ በ1969 የዛኑ ፓርቲ መሪ ሆኑ፡፡ በ1972 የትንሽ ነጮች የበላይነት ያለበትን አገዛዝ ለመጣል ወደ ትጥቅ ትግል በሰሜን ምስራቅ ሮዴዢያ በኩል ገቡ፡፡ የሽምቅ ውጊያ ማረፊያቸውንም በሞዛምቢክ ግዛት ውስጥ አደረጉ፡፡ ከቻይና ድጋፍ ያገኙ ነበር፡፡ በሌላ በኩል ጆሹዋ ንኮማ የሚመራው የዚምባቡዌ አፍሪካንስ ፒፕልስ ዩኒየን በምዕራብ ሮዴዢያ ውጊያ ከፍቷል፡፡ ከዛምቢያ ግዛት በመነሳት ነበር ጥቃት የሚከፍቱት፡፡ ወደ ውጊያው ቀጠና የገቡት፡፡ ከሶቨየት ሕብረት ድጋፍ ያገኙም ነበር፡፡ ሁለቱም የፖለቲካ ኃይሎች ከነበራቸው የፖለቲካ ርዕዮተዓለም አንፃር ከሶሻሊስ ሀገሮች ድገፍ ያገኙ ነበር፡፡ ትግሉ፤ በጥቂት ነጮች የበላይነት በተያዘው ኢኮኖሚና ፖለቲካ እና በጭቁን ጥቁር ሕዝቦች መካከል እልህ አስጨራሽ ትግል ነበር፡፡

በ1974 ሞዛምቢክና አንጎላ ከፖርቱጋል ቅኝ ግዛት ነፃ ወጡ፡፡ የሁለቱም ሀገሮች መሪዎች ማርክሲስቶች ስለነበሩ፣ የደቡብ አፍሪካ ሀገሮች የሃይል ሚዛን ወደ ማርኪስቶች አዘነበለ፡፡ የደቡብ አፍሪካ ሕብረት ቀጨጨ፡፡ የደቡብ አፍሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሮዴዢያ ላይ አነጣጠረ፡፡ ዛምቢያ፣ ታንዛኒያ እና ሞዛፒክ በድንበራቸው ዙሪያ ወደጦርነት ውስጥ ገቡ፡፡ ቻይና እና ሶቨየት ሕብርት ድጋፋቸውን አጠናክረው ሰጡ፡፡ እነሮበርት ሙጋቤ ነገሮች ሁሉ ወደ እነሱ እያዘነበሉ መምጣታቸውን አወቁ፡፡ ትግላቸውንም አፋፋሙት፡፡

 

ወሳኝ ለውጥ የተደረገበት ሁኔታ

በ1976 ጦርነቱ ተቀጣጠለ፡፡ የሮዴዢያ የፀጥታ ኃይሎች ከሞዛምፒክ ድንበር ጠባቂዎች ጋር ውጊያ ገጠሙ፡፡ የሮዴዢያ አየር ኃይል የሞዛምፒክ ግዛት በመዝለቅ ድብደባ ፈጸመ፡፡ ድብደባውን ተከትሎ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የነበረው ድንበር ተዘጋ፡፡ ሮዴዢያ በሞዛምፒክ ትገለገልበት የነበረው የባቡር ትራንስፖርት ተቋረጠ፡፡ የገቢ እና የውጭ ንግዷ ቀዘቀዘ፡፡ የቱሪዝም ኢንዱስትሪዋ በሽምቅ ኃይሎች ትንኮሳ ደበዘዘ፡፡

ይህ በእንደዚህ እያለ፤ በ1976 በምዕራብ ጀርመን ውስጥ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄነሪ ኪስንገር ከደቡብ አፍሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር መገናኘታቸውን ተከትሎ፤ አሜሪካ ደቡብ አፍሪካን ጫና ውስጥ የሚያስገባ ጥያቄ አቀረበች፡፡ የደቡብ አፍሪካ መንግስት አያን ስሚዝ ላይ ጫና በማሳደር ወደ ብዙሃን ውክልና ወዳለው የመንግስት አስተዳደር ሮዴዢያ አገዛዝ በሁለት ዓመት ውስጥ እንዲገባ ማስገደድ እንዳለባቸው፣ ሄነሪ ኪስንገር ቀጭን ትዕዛ አስተላለፉ፡፡ የአሜሪካን ጫናን መቋቋም ያቃታቸው የደቡብ አፍሪካው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በቀረበው ሃሳብ ተስማሙ፡፡ አያን ስሚዝ በበኩሉ በደቡብ አፍሪካ ክህደት እንደተፈጸመበት ቢቆጥረውም፣ ሃሳቡን በመቀበል ለዘብተኛ የነፃነት ታጋዮች ወደ ሥልጣን ቢመጡም ብዙ ችግር እንደሌለው አድርጐ ተቀበለው፡፡ ሆኖም አክራሪ ብሔርተኛ የነበሩት ሙጋቤ እና ንኮማ ወደ ሥልጣን መምጣት እንደሌለባቸው ከስምምነት ደረሱ፡፡ እንዲሁም የፖለቲካ ስልጣናቸውን ቢያጡም የኢኮኖሚ የበላይነታቸው ተጠብቆ እንዲቀጥል ፍላጎታውንም አሳይተዋል፡፡

ሆኖም ግን በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በሶሻሊስት ሀገሮች እና በተባበሩት መንግስታት ጫና በ1980 በተደረገው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ የዛኑ ፒኤፍን ፓርቲን በመወከል ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.