ሕወሃት ጠንካራ ሆና አታውቅም፤ የምትገዛው እኛ ደካማ ስለሆንን ነው #ግርማ_ካሳ

 

እጅግ በጣም ብዙ ወገኖች በግፍ ታስረዋል። የነርሱ ነገር ምንም መፍትሄ ሊያገኝ አልቻለም። ኦህድዶች የኦፌኮ እስረኞች እንዲፈቱ ጥያቄ አቀረቡ። ሕወሃቶች ግን በካልቾ ብለው አባረራቸው። ድፍን ጎንደር እንደ ጀግና የሚቆጥራቸውን የወልቃይት ኮሚቴ አባላትን ሕወሃቶች በወህኒ ሲያሰቃዩና ሲያንገላቱ፣ ብአዴን ትንሽ ደፍሮ እንኩዋን እንዲፈቱ አልጠየቀም። ሌሎቻችንም በእስረኞች ላይ የሚደርሰው ግፍና ሰቆቃ እያበሳጨን፣ ልባችንን እየሰበረው ፣ ከማዉገዝ፣ አገዛዙን ከመራገምና ከመኮነን ያለፈ ነገር መስራት አልቻልንም። በአንጻሩ ሕወሃቶች ኣሮሞ የለ፣ አማራ የለ፣ ጉራጌ የለም፣ ወላይታ የለ…ሁሉንም እንደፈለጉ እያሰሩ፣ እንደፈለጉ እያፈኑና እያዋረዱ መግዛታቸውን ቀጥለዉበታል።

እነርሱ እጅግ በጣም ጥቂቶች ሆነው፣ እኛ ግን አሥር ሚሊዮኖች ሆነን እንዴት ግን ይሄን አሳዛኝ ነገር መቀየር አቃተን ? ሁሉም ለብቻው ከዘሩ ወይንም ከጎሳው ጋር ያለቅሳል። ሁሉም ምሬት አለው። ሁሉም እርሱ ወይንም የርሱ ዘር ሲነካ ብቻ ነው የሚጮኸው። ሁሉም የራሱ ቤት ሲንኳኳ ብቻ ነው ተቃዉሞ የሚያሰማው። የከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ ከሕወሃት የተሰጣቸውን መመሪያ በማንበብ፣ ጋዜጠኛ እስክንደር ነጋ፣ አንዱዋለም አራጌና ሌሎች ላይ የፍርድ ዉሳኔ ሲሰጥ የእስክንደር ባለቤት ሰርካለም ፋሲል ያኔ የተናገረችው ነገር ነበር። “ይሄ ሁሉም ቤት ያንኳኳል” ነበር ያለችው። እዉነቷን ነበር።፡እነ እስክንድር ከታሰሩ በኋላ ስንቱ ታሰረ ? ገና ወደፊት በጋራ፣ በአንድነት፣ በዘር ሳንከፋፈል እስካልተነሳን ድረስ ፣ እድል ፈንታችን መታሰር ነው የሚሆነው።

ይሄ እንዲቀየር ከተፈለገ ፣ ሕወሃት ላለፉት 25 አመታት እንደገዛው ለሚቀጥለው 25 አመታት እንዳይገዛ ከፈለግን ያለፉት ስህተቶች መድገም ሳይሆን በአዲስ መልክ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ፣ ከስሜት የጸዳ ፣ ያልተከፋፈለ፣ የሁሉንም ዜጎች መብት በማክበር ላይ የተመሰረተ ፣ ሁሉንም ያቀፈ እንቅስቃሴ ያስፈላጋል።

– አንደኛ በአስተሳሰባችን የሳልነውን የሕወሃትን ምስል ማጥፋት አለብን። እነርሱን እንደ invincible አድርገን ነው የምናያቸው። ያ መቆም አለበት። ሕወሃቶች መቼም በራሳቸው ጠንካራ ሆነው አያውቁም። እየገዙ ያሉት እኛ ደካሞች በመሆናችን መሆኑን መረዳት አለብን።

– ሁለተኛ እኛ ሚሊዮኖች መሆናችንን በመረዳት በራሳችን መተማመን አለብን። የሕወሃት የጥንካሬ ምንጭ የኛ ፍርሃትና ዝምታ መሆኑን መረዳት አለብን።

– ሶስተኛ አንድ መሆን አለብን። በጎንደር “አማራ፣ አማራ” እያልን፣ በወለጋና አርሲ “ኦሮሞ ኦሮሞ” እያለን፣ በዘር ተከፋፍለን ፣ ባልተቀናጀ መልኩ የምናደርገውን እንቅስቃሴ ማቆም አለብን። አንርሳ የአማራ ተጋድሎና የኦሮሞ ተቃዉሞ ሄዶ ሄዶ ቆሟል። ገፍቶ መሄድ አልቻለም። በዘር ላይ የተመሰረተ ትግል ገደብ አለውና።

-አራተኛ ትግሉ መቀናጀት አለበት። አምቦ ለብቻው ሲነሳ የሚመታበት፣ ጎንደር ለብቻው ሲነሳ የሚመታበት ምክንያት መኖር የለበትም። በአንድ ጊዜ አገር አንቀጥቅጥ ህዝባዊ ተቃዉሞ በጎንደር፣ በአምቦ፣ በአርባ ምንጭ በሁሉም የአገሪቷ ክፍል እንዲደረግ መስራት ያስፈልጋል። ሁሉም ከተሞች ከተነሱ ጥቂት የአጋዚ ታጣቂዎች በሁሉም ቦታ ሊሆኑ አይችሉም። በስሜት በግብታዊነት አምቦ ለብቻዋ ብትነሳ ትርፉ ወጣቶችን ማስጨረስ ነው። በጎንደር ወይም ባህር ዳርም እንደዚሁ።

– አምስተኛ ሕዝባዊው እንቅስቃሴ ፍጹም ሰላማዊ የሆነና በጥላቻና ቂም በቀል ላይ ያልተመሰረተ መሆን አለበት። ሕዝባዊ ተቃዉሞዎች ዘር ተኮር ሆነው ሌላ ማህበረሰብ የሚያጠቁ፣ ሌሎች እንዲፈሩ የሚያደረጉ መሆነ የለበት።፡በአንጻሩ ግን ሌላዉን የሚያሰባስብና የትግሉን ድንኳን የሚያሰፋ መሆን ነው ያለበት።

– ስድስተኛ የኦህዴድንና የብአዴንን ማባባልና ባዶ ተስፋ ማዳመጥ ማቆም ያስፈለጋል። ኦህዴዶና ብአዴኖች ውስጥ ለውጥ ፈላጊ የሆኑ አመራሮች አሉ። አቶ ገዱና አቶ ለማ ሕዝብን የሚያከብሩ ነው የሚመስሉኝ። ሆኖም ግን በኢሕአዴግ አብዮታዊ የድርጅት ማአከላዊነት መሰረት ንግግሮች ከማድረግ ዉጭ የሚፈይዱት ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም። ኦህዴድን በነ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ በኩል፣ ብአዴንን በነ አቶ አለምነህ መኮንን በኩል ሕወሃት ጠፍሮ የያዘ ነው የሚመስለው። ያ ብቻ አይደለም ህወሃት፣ ኦህዴድና ብአዴንን የሕዝቡን የነጻነት፣ የፍትህና የ እኩልነት ጥያቄዎች በባዶ ተስፋ እንዲያማልሉና የትግሉን ግለት እንዲያቀዘቅዙ ሲስተማሪካ በሆነና በረቀቀ መልኩ እየተጠቀመባቸው ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.