ማሙሸት አማረ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የላከው ደብዳቤ – “ይድረስ ለአማራና ለኦሮሞ ህዝቦች”

አሁን ደመ ነብሴ ትነግረኝ የነበረው ደረሰ፡፡ እነዚህ ትልቅ ህዝቦች ለዘመናት የተጋቡ፣ የተዋለዱ፣ አንዱ፣ አንዱን አክብረው በደስታም ኾነ በመከራ አንድ ኾነው የኖሩ ህዝቦች የመነጠልና የመነጣጠል፤ የማጣላት፤ የማፋጀት፤ የማጋደል፤ ወንድምን ከወንድም፤ ባልን ከሚስት፤ ልጅን ከእናት፤ ልጅን ከአባት፤ ዘመድን ከዘመድ በአጠቃላይ በወንድማማቾች መኻል ፀብን የመዝራት በአባዜ ይዘው በ1967ዓ.ም ጫካ የገቡት የእውቀትም ኾነ የመንፈስ ድኾች ለድፍን 26 ዓመታት በኹለቱ ህዝቦች መካከል ሊፈርስ አይችልም፡፡ ብለው የገነቡትን የጥል ግድግዳ በኹለቱ አስተዋይ ህዝቦች ፈርሶ አይቼዋለሁና እናም የተወደዳችሁ የኹለቱ አስተዋይ ታላቅ ህዝቦች አኹን የጀመራችሁትን አጠናክራችሁ በመቀጠል ዘረኛውንና ጎጠኛውን የታላቋን የኢትዮጵያ ነቀርሳ ህወሓትን ወደማይመለስበት ጥልቅ ጉድጓድ የምትጥሉበት ጊዜው አኹን ነው፡፡ “ጥልቅ” የሚለው ቃል እነሱ የፈጠሩት ባይኾንም የሰሞኑ የእነሱ የጥልቅ መታደስ ወሬ በመኾኑ ይህንን ቃል ስሰማም ትዝ ያለኝ ስምን መላእክ ያወጣዋል እንዲሉ አበው በጥልቅ መታደስ ባሉበት ማግስት ወደ ጥልቅ ጉድጓድ የሚወድቁበት ጊዜ መኾኑ ትዝ ሲለኝ ገረመኝ፡፡

በእዚህ አጋጣሚ ለብአዴን እና ለኦህዴድ አባላት እና አመራሮች የምላችሁ ነገር ቢኖር በየጊዜው የምትሉት እውነት ከኾነ ይበል የሚያስብል ነው፡፡ ነገር ግን አሁንም እያደረጋችሁ እንደነበረው ለህወሓት ተላላኪ ሆናችሁ በእዚህ መንገድ “የህዝቡን ትግል እናቀዘቅዛለን!” ብላችሁ አስባችሁ ከኾነ እውነት እላችኃለሁ “የሞት፣ ሞትን ትሞታላችሁ” ምክንያቱም ህዝቡ አኹን የሚፈልገው የህወሓትን መጨረሻ ነው፡፡ እናንተ እንደምትሉት “በፕሮፖጋንዳ የህዝቡን ጥያቄ እንመልሳለን፡፡” ገለ መሌ እንድትሉ አይደለም፡፡ የህዝቡ እንቅጩን ጥያቄ “ህወሓትን ማየት አንፈልግም!” ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ እናንተ ከህዝቡ ጎን መቆማችሁ፡-

እናንተ እራሳችሁን ከሞት እና ከመጣው ውርደት ታደጋችሁ ማለት ነው፡፡
ከብዙ መስዋዕትነት ሀገሪቱን ታድጋችሁ እና እራሳችሁን ከታሪክ ወርቃማ መዝገብ ላይ አሰፈራችሁ ማለት ነው፡፡ ይህንን እናንተ የማታደርጉት ከኾነ ግን፡- “እናንተም የሞት ሞታችሁን ሞታችሁ፤ ታሪካችሁንም ታበላሻላችሁ” ብዙ መስዋዕትነትም ቢኾን ተከፍሎ “ለውጥ እንደማይቀር አስረግጬ ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡” ስለዚህ፡- “ብአዴንና ኦህዴድ ሆይ በእውነተኛ መንፈስ ከህዝቡ ጎን በመቆም ለሀገርም ኾነ እናንተን ተላላኪ አድርጓችሁ ለዘመናት የኖረው ጦር የኾነውን ህወሓትን ከስሩ ንቀሉት” ብዬ ወንድማዊ ምክሬን እለግሳለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

ማሙሸት አማረ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.