በኢትዮጵያ ያለው ስርዓት በኢኮኖሚው ዘርፍ ሀገሪቱን ወደ አደገኛ ሁኔታ እየወሰዳት እንደሚገኝ ተጠቆመ

BBN news November 27, 2017

በኢትዮጵያ የሚገኘው ስርዓት ሀገሪቱን ወደ አደገኛ አቅጣጫ እየወሰዳት እንደሚገኝ ተነገረ፡፡ ስርዓቱ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊም ሆነ በሌሎች ዘርፎች እየተከተለ የሚገኘው መንገድ ሀገሪቱን ዋጋ እንዳስከፈላት ይታወቃል፡፡ በተለይ በአሁን ሰዓት ያለው የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዞ ግን እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የሚናገሩት፡፡ ባለሙያዎቹ፣ ስርዓቱ እየተከተለ ያለውን የኢኮኖሚ ጉዞ ቆም ብሎ እንዲመለከት ማስጠንቀቂያ እና ምክር አዘል ሀሳባቸውን በማጋራት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከብር የመግዛት አቅም መዳከም ጀምሮ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ በየወሩ በገበያ ውስጥ እየተፈጠረ ያለው የዋጋ ንረት እና መሰል ጉዳዮች፣ ስርዓቱ በፕሮፓጋንዳው ዘርፍ ሲመካበት የኖረውን ‹‹የኢኮኖሚ እድገት›› በቅርብ ጊዜ ውስጥ ገደል እንደሚከተውም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ ያስጠነቅቃሉ፡፡ በተለይ በውጭ ምንዛሬው በኩል የተፈጠረው አስደንጋጭ ችግር፣ ዕቃዎች ከወደብ ወደ መሐል ሀገር እንዳይገቡ እያደረገ እንደሆነ የሚገልጹት ባለሙያዎቹ፣ ችግሩ በዚህ ሳይወሰን በሀገር ውስጥ እየተካሔዱ ያሉ የኢንቨስትመንት ስራዎችንም እያስቆመ እንደሚገኝም ባለሙያዎቹ ያክላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ስርዓቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር እያሸጋገርኩት ነው ለሚለው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መርዶ መሆኑም መረሳት እንደሌለበት ነው የባለሙያዎቹ ገለጻ የሚያስረዳው፡፡

በሆቴል፣ በጨርቃ ጨርቅ እና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በስራቸው ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እያደረሰ እንደሚገኝ በምሬት እየገለጹ ናቸው፡፡ ሌሎች ባለሀብቶች ደግሞ በተፈጠረው የምንዛሪ እጥረት የተነሳ፣ ስራቸውን በከፊል ከመስራት ጀምሮ፣ ሙሉ ለሙሉ ስራውን ወደማቆሙ ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ በመናገር ላይ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የግል ባለሀብቶች በፈጠሩት የስራ ዕድል ተቀጥረው የሚሰሩ ዜጎች፣ መንግስት በፈጠረው የስራ ዕድል ተቀጥረው ከሚሰሩ ዜጎች ያልተናነሰ ቁጥር እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የግሉ ዘርፍ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ስራውን ሲያቆም፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለስራ አጥነት ችግር እንደሚጋለጡ ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስራ አጥነት ቀውስ እንዲፈጠር ምክንያት መሆኑ አይቀርም የሚሉ ታዛቢዎች፣ ስርዓቱ እየሔደበት ያለውን አደገኛ መንገድ መርምሮ ለተማሩ ሰዎች ዕድል እንዲሰጥ ታዛቢዎቹ ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.