የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሰላሳ ቀናት ውስጥ በሶስት የአውሮፓ ከተሞች ቤተ ክርስቲያን ገዛች

የኦስሎ ቤተክርስቲያን ህንፃ ኮሚቴ ትውልድ አኩሪ እንቅስቃሴ ማድረጉ አስመስግኖታል።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን የተመለከተ የፔው ምርምር ማዕከል አዲስ ዓለም አቀፍ ጥናት ይፋ አደረገ

ኦስሎ፣ኖርዌይ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አቡነ ሕርያቆስ ቀሲስ ካሳሁን እና ዲያቆናት እሁድ ህዳር 17/ 2010 ዓም  ቅዳሴ ሲያሳርጉ 


ጉዳያችን / Gudayachn

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሰላሳ ቀናት ውስጥ  በሶስት የአውሮፓ ከተሞች ቤተ ክርስቲያን ገዛች

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሶስት የአውሮፓ ታላላቅ ከተሞች  ሶስት አብያተ ክርስቲያናትን ገዝታለች።እነርሱም በፍራንክፈርት ጀርመን የመድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ኦስሎ ኖርዌይ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት እና ለንደን እንግሊዝ የደብረ ገነት ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን ናቸው።አውሮፓ ውስጥ ሃይማኖተኛ ሳይሆን በእግዚአብሔር ማመን እና አምልኮት መፈፀም ብርቅ እየሆነ የመጣበት አህጉር ሆኗል።በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ ድንቅ ጥበብ የታዩባቸው በርካታ ህንፃ አብያተ ክርስቲያን ይገኛሉ። እነኝህ አብያተ ክርስቲያናት ግን በሰንበት ቀኖችም ሆነ በበአላት ቀናት በውስጣቸው አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈፅም ምእመናን አይገኙም።በእርግጥ ለአውሮፓውያን የልደት በዓል ዋዜማ አመታዊ ኮንሰርት የሚደረግባቸው አብያተ ክርስቲያናት በዋና ዋና ከተሞች ውስጥ አሉ። 

 

አሁን አውሮፓ ውስጥ እየሆነ ያለው ከእዚህ የከፋም ነው። አብያተ ክርስቲያናት ለምሽት ክበቦች የመሸጥ እና የመከራየት ዕጣ እየደረሰባቸው ነው።ይህ እየሆነ ባለበት ሰዓት ነው እንግዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር እያወጣች እየገዛች ያለው።ግዥዎቹ የተፈፀሙት በአውሮፓ የሚኖሩ ምእመናን በሚያዋጡት እና ከባንክ በሚገኝ የእረጅም ጊዜ ክፍያ ብድር ነው።

አዲስ የተገዛው  የለንደን እንግሊዝ የደብረ ገነት ቅድስት ስላሴ ቤተ ክርስቲያን
አዲስ የተገዛው የኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን
ጀርመን ፍራንክፈር የመድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ግዢ ሲፈፀም የደብሩ አስተዳዳሪ መላከ መዊ ልሳነ ወርቅ ሲፈርሙ 
 
የኦስሎ ቤተክርስቲያን ህንፃ ኮሚቴ ትውልድ አኩሪ እንቅስቃሴ ማድረጉ አስመስግኖታል
ኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የህንፃ ጨረታ ሂደት እና ለግዥ የሚሆን የገንዘብ ማሰባሰብ (አብዛኛውን ገንዘብ) ስራውን በአንድ ወር ውስጥ ማሰባሰብ መቻሉ እና ምእመናንን በሚገባ ማንቀሳቀሱ ከፍተኛ አድናቆትን አስገኝቶለታል።የህንፃ ኮሚቴ በቅርብ አመታት ውስጥ በአዲስ መልክ ከተመሰረተ በኃላ መሬት ገዝቶ ቤተ ክርስቲያን የመገንባት፣ አብያተ ክርስቲያናትን መግዛት ወይንም የባህል ማዕከል ገዝቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን መቀየር የሚሉ አማራጮችን ይዞ ወደ ሥራ ገብቷል።
ይህ በወጣቶች የተገነባው የህንፃ ኮሚቴ በተለይ ባሳለፍነው ወር ውስጥ የህንፃ ጨረታ ግዢ ሂደት ላይ ኮሚቴው በበቂ መልኩ ያደረገው የአሰራር ብቃት፣ከምእመናን ጋር የነበረው የግንኙነት መስመር እና ሁሉንም ምእመን የማስተባበር ሥራ መሰራቱ ከእግዚአብሔር ፍቃድ ጋር ተጨምሮ ለፍሬ ሊበቃ ችሏል።የህንፃ ኮሚቴው አባላት እንቅልፍ አጥተው ያደሩባቸው ሌሊቶች፣ ከስራ ለበርካታ ቀኖች የቀሩባቸው ጊዜዎች እና በታማኝነት የምመናንን አስተዋፅኦ ጠብቀው ለቤተ ክርስቲያን ጨረታ መልካም ውጤት ቤተ ክርስቲያንን አድርሰዋታል።ከእነኝህ ውስጥ ሁለቱን ክስተቶች ብቻ መጥቀሱ የነበረውን ውጣ ውረድ ሊያሳይ ይችላል።
የእሁዱ ለቅሶ 
 
የኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ህንፃ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ተክሉ ጨረታው በተሰማበት የመጀመርያ እሁድ ከቅዳሴ በኃላ ስለ ጨረታው ምንነት፣ ቤተ ክርስቲያን ያላት ገንዘብ መጠን እና ከባንክ ሊገኝ የሚችለው ገንዘብ እና  ኮሚቴው ሊሰራ ያሰባቸውን ስራዎች አብራሩ።ይህች እሁድ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን በስሜት ያለቀሱበት፣ ሁሉም በአንድነት በተሰበረ ልብ ሆነው ምን እናድርግ እያሉ የተመካከሩበት ሰንበት ነበር። በእዚህ ሁሉ መሃል የህንፃ ኮሚቴ አባል ወ/ሮ ሶስና ሳግ በቀላቀለው እና ከውስጧ ፍልቅል ብሎ በወጣ የለቅሶ ድምፅ  እያሰማች ቆመች እና መናገር ጀመረች: –
” እኔ በጣም ይቅርታ አድርጉልኝ ይህንን ነገር ሳልናገረው ማለፍ አልችልም። ትናንት ምሽት ላይ ከአረብ ሀገር ቤተ ክርስቲያን ጨረታ ላይ መሆናችንን የሰማች እህት እያለቀሰች ያወራችኝን ልንገራችሁ።ልጅቷ ከአሳዳርዎቿ ተደብቃ መንገድ ላይ ወጥታ እንደምትደውል ስትነግረኝ እያለቀሰች ያለችኝ 200 ዶላር አለች ከሰራሁት እሷኑ እልካለሁ አለችኝ”  ብላ ወ/ሮ ሶስና ስትናገር ምእመናን ስሜት ይብሱን ተነካ።ለጥቂት ሰኮንዶች ፀጥታ ሰፈነ።በአረብ ሀገር በጉልበት ሥራ የምትሰራ እህት አውሮፓ ላለ ቤተ ክርስቲያን ልቧ ተነክቶ እንቅልፍ አጥታ አምሽታ ምሽት ላይ መንገድ ዳር ወጥታ ስልክ ደውላ ከሰራቻት የወር ክፍያ ላይ 200 ዶላር ለመክፈል ያውም ከእንባ ጋር ለሕንፃ ኮሚቴ አባል ደውላ ጠይቃለች።ጉዳዩ እራስን ለመመልከት እና እኔ ምን አደረኩ? የሚያስብል ልዩ ድባብ የፈጠረ ሰንበት ነበር።
 
 ለሁለተኛ ጊዜ የተራዘመው እና የመጨረሻው ጨረታ ሊጀመር 24 ሰዓታት ሲቀሩት 
የቤተ ክርስቲያኑ የጨረታ ጊዜ ሁለት ጊዜ ተራዝሟል።ለእዚህም ምክንያቱ አዳዲስ አመልካቾች በመምጣታቸው ነበር።የኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ጨረታ ልዩ የሚያደርገው አንዱ ምክንያት በኖርዌይ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ለጨረታ ብቻ ሳይሆን ለሽያጭ ማቅረብ ከቆመ አመታት ሆኖታል ሆኖም ግን የእግዚአብሔር ፍቃድ ሆኖ ይህ የተገኘው ቤተ ክርስቲያን ቀደም ብሎ በግለሰብ ተይዞ በመኖሩ ለሽያጭ ሊቀርብ ችሏል።ይህ ምናልባት ከብዙ አመታት በኃላ የሚያጋጥም ዕድል ነው።
በጨረታው ላይ ከአምስት በላይ ድርጅቶች ከመሳተፋቸው በላይ ለሁለት ቀናት ያህል የቆየ እልህ አስጨራሽ ነበር።ከጨረታው ከመጀመሩ 24 ሰዓታት በፊት በሕንፃ ኮሚቴው ውስጥ በወሳኝ አገልግሎት ላይ ከሚገኙት ውስጥ የኮሚቴው ሰብሳቢ ዶ/ር ተክሉ በድቁና ከሚያገልግሉት አንዱ ልጁ እንዳመመው ይሰማል።ይህ ሲሆን ሁለት ቀናት በጨረታ በጋራ ከሚከታተልበት ከአቡነ ሕርያቆስ ቤት ነበር።ሆኖም ግን ልጁን ሄዶ ለማየት አልቻለም።ልጁ ሆስፒታል ደርሶ ሲመለስ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ እዚህ እየጠበቀው ነበር እና አሁንም ሄዶ ማየት አልቻለም።
ዶ/ር ተክሉ አባቴ የኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ህንፃ ኮሚቴ ሰብሳቢ
 
በሌላ በኩል የኮምቴው የሂሳብ ሹም ዶ/ር ዳዊት ሻወል ጨረታው ሊጀመር ሀያ አራት ሰዓታት ሲቀሩት ለስራ ከኖርዌይ ውጭ ወደ እንግሊዝ እንዲሄድ መስርያቤቱ ያዘዋል።ሁኔታው በወቅቱ ሁሉም የኮሚቴ አባላት የመገኘታቸው አስፈላጊነት አንፃር እራሱን የቻለ ድባብ ይዞ መጥቶ ነበር።
ዶ/ር ዳዊት ሻወል የህንፃ ኮሚቴ ሂሳብ ሹም

በሌላ በኩል ከህንፃ ኮሚቴው ጭንቀት እና ውጥረት በተጨማሪ በኖርዌይ እና በመላው ዓለም የሚኖሩ ዜናውን የሰሙ ኢትዮጵያውያን ውጤቱን በጭንቀት ይከታተሉ ነበር።በመቶዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በቫይበር ግሩፕ የተሰባሰቡበት የምእመናን ስብስብ እራሱ የቻለ የጨረታው ገፅታ ነበር።ለሁለት ሳምንታት ከጨረታው በፊት በነበሩ እያንዳንዱ ምሽቶች የሚገናኘው ይህ የምእመናን ግሩፕ በጎፈንድ የተከፈተው ሂሳብ ከመቶ ሺህ የኖርዌይ ገንዘብ በላይ እንዲሰበሰብ አግዟል።ባጠቃላይ የኦስሎ ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ህንፃ ኮሚቴ አባላት ከሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እና ከቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ እና የአቡነ ኤልያስ ረዳት አቡነ ሕርያቆስ ጋር በተቀናጀ መልኩ የሰሩት ሥራ ምእመናንን በጣም ያስደሰተ ታሪካዊ ሥራ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን የተመለከተ የፔው ምርምር ማዕከል አዲስ ዓለም አቀፍ ጥናት ይፋ አደረገ
 
ፔው የምርምር ማዕከል በዓለም ላይ ባሉ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት አዲስ ጥናት አውጥቷል።በጥናቱ በዓለም ላይ ከሩስያ ቀጥሎ ከፍተኛ የኦርቶዶክስ አማኞች ያሉባት ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን እና በሰንበት እለት ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ቁጥር እንደያዘች ይገልጣል። የጥናቱ ውጤት ከእዚህ በታች ይመልከቱ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.