ፍተሻ – ስለሞት ዕወጃው። (ሥርጉተ ሥላሴ)

 

ሥርጉተ ሥላሴ 01.12.2017 (ዙሪክ – ሲዊዘርላንድ)

“የዝንጉዎች ጉባኤ ሁሉ ለጥፋት ይሆናል፣ የጉቦ ተቀባዮችንም ድንኳን እሳት ትበላለች። ጉዳትን ይፀንሳሉ፣ በደልንም ይወልዳሉሆዳቸውም ተንኮልን ያዘጋጃል።“

                                   (መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ ፲፭ ቁጥር ከ፴፬ እስከ ፴፭ )

የሞት ዓዋጅ።

ሥርጉተ ሥላሴ

የወያኔ ሃርነት ትግራይ የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ፤ የማዕከላዊ ኮሜቴ ስብሰባ፤ የፖሊት ቢሮ ስበሰባ እንዲሁም የመሰረታዊ ድርጅቶች ጠቅላላ ስብሰባዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ቀጥቅጦ፤ እንደ ብረት አቅልጦ የሚገዛ ብቻ ሳይሆን የመላዕክ ሞት ዓዋጅ ነው። ይህ ሂደት የአንድ „ክልል“ የትግራይ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የህውሃት ጉዳይ ብሄራዊ፤ ሐገራዊ ብቻም ሳይሆን ዓለምአቀፋዊም ጉዳይ ነው – ዕድምታው። በቀላል ስሌት፤ በገረፍ – ገርፍ የፖለቲካ ስብከት ወይንም ግብታዊነት በሚጫነው ስሜት ብቻ ተነካክቶ መታለፍ ያለበት አይመስለኝም። የህውሃት ተፈጥሮ ፓርቲው ከፍልስፍናው ጀምሮ ኢትዮጵያን የተመኟት ሁሉ በእጅ አዙር የፈለጉትን ያገኙበት አናት አመክንዮ ነው። ፈታኝ ክስተት። ኢሳት በዚህ ላይ የሰጠው/ የሚሰጠው ተከታታይ አትኩሮት ሆነ የሚያደርገው የሦስትዮሽ ውይይት በፍጹም ሁኔታ የተገባ ነው። „ስለወያኔ ያልተባለ የለም የሚሉ“ ወገኖች አሉ። መቼ ነክተነው ኦፕራሲዮኑን። በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ስለምንጠመድ። አምክንዮው ከአጀንዳ ባላይ ነው። የ95 ሚሊዮን የነፍስ መቋጠሪያ ዘለበት። የዛሬውም መነሻዬ ይሄው ነው። ለዚህም ነው ከወያኔ ሃርነት ትግራይ መንፈስ ጋር የነበሩ ግን ፈንገጥ ብለው አቅሞችን በጥንቃቄና በማስተዋል ልናስጠጋቸው ይገባል የምለው። ይሄ ሃጢያት እዬጉረጎሩ እንቅፋት መሆን የቅንጥ – የቅልጣንም ነው – ለእኔ። በምንም ዘመን እንዲህ ዓይነት የአገዛዝ ውስብስብ ወጥመዳዊ ሂደት ኢትዮጵያን ገጥሟት አያውቅም።

መነሻ።

ችግርን የእኔ/ የእኛ ለማለት ሂደቱን ከውስጡ ሆኖ በማስተዋል ማጥናትን የሚጠይቅ ይመስለኛል – መፍትሄ አምንጩም የችግርን ጥልቀት በውስጥ ካሜራ ማንሳት ሲቻል ብቻ ይሆናል – እንደ እኔ። ለአቅም ሊኖረን የሚገባም አክብሮት ከዚህ ተራራዊ የተጋድሎ ጠረፍ መነሳት ስንችል ብቻ ነው። እኛ እኮ „አቅም“ ማለትን በመሆን ማቅለም ሳንችል፤ ነገር ግን የነፃነት ረሃብተኞች ነን። በፍላጎታችን ለመኖር ውሳኔያችን ገና ለጋ። መቁረጥን በእልህ ክታብ ያለጸናን።

https://www.youtube.com/watch?v=Q2TQYRQnpbU

ESAT Special Efeta Nov 29, 2017 – የኢሳት ልዩ ተልዕኮ ህዳር 29, 2017

https://etzena.com/amharic/archives/42142 በወ/ሮ አዜብ መስፍን ዕግድ ላይ የሕውሐት ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚወስን ተጠቆመ።“

መቅድም።

ደስ ይለኛል የጋዜጠኛ መሳይ ሰብሳቢነት። ጥሩ ነው የሚያወያዬው። ወደ ስምንት ወር ሆኖታል በሰብሳቢነቱም የሚወያያቸውን ጋዜጠኞች ሳይቀር አቅም ባለው አምክንዮ ይሞግታል። አንዳንድ ጊዜ ውስጤ ያለ እስኪመስለኝ ድረስ። የዚህ የህዳር 29ኙ ውይይት ብስጭት አልነበረበትም፤ የተረጋጋ መንፈስ ነበረው። አንድ አቅጣጫ አይደለም። ሙግት ነበረበት። ሰላማዊ ፍጭት ታይቶበታል። አዳዲስ አነሳሽ ሃሳቦች ተስተውለውበታል። ሙግት እንዲህ ሲጦፍ ህይወት ነው። ት/ቤትም ነው። መማር የግድ ዩንቨርስቲ ብቻ ገብቶ አይደለም። ስለሆነም ህሊናን የማልማት አቅም አለው ይሄ የሦስትዮሽ ውይይት። እምታደውም እዚህ አውደ ምህረት ብቻ ነው። ስለማተርፍበት። በሌላ በኩል የተለዩ አማራጭ ሃሳቦችን ስለሚያስተናግድም አይሰለችም። በሃሳብ ዙሪያ የሌላውን መንፈስ ሳይጫኑ ውይይቶች ከተካሄዱ አጓጒ እና ተናፋቂ ይሆናሉ። ስሜቱ ነው በራሱ ጊዜ እና አቅም ወደ ሚፈልገው አቅጣጫ የሚወስደው። እውነተኛ ስበሰባ ላይ የተቀመጥኩ እስኪመስለኝ ድረስ ወስጤን ፈቅጄ ሁለት ጊዜ አዳመጥኩት።

የእኔ ዕይታ።  

ከጋዜጠኛ ምናላቸው ስማቸው ስነሳ፤ የህውሃት ማዕከላዊ ኮሜቴ ውሳኔውን ወደ ታች አውርዶ የማወያዬት ጉዳይ ሊሆን እንደማይችል ነው በአጽህኖት የገለጸው። ጋዜጠኛ ኤርምያስ ለገሰ ደግሞ ከዚህ ቀደም የነበረውን „የባድመን“ ጉዳይን አንስቶ አባላቱ እንደገና ሊወያዩበት ሊወስኑበት /የውሳኔ ሃሳብ ሊያቀርቡበት/ እንደሚችሉ ገልጧል። ውሳኔ ሊያሰጡ የሚችሉ ጉዳዮች የትኛቹ ናቸው፤ የማያስፈልጋቸውስ …? ስለምን?

በዚህ እሳቤ እንደ ፓርቲ ህገ – ደንብ ከተሄደ ጋዜጠኛ ምናላቸው ስማቸው ያለው ትክክል ነው። መርኽም ነው። እኔም እምጋራው የእሱን ጽኑ አቋም ነው። ስለሆነም ትንሽ ዘለግ አድርጌ አብራርቼ የጋዜጠኛ ምናላቸውን ሃሳብ በንደፈ ሃሳብ ላጠናክረው እንሆ ፈቀድኩኝ። ስለምን? የማርክሲስት ሌኒኒስት የፓርቲ አደረጃጃት መርሁ ለሚከተለው ለወያኔ ሃርነት ትግራይ የጎሳ ኪሚልሱንጋዊ ፓርቲ የቁመናው መለኪያ መሰረት ስለሆነ። የውስጥ አካሉ Organ ነው። የእኛም አትኩሮት ሆነ ልብ ፍተሻው በዚህ ዙሪያ ሊሆን ይገባዋል የሚልም ዕድምታም አለኝ። ነጮቹ እራሳቸው ይህን ጉድ አያወቁትም። የደህንነት አካሎቻቸው እራሱ ስለምን በዚህ ዙሪያ እንደማያተኩር አይገባኝም። ግራ ነገር።

ማሳሰቢያ።

በስበሰባ ሥርዓተ – ደንብ ማሳሰቢያ ይቀድማል። ስለሆነም በምዘረዝራቸው መንፈሶች ሁሉ ኢትዮጵያ በምን ዓይነት የአማራር ሁኔታ፤ በእነማን የህሊና አቅም እዬተመራች እንዳለ፤ በዬትኛው ርዕዮት ዓለም እዬተጓዘች እንደሆነ፤ በዬትኛው የአደረጃጃት መርህ እዬተጠቃች እንደሆነ፤ እያንዳንዱ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ተራ አባል በኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ያለው ሙሉዑ አቅም እና ችሎታ ከዬት እንደመነጬ፤ የችግራችን መባዮ በምን መልክ እንደሚዋቀር፤ ሁሉንም ልጆቿን ሊወክል በማይችል ዝንጣፊ ውክልና ምን ያህል ዓመት እንደ ቆጠረች …  ሁሉንም ዕይታዎቼን ስገልጽ „ኢትዮጵያን“ አብራችሁ እንድታዩት ማስገንዘብ እሻለሁ – በትህትና።

እህት ድርጅቶችም የሚባሉት የክልላዊ ፕሬዚዳንትን ሆነ „ክልላዊ“ ሥልጣናቸው ምንጩ፤ ሃይሉ ከዬት እንደሚቀዳ፤ እያንዳንዷ ስንዝር የኮቲያቸው ትንፋሽ በማን የውሳኔ ምርኩዝ እንደሚጸድቅ በማስተዋል ሆነው ሊያስብቡት ይገባል። „ልብ ያላቸው ከህሊናቸው ጋር ያሉ ክልሎች ካሉ“ በተጨማሪም እንዴት በአንድ የወያኔ ሃርነት ትግራይ አባልነት ባለው ሚና በብልጫ እነሱ አለን የሚሏቸው አባላት እስከ ታችኛው መዋቅራቸው ድረስ እዬተገዘገዙ ስለመሆኑም ልብ ብለው እንዲከታተሉት ማሳሰብ እሻለሁ – በአክብሮት። ስለምን? „ወያኔ ሃርነት ትግራይ በሚሰጠን አጀንዳ ላይ ይተኮራል“ ለሚሉት ወገኖቼም የተስፋችን፤ የራዕያችን ማነቆ ሆነ የጉሮሮ አጥንት ማዕከል ይህ የወያኔ ሃርነት ትግራይ የጎሳ ኪሚልሱንጋዊ ፓርቲ ስለመሆኑ ከልባቸው ሁነው ሊያስተውሉት ስለሚገባ ነው ዛሬ ይህን ጹሑፍ መጻፍ ያሰኘኝ። እነዚህ እህት ድርጅቶች የሚባሉትም በሙሉ ከዚህ የተሻለ ጊዜ የላቸውም በጨርቅ የተጠቀሉበትን „ኢህድግ“ የሚሉትን አውጪ ጃኬት አውልቀው የሚያቃጥሉበት። አውጪ እንሰሳ ነው። አነር ይመስላል። የሚሄደው በደረቱ ነው። ሌሊት – ሌሊት ትኩስ የሰው ሬሳን እዬቆፈረ – እያወጣ የሚበላ እነሰሳ ነው።

ስሆነም የወያኔ ሃርነት ትግራይ ጎሳዊ የኪሚልሱንጋዊ ፓርቲ የሚያካሂደው የአባላቱ የውክልና ጠቅላላ ጉባኤ/ ማዕከላዊ ኮሚቴ/ ፖሊት ቢሮ  ስብሰባዎች ብሄራዊ/ ሐገራዊ ስለመሆኑ ለአፍታም ልንዘነጋው አይገባም። ክራሞቱን የባጀውን የህውሃት ማዕከላዊ ኮሜቴም የትግራይ ብቻ ጉዳይ አድርጎ መመልከት ጅልነት ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ በሶሻሊዝም ርዕዮት፤ በጎሳዊ ፍልስፍና ስለመመራቷም ለአፍታ ቸል ልንለው አይገባም። ከዚህ ላይ ከሶሻሊዝም ከሥነ- ምግባሩ ያፈነገጡ፤ ከኢትዮጵያዊንት ሞራላዊ ሥነ – ምግባሮችም በእጅጉ የወጡ የወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች በደባልነት የተቀዳጇቸው ተጨማሪ ያዘሏቸው ህጸፆች በተደራቢነት እንደ ተጠበቁ ሆነው።

የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ።

በዬትኛውም ደረጃ የሚካሄድ የአባላት የውክልና ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው ትልቁ ወይንም በኽረ አካል ነው። እጬጌ ነው። ማናቸውም ውሳኔ የሚሰጥበት፤ ፕሮግራሙና ደንቡ የሚጸድቁበት ወይንም የሚሻሸሉበት፤ ወይንም አዲስ ፕሮግራም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አባላቱ በረቂቁ ከተዋያዩበት በኋዋላ ይሁንታ የሚያገኝበት። የተከናወኑ ተግባርት ሪፖርት የሚደመጥበት። ለቀጣዩ ጊዜ ዕቅድ/ ፖሊሲ የሚነደፍበት። ጉባውኤው እስኪሰበሰብ ድርስ የፓርቲውን ተግባርና ሃላፊነት፤ የሚወጡ መሪ አካላቱ የሚሚመረጡበት ነው።

  • በድንቡ ውስጥ ዓርማው፤ የአባላት መብትና ግዴታ፤ የፓርቲው መጠሪያ …. የሚጸድቅበት ሲሆን የፓርቲው ደንብና ፕሮግራም የአባላቱ የፖለቲካ ህይወት መርሆዎች ናቸው – እስከ ሞት ድርስ። ቃልኪዳኑም ጥብቅና ገራራ ነው።

ታላላቅ የፓርቲው መዋቅራዊ አካላት ማለትም ማዕከላዊ ኮሜቴ እና ኤዲቲንግ/ ቁጥጥር አካላት በድምጽ ብልጫ በድርጅታዊ ሥራ የሚመረጡበት በአባላት የውክልና ጠቅላላ ጉባኤው ነው። ከወያኔ ሃርነት ትግራይ አንጻር ስንሄድ ገዢ ፓርቲ ስለሆነ ኢትዮጵያን ቀጥ አድርጎ የሚመራት ይሄው አካል ነው።

የማዕከላዊ ኮሚቴው እና የቁጥጥር አካላት ተጠሪነት።

ማዕከላዊ ኮሜቴው እና ቁጥጥር አካሉ ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለጠቅላላ ጉባኤ ይሆናል። የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የቁጥጥር አካሉ/ ኤዲቲንጉ ምርጫ የሚከወነው በጠቅላላ ጉባኤ ይሆናል። ማዕከላዊ ኮሜቴ የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ በሰጠው ሥልጣን መሠረት፤ የራሱን ስብሰባ ያደርግ እና የፖሊት ቢሮውን በሚስጢር ወይንም በግልጽ ድምጽ አሰጣጥ ሥርዓት ይመርጣል፤ የሥራ ድልድም ያደርጋል። ቁጥጥር አካሉም/ ኤዲቲንግ አካሉም የራሱን ስብሰባ አድርጎ ሰብሳቢውን እና ጸሐፊውን በመምረጥ የሥራ ድልድል ያደርጋል።

ማዕከላዊ ኮሚቴው እና ቁጥጥር ኮሜቴው ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለመረጣቸው አካል ብሄራዊ/ ክልለላዊ ለጠቅላላ ጉባኤ ብቻ ይሆናል። ሥልጣን የሰጣቸው እሱ ነውና። በዬትኛውም ደረጃ የሚካሄደው የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ እሱ ድጋሚ እሰኪሰበሰብ ድረስ በመደበኛ ይሁን በአስቸኳይ ጉባኤ ካልገጠመው በስተቀር በመደበኛ የጉባኤው የጊዜ ሰንጠረዥ እስኪመለስ ድረስ ሙሉ ሥልጣኑን ለማዕከላዊ ኮሜቴው እና ለቁጥጥሩ አካሉ ይሰጣል። ይህ ማለት የአባላት ጠቅላላ የውክልና ጉባኤ እስኪሰበሰብ ድረስ ፖሊት ቢሮው ያላተሸራረፈ፤ ያልተበጣጠቀ፤ ያልተበቀ ሙሉዑ ስልጣን አለው ማለት ነው። የማዕከላዊ ኮሜቴው አባላት ቅሬታ ቢኖርባቸው የፈለገ መረብ ቢሰሩ በግል ባለ ቅሬታዊ ትንኮሳ የሻቱትን ለማግኘት ይህንን መርህ ጥሶ መውጣት አይቻልም። ሥነ – ምግባሩ ጥብቅ ነው – ከብረትም።

የማዕከላዊ ኮሚቴው ሥልጣንና ቁልፍ ሃላፊነት።

የኢትዮጵያ የተስፋ ሞት የሚታወጅበት ነው። ለቀጣዩ ጊዜ የትግራይ ሥረወ – መንግሥት በኢትዮጵያ ስለሚቀጥልበት ሁኔታ የሚመከርበት፤ የሚዘከርበት የጭቆና ስልት ሴራም በረቀቀ ሁኔታ ከተጨባጩ ገዢ ሁኔታ ጋር ተገናዝቦ የሚታጭበት ነው። ለተፈጻሚነቱ ለአባላቱ አዲስ ድርጅታዊ ግዴታ የሚታደለበት ሲሆን፤ ሌሎች እህት የሚባሉት ፓርቲዎች ደግሞ እንዴት ሰጥ-ለጥ ብለው፤ ክብራቸውን ሽጠው፤ ውስጣቸውን ሸልመው፤ በራሳቸው ውስጥ ወልቀው የሚመሩትን ህዝብ እያሳረዱ፣ እያሳስሩ ተቀጥቅጣው የሚገዙበት ንድፍ የሚቀረጽበት እና የሚጸድቅበት ነው። ሪፖርተር ጻፈው አልጻፈው ዕውነቱ እራሱ ይህን ይጸፈዋል። የኢትዮጵያ ማናቸውም ውሳኔ፤ ፖሊሲ፤ ዓዋጅ፤ ህግ መንግሥት፤ የአፈጻጻም መመሪያ የሚፈልቀው ከዚህው ከወያኔ ሃርነት ማንፌስቶ ማህጸን ነው። ሰከን ባለ ሁኔታ ተመስጥሮ የሚያዙ የሸር ሰንሰሎቶች ለመዘርጋት የሚሰናዱበት፤ የኢትዮጵያ የመከራ ዓውደ ነው የወያኔ ሃርነት ትግራይ የማዕከላዊ ኮሜቴ ስበሰባ። ጉባኤ ላይ የማይነሱ ግርዶሻዊ አመክንዮች ሁሉ እርገታቸው በዚህው ስብሰባ ተመስጥሮ ይከወናል። የሴራ ዋሻ ነው ለሐገር ውስጥ ይሁን ለውጪ ሐገር ዲፕሎማሲያዊ ቀጣይ ግንኙነትም።

የፖሊት ቢሮው ተጠሪነት።

የፖሊት ቢሮው ሥ/አስፈጻሚ ኮሜቴው ተጠሪነቱ ለመረጠው አካል፤ ሥልጣኑን ለሰጠው አካል ለማዕከላዊ ኮሜቴ ብቻ ይሆናል። እንደ ቁጥጥር/ ኤዲቲንግ አካሉ ለጠቅላላ ጉባኤው አይደለም። ምክንያቱም ፖሊት ቢሮው የወጣው/ የሚወለደው ከአባላት የውክልና ጠቅላላ ጉባኤ ሳይሆን፤ ጉባኤው ከመረጠው ከማዕከላዊ ኮሜቴው ነው የሚወለደው። ጉባኤው ለፖሊት ቢሮው አያቱ ነው። ፖሊት ቢሮው የማዕከላዊ ኮሜቴው ልጅ ነው። ማዕከላዊ ኮሜቴው በመደበኛ ይሁን በአስቸኳይ ስበስባ ጊዜ እስኪገናኝ ድረስ ሙሉ የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ለማዕከላዊ ኮሜቴው የሰጠውን ሙሉ ሥልጣን እና ሃላፊነት ደግሞ ለፖሊት ቢሮው ያሰረክባል። ይህ ማለት ፖሊት ቢሮው ማዕከላዊ ኮሜቴ የሚወስነውን ማናቸውንም ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ ዕለታዊ ትንፋሹ ይሆናል። ይህ ሥልጣን ለፖሊት ቢሮው የሰጠው የአባላት የውክልና ጠቅላላ ጉባኤ ሳይሆን ማዕከላዊ ኮሚቴው ነው። ፖሊት ቢሮው የተሰጠውን ሃላፊነት ተግባራዊ ለማድረግም በሥሩ የተለያዩ አጋዥ አካላትን የመምረጥ፤ የአፈጻጸም መመሪያዎችን አውጥቶ የማስተላለፍ፤ አፈጻጸማቸውን በቅርብ የሚከታታል ተጨማሪ አካላትን የማዋቀር፤ መደበኛ ሠራተኞችን ከአባላቱ ውስጥ የመምረጥ፤ የመመደብ፤ ውሳኔ የመስጠት፤ ለስልጠና የመላክ፤ በተሰጠው የሃላፊነት ዙሪያ የመንቀሳቀስ ሙሉ ሥልጣን አለው። ይህ ማለት ፖሊት ቢሮ የሚወስዳቸው ማናቸውም እርምጃዎች፤ የሚያስተላልፋቸው ማናቸውም የአፈጻጻም መመሪያዎች፤ ውሳኔዎች እሰከ ሴል ድረስ ተፈጻሚ ይሆናል ማለት ነው። ፖሊት ቢሮው ሥልጣኑ ከራሱ ከጎሳ ፓርቲው የተዋረድ የውስጥ መዋቅራዊ አመራር ጋር ብቻም ሳይሆን መንግሥታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትንም በባላይነት ይመራል። ፖሊት ቢሮው ስለከወናቸው ተግባራት እና ስለገጠሙት የአፈጻጻም ችግሮች ሪፖርትም ለማዕከላዊ ኮሜቴው ያቀርባል።

በዚህ ስሌት በፓርቲው ህይወት ውስጥ የዕለት – ተለት ተግባርን የሚከውነው ተጠሪነቱ ለማዕከላዊ ኮሜቴ የሆነው የሥራ አስፈጻሚው ወይንም የፖሊት ቢሮ አካል፤ እና ተጠሪነቱ ለማዕከላዊ ኮሜቴ ያለሆነው የቁጥጥር/ ኤዲቲን አካሉ ይሆናሉ ማለት ነው። አበክሬ መግለጽ የምሻው የተጠሪነት ጉዳይ ቀደም ብዬም እንደገለጽኩት ቁጥጥር/ ኤዲቲ ኮሜቴው ሥሙ እንደ የፓርቲው ዓይነት ሊለያይ ይቻላል፤ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለጠቅላላ ጉባኤው ሲሆን ከማዕከላዊ ኮሚቴው የወጣው የፖሊት ቢሮ/ ወይንም ሥ/አስፈጻሚው ግን ተጠሪነቱ ለማዕከላዊ ኮሜቴ ብቻ ይሆናል። ሁለቱ የሚኖራቸው ግንኙነት ጎናዊ ነው።

ይህ ማለት ማዕከላዊ ኮሜቴ እሰኪሰበሰብ ድረስ የፓርቲውን ዕለታዊ ተግባር ፖሊት ቢሮው በበላይነት እንዲከውን ማዕከላዊ ኮሜቴው ለልጁ ለፖሊት ቢሮው ሙሉ ሥልጣኑን  ይሰጠዋል ማለት ነው። ይህ ህግ ነው። የማይደፈር – የማይገሰስ የሶሻሊዝም ፍልስፍና። አባላቱም አባል ሲሆኑ ይህን ህገ – ደንብ የህይወታችን መርህ ብለው አምነው ተቀበለው ነው። የመምረጥ ሆነ የመመረጥ መብት አባላቱ እንዳላቸው ሁሉ፤ በዬደረጃው ባሉ የበላይ የተዋረድ የውክልና አካላት የሚሰጡትን መመሪያም ያለምንም ማቅማማት የመፈጸም እና የማስፈጸም ጽኑ ግዴታ አለባቸው። በማርክሲስት ሌኒኒስት ፍልስፍና ማዕከላዊነቱ ጥብቅ ሲሆን ዴሞክራሲው ደግሞ ልል ነው። ይህን በራሺያ፤ በግማሿ ኮርያ፤ በቻይና እና በኪዮባ ማዬት ይቻላል። በኢትዮጵያም በዘመነ ኢሠፓ ይሄው የአሰራር ሂደት ነው የነበረው። ልዩነቱ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የጎሳ ለዛውም የአንድ ጎሳ እና የአንድ ክ/ሐገር ብቸኛ መሪ ፓርቲ ከመሆኑ ላይ ብቻ ሲሆን ኢሠፓ ደግሞ 13ክ/ሀገራት እና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያያዙ አባላት ነበሩት። ኢሠፓ ሆነ ህውሃት የርዕዮት ዓለም ሆነ የአደረጃጃት መርኽ ልዩነት የላቸውም። በሁለቱ መንፈስ ውስጥ ሶሻሊዝም ነው ያለው። በእነሱ ብቻም አይደለም በማሌ ርዕዮት የተገሩ ሀገራዊ ፓርቲዎች ሁሉ በዚህ ቅኝት ውስጥ ናቸው። ስለምን? ስልጣን የማይከፋፈልበት የመዋለ ዕድሜ ሊቀመንበርነት/ ሰብሳቢነት የሚረጋገጥበት፤ ሌላውን እያደካሙ ወይንም እዬዋጡ የራስን ማንፌስቶ አውራ ፓርቲ አድርጎ የሚያኖር፤ የዕድሜ ልክ የሥልጣን ሐዋልትነት የሚቸረው ደጉ ሶሻሊዝም ብቻ ስለሆነ። የተፎካካሪ ፓርቲ የፈቃድ አሰጣጥ የሚባለው የለበጣ ነው። ቀን ስብከት ማታ ንደት እና ፍረሰት እኩይ ውርሰቱ ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መርሁ ያደረገው ከሶሻሊዝም/ ህብረተሰባዊነት ፍልስፍና የተቀዳ ነው።

እጅግ የሚገርመኝ እና የሚደንቀኝ ጀርመኖች ይህንን መከራ እንዴት ተሻግረው ለዛውም በሶሻሊስቱ መንደር፤ የማሌን ርዕዮት ወተት ጠጥተው ያደጉት የደግነት፤ የመቻቻል ግሎባል እናት የሆኑት ክብርት ጠ/ሚር አንጅላ ሜርክል ለዚህ ዓለም አቀፍ አብነት እንደበቁ ነው። ልቅላቂ ነገር የለውም ካቢናቸው። ለዛውም ካርል ማርክስ በተፈጠረበት ሐገር። ዘመነ ሂትለርም እዛው ነው። ይህን ሽንቁርቁር ፈተና አልፈው፤ አሸንፈውም ዕውነተኛው የሰብዕዊነት መንፈስ፤ ዕውነተኛው የዴሞክራሲ ህይወትን እዛ ታዬቱላችሁ፤ በሥልጣን ተዋረዱ ብቻ ሳይሆን በሚዲያው፤ በኤኮኖሚው፤ በፍትሁ፤ በማህበራዊ ህይወቱ፤ በህግ ጥበቃው፤ በሃይማኖታዊ ተቋማት፤ በወጉ፤ በልማዱ፤ በባህሉ፤ በአዳዲስ ሃሳብ አፍላቂ ፈላስፋዎች፤ በጸሐፍት ክብር እና ድጋፍ ጥበቃና ዕውቅና በመስጠቱ፤ አዳዲስ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በቅንነት በማሳተፉ፤ በብሄራዊ ሐገራዊ ንጹህ ፍቅር ጥበቡ ለዛው – ጠረኑ ልዩ ነው። ለጋህዱ ዓለም የመንፈስ ቅዱስ ምግብ ነው። አዲስ የተፈጠረው ናዚዝም ፓርቲ በጀርመን ዕድሉን አግኝቶ ሁለቱን ታላላቅ ፓርቲዎች እጅግም ፈታኝ ተፎካካሪ ፓርቲ ሆኖ ነበር የዘንድሮው ምርጫው የተጠናቀቀው። ቀደምቶች ከሌላ ፓርቲ ጋር ተዳብለው አብላጭ ድምጽን የማግኘት ስልት እሰኪ ነድፉ ድረስ ያስገደደ። የሚገርመው ይህ አዲስ ናዚዊ ፓርቲ ሌሎችን ቀደምቶችን፤ ተወዳጆችን ፓርቲዎች እንደ ግሪን ፓርቲዎችን ዘርሮ ጠንካሮችን አንጋፋ ሁለቱን ፓርቲዎችን ድምጻቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሸርሽሮና ውስዶ ሦስተኛ ፓርቲ ለመሆን በቅቷል። እኛ ይሄን እንዴት ልናመጣው እንችል ይሆን? ከሶሻሊዝም ልቅላቂ መንፈስ ጋር ፍቺ በዘለቄታ ካልመጣ በስተቀር ቅንነት አይገኝም። ቅንነት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የጾም ውሃ ነው። ቅንነት ከሌለ ደግሞ ሐገራዊ ህልሙ ርቃን ነው። ይሄ ለእኔ እረፍት የማይሰጠኝ የአመክንዮ ንጥረ ነገር ነው። ሌላውን ስንተች እኛ በተቸነው ሂደት ውስጥ ስለመሆናችን እንኳን ማዬት የተሰነን ነን። እኛን ለመገሰጽ ቆራጣ – ቆራጥ ፍላጎት የለልን። ስህተታችን ተነግሮን እንኳን ለማረም የማንፈቅድ። ተሽሎ መገኘት የታከተን።

የሥልጣን ሹም ሽር።  

የፖሊት ቢሮውን የማሰናበት፤ ከሥልጣን ዝቅ የማድረግ፤ የማገድ፤ ወይንም የማሸጋሸግ መብት ያለው ማዕከላዊ ኮሜቴው ብቻ ይሆናል። ነገር ግን አንድን የማዕከላዊ ኮሜቴ አባል ከማዕከላዊ ኮሜቴ አባልነት የማገድ ወይንም የማባረር ሥልጣን ማዕከላዊ ኮሚቴ በፍጹም ሁኔታ የለውም። ከማዕከላዊ ኮሜቴ ለማባረር የግድ ጉባኤውን መጠበቅ ግድ ይላል። አሁን የወ/ሮ አዜብ መስፍን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እገዳ የሚታዬው ከዚህ አናፃር ነው። ማዕከላዊ ኮሜቴ ውክልና ከሰጠው፤ ራሱ ከመረጠው ከፖሊት ቢሮ ወይንም የማሰናበት ሥልጣን ቢኖረውም፤ ከማዕከላዊ ኮሜቴ ግን አይችልም። ስለምን? ማዕከላዊ ኮሜቴውን የመረጠው የአባላቱ የውክልና ጠቅላላ ጉባኤው ስለሆነ። ማዕከላዊ ኮሜቴው አንድን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የማገድ ሆነ የማግለል ሥልጣኑ የእሱ ስላልሆነ። ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ከማዕከላዊ ኮሜቴ ማገዱ በራሱ በዚህ እነሱ በሚከተሉት የማርክስት ሌኒኒስት የአደረጃጃት መርህ አይፈቅድም። የአባላቱን ጠቅላላ ጉባኤው መጠበቅ ነበረበት ወይንም የወያኔ ሃርነት የጎሳ ፓርቲው አስቸጋሪ ጊዜ ላይ ስለሆነ መደበኛውን የጉባኤ ጊዜ ሳይጠብቅ ልዩ የጉባኤ ጥሪ ማድረግ ነበረበት። ይህ ዝበት አለበት። እንግዲህ መከላከያው ከወ/ሮ አዜብ ጎን መሆኑ ስለሚታወቅ አዲሶቹ ባልሥልጣናት በስልትና በዘዴ እስኪደላደሉ ድረስ መከላከያውን ለማዘናጋት የፈጠሩት፤ ፈንገጥ ያለ ስልት ይመስላል። የፈሩት ነገር እንዳለም ቁርጥራጭ ፍንጭም ይሰጣል። ስለዚህ በመሃል ያልታሰበ አዲስ ያፈነገጠ ነገር ሊኖር ይችል ይሆን ያሰኛል …

በሌላ በኩል ግን ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ከሥራ አስፈጻሚ አካልነት ማገድ የአባላት የውክልና ጠቅላላ ጉባኤው እስኪሰበሰብ ጊዜ ድርስ ሳይሰጠብቅ ጉባኤው በሰጠው ሙሉ ሥልጣን ተጠቅሞ ማዕከላዊ ኮሜቴው የፖሊት ቢሮ አባላነታቸውን የመሰረዝ ሙሉ መብትም አለው። አይደለም ለተወሰነ ጊዜ የማግለል … እንደገናም ይህ ውሳኔ ታች ወርዶ ውይይት አይደረግበት – በፍጹም። አባላቱ እኮ ሥልጣኑን አስረክቧል ለማዕከላዊ ኮሜቴው። ፖሊት ቢሮው ደግሞ የተወለደው ከማዕከላዊ ኮሚቴው ነው። ስለዚህ አባሉ መቀበል ብቻ ነው መብቱ።

ከዚህ ላይ ነው የእኔ እና የጋዜጠኛ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ሙግት የማይጣጣመው። በሌላ በኩል የጋዜጠኛ ምናላቸው ስማቸው ሃሳብ ደግሞ ከእኔ ሃሳብ ጋር የሚዋዋጠው። ልድገመው … ይህን ወ/ሮ አዜብን ከፖሊት ቢሮ አባል የማገድ ውሳኔ አባላቱ የመቀበል እንጂ የመሻር ወይንም የመለወጥ ቁራጭ ስልጣን የላቸውም። ምክንያቱም የጉባኤ አባላት ማዕከላዊ ኮሜቴውን ሲመርጡ መብታቸውን ተጠቅመው ሙሉ ሥልጣናቸውን ለማዕከላዊ ኮሜቴ ፈቅደው እስከ ሰጡ ድረስ። ማዕከላዊ ኮሜቴ ደግሞ በተሰጠው ሥልጣን ተጠቅሞ በድምጽ ብልጫ ፖሊት ቢሮውን የመምርጥ፤ ከሥልጣን የማወረድ፤ የማገድ፤ የማባረር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል። ማዕከላዊ ኮሚቴው የፖሊት ቢሮ አባላትን ሲያስወግድ ሥር ላይ የሚገኙትን የመሰረታዊ ድርጅቱ የአባላት ይሁንታ መጠበቅ በምንም ሁኔታ አያስፈልገውም። የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ መብታቸው የነበረው አሁን ያለውን ማዕከላዊ ኮሜቴ አባላትን የመረጡ ዕለት ነበር። ከምርጫ በኋዋላ የሚኖረው ያን ጊዜ በድምጽ ብልጫ እንዲመረጥ ያደረጉትን የማዕከላዊ ኮሜቴ ውሳኔ የመፈጸም ግዴታ ብቻ ነው ያላቸው። ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በዚህ መልክ ነው ወደ ተግባር የሚሸጋገረው። እስከ ከጣዩ የጉባኤ ጊዜ ድረስ ይህ ውሳኔ የጸና ይሆናል። ለዚህም ነው ማዕከላዊ ኮሜቴ በፖሊት ቢሮው ላይ ማናቸውንም እርምጃ የመውሰድ ሙሉዑ ሥልጣን የሚኖረው። ለዚህም ነው የወያኔ ሃርነት ትግራይ የአባላት የውክልና ህጋዊ ጠቅላላ ጉባኤው ከመካሄዱ በፊት እርምጃው እንዲቀድም ያደረገው … ጉባኤው እሰኪሰበሰብ ድርስ የመቆዬት ግዴታ የለበትም።

ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ ተጨማሪ ጹሑፍ ያነበብኩት ከላይ ለጥፌዋለሁ የወ/ሮ አዜብ መስፍን ጉዳይን የአባላት የውክልና ጉባኤ በቀጥታ ፖሊት ቢሮውን ሊመርጥ አይችልም። በፍጹም። ጉባኤው ያለው መብት ማዕከላዊ ኮሚቴውን ነበሩን እንዲቀጥል፤ እንዲሸጋሸግ፤ ወይንም በሙሉ አውርዶ አዲስ መምረጥ ብቻ ነው። ፖሊት ቢሮው የሚወለደው ከማዕከላዊ ኮሜቴ  እንጂ ከጉባኤው አይደለም። ነገር ግን ወ/ሮ አዜብን መስፍንን የተጠለባቸውን የማዕከላዊ ኮሜቴ እግዳ ሊያነሳላቸው ወይንም ውሳኔውን ሊያጸድቅባቸው ይችላል – ጉባኤው። የማዕከላዊ ኮሜቴ አባልነታቸውን የሰጣቸው ይህ አካል ስለሆነ – ጉባኤው። ወደ ፖሊት ቢሮ አካልነት ግን መብቱ የማዕከላዊ ኮሜቴው እንጂ የጉባኤው አይደለም።

ሌላው አባላቱ የህውሃት ጠንካራ ሙሉ አቅም ያላቸው ስለመሆናቸው ጋዜጠኛ ኤርምያስ ለገሰ ነግሮናል። አሁን ከዚህ ላይ የአባላቱ አቅም ሳይሆን የመርህ አፈጻጸም ነው የሚታዬው። ጠቅላላ ጉባኤው ማዕከላዊ ኮሚቴውን ሲመርጥ ነው ይህ መብት ተላልፎ  ለማዕከላዊ ኮሜቴ የተሰጠው። የማከብርህ ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ኤርምያስ ለገሰ ስትመርጥ አንጻራዊ መብት ሲኖርህ፤ ከመረጥክ ብኋዋላ ግን አንተ የመረጥከው አካል ለሚያሳልፈው ውሳኔ፤ ለሚወስዳቸው እርምጃዎች ተገዥ የመሆን ጽኑ የማሌ ፓርቲ ግዴታ አለብህ። ሌላው ቀርቶ ውሳኔ ላይ የድምጽ ልዩነት/ ተዕቅቦ ቢኖርህ እንኳን እያንዳንዱ የፓርቲ አባል የብዙሃኑ ውሳኔ በጥቂቱ ዘንድ ተፈጻሚ እንዲሆን መፍቀድ ከግዴታቸው ውስጥ አንኳሩ ነው። ይህም ብቻ አይደለም በዚህ መንፈስ ውስጥ ኩርፊያ እንኳን ሊኖር አይገባም። በዕውን ለአንድ የፓርቲ ደንብ ለሚገዛ ዲስፕሊንድ የፓርቲ አባል። የአንተ ሃሳብ ተሸናፊ ሲሆን ደስ ብሎህ ነው የምትፈጽመው። በዚህ ድርድር የለውም። ዲስፕሊኑም አይፈቅድም። ማፈንገጥ ከመጣ አናርኪዝም ነው የሚሆነው። አላስፈላጊ መስዋዕትንትንም ነው የሚያስከፍለው። ይህን በምልሰት የቮልሸቢክ እና የሜንሼቢክን ታሪክ ማንበብ ይጠይቃል። በዚህ ትርምስ ውስጥ ፉክክሩ በበላይነት በመምራት በኢጎ ላይ ከተመሰረተ ግን አሁንም አድብቶ/ ሸምቆ የቆዬ አፈንጋጭ መንፈስ በመፈንቅለ መንግሥት ፍንገጣውን ሊያወራርድ ይችል ይሆናል … ይህንም መጠበቅ አይከፋም። መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በዕድሉ የለውጥ ፈላጊው እንዴት ልጠቀምበት እችላለሁ፤ ቢሆን እንኳን ብሎ የትንበያ ማህደር ቢኖረው አይከፋም።  … ስልትና እስትራቴጅም በመንፈሱ መንደፍ ይኖርበታል፤ ግን እንደ ተለመደው በዓዋጅ መሆን የለበትም፤ ጠብቆ ማቆዬት። የስልት እና የስትራቴጅ ሚስጢር ከተዘረዘረ እንደ ቄጠማ መሸነፍ ከተጠበቀ ማሸነፍም ነው።

የአደረጃጀት መርህ።

ለአንድ ለማርክሲስት ሌሊኒስት ፓርቲ የአደራጃጀት መርህ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ጭንቅላቱ ነው። ደሙ ነው። መተንፈሻ ቧንቧው ነው። መርሁ ዴሞክራሲ መብትን/ ማዕከላዊነት ግዴታን አጣምሮ የያዘ ፍልስፍና ነው። „መብት“ ስለሚለው ዝቅ ብዬ ራሱን አስችዬ አብራራዋለሁ። የሆነ ሆኖ በዚህ ፍልስፍና አንድ የፓርቲ አባል መብቱን ተጠቅሞ ውሳኔ ካሳለፈ በኋዋላ ላሳለፈው ውሳኔ የመገዛት ግዴታ አለበት ማለት ነው። ይህ ማለት ጠቅላላው ጉባኤ እሰኪሰበሰብ ድረስ የጠቅላላ ጉባኤውን ሙሉ ሃላፊነትና ሥልጣን የሚረከበው ማዕከላዊ ኮሜቴ ይሆናል ማለት ነው። ስለሆነም ማዕከላዊ ኮሜቴ የሚያሳልፈው ውሳኔ በሁሉም በአባላቱ ዘንድ ተፈጻሚ የመሆን ግዴታ አለበት። በዚህ መርህ መሰረትነት ማዕከላዊ ኮሜቴ እስኪሰበሰብ ድረስ ደግሞ የፖሊት ቢሮ የማዕከላዊ ኮሜቴው ማናቸውንም ሥልጣን ተረክቦ ሲሰራ ፖሊት ቢሮው ለሚያሳልፈው ማናቸው ወሳኔ እና የአፈጻጻም መመሪያ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ወታደሮች ይሆኑለታል ማለት ነው። ለመረጡት አካል አቅም ይሆኑለታል። እንቅፋት እንዳይገጥመው ደጀን ይሆኑለታል። ስለዚህም ማዕከላዊ ኮሚቴው አስኪሰበሰብ ድረስ ፖሊቲ ቢሮው የሚያሳልፈው ማናቸውም ውሳኔ አስከ ፓርቲው ሴል/ ህዋስ ድረስ ተግባራዊ ይሆናል። ማዕከላዊ ኮሜቴው ሆነ ፖሊት ቢሮው የአባላት ውክልና ሙሉ ሥልጣን አላቸው ማለት ነው። ለዚህም ነው በዬደረጃው ስብሰባዎች እዬተካሄዱ የሥልጣን ወርርሶች የውክልና ፈሰሶች የሚከወኑት። ወንዙ ግን ያው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ነው። ይህ መርህ የፓርቲው አካላት በተለይም ፖሊት ቢሮው እንዳሻው እንዲዋኝ መተንፈሻ ቧንቧ ነው። ፖሊት ቢሮው ችግር ቢገጥመው አስቸኳይ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስበሰባ እንዲኖር ጥሪ ያቀርባል።

ኤዲቱ/ ቁጥጥር አካሉ ግን ይህን መሰል የከፋ ችግር ቢገጥመው በቀጥታ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራለት ነው የሚያመለክተው። ስለምን? ማዕከላዊ ኮሜቴው እና ቁጥጥር አካሉ  የወጡት ወይንም የመረጣቸው የአባላት ጠቅላላ ጉባኤ ስለሆነ። ስለሆነም በፖሊት ቢሮ ጉዳይ ላይ ማዕከላዊ ኮሚቴው ሙሉ ሥልጣን እና ሙሉ የማድረግ ሃላፊነት አለው ማለት ነው። በዬደራጃው የሚገኙ የፓርቲ አካላትም በዚህ መንፈስ ነው የሚዋቀሩት – የሚሠሩትም።

 መብት በሾሻሊዝም።

ዴሞክራሲ ማዕከላዊነት ላይ የመብትና የግዴታ ቀለበት ውህድነት ይታያል። የሶሻሊዝም የአደረጃጃት መርህ ነው። በዚህ መርኽ መብት የሚባለው ሙሉ አይደለም ሽርፍራፊ ነው። ተከታታይም አይደለም ወጣ ገብ ነው። ጎርባጣ። ቋሚም አይደለም – የተቆራረጠ ጫና የበዛበት መብት ነው። መጠራቅቁ በሴራ የተፈተለ ነው። ግዴታው እጅግ በጣም ተጫኝ Dominant ነው። የሚሰጠው ግዳጅ ሁሉ ነገር በድርጅታዊ መልክ ነው። በራስ ውስጥ ለመኖር ፈቃድ የለም። የነፃነት ነፍስ የተቀበረበት ነው። የጦር ሜዳ የውትድርና ህይወት ነው።

ለምሳሌ ምርጫን እንይ … አባሉ ነፍሱ የሚመርጠውን አይደለም የሚመርጠው፤ በወረቀት እንዲመርጥ በሰንጠረዥ ተሠርቶ የተሰጠውን ብቻ ነው የሚመርጠው። አስፈሪ ሁኔታ ከገጠመ፤ ጠንክር ያለ ሞጋች፤ ተደማጭነት ያለው፤ አዲስ ሃሳብ አፍላቂ ተፎካካሪ ከኖረ፤ ወይንም የማይፈለግ ከሆነ፤ ተፎካካሪው የራሱን ምክንያት ሳይሆን ድርጅቱ የጫነበትን ምክንያት ሰጥቶ እራሱን ከውድድሩ እንዲያገል ድርጅታዊ ግዴታ ይሰጠዋል። ይህን ካልተቀበለ ሞት ነው የሚጠብቀው። ይህ በሶሻሊዝሙ ዓለም ርዕዩት የተቀረጹ ፓርቲዎች፤ በማሌ ፍልስፍና በተቀመሙ በተጠመቁ ማንፌስቶዎች ውስጥ ያሉ የዛ ዘመን ሰዎች ሁሉ የጎሳ በሉት፤ የህብረ ብሄር ፓርቲ የመሠረቱት ሁሉ የሚጋሩት የወል መስመራቸው ይሄው ነው። በሽታም ነው። በሶሻሊዝም የሥልጣን ተዋረድ ለሁልጊዜ፤ ለዕድሜ ልክ መሪነት የሚሆንበትም ምክንያት ይህው ነው። ሥልጣን ያለገደብ ዘላለማዊነት ያጸና ነው። ለዚህም ነው የፖለቲካ ሊሂቃን የፓርቲ መሪዎች ይህን ፍልስፍና የሙጡኝ የሚሉት። ምክንያቱም ስልጣናቸውን ስለሚያዘልቅላቸው። በሶሻሊዝም አንድ ሰው ተመረጠ ከተባለ ሞት ነው የሚገላግለው። ወይንም መፈንቅለ መንግሥት … ይህ ደግሞ በባህሬው ቆሌው አውሬነትን የሚያሸክም ነው የሚሆነው …

የመሠረታዊ ድርጅቶች ሚና እና ድርሻቸው።

የመጨረሻው አካል መሰረታዊ ድርጅት ነው። የመሰረታዊ ድርጅት ስብሰባ አባላቱ በሙሉ ከአለ ውክልና በቀጥታ በአካል በጠቅላላ የሚገኙበት ይሆናል። ከ2/3ኛ በላይ አባላቱ ከተገኙ ምልዕተ ስብሰባው ይካሄዳል። የሚሳልፋቸውም ውሳኔዎች በስበሰባው ባልተገኙት ላይ ሁሉ ሙሉ ተፈጻሚ ይሆናል። የትኛውም ደረጃ ለሥልጣን የሚበቁ አካላት ሁሉ የሚመረጡበት፤ ውክልና የሚያገኙበት ከዚህ መሠረታዊ ድርጅት ይሆናል። የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የኤዲቲንጉ አካልም መነሻቸው ይሄው ነው። መሰረታዊ ድርጅት ላይ ያልተመረጠ ወይንም ለላይኛው የጉባኤ አባልነት ያልተመረጠ አባል የማዕከላዊ ሆነ የፖሊት ቢሮ አባል የመሆን ዕድል የለውም። አፈጻጸሙ ደግሞ በተሟላ የአባላት መብት ሳይሆን በቀጭን ትእዛዝ በድርጅታዊ ሥራ የሚከውን ነው የሚሆነው።

የመሠረታዊ ድርጀቱ ዕለታዊ ተግባር የአባላት መዋጮ መሰብሰብ፤ አዳዲስ አባላትን መመልምል፤ ሴሎችን ማደራጀት፤ መምራት፤ በፓርቲው የበላይ አካላት የሚላኩለትን መመሪያወች ማጥናት – መፈጸም። የጥናት ክበብ ማደራጀት። ሴሎችን/ ህዋሶች በቅርብ መምራት። ሴሎቹ/ ህዋሶች የመረጃ መረብ ማያያዣ ናቸው። በዬትኛውም ሁኔታ በዬትኛውም ቦታ የወያኔ ሃርነትን ጎሳዊ የማሌ ፓርቲ የደህንነቱን ተግባር የሚከውኑ በዚኸው በመሠረታዊ ድርጅቱ አማካኝነት ነው። ወሬ ለቃሚዎች ናቸው። ማህበረ እርኩም። አፋቸው የሾለ ነው። በዬትኛውም ኢትዮጵያዊ „ክልል“ ከላይ አስከታች ቢያንስ ሴሉን ወያኔ ሃርነት ትግራይ ዘርግቷል። ይህ ዕድል ኦህዲድ ኦሮምያ ተብሎ ከተከለለት ውጪ አይኖረውም። ሌላውም እንዲሁ። ምክንያቱም አውራ ፓርቲዎች አይደሉም። ህውሃት ግን ይችላል። ስለምን? ህውሃት ስውሩ ብሄራዊ ፓርቲ ነው እና። ህውሃት ሥውሩ የኢትዮጵያ መንግሥት መሪ ድርጅት ነውና። በዬትም ሁኔታ የትኛውም ክልል ያሉ የትግራይ ልጆች ቢያንስ በሴል/ በህዋስ ደረጃ የተደራጁ ናቸው። በትምህር ተቋማት፤ በመኖሪያ አካባቢዎች፤ በዕምነት ዓውዶች፤ በሥራ አካባቢዎች ውጪ ሐገር ሳይቀር ሴሎች/ ህዋሶች አሉት ህውሃት። ሊንክ አለው … ደህንነቱን ቀጥ አድርጎ የሚይዝበት፤ መረጃዎችን በግልጽነትና በተጠያቂነት የሚቀበልበት/ የሚጠቀምበት/ ለአፈጻጻም በሚያመቸው መልክ አደራጅቶ ወደ ታች እንደገና የሚያፍስበት የትግራዊነት ልዩ ማገር … ምሰሶ … ናቸው ሴሎቹ/ ህዋሶቹ። ለዚህ ጥብቅ የሃላፊነት ሰንሰለት ደሙ ወሳኝ ሚና አለው። ትግራዊነት። ሌላ ሥራዐት ቢመጣም ይህነን በጥብቅ ሥነ ምግባር በመጠቀ ክህሎት ለመናድ ወይንም ለመበጣጠስ የአንድ ትውልድ ጊዜ ይጠይቃል። ለዛውም ብልህ መሪ አማላክ ከሰጠ። ሥርን፤ ውስጥን በማስተዋል የማጥናት አቅም ብቻ ሳይሆን ቅድመ ትንብያ የታደለው ባለመክሊት እረኛ ከተገኘ። ገንዘብ ወርሃዊ መዋጮ ስለከፈለ አይደለም አባልነት ለወያኔ ሃርነት ትግራይ የሚያደርገው። ጽናት እንደ አለት ከተሟላ የፓርቲ ሥርዓት አክባሪነት ጋር ነው። ለትግራይ ልማት ማህበር/ ለማህበረ ተጋሩ/ ግን ተወልጀው ሁሉ አባል ለመሆን ክፍት ነው በሩ።

ሥርዓት

ትልቁ አካል በቀጥታ ለትግራይ / በተዘዋዋሪ ለኢትዮጵያ የአባላቱ የውክልና ጠቅላላ ጉባኤው ሲሆን፤ ይህ ጉባኤ ከታች ከመሠረታዊ ጀምሮ አባላቱ እዬተወከሉበት ሪጅኑን ይፈጠራሉ፤ ሪጅኑ ደግሞ ትግራያዊ አካሉን ጉባኤውን ይፈጥራሉ፤ ጉባኤው ማዕከላዊ አካሉን ይፈጥራል፤ ማዕካላዊ አካሉ ዋንኛ ነፍሱን/ ህይወቱን/ አስኳሉን ፖሊት ቢሮውን ይፈጥራል። በዬትኛውም ደረጃ ለሚገኝ የጉባኤ መደበኛ ሆነ አስቸኳይ፤ የማዕከላዊ ኮሜቴ እንዲሁም የሥ/አስፈጻሚ ወይንም የፖሊት ቢሮ አባል ስብሰባ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ አጀንዳው ለእያንዳንዱ ውክል ተሳታፊ አካል በነፍስ ወከፍ ይላካል። በተሰጠውም የጊዜ ገደብ ተጨማሪ አጀንዳ የማያስያዝ መብትም ይኖራል – ለትግራይ ተወላጅ የህውሃት አባላት ብቻ። የህውሃት መደበኛ ይሁን አስቸኳይ ስብሰባዎች ብቻ ሳይሆን አጀንዳቸው ብሄራዊ መሆናቸው ግድ ነው። ትግራይ ላይ መሆኑም የተገባ ነው። የታላቋ ትግራይ የማንፌስቶው አንጎል ትግራይ ናት። ይህ በራሱ የመንፈስ / የሥነ – ልቦና አቅም ማማረቻ ልዩ ፋፍሪካም ነው … ትንሽ በጥልቀት ገባ ብሎ ውስጡን መፈተሽ ያስፈልጋል ያልኩትም ለዚህ ነው። ወደ ህሊናም ተመልሶ 26 ዓመት የኢትዮጵያ ዘመን የቆረፈደበትን/ የኢትዮጵያ ዘመን ያላቀሰበትን/  የኢትዮጵያ ዘመን የተጫመተረበትን ማጥናት ይጠይቃል። ይህን የአሰራር ሰንሰለት ወያኔ ሃርነትን የሚወቀሱ የትግራይ ልጆች እንዳይነካ የሚፈልጉት አንጎል ጉዳይ ነው። ለዚህ ነው ዶር. አረጋይ በርሄ ላንቃቸው እስከደርቅ ድረስ „በኢትዮጵያ ከሁሉም የተውጣጣ አዲስ ጨቋኝ መደብ ተፈጥሯል እያሉ የሸር ግርዶሽን ሳይታክቱ በተከታታይ እና በታታሪነት የሚገነቡት።“ ይህ ህሊናን ስልብ፤ የተገነዘ የማድረግ ጽልመታዊ ተልዕኮ ነው። ዶር አረጋይ ጥሩ የጥቁር ግርዶሽ ቲያትር/ ተውኔት ጸሐፊ ናቸውና።

የውሳኔ ተፈጻሚነት።

በማናቸውም ጉባኤ/ ማዕከላዊ ኮሜት/ ፖሊት ቢሮ ስበሰባዎች ላይ የተወሰኑ ውሳኔዎች በአባላቱ ዘንድ ካለምንም ማመናታት ተፈጻሚ ይሆናሉ። ከዚህ ላይ በሚስጢር ደግሞ በማናቸውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ላይ ማናቸውም የወያኔ ሃርነት ውሳኔ ተፈጻሚ ይሆናል። ልዩነቱ የትግራይ ልጆች በወሰኑት ላይ ለመረጡት አካል ውሳኔ ተገዢ ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ትንፋሹ በሌለበት ነው ጫን ተደል ቻል ተብሎ የሚጫነው። የተቀረቀረ ሰምጥ የጭቆና ሸለቆ።

ትግራዊው ጥቂቱ ለብዙሃኑ የወያኔ ሃርነት ውሳኔ ይገዛሉ። የብዙሃኑ ውሳኔ በጥቂቶች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል። ለኢትዮጵውያን ግን የጥቂቱ የትግራይ ፖሊት ቢሮ ውሳኔ 5% የትግራይ ህዝብን ውክል አካል የብዙሃኑን 95% ሚሊዮኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ተጭኖ/ ፈጥርቆ ይዞ ይገዛል፤ ያስተዳድራል፤ ይመራል። ይህንን በብልሃት ማዬት ያስፈልጋል። እያንዳንዱን ዜጋ እዬገዛው ያለውን መንፈስ ማን እንደሆነ፤ አጠገቡ ያለ አንድ የህውሃት አባልስ ስለ እሱ ኑሮ / መንፈስ ወሳኝ ስለመሆኑ፤ ፕሮፌስር ይሁን ዶር.፤ ተማራማሪ ይሁን ፈላስፋ፤ ጥበበኛ ይሁን ሊቅ ብቻ አንድ ተራ የህውሃት አባል በመንፈሱ ውስጥ በቅርቡ፤ በአጠገቡ ሆኖ ያ ኢትዮጵያዊ ስለሚከውናቸው ተግባራት ይከታተላል። ሪፖርትም ለበላይ አካሉ ያቀርብል። እስር ቤቱ ቃልቲ፤ ቅሊንጦ፤ ዝዋይ፤ ማዕከላዊ ብቻ ሳይሆን ምን በመሰለ በተንጣለለ ቢሮና ምቹ ሶፋ የሚንፈራሰሰው/ የምትንፈራሰሰው ሚ/ር ወይንም ዲያሪክተር፤ ምን በመሰለ ቅጽር ግቢ የሚንጎባለለው/ የምትንጎባለለው ወ/ሮ እምቤት ድሎተኛ፤ በዛች በወደቀች ዛኒገባ የምትኖረው ምስኪን፤ ጎዳና ላይ ወድቆ የቀን ሃሩሩን የክረምት ዶፉን የተሸከመ/ የተሸከመች ምንዱባን፤ አንጋቹ ሁሉ ለአንድ የወያኔ ሃርነት ትግራይ አባል መንፈስ እጁን የሰጠ ነው። በየሰፈሩም እንዲሁ። አንድ የወያኔ ሃርነት ትግራይ መንፈስ ያረፈበት ትግራዊ/ ያረፈባት ትግራዊት አብሮህ ሲሳራ/ አብራህ ስትሰራ ካለ ግዳጅ እና ካለ ተልዕኮ አይደለም። ይህ እህት ድርጅት የእኔ አባል የሚለው ሁሉ ቅኔው/ ማክዳው ሲገለጥ በቁጥጥር ሥር የዋለ ደመነፍስ የቁጥር ብቻ አባልን ነው የተሸከመ ነው።

ነገረ – የአቶ አባይ ወልዱ።

ወደ አቶ አባይ ወልዱ የውሳኔ አሰጣጥ ስመጣ የአቶ አባይ ወልዱ ጉዳይ አባላቱ እንዲዋያዩበት ወደታች በፍጹም ሁኔታ አይላክም። ወሳኔው የተፈጸመው አሁን ያለው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሜቴን የህውሃት ጠቅላላው ጉባኤው የወሰነ ዕለት ነበር። አባላቱ መቀበል ብቻ ነው ያላቸው ምርጫ። በሌላ በኩል አቶ አባይ ወልዱ የተገለሉት ከፖሊት ቢሮ አባልነት እንጂ ከማዕከላዊ ኮሜቴ አባልነት አይደለም። ከማዕከላዊ ኮሚቴው ቢታገዱ ግን ውሳኔ የሚሰጠው የአባላቱ ጠቅላላ ጉባኤ ስለሆነ የሚጠበቅ አዲስ ነገር ሊኖር ይችል ነበር። ተመልሶ የፖሊት ቢሮ አባል የመሆን እድሉ ያለው አሁን ሥራ ላይ ያለውን የማዕከላዊ ኮሜቴ አባላት ቀጣዩ ጉባኤ ሙሉ ለሙሉ ከአስወገደ ወይንም አሸጋሽጎ ነባሮችን የተወሰኑትን አሰናብቶ አዲሶችን ከተቀበለ ብቻ ነው። ይህም ቢሆን በድምጽ ብልጫ የማሸነፍ አቅም የእነ አቶ አባይ ወልዱ ቡድን ከኖረው ነው።

መቼም የአሁኖቹ ሹመኞች ተኝተው አይጠብቁም፤ ተግተው ይሠራሉ። ተቀናቃኞቻቸውን ሁሉ በግልጽም በስውርም መልክ ያስይዛሉ። እሰከተፈለገው ድንበር ሄደው ጸጥ ያደርጓቸዋል። የወያኔ ሃርነት ትግራይ በዚህ የሰለጠኑበት ነው። ሽፋን ሊሰጡ ይችላሉ ያሏቸውን ሹመኞች ሁሉም ደረጃ በደረጃ ይመነጥራሉ። አቅም ያላቸውንም ቢሆን በተቀናቃኝነት ከተጠረጠሩ፤ ከተንጠራሩም ምንጠራው ያዘንዠብባል። በተለይ መከላከያ ሃይሉን ወደ እነሱ ማስጠጋት ከቻሉ። አሁን የተመረጠውን የሚደግፈው ሚዲያውም አለ እኔ እንደማዬው ከሆነ ብሄራዊ ሚዲያውን ይዟል፤ በሌላ በኩልም ከእህት ፓርቲዎችም ያው ወደ ራስ ለማድረግ አዲስ ፉክክር ጡፎ ይጀመራል … ማራቶን …. ይህ ቀጣዩ የውጊያ/ የፍትጊያ የጉግስ መስክ ትዕይነት ይሆናል።  ማን ይባል „ዘመቻ መልሶ ታላቅነትን ማዳን“ „ዘመቻ ከገደል አፋፍ ላይ የተንጠለጠለውን ታላቅነትን መታደግ“ ከቶ ማን ይባል …?

ከዚህ ላይ ግን የአቶ አባይ ወልዱን ከፖሊት ቢሮ አባልነት እንዲሁም ከሊቀመንበርንት ያስወገዳቸው በኢትዮጵውያን ላይ የፈጸሙት ግፍ አይደለም። ጎንደርን ያው የኢትዮጵያ ሥውሩ መሪ ስለሆኑ በሥልጣናቸው፤ በመብታቸው ተጠቅመው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ባሩድ አፍስሰዋል። ስለሆነም በራስ ጥፋት ህይወታቸው ባለፉ ትግርውያን ምክንያት ነው ከፖሊት ቢሮ አባልነት/ ከሊቀመንበርነት ያስወገዳቸው። እንጂ ለዛ ሁሉ የደም ጎርፍ በአማራ መሬት ለፈሰሰው፤ ወይንም በወልቃይት፤ በጠገዴ በራያ ላይ በሚያፈሱት የጭቆና በረድ፤ ወይንም ወንበዴዎቻቸውን አደራጅተው ቅዳሜ ገብያን በማንደዳቸው፤ ወይንም የንግሥት ይርጋ ጥፍር መነቀል ወይንም የአጋራቸው የኮ/ ደመቀ ዘውዴ እስር እንግልት፤ ለወያኔ ሃርነት ትግራይ ጉዳዩ ሆኖ አይደለም። ወይንም 20 ሺህ ወጣቶች ስንቅ አልባ በርሃ ላይ በእስር ስለመከዘናቸው አጀንዳንዳቸው አይደለም። የሚጨነቁት የሚጠበቡት ዜጎቻቸው የበደሉትን በድለው፤ የገደሉትን ገድለው፤ የአንኮላሹትን አንኮላሽተው፤ ጥፍር የነቀሉትን ነቅለው፤ የተጫወቱበትን ነፍስ እንዳሻቸው መሞከሪያ አድርገው የትግራይ ልጆች ማህበራዊ ሰላማቸው እንዳይታወክ ነው እነ baby። ኢትዮጵያዊ ፍጥረት አይደለም ለእነሱ የመንፈስ አመክንዮ፤ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሜቴ አጽህኖት ሰጥቶ የተወያዬበት አመክንዮ እንዴት አንዲት ቀንጣ የትግራይ ነፍስ ስለምን ይጠፋል ነው? የትግራይ ደም ስለምን ጎንደር ላይ ፈሰሰ ነው? በቃ! ኢትዮጵያ ጃኬት ናት ትግራይ ግን ውስጥ ናት። ኢትዮጵውያን እንደ ፍጡር አይታዩም ትግራውያን ግን የደም ሥር ህዋስ ናቸው። ከአፓርታይድም በላይ።

ለለውጥ ሃይሉ ክፍተት ተፈጥሯል …

አዬ እናትዬ ጋዜጠኛ ኤርምያስ ለገሰ ስንት መቶ ጊዜ ነው ክፍተት የሚጠበቀው። ከሰማይ መብረቅ ወርዶ እኮ ነበር። ስንጥቅጥቅ የሚያደረግ። እያንዳንዱ የትግል ቀን በራሱ ቀለምና ህብር ገጸበረከቱን የነፈገበት ዕለት/ ወር/ ወቅት/ ዓመት አለን? በዓይነት በሽ ነበር፤ እንኳንስ አቅሙን መጠቀም መተርጎም እንኳን አልተቻለም።

እንደ እኔ ይህ ክፍተት ወያኔ እራሱን ለማጠናከር ቢረዳው እንጂ አንዲትም ብጣቂ ለለውጥ ሃይሉ ሊያመጣ የሚችለው ትርፍ የለም። እነሱ ክፍተቱን በዲስፕሊናቸው ያርቁታል። ባለ 100 ዓመት የታላቅነት – የሉዕላዊነት ህልመኞች ናቸው። በተከታታይና በታታሪነት ነው የሚሠሩት። ስብሰባቸው ላይ በስማ በለው „እንዲህ ይሆናል እንዲያ ሊሆን ይቻላል“ ብሎ ከመተንበይ ውጪ የጭብጡን መንፈስ ቀርቶ ጭራውን ማግኘት አልተቻለም። ቀዳዳ የለም። የትግሬ የትውልድ ዝርያ ያላቸው፤ በህውሃት እረጅም ጊዜ ያሳለፉት፤ ለማንፌስቷቸው ተፈጻሚነት ተምክሯቸውም ዝቀሽ የሆኑት መረጃውን የሚሰሙት እኮ ልክ እንደ እኛ ነው። ህውሃት እንዲሰማለት የሚፈለግውን ለታማኞቹ ሚዲያ ሹክ ሲል ነው እኛም እነሱም ተወላጆች ሁላችንም እኩል የምንሰማው። ከዚያ ውጪ ግን ልክ እንደ ትናንቱ አሁንም ከወያኔ ሃርነት ትግራይ የደም እና የዝርያ ሐረግ ውጪ የሆኑት የወያኔ ሃርነት ትግራይን በፖለቲካ አቅም ልቅና ሊተረትሩት፤ ፈንቅለውም/ ሰንጣጥቀው ለድል ሊበቁ ቀርቶ ሰርገው ገብተው ትክክለኛውን መረጃ ሊያገኙ እንኳን አይችሉም። ከአንድ ተራ የመዝገብ ቤት ሠራተኛ ከሚገኝ የሥም ዝርዝር ያለፈ አሸናፊ ሊያደርግ የሚችል አቅም ያለው መንፈስ በእጅ ለማስገባት እንጃ ነው። ያለፍንባቸው ጊዜዎች ጭብጣቸው ጭንብልን ፈቅደን ካላለብስናቸው ማውጫችን ነው።

አቶ ሰዬ አብርሃም እኮ ከምንም እና ከማንም በላይ የአምክንዮ አቅም የነበራቸው ፖለቲከኛ ናቸው። አሳቸውን የራስ ለማድረግ የነበረው ጥድፊያና ፉክክር፤ ከንቱ ውዳሴም፤ ቁልምጫም፤ ቀዩ ምንጣፍም ተመልክተናል። በሠራዊቱ በነበራቸው ተደማጭነት፤ ባላቸውም አቅም መንፈሳቸውን የራስ ለማድረግ ጉጉቱ ተጧጡፎ ትውናውን ደርቶ እናይ ነበር። ሌላ ሰው ዓይነ – ገብ ለማግኘት የኢትዮጵያ መሬት እንዲህ ጠፍ ነውን እስኪያሰኝ ድረስ ሽሚያው ይደንቅ ነበር። ዛሬ የምናዬው የትውልድ አጨዳ በመላ ኢትዮጵያ የተለዬ ጥበቃና እንክብካቤ ለትግራይ እናቶች መርኽ ነዳፊው እኮ አቶ ሰዬ አብርሃም ነበሩ „የትግራይ እናት ከእንግዲህ አታለቅሽም“። እርግጥ ነው ዛሬ ከፖለቲካው ዓለም ራሳቸውን ከአገለሉ በኋዋላ በውስጥ የሚሰጡት የምክር አገልግሎት እንደተጠበቀ ሆኖ ፊት ለፊት ወጥተው ግን ሲያነኩሩ አለመታየታቸው አብነታቸው አንቱ መሆኑን ሳልጠቅሰው ማለፍ አልፈልግም። ልባም ናቸው። አቋማቸውን ከልቤ አከብርላቸዋለሁ ለዚህም ነው በጹሑፌ አንስቻቸው የማላውቀው። የሆነ ሆኖ ያን ጊዜ በሳቸው ዙሪያ በነበረው የሊሂቃኑ ስስ፤ መሬት ያልያዘ የፖለቲካ ግንዛቤ፤ እኛም ታድመንበት ክርክሩ ምን ያህል አቅም እንደበተነ ይታወቃል፤ እንኳንስ የለውጥ ሃይሉ አዲስ አቅም አግኝቶ አንድ ርምጃ ሊጓዝ ቀርቶ …. አሁንም አንጋጦ መጠበቁ ምንም የሚያዋጣ አይሆንም። ወደኛ የሚመጡ አቅሞችን፤ ቅንነቶችን አክብሮ መጠጋጋት ከተቻለ … ያም ብልህነት ነው። ግን ሰብዕናቸውን የአለመዳፈር የአመራር ጥበብ ይጠይቃል። የመከባበርን አመክንዮ ታላቅነት ሊሂቃኑ ት/ቤት ቢገቡ የሚሻላቸውም ይመስለኛል። ናሙናዊ ጉዟቸው ዝለት ያሰኘው ነው።

መሠረታዊ ጉዳይ መሬት ላይ ነፍስን የሚገዙ የበሰለ ተግባር፤ የበለጠ ክህሎትን ይጠይቃል። በልጦ መገኘት። ተፈረካከሰም፤ ተናካሰም፤ ተቦዳደሰም አሁንም የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በወያኔ ሃርነት ትግራይ ሥር የወደቀ ነው። ኢትዮጵያን የሚመራው ህውሃት ነው እኛ አቅም ባለው ብልህ አመክንዮ ልንበልጠው ስላልቻልን። የእኛ አቅም ከወያኔ ሃርነት የሴራ፤ የተንኮል የሸር አቅም ቁመና አገር ሊመጥን ስላልቻለ። ካጠቃን በኋዋላ ነው የምንባትተው። እህት ድርጅቶችንም ሰጥ – ለጥ አድርጎ፤ አንቀጥቅጦ፤ ሱሪውን አስወልቆ የሚገዛው ህውሃት ነው። መሬት ላይ ያለውን ጭብጥ የ44,000 ኢትዮጵያዊ 500 የውጭ ዜጎች የተሳተፉበት ሩጫ ኢትዮጵያ ሐገሬ የሚለውን ህዝባዊ መዝሙር እንኳን በወል ሊዘመር አልቻለም ሌላው ቀርቶ። በጋራ እኮ ሲነሳ „በቃ በቃ እዬሮጥን ነው፤ በቃ … በቃ እዬሄድን ነው፤ በቃ በቃ እየተጓዝን ነው፤ እያለ መዘመር ይችልም ነበር ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ  … አንድም የነጻነት ፍላጎት ያልታዬበት ሙት ደመነፍስ በርዶ ነበር። የጎንደር የታጠቅ አንበሶች እኮ 500 ቲሸርቶችን በራሳቸው ወጪ አሰርተው ልጅ ሞላን አስገዶምን „የፈራ ይመለስ“ ሲሉ ሞግተዋቸዋል። ወያኔ ሃርነት ትግራይም እዬለቀመ እነዛን የዘመን ልቦችን አመድ አድርጓቸዋል። አሁን የጎጃም የወሎ ወጣቶች ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ የነጻነት ዜማዎችን ሌላውን ሳይተናኮሉ በዬኳስ ሜዳው ያቀነቅናሉ። ሌላ ዓለም ነው እዛ ያለው የተጋድሎ ጤነኛ መንፈስ … ሰላማዊ የሆነ አስተማሪ። ይህን ማድረግ ያልቻለ የሀገርቤት ሰላማዊ ታጋይ ድርድር እያለ በበረዶ ግግር ልባችን ያወልቀዋል። ነገ ደግሞ መከረኛ የአማራ መሬት ምረጠኝ / ቀብጥርሰኝ /ቅበረኝ ተብሎ መዋቅር ይዘረጋል። ለተጨማሪ ቅጣት አማራ የሰው ብርንዶ አቅራቢው ሊኳንዳ ቤት ይከፈትለታል። ሁልጊዜ እንደ ሞሞከሪያ ጥንቸል … ይፈተናል …

ቀጣዩ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ጉባኤ እና የሰሞናቱ ውሳኔ ዕጣ ፈንታ

ዕድሉ ያለው በቀጣይ ጉባኤ ነው። ይህ ክፍት ነው። የወያኔ ሃርነት ትግራይ የአባላቱ ጠቅላላ ጉባኤ አሁን ያለውን የማዕከላዊ ኮሜቴ ሙሉ ለሙሉ የመቀዬር፤ የመበወዝ ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል። ይህን ካደረገ ቀጣዩ ጉባኤ ወ/ሮ አዜብ መስፍን እንደገና ወደ ማዕከላዊ ኮሜቴ አባልነት የማምጣት ሥልጣን ይኖረዋል። የፖሊት ቢሮ አባል ለመሆን ግን ማዕከላዊ ኮሜቴ በድምጽ ብልጫ ከመረጣቸው ብቻ ይሆናል። ግን ነገር ግን ጉባኤው ዕገዳውን ካነሳላቸው ብቻ ነው ይህ የመመለስ የተስፋ ሂሳብ የሚወራረደው።

የፈጸሙት ግድፈት ግን ስበሰባውን ረግጠው መውጣት ማለት የወያኔ ሃርነት ትግራይን ጉባኤ ረግጠው መውጣት ማለት ነው። የመሠረታዊ ድርጅታቸው የሰጣቸውን የውክልና አቅም አቃለውታል። የወያኔ ሃርነት ትግራይ አባላት ሙሉ ሥልጣን የሰጠውን አውራ አካል መርገጥ ማለት ነው። ስለምን? ማዕከላዊ ኮሚቴው የወጣው ከጠቅላላው ጉባኤው፤ ጠቅላላው ጉባኤው የወጣው ደግሞ ከወያኔ ሃርነት ትግራይ ጠቅላላ የመሰረታዊ ድርጅት የቀጥታ የአባላት ስበስባ ነው። ጠቅላላ አባላቱ የተፈጠሩት ደግሞ ከትግራይ ማህጸንና እና አብርክ ነው። ይህም ማለት የወያኔ ሃርነት ትግራይ መሠረቱ የትግራይ ህዝብ ነው። የወ/ሮ አዜብ መስፍን የማዕከላዊ ኮሜቴውን ስብሰባ ረግጦ መወጣት ትግራይን ረግጦ መወጣትም ማለት ነው። ትግራይ ትክል ድንጋይ አይደለም። ትግራይ ማለት ህዝቡ ነው። ስለዚህ የትግራይ ህዝብም ተረግጧል/ ተንቋል ማለት ነው። በፈለገው መስፈርት ቢኬድ ሰው የራሱን ክብር ተረግጦ ሌሌላው ክብር ሊያለብስ ፈጽሞ አይፈቅድም። ለፈለገው ተጋዳይ የሥልጣን፤ የዝርፊያ ቁንጮ መሰላል ሊሆኑ ይችላሉ ወ/ሮዋ። ነገር ግን የትግራይን የማድርግ/ የመግዛት፤ የታላቅነት ልዕልና አስከ ረገጡ ድረስ ይቅርታው እንዲህ በቀላሉ ሽምግልና እና በብጥቅጣቂ ጉዳይ ይሁንታ ያገኛል ብዬ እኔ በግሌ አላስብም። በዚህም እኔ ከጋዜጠኛ ኤርምያስ ለገሰ አቋም ጋር እለያለሁ።

አዬህ እናትዬ ክብርህ ሲነካ አንተ የለህም። አንተ ሳትኖር ለሌላው መኖር ብልህነት አይደለም። አንተን ለናቀህና ለረገጠህ ጥብቅና ልትቆምለት አይገባም። እኔ በአንድ ሐገራዊ ስብሰባ ክብሬ ተነካ በ2015። ያቺ ቅጽበት ግዴታዬን ባፋጣኝ ተወጥቼ ስብሰባውን ሳልጨርሰው እንደወጣ አደረገኝ። አልተመለስኩም። ወደፊትም አልመለሰም። ክብርህን ሲጠበቅ ውስጥህ ታደርገዋለህ፤ ክብርህን ሲወልቅ አክብረኸው የኖርከውን፤ ያከበርከውን፤ የእኔ ያልከውንም ሞጥጠህ ታወጣዋለህ ከውስጥህ። አንድ ሰው አንድን አካል ወክሎ ሲመጣ ጠንቃቃ መሆን አለበት። ወክሎ ለላከው አካል ሁነኛ ተቀባይነትን ለማስገኘት የታዳሚውን ነፍስ ማክበር አለበት። መጎርበጥ የለበትም። ብዙ ነገር ነው ከጥንቃቄ ጉድለት የሚናደው። በፓለቲካ ህይወት ውስጥ ተደማጭነት ሆነ ተቀባይነትን በጥንቃቄ፤ ምራቅን በመዋጥ፤ በዝግታ መራመድን ይጠይቃል። ትርፍን በሞራላዊ ዕሴት መገንባት ነው መንገድ ሊሆን የሚገባው። አንተን አክብሮ የመጣን ሰው መንፈሱን መቀጥቀጥ የለብህም። ለምን ተቀናቃኝህ አይሆንም። ትህትና፤ ርህርህና አስተምረህ ውስጡን ያንተ ማድረግ ነው ብልህነት። ከታዳሚ በላይስ ማን ሊከበር ይገባል?

የወ/ሮ አዜብ መስፍን ደግሞ በፖለቲካ አመራር ውስጥ ለዛውም ኢትዮጵያን ታህል ሀገር ሰጥ ለጥ አድርጎ አንበርክኮ የሚገዛን የታላቋን ትግራይን ክብር ድጠውታል፤ አላውቅህም ብለውታል። ታላቋ ትግራይ ለሰጠቸው የልዕልና ቀዳማይ እመቤትነት ደረጃ ብናኝ ክብር አልነበራቸውም። ግብታዊነትም እኮ ነው ይሄ። በስሜት የሰከረ ትዕቢትም ነው። ስለዚህ ይህን እንኮፍ የሆነ ሽንፍላ መንፈስ ይዞ ቀጣዩ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ጉባኤ ስለ እሳቸው ተሟግቶ የተጨማሪ የማዕከላዊ ኮሜቴ የአባልነት የሥልጣን ጊዜ ይሰጣቸዋል የሚለው ለእኔ ይቸግረኛል። ከአባልነት ካልተሰረዙም ዕድለኛ ናቸው። በዛ ላይ ዝረፊያውም በሁሉም በኩል ሁሎችም የበከቱበት አዘቅት ነው። ትግራይ በልጆቿ ልትኮራ ሳይሆን ታሪኳ የጠቆረበት ጥቁር ዘመኗ ነው – ለእኔ። የመላ ኢትዮጵያ መንፈስ ሁሉ ትግራይን ያገለለ ነው። ለሃጣን የመጣ ለጻድቃን ሆኖ የትግራይ የሆነ ሁሉ እዬከሰኮሰን ነው። እኔ ግልጽና ቀጥተኛ ስለሆንኩኝ እውነቱን ነው የምናገረው። እማሽሞነሙነው ምንም ነገር የለም። እህቴ እዛ ጥፍሯ እዬወለቀ፤ ወንድሜ እርቃኑን በህዝብ ማህል ልብሱን አውልቆ ሃፍረተ ሥጋውን ፍርድ ቤት ላይ በጠላቶቹ፤ በአዋረዱት፤ በናቁት ማህል ፍትህ አገኛለሁ ብሎ እያሳዬ፤ ያን የክብር ተክሊል የሆነውን ኢትዮጵያዊ ባህል – ወግ – ልማድ  – የመከራው ክርፋት መሸከም አቅቶት ይህን በእኛ ዘመን ማዬት በእውነቱ ከእህል አውሃ ጋርም እኮ የሚያገናኝ አይደለም። ስለዚህ ውስጣችን በእጅጉ ተጎድቷል። እኔ በግሌ አዝኛለሁ።

ይህም ብቻ አይደለም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለሥጋ ፈቃድና ርካሽ ሴሰኝነት ተቧድኖ እንዲህ የወረደ፤ የተዋረደ ሰብዕና ኢትዮጵያን ያህል የሰው ልጅ መፈጠሪያን ሐገር ሲመራ ኢትዮጵያ በታሪኳ እያፈረች/ እዬተሸማቀቀች ይህንን ገመና ተሸካሚ መሆኗ የመጀመሪያዋ ነው። አንገቷንም ደፍታለች። ለሥጋ ፈቃድ ሰለባ መሆን በወልዮሽ የሁሉም በሽታ ሆኖ መገኘቱ በፍጹም ሁኔታ አጸያፊ እና ትውልድን ከመሰረቱ፤ ከዕሴቱ የሚነቅል ቆሻሻ ገመና ነው። ይህም ቀጣዩ ሀገራዊ /ብሄራዊ /ትግራዋዊው ጉባኤ የሚፋጥጠው በኽረ ጉዳይ ነው። እስልምናም ክርስትናም ሁለቱም ሃይማኖቶች በገነኑበት ትግራይ ውስጥ ይህን መሰል እንደ እንሰሳ፤ ከእንሰሳም ባነሰ ስሜትን አለመግዛት፤ አለመቆጣጠር፤ በደም መታጠብ ከትውፊት ውጪ የሚያደርግ የበከተ ሂደት ትግራይ ተሸክማ ስለመዝለቋ አነጋጋሪ ነው። ርግብ እኮ ይሄን ሰማያዊ ጸጋ አትዳፈረውም … እንኳንስ የሰው ልጅ ለዛውም ኢትዮጵያዊ። ለዛውም ወግ አጥባቂው ትግራይ … ገመና በገመና … በልጆቹ።

ሌላም የሌብነት የትምህርት ካርኪለም፤ የጭካኔ – የአረመኔነት አብነት፤ የፈላጭ ቆራጭንት – ትዕቢት፤ የራስህን አማራ ወገንህን እዬተንቋሸሸ ሲደበደብ ከትግራይ ቀደምት ዕሴት ጋር የሚገጥም፤ የሚመጣጠን ከሆነም ቀጣዩን ጉባኤ የፈተና አውድ ያደርገዋል ብዬ አስባለሁ። ህሊና ያላቸው ከተገኙ።

የእናት ሀገር የኢትዮጵያ ጉዳይ ዕጣ ፈንታ፤ የልጆቿ የዕንባ ውቅንያኖስም የሚወሰነው በትግራይ ልጆች፤ በትግራይ ማህጸና ባፈረቻቸው፤ የትግራይ አብራክ በፈጠራቸው ፍሬወች የተወሰነ ነው። ትግራይ ከአውሬነት ወደ ሰውነት፤ ከአረመኔያዊነት ወደ ተፈጥሮነት የምትመለስበት ወቅት ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ ቀጣዩ – ጉባኤቸው፤ በማህል የሚጠበቁ ክስተቶች እንደተጠበቁ ሆነው። መቼስ ተስፋ አያልቅ ወይንም ሽልንግ አያስከፍል …

የአቦይ ስብሃት ቅርንጫፊያዊ ሰናይ …

አሁን በህውሃት የተፈጠረው ሽኩቻ ዘላለማዊውን በትረ ሥልጣን እንዳይሆን የሬገን ህንጻ ስለደረመሰው ነው እንጂ እሰከ የልጅ ልጅ ቀጣይ የነበረው የአቶ መለስ ባለቤት/ ልጅ/ የልጅ ልጅ እያለ ይቀጥል ነበር። አቶ መለስ ዜናዊ ህልማቸው የነበረው የትዳር አጋራቸውን ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ለማስቀጠል ነበር። አሁን የአቦይ ስብሃትም መንፈስ ይሄው ነው። ዘራቸውን ተክለው ለማለፍ ነው። እርግጥ አሁን ለጥቂት ህልማቸው ስቷል። በመጠጋጋት ተከውኗል። የእሳቸው ቡድን ቢያሸንፍም ከእሳቸው የኪምልሱንግ ዘር ግንድ ግን ወጥቷል። ሊቀመንበሩ በህይወት ካልቆዩ ግን ቦታው ይገኛል። የሆነ ሆኖ አሁን ባለው ሁኔታ አቦይ ስብሃት አና የዘረፋ ዝነኛው የቤተሰብ ካቢኔያቸው ሥልጣኑን ለመዘወር በእጅ አዙር እንጂ ቀጥታዊ አይሆንም። በሌላ በኩል ዶሩ. የራሳቸውን መንፈስ በማደራጀት ሰንሰለት በመዘርጋት እረገድ ተኝተው በለኝ የሚሉ አይሆንም። ሥልጣን በሽታ ነው። ዕጽ ነገር። ቁሞ የሚጠብቅ ምንም አመክንዮ ስለሌላ ፍቅሩም ብን ሊል ይችላል – ነገ ወይንም አሁን ጀማምሮት ይሆናል። የወያኔ ሃርነት የአሁኑ ህይወቱ በጥርጣሬ የተዋጠ፤ መተማመን የመከነበት፤ በስጋት እንደ ቆዳ የተወጠረ የአገዛዝ ዘመን ይሆንል ብዬ አስባለሁ።

እንደ መከወኛ። የለውጥ ፈላጊው እና አቶ ሂደቱ።

ለለውጥ ፈላጊው ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት አሁንም አንጋጦ ማዬቱ ብዙም ትርፋማ አይደለም። የፖለቲካ ትርፍ ትግሉን እያዘናጉ በፕሮፖጋንዳ ማዛል ሳይሆን ሥራ መሥራት ነው። የእነሱን ክፍተት በማስተሽ ደፋፍነው አሁንማ በእውቀትም እኩል የሆነ አቅም የወያኔ ሃርነት ትግራይ አለው በሚያሰኝ ሁኔታ ያው ፉክክር ስለሆነ ዶር. ነው መሪያቸው። እንዳደመጥኩት ከሆነ ሥብጥሩ ሶስት በዶር. ደረጃ ያሉ ሲሆን በጾታም ሆነ በዕምነት ተዋጾዖም የተደረገው ሽግሽግ ነጮችን አማራጭ እንዲፈልጉ አያደርጋቸውም። በዛ ላይ የሎቢ ሥራው በመደበኛ በንቃት እና በተከታይነት የሚከውን፤ ሙቀቱን ጠብቆ የሚጓዝ እንጂ እንደ እኛ በለብታ የንፋስ ውዝዋዜ የሚመራ አይደለም። ቋሚ አንቱዎችም የሎቢ አርበኞች አሏቸው።

ህዝቡም ከሚገባው በላይ መስዋዕትነትን ከፍሏል፤ እዬከፈለም ነው ግን ይህንን በጥበብ እና በስልት አቅሙን የሚጠቀም ሃይል ግን ከላፉት ጊዜያቶች በተሻለ ነጥሮ የወጣ ነገር የለም። የለም። እራሱ የኦህዲድ ሙቀት ብርድ ብርድ እያለው፤ የጠነከረው የተሰባሰበው መንፈስ እዬደነዘዘው፤ እነሱ ቀዳዳቸውን እሰኪወታትፉ ድረስ የተገኘው የመንፈስ ጥሪት እዬነዘረው ይሆን ያሰኛል። ትንታ ሆነ ትነት እንዳይገጥመው ያሰጋል። መዝግዬት ይታያል። መዘግየት መበለጥን ብቻ ሳይሆን መዋጥንም/ መጠቃትንም ያመጣል። እኔ በኢህአፓ ቅርንጫፉ በባህርዳሩ እንኮሸሽሌ ተስፋ አድርጌ አላውቅም ልብ የተገጠመለት የምድር እንቦይ ስለሆነ።

ማስተዋልን የሠራልን አምላክ እንጠቀምበት ዘንድ ህሊናችን ያብራልን። አሜን!

እግዚአብሄር ይስጥልኝ። መሸቢያ ጊዜ

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.