የአንዲት ሶማሊያ ብሄርተኝነት እና ግብፅ የአማራ ህዝብ ትግል አጋሮች እንጂ ባላንጣዎች አይደሉም (በሀይለኢየሱስ አዳሙ)

መግቢያ

በሶማሊያ እና ግብፅ ጉዳይ እኛ አማራዎች ይዘነው የነበረውን አቋም አሁን ካለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ እና የአማራ ህዝብ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከተጋረጠበት የህልውና አደጋ አንጻር እንደገና ልንፈትሸው ይገባል። ይህን ከዚህ በታች ያሰፈርኩትን ሀሳብ አሁንም ለኢትዮጵያ አንድነት እንታገላለን ለሚሉ ሰዎች ኢትዮጵያን እንደ መክዳት ወይም የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ እንደመስጠት ሊመለከቱት ይችላሉ። ቅሉ ግን  የአማራ ህዝብ አሁን ከተለያየ አቅጣጫ የተጋረጠበትን የፈፅሞ መጥፋት አደጋ ለተገነዘቡ እና የኢትዮጵያ የሀገር አንድነት በ1966ቱ አብዮት በሀይል ተንዶ በ1983 ደግሞ በይፋ እንዳከተመለት ለተረዱ ወገኖች እኔ ከዚህ በታች ያሰፈርኳቸው ነጥቦች አዋጭ እና ዘመኑን የዋጁ ለአማራ ህዝብ የህልውና ትግል አቅጣጫ የሚያሳዩ እንደሆኑ በቀላሉ ይረዱታል። በርግጥ እንደዚህ አይነት ያልተለመዱ አዳዲስ ሀሳቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰሙ ከፍተኛ ክርክር ያስነሳሉ። በሂደት ግን ተቀባይነት ያገኛሉ። የዛሬ አምስት አመት በፖልቶክ Hara Ethiopia በሚለው የፖልቶክ ስሜ “Ethiopia as Amhara state” የሚል ሀሳብ ሳቀነቅን በየ ሩሙ ban እና bounce ብደረግም ይሄው ያ ሀሳብ ባጭር ጊዜ ውስጥ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ ሌሎችም አሳድገውት እና አጎልብተውት የአማራ ተጋድሎን እና ብሄርተኝነትን ወልዶ ወደ አንድ አማራ Pan-Amhara እየመጣ ይገኛል።

የአማራ ህዝብ በዮዲት ጉዲት በግራኝ አህመድ በኦቶማን ቱርኮች በኦሮሞ ወረራ እና በጣሊያን ወረራ ከፍተኛ ጭፍጨፋ እና የዘር ማጥፋት የተፈፀመበት ህዝብ ነው። እነዚህን ሁሉ አደጋዎች በጀግንነት ፣ አርበኝነት እና መንፈሳዊ ብርታት አልፎ ኢትዮጵያን እና አፍሪካዊያንን የሚያኮራ ስልጣኔ እና ታሪክ ገንብቶ እዚህ የደረሰው የአማራ ህዝብ በአሁኑ ሰአት ከሌሎች ሁሉ ግዜዎች የከፋ የፈፅሞ መጥፋት አደጋ በትግሬዎች ተጋርጦበታል። ይህን አደጋ የከፋ የሚያደርገው ትግሬዎች የአማራን መሬት የሚችሉትን ራሳቸው ወስደው ቀሪውን በዋናነት ለሱዳኖች እና ኦሮሞዎች በመስጠት የአማራን ህዝብ በሁሉም አቅጣጫ የማስጨፍጨፍ ፖሊሲ መቅረፃቸው ነው። በመሆኑም የአማራ ህዝብ እንደ ተክለሀይማኖት መንፈሳዊነት፥ እንደ ቴዎድሮስ ጀግንነት ፥ እንደ በላይ ዘለቀ አርበኝነት እንዲሁም እንደ ሚኒልክ እና ጣይቱ አስተዋይነት እና ጥበብ የተሞላበት የትግል አካሄድ ያስፈልገዋል። አሁን ባለው የአማራ ትውልድ ጀግንነቱ ፥ አርበኝነቱ እና መንፈሳዊነቱ በደንብ እየታየ ነው።

የሶማሊያ ጉዳይ ለአማራው ትግል እንዴት አጋዥ ይሆናል?

የታላቁዋ ሶማሊያ እቅድ በምስራቅ አፍሪካ መረጋጋት ያመጣል። ለአማራ ሕዝብም  ስልታዊ እና ዘለቄታዊ ጥቅምም አለው። በፅንፈኛ የኦሮሞ ወራሪዎች የተጋረጠበትንም አደጋ ይቀንሳል።
እንደምታውቁት ሶማሊያ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣችበት ግዜ ጀምሮ የሶማሊያ ብሄርተኞች ሶማሊዎች የሚኖሩበትን እና ይኖሩበት የነበረውን ታሪካዊ ቦታ ያካተተ ታላቁዋ ሶማሊያን የመፍጠር እቅድ ነበራቸው። ይሄ እቅድ ሶማሊላንድ፥ የአሁኑዋ ሶማሊያ፥ ፑንትላንድ ፥ ጅቡቲን ጨምሮ አሁን ኦጋዴን የሚባለውን እንዲሁም ሐረርጌን እና የባሌ ቆላማ ቦታዎችን የሚያጠቃልል ነው። የአማራ ሕዝብ ለ ኢትዮጵያ አንድነት በሚል ሶማሊያ በዚያድ ባሪ ግዜ ወረራ አደረገች ተብሎ ውድ ህይወቱን አጥቱዋል። በሚገርማችሁ ሁኔታ ብዙ ኦሮሞዎች በወቅቱ ከዚያድ ባሪ ጦር ጋር በአንድነት ቁመው ለታላቁዋ ሶማሊያ ምስረታ ተሰልፈው ነበር። ያኔ ለ ኢትዮጵያ አንድነት በሚል በ ኢትዮ ሶማሊ ጦርንት ግዜ  የተከፈለው መስዋእትነት ዛሬ ለአማራው ምን ጠቀመው? ለባድመ መሬት ብሎ የከፈልነው መስዋዕትነት ምን ጠቀመው? መልሱ ምንም ነው። የራሳችንን አሳልፈን እየሰጠን፣ እራሳችንን እየጎዳን ሌሎች የኖርንበት ዘመን ነበር።

አሁን ያለው ተጨባጭ እውነት የሚያሳየን ፅንፈኛ አክራሪ ኦሮሞ መቸም ቢሆን ከተስፋፊነት እና ወራሪነት የማይቆጠብ የፖለቲካ ልሂቃን እንዳሉት ነው።
ሶማሊዎች ከአማራ ሕዝብ ጋር የሚያጋጫቸው ምንም አይነት ምክንያት የለም። እኛም ከሶማሊዎች ጋር ሊያጋጨን የሚችል አንዳችም ነገር የለንም። እንዲያውም ታላቁዋ ሶማሊያ ብትመሰረት አማራው እና ሶማሊው በመልካም ጉርብትና በሰላም እና መረጋጋት መኖር ይቻላሉ።
ይህ የታላቁዋ ሶማሊያ እቅድ ከአማራ ሕዝብ ጋር ሶማሊዎችን የሚያጋጭ ሁኖ አላገኝሁትም። በአሁኑ ሰዓት እንደምታዩት ፅንፈኛ የ ኦሮሞ ወራሪ ተስፋፊዎች የአማራን ሕዝብ መሬት በወረራ መያዛቸው ሳይበቃቸው ሸዋን እና ላኮመልዛን ጭምር የእኛ ነው  እያሉ በእንግድነት በመጡበት ሀገር ላይ ነባሩ ባለርስት ሕዝብ ላይ የዘር ፍጅት ለመፈፅም ሕዝባቸውን  በቅስቀሳ እያሳመኑ ይገኛሉ። ታላቁዋ ሶማሊያ አስፈላጊ ናት። እኛ አሁን ትኩረታችን በወያኔዎች በኩል የተጋረጠብንን የህልውን አደጋ መመከት ነው። በሌላ በኩል ግን የኦሮሞ ፅንፈኛ ፖለቲከኞች በአማራ ሕዝብ እና በቀሪው የ ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጋረጡትን የዘር ፍጅት ለመከላከል የ ታላቁዋ ሶማልያ እቅድ አንዱ አጋዥ ኃይል ነው የሚሆነው። በአሁኑ ሰዓት ሶማሊዎች ኦሮሞን አፈናቀሉ የሚባለው ነገርም አጠራጣሪ ነው። ምክንያቱም የኦሮሞ ፖለቲከኞች የአማራ ፣ የጉራጌ፣ የሃድያን፣ የሲዳማን፣ የከንባታን፣ የየም፣ የከፋን እና የሌላውን ኢትዮጵያዊ መሬት በወረራ ይዘው እያሉ እነሱ እንደተወረሩ የሚያስወሩት የውሸት ትርክት ስላለ አሁንም ሶማሊ ወረረን የሚሉት የፈጠራ ክስ ሊሆን ይችላል። የ ኦሮሞ ትግል ለፍትህ እና ለነፃነት የሚደረግ ቢሆን ኑሮ ሁላችንም ለመደገፍ ዝግጁ ነበርን ነገር ግን የአክራሪ ኦሮሞዎች ትግል የሌላውን ሕዝብ መሬት የመውረር እና በዘር ፍጅት እና ጥላቻ ላይ የተሞላ ስለሆነ ሁላችንም በአይነ ቁራኛ ልንከታተለው ይገባል። በርግጥ አሁን ከትግሬ ጋር የሚያደርጉት ትግል ካለ ግዚያዊ ትብብር ወይም እነሱን አለመቃወም ሊያስኬድ ይችላል። በዘላቂነት ግን ከሶማሊያ ሕዝብ ጋር የሚኖር ትብብር ይህን የ ፅንፈኛ አክራሪ ኦሮሞዎችን  የተስፋፊነት እና ወራሪነት አደጋ ለመቀነስ ያስችላል። ነገሮችን ከአማራ ሕዝብ የአጭር እና የረጅም ግዜ  ዘለቄታዊ ጥቅም አንፃር ማየት ያስፈልጋል። ከኦሮሞዎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር አማራ የሄደበትን እርቀት ማየት ይቻላል። ከማንም በፊት የኦሮሞን ትግል ለመደገፍ ፍላጎት እና ተነሳሽነት ያሳየሁት እኔ ነኝ። ዳሩ ግን ፅንፈኛ ኦሮሞዎች ዛሬም ትግሬ እየገደላቸው ጠላታችን አማራ ነው የሚሉት። የ ኦሮሞ ፅንፈኛ ፖለቲካ በ አማራ ጥላቻ ላይ የተገነባ ሁኖ አግቼዋለሁ። በመሆኑም አማራው ነገሮችን በአዲስ መልክ ማየት ይኖርበታል። ከሶማሊዎች ጋር በዚህ ጉዳይ ቀርቦ መነጋገር ያስፈልጋል።
የግብፅ እና አባይ ጉዳይ ለአማራ ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?ባለፈው ከግብፅ ጋር ትብብር ማድረግ ወያኔን ለመጣል እና የአማራ ሕዝብ የተጋረጠበትን አደጋ ለመከላከል እንዴት እንደሚጠቅም ለማሳየት የሞከርኩበትን በሳተነው ድህረ ገፅ ላይ በእንግሊዘኛ ያወጣሁትን ፅሁፍ  አንኩዋር ነጥቦች በአማርኛ ከዚህ በታች አስፍሬዋለሁ። ፁሁፉ በእንግሊዘኛ የተፃፈበት ምክንያት የግብፅ ሙሁራንም እንዲያነቡት በማሰብ ነው። በግብፅ ሚዲያዎችም ላይ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ፁሁፎችን የማውጣት እቅድ አለኝ። ሌሎች የአማራ ልሂቃንም በዚህ ጉዳይ ላይ ቢፅፉበት መልካም ነው። የፁሁፉ አንኳር ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው።

1. ግብፅ የአማራ ህዝብ አጋር መሆን ትችላለች። የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ እና በምሥራቅ አፍሪካ በቁጥር ትልቁ ህዝብ ሲሆን ከግብጽ ጋር የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ያለው ህዝብ ነው። የግብፅ እና የአማራ ህዝቦች በአባይ ወንዝ የተሳሰሩ ሁለቱም የአባይ ውሃን ጠጥተው ያደጉ ናቸው።
2. በአሁኑ ሰአት የትግራይ መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ መጠነ ሰፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈፀም ላይ ይገኛል። የግብፅ መንግስት እና ህዝብ የአባይ ወንዝ ጉዳይ እጅግ ያሳስባቸዋል። የትግራይ አናሳ አገዛዝ የተለያዩ ግድቦችን እና የስኳር መስኖ ስራዎችን በአባይ ወንዝ እና ጣና ሀይቅ ላይ በመፈፀም ላይ ይገኛል።
3. ጥቁር አባይ ሙሉ በሙሉ የአማራ ህዝብ ሀብት ነው። እነዚህ ግድቦች እና የስኳር የእርሻ ቦታዎች በሙሉ የተሰሩት በአካባቢው የሚኖረውን በሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎች ከቀያቸው በማፈናቀል ነው። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑት የጢስ አባይ ግድቦች, የጣና በለስ ግድብ እና የስኳር ፕሮጀክት እንዲሁም አሁን በመተከል የሚሰራው የህዳሴ ግድብ ሲሆኑ እነዚህ ግድቦች በአማራው መሬት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ አርሶ አደሮችን ከቀያቸው በማፈናቀል የተሰሩ ናቸው። እነዚህ ግድቦች ከማፈናቀሉ በላይ በአካባቢው ብዝሀ ህይወት ላይ እያደረሱት ያለው አደጋ በአማራ ህዝብ ላይ የህልውና አደጋ ጋርጡዋል። ለምሳሌ የጣና በለስ የኤሌክትሪክ እና የስኳር ፕሮጀክት ወደ ጣና እና አባይ የሚገቡ ሁለት ገባር ወንዞችን በመገደብ ሰስት አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የጣና ሀይቅ በአንድ ሜትር እንዲቀንስ አርገጎታል። አሁን የጣናን ህልውና እየተፈታተነ ያለው እምቦጭ እንደዚህ መስፋፋት ዋና ምክንያት የጣና በለስ ግድብ ነው። የጢስ አባይ ግድብም የጢስ አባይ ፏፏቴ ጨርሶ ጠፋ እስኪባል ድረስ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሁኔታ እያዛባ ነው። ይሄ ሁሉ የሚደረገው ደግሞ ትግራይን ለማልማት ነው። ባለፍት 27 አመታት ለአማራ ህዝብ አንድም ትራንስፎርመር አልገባለትም። የስኳር ፋብሪካውም ትግሬዎች የውጭ ምንዛሬ የሚሰበስቡበት እንጂ ለአማራ ህዝብ የሚሆን አይደለም። በመሆኑም በአባይ እና ጣና ላይ የሚሰሩት በሚገባ የአካባቢ ጥናት ያልተደረገባቸው ፕሮጀክቶች የአማራ እና የግብፅ ህዝብን እኩል የሚጎዱ ናቸው።

4. በመሆኑም የአማራ ህዝብ “የአማራ የአባይ እና ጣና ኮሚሽን” አቋቁሞ ከግብፅ እና ሌሎች ሀገሮች ጋር በቀጥታ ውይይት እና ድርድር ማድረግ ይኖርበታል። በአባይ ጉዳይ ትግሬዎች አይመለከታቸውም ምክንያቱም አባይ ከአማራ አብራክ ፈልቆ በአማራ መሬት ላይ ነው ተንጣሎ የሚገኘው። አማራው በሰሜን ትግሬዎች ጨርሰው ሊያጠፉት ቆርጠው ተነስተዋል። የኤርትራ መንግስት ከትግሬ መንግስት ጋር ቢጣላም ሁለቱም የአንድ የትግራይ ትግርኛ ጎሳ አባላት ናቸው። በመሆኑም አማራውን ሊያግዙ አይችሉም። ሱዳኖችም የትግሬ መንግስት የአማራውን መሬት እየሰጣቸው ስለሆነ ለአማራ ወዳጅ ሊሆኑ አይችሉም። ግብፅ ግን ከአማራው ምንም የሚያጋጫት የመሬትም ይሁን ሌላ ጉዳይ የላትም። በአባይ እና ጣና ላይ የሚሰሩ ትላልቅ ግድቦችን በጋራ እንቃወማለን። የአማራ ድርጅቶች ከግብጽ ጋር አብረው ለመስራት መቀራረብ ይኖርባቸዋል። በጣና ላይ የተጋረጠው አደጋ የሚያሳስበው የአማራን ህዝብ እና የግብፅ ህዝብን እንጂ ጨቋኟ የአማራ ብሄር እረፍት ማግኘት የለባትም ብሎ በድርጅቱ ፕሮግራም ላይ ቀርፆ በመምጣት የአማራን ህዝብ እየጨፈጨፈ ያለውን የትግሬን መንግስት አይደለም። በአግባቡ ከተጠየቁ እንቦጭን ለማስወገድ የሚሆን የማሽንም ይሁን የኬሚካል እርዳታ ግብፆች ሊያደርጉ ይችላሉ። ከዚህም በላይ ትግላችንን በተዘዋዋሪ መንገድ ሊደግፉትም ይችላሉ።

መደምደሚያ

የአማራ ህዝብ በረጅም ጊዜ ታሪኩ ካጋጠሙት አደጋዎች ሁሉ የከፋ ፈፅሞ የመጥፋት የህልውና አደጋ ተጋርጦበታል። የአማራ ህዝብ ከዚህ የከፋ አደጋ ለመውጣት  ነገሮችን በአማራነት መነፅር ማየት ይኖርበታል። ከሶማሌዎች እና ግብፆች ጋር በጋራ ጥቅሞች (common interests) ላይ አብሮ ለመስራት ዝግጁነት ማሳየት ያስፈልጋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.