የኢትዮጵያ የባህር በር መዘጋት በሀገሪቱ ላይ ከተፈጸሙ በደሎች ቁንጮ አድርጌ ነው የማየው – ዶ/ር ያዕቆብ ሃይለማሪያም

በአንድነት በጋሻው | ሃገር ቤት ከሚታተመው አዲስ ታይምስ መጽሔት የተገኘ

ዶክተር ያዕቆብ ሃይለማሪያም

ዶክተር ያዕቆብ ሃይለማሪያም በዊንጌት ተምረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።ከዚያም በአሜሪካም ተምረዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሩዋንዳን ጉዳይ በአቃቤ ህግነት እንዲሰሩ ተመድበው አገልግለዋል። ከዚያም በናይጀሪያና ካሜሩን መካከል የነበረውን የወሰን ጭቅጭቅና ግጭት ለመዳኘት የህግ አማካሪም ሆነው አገልግለዋል።

ሴኔጋል እያሉም ‹‹በ1997 ዓመተ ምህረት እንከን የለሽ ምርጫ ይደረጋል ተብዬ ወደ አገሬ መጣሁ ›› የሚሉት ምሁሩ በቅንጅት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ አባል ነበሩ።

በጉራጌ ዞን ችሃ ምርጫ ክልል ተወዳድረው አሸንፈው እንደነበር ይናገራሉ።
ዶክተር ያዕቆብ አሰብ የማናት በሚለው መጽሃፋቸው የሚታወቁ ሲሆን መጽሀፉም 8 ጊዜ ታትሟል።

እኛም በወቅታዊው የአገሪቱ ፖለቲካ፣ የአገሪቷ የወደብ እጣ ፋንታንና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ከዓለም አቀፉ የህግ ምሁሩ ጋር ቆይታ አድርገናል

ሸገር ታይምስ፡- በቀጣናው ሃያላን አገራት የጦር ሰፈር እየገነቡ ናቸው፣ አገራቱ የጦር ሰፈር እየገነቡ ያሉት ደግሞ ኢትዮጵያ የወደብ አማራጮቼ በምትላቸው አካባቢዎች ነው፣ ይሄ የሃያላን አገራት እንቅስቃሴና ከበባ ኢትዮጵያን የት ድረስ ያሰጋታል

ዶክተር ያዕቆብ፡- ጉዳዩ በጣም ያሳስባል። ምንም አያጠራጥርም፣አሰብ ላይ ሳውዲ አረቢያና ኢሚሬትስ የጦር ሰፈር ሰርተዋል፣ ከዚያም ግብጽ አሁን ሱማሌ ላንድ ላይ እንደዚሁ የጦር ሰፈር ለማቋቋም ውይይት እያደረገች ነው። ግብጽም ሆነ ሌሎቹ የአረብ አገራት ጅቡቲ ዉስጥ ብዙ እንቅስቃሴ አላቸው።አንዳንድ ሰፈሮችም ሰርተዋል።ከዚያም አልፎ ግብጽ ቀጣናውን አልፎ አንዲያውም ከደቡብ ሱዳን አንድ ስምምነት ተደርጓል። ስምምነቱ ምን እንደሆነ ብዙ ሰው አያውቅም።ስለዚህ አሁን ኢትዮጵያ ቀለበት ውስጥ ገብታለች።ተከባለች ማለት ነው። ስለዚህ በተከበበችበት ሁኔታ እነዚህ የጦር ሰፈር መስራት በተጨማሪም ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ግብጽ አውሮፕላን የሚመጠቅበት የጦር መርከብ ገዝታለች።እና ይሄ ሁሉ ለምንድነው ግብጽ ያስፈለጋት የሚለው ጥያቄ ሲነሳ የኢትዮጵያ ሁኔታ እዚያ ውሰጥ መግባቱ የሚያጠራጥር አይደለም።

ስለዚህ አገራችን እርግጥ ነው በጣም አስቸጋሪና አደገኛ ልለው የምችል ደረጃ ላይ ነው ያለችው።በዛ ላይ ደግሞ መቼም አሁን በአገራችን የተከሰተው አለመግባባትና በህዝቡ መካከል ያለው መናቆር በየቦታው የሚነሱ ሰላማዊ ሰልፎች ምንድነው የሚያመለክቱት በህዝቡ በኩል አንድ አንድነት እንደሌለ ነው ህዝቡ ተከፋፍሏል።በተከፋፈለ ሁኔታ ለውጭ ጠላት አመቺ ይሆናል።ስለዚህ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥም ባለው በውጭም በተጋለጥንበት ሁኔታ በጣም አስጊ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለችው ነው የምለው።

ሸገር ታይምስ ፡-አገሪቷ ወደብ ተከራይታ እቃዎችን ከማስገባትና ከማስወጣት በዘለለ ዘላቂ አማራጭ ይኖራት ይሆን?
ዶክተር ያዕቆብ፡- በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ወደብ ከሌላቸው አገራት በህዝብ ቁጥርም በስፋትም የመጀመሪያው ላይ ትሰለፋለች።ስለዚህ ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ በተለይ ደግሞ አገር ውሰጥ ትብብር አንድነት በሌለበት ሁኔታ እንዲህ አይነት ከበባ በኢትዮጵያ ላይ መደረጉ በጣም አስጊ ሁኔታነው የሚፈጥረው።

ወደብ እኮ ለኢኮኖሚ ብቻ አይደለም፣ለኢኮኖሚም በጣም ጠቃሚ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ምሁራን ሲጽፉ ወደብ የሌላት አገር በደንብ ልትበለጽግም አትችልም ይላሉ።በዓለም 44 ወደብ የሌላቸው አገሮች አሉ።ከ44ቱ የድሃ ድሃ የሚባሉት 13 ናቸው፣ ከነኝህም ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ነች።እና ወደብ ለኢኮኖሚ በጣም በጣም አስፈላጊ ነው።አንድ ኩባንያ ከሌላ አገር ከለሙ አገሮች ገንዘቤን በስራ ላይ ላውል ብሎ ሲያስብ ሲያሰላስል ከሚጠይቃቸው ጥያቄዎች አንዱ የፖለቲካ መረጋጋት አለወይ፣ሁለተኛ ደግሞ ያ አገር ወደብ አለው ወይ ነው ብሎ ነው የሚጠይቀው። ወደብ ከሌለው ብዙ ብዙ የሚያመርታቸው ዕቃዎች ውድ ነው የሚሆነው።ማጓጓዙ አስቸጋሪ ይሆናል።እና ብዙ ብዙ ነገሮች ይከተላሉ ከኢኮኖሚው አንጻር።

ከአገር ደህንነት አንጻር ደግሞ በጣም ወሳኝነት አለው በታሪክ እንደሚታወቀው ብዙ ጊዜ የተወረርነው በዚሁ በቀይ ባህር በኩል ነው። ና ኢትዮጵያ በአጼ ሃይለስላሴ ጊዜ በጣም የዳበረ የባሀር ሃይል ነበራት።ያ የባህር ሃይል ጠላት ለመመከት በጣም አመቺ ነው።እና አሁን ተጋልጣለች።በቀጥታ ከቀይ ባህር ወደ ኢትዮጵያ ነው የሚዘለለው።እና አሁን አካባቢው ደግሞ በዲፕሎማሲ አካባቢ ብናስበው ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ምንም ጥቅም የላትም ።የዓለም ማህበረሰብ ውይም ሃያላን መንግስታት ኢትዮጵያን የሚፈልጉበት ምንም ምክንያት የለም። አሁን የዓለም ሃያላን መንግስታት በሙሉ የከተሙት ጅቡቲ ላይ ነው። ኢትዮጵያ ጠቃሚነት የላትም ወደበ ስለሌላት። ምንም የምትጠቅም አገር አይድለችም ለስትራቴጂክ ዓላማ።

እርግጥ ኢትዮጵያ ከዚህ ከአሰብ ወደብ አልባ በመሆኗ አንደኛ ደህንነቷ ስጋት ላይ ወድቋል፣ ሁለተኛ ኢኮኖሚዋ በጣም በጣም ተጎድቷል።ሶስተኛ በዓለም ማህበረሰብ መንግስታት አካባቢ ምንም ክብደት የሚሰጣት አገር አይደለችም።ከኢትዮጵያ የበለጠ እንዲያውም ክብደት የሚሰጣት ጂቡቲ ናት። እና ወደብ አልባ መሆኗ በጣም ብዙ ጉዳት እንዳለው ከዚሁ መረዳት ይቻላል።ብዙ በዙም ነገሮች አሉ።እንግዲህ መፍትሄው ምን እንደሆነ እስቲ እንነጋገርበታለን።

ሸገር ታይምስ ፡-እርስዎ አሰብ የማናት በሚለው መጽሃፍዎ ላት በዓለም አቀፍ ህግ ኢትዮጵያ ወደብ ማግኘት ትችላለች ብለዋል። ይህ አንደት ነው የሚሆነው ምንድነው አማራጩ?

ዶክተር ያዕቆብ፡- እንግዲህ ኢትዮጵያ በዓለም አቀቀፍ ህግ መሰረት ወደብ የምታገኝበት ዕድል አለ የምለው አሰብ የኢትዮጵያ ሀብት ነበር ከሚለው ተነስቼ ነው። አሰብ በእውነትም የኢትዮጵያ ንብረት ነበረች። ከኤርትራ ጋር የተቀላቀሉት እኮ ከ15 ዓመታት በኋላ ነው።መጀመሪያ ሮሚታኖ የሚባል የጣሊያን ኩባንያ ነው የያዘው ከዛ በኋላ አሰብ ሱልጣን ኢብራሂም የሚባለው የአሰብ አስተዳዳሪ ሸጣት ከአጼ ምኒልክ ዕውቅና ውጭ። ከዛም ደግሞ በ1952 ዓመተ ምህረት ኢትዮጵያና ኤርትራ

በፌዴሬሽን ሲቀላቀሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤርትራን ህዝብ ስሜት በማገናዘብና በተለይም ይላል ቃሉ በተለይም የኢትዮጵያን የባህር በር መብት ለማስከበር ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ተቀላቅላለች ይላል። እና በዓለማቀፍ ህግም የተባበሩት መንግስታት የሚያወጣቸው ህጎች የዓለማቀፍ ህግ አካል ናቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያ በዓለማቀፍ ህግ ያላት መብት ነው። እና አሁንም ቢሆን ይህንን ጥያቄ ልታቀርብ ትችል ነበር። እንዳውም በአልጀርስ ስምምነት ጉዳይ የወደብ ጉዳይ ጭራሽም አልተነሳም። በፍጹም አልተነሳም የአልጀርስ ስምምነት በሚደረግበት ጊዜ በሚደራደሩበት ጊዜ የኢትዮጵያ የወደብ ጉዳይ አንድም ጊዜ አልተነሳም ይሄ በእውነት የአገር ክደት አድርጌ ነው የማየው።

ሸገር ታይምስ ፡- ኢትዮጵያ አሰብን ማስመለስ ትችላለች የሚሉ ሰዎች አሉ። ከመንግስት ወገን ያሉት ደግሞ አሰበን ስለማስመለስ ማውራት የሌላ አገርን ሉዓላነት መጋፋት ነው ይላሉ። እነዚህን ሃሳቦች ምንድነው የሚያስታርቃቸው?

ዶክተር ያዕቆብ፡- እነዚህን ሃሳቦች ማስታቅ ይቻላል። ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት አገር ነች። እና 100 ሚሊዮን ህዝብ በእግር መንገድ ርቀት ወደብ አልባ ትሁን ወደብ ይዘጋባት ማለት ፍትሃዊ አይደለም። ደግሞ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ሀብትና ንብረት እንደመሆኑ መጠን አሁንም ወደ ኢትዮጵያ መመለስ አለበት። ወይንም ከኤርትራ ጋር አንድ ስምምነት መደረግ አለበት። እንጅ ኢትዮጵያ በእግር መንገድ ርቀት በ60 ኪሎ ሜትር ፣ ይሄ 60 ኪሎ ሜትር በዓለም በጣም ትንሹ ርቀት የሚባለው ነው። በወደብና በየብስ መካከል ያለው ትንሹ ርቀት ነው።እና በዛ ርቀት ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ትሁን ሲባል ፍትሃዊ አይደለም እና ስለዚህ ለሰላም ሲባል ምናልባት ከኤርትራ ጋር መደራደር ይቻል ይሆናል። በኤርትራ በኩል ምናልባት አሰብ የሁለቱም የጋራ ንብረት ሊሆን ይችላል ኤርትራም ኢትዮጵያም በጋራ ሁለቱም በሉአላዊነት ሊይዙት ይችላሉ።

ይሄ ለሰላም ሲባል ነው እንጅ አሰብ የኢትዮጵያ ንብረት የኢትዮጵያ ሀብት ለመሆኑ ለመካድ አይደለም። ግን እንዳው ለሰላም ሲባል ከኤርትራ ጋር ጣምራ ሉአላዊነት ቢኖራቸው እንግዲህ አሰብ ራሱን የሚያስተዳድር አንድ አስተዳደር ይሆናል። ወደብን በመጠቀም ላይ ግን ሁለቱም እኩል መብት እንድኖራቸው ማድረግ ይቻላል። እንዲህ አይነት ሁኔታዎች አሉ። በተለያዩ አገሮች እንዲህ አይነት ሁኔታዎች አሉ። እና ምናልባት ኤርትራውያን ወንድም አህቶቻችን ናቸው ከነርሱም ጋር ለመቀራረብ ለወደፊቱ ለሰላምም ሲባል ምናልባት አሰብም በጋራ ሁለቱም በጋር ሊጠቀሙበት የሚችል ሁኔታ መስማማት ይቻል ይሆናል።

ሸገር ታይምስ ፡- ይህንን ወደ ክርክር ለመውሰድና አሰብ የኢትዮጵያ ነች ለማለት የሚያስችል ሁኔታ ምንድነው?

ዶክተር ያዕቆብ፡- አንደኛ መጀመሪያውኑ እስከመነሻው አሰብ የኢትዮጵያ ግዛት ነበረ። እና ኤርትራ የሚባለው አገር ከመፈጠሩ በፊት አሰብ ነበረ። ሩባቲኖ ኩባንያ ገዘቶት ነበር።ከ15 ዓመታት በኋላ ጣሊያኖች ኤርትራ የሚባል አገር ፈጠሩ። ከዛ በኋላ አሰብን ወደዛ አጠቃለሉት። አጼ ምኒልክ ደግሞ ግዛታቸውን ለዓለም ማህብረሰብ ሲያስታውቁ ግዛቴ የሚሸፍነው ቀይ ባህር ነው። ወሰኑ ቀይ ባህር ነው ፣ በደቡብ በኩል ኬንያ ነው። የኢትዮጵያ የባህር በር መዘጋት እኔ በኢትዮጵያ ላይ ከተፈጸሙ በደሎች ቁንጮ አድርጌ ነው የማየው።

በምዕራብ ደግሞ እስከ ሱዳን ይደርሳል ብለው ለዓለም ህብረተሰብ አስታውቀዋል። እና አጼ ምኒልክ ሳያውቁ ነው ሱልጣን ኢብራሂም አሰብን የሸጠው። እና አሰብ በሱልጣን ኢብራሂም በአጼ ምኒልክ ስር ነበር።በርግጥ በዛን ጊዜ ብዙ ቁጥጥር አይኖርም። በኮሚኒኬሽን ችግር ምክንያት ብዙ ቁጥጥር አይኖርም እና አጼ ምኒሊክ አላወቁም አሰብ ሲሸጥ እንጅ ሽያጩ ደግሞ ትክክል አልነበረም።

ሸገር ታይምስ ፡- ከ95 በመቶ በላይ የሀገሪቷ ወጪና ገቢ ንግድ በጂቡቲ ወደብ የሚያልፍ ነው። ጂቡቲ አንድ ቀን ለአገሪቷ በጣም አስፈላጊ ቁሳቁሶች እንዳይገቡ ብትከለክል የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ ምንድነው?

ዶክተር ያዕቆብ፡- በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት አንድ አገር የሌላ አገርን ወደብ ተጠቅሞ ሰላማዊ ዕቃዎች ማስገባት ይችላል። ሰላማዊ ዕቃዎች የጦር መሳሪያ ሳይሆን፣ የጦር መሳሪያም ማስገባት ይችላል ግን ያ አገር አይ ከሚያስፈልግህ በላይ ነው አላስገባም ሊል ይችላል።ጂቡቲ ለምሳሌ የጦር መሳሪያ ወደ ኢትዮጵያ አላሳልፍም ልትል ትችላለች። በቂ የጦር መሳሪያ አላችሁ ልትል ትችላለች።

ያኔ ከኤርትራ ጋር በተደረገው ጦርነት ጂቡቲ ያኔ ከኤርትራ ጋር ግጭት ነበራት ። ጂቡቲ ባትፈቅድ ኖሮ ኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና ውስጥ ነበር የነበረችው። እንዳውም እኮ በጣሊያኖች ድል ለመሆናችን አንዱ ምክንያት ፈረንሳዮች በጂቡቲ በኩል ጦር መሳሪያ አናሳልፍም ስላሉ ነው ይባላል። አንዱ ምክንያት እርሱ ነው ይባላል።
በማይጨው ጦርነት ላይ አንዱ ምክንያት እርሱ ነው። የሚባለው ለሽንፈታቸን ምክንያት እርግጥ በጣም በጣም አደገኛ ሁኔታ ነው የሚፈጥረው።
እርግጥ ሞምባሳ አለ ወይንም ደግሞ ፖርት ሱዳን አለ፣ ግን ደግሞ እነ ሞምባሳ ለሰሜን ኢትዮጵያ ከ1800 ኪሎ ሜትር በላይ ነው ርቀቱ በጣም በጣም ሩቅ ነው። እና ደግሞ መንገዱም አመቺ አይደለም። ኬንያና ኢትዮጵያን የሚያገናኘው መንገድ በኬንያ በኩል ተሰርቶ አላለቀም።

እና በጣም አደገኛ ሁኔታ ነው የሚፈጥረው። ወደብ አስፈላጊነቱ ለኢኮኖሚ ብቻ አይደለም። በቀን ለጂቡቲ 5 ሚሊዮን ዶላር ነው የሚከፈለው ነው የሚባለው። ጂቡቲ ደግሞ ያንን የምታስከፍለውን በፈለገች ጊዜ ለመጨመር የሚከለክላት ነገር የለም። እንዳውም በአንድ ወቅት በ25 በመቶ ታሪፍ ጨምራ አቶ መለስ ራሱ ጂቡቲ ሄዶ መደራደር ነበረበት። ግዛቷ ነው የፈለገችውን ያህል ልታስከፍል ትችላለች። ካልፈለገች ደግሞ አንዳንድ መሳሪያዎችን የመሳሰሉ ነገሮች አላስገባም ልትል ትችላለች።
እና በእውነት ኢትዮጵያ እዚህ ላይ ታሰረች ማለት ነው። ሆስቴጂ እስረኛ ሆነች ማለት ነው። በጣም መጥፎ በጣም ከባድ ነገር ነው በእውነት። ሰዉ ተረድቶት እንደሁ ኢትዮጵያ የባህር በር መዘጋት እኔ በኢትዮጵያ ላይ ከተፈጸሙ በደሎች ቁንጮ አድርጌ ነው የማየው፣ ከማይጨውም ከአድዋም ይበልጣል።አድዋም አሸንፈናል፣ ማይጨውም በሂደት አሸንፈናል። ይሄ ግን በእውነት መቋጫ የሌለው ከባድ ነገር ነው።

ሸገር ታይምስ ፡- ወደብ ሚስጥር ነው ይባላል ምን ማለት ነው?
ዶክተር ያዕቆብ፡- አዎ ወደብ ሚስጥር ነው ትክክል ነው። በዚህ በአሰብ በኩል ገብተው በቀይ ባህር ገብተው ኢትዮጵያን መሰለል በጣም ቀላል ነው የሚሆነው ። በተለይ ደግሞ አሁን ሳውዲ አረቢያና ኢሚሬትስ የጦር ካምፕ ሰርተውበታል። እነ ሳውዲ ብዙዎቹ ዉሃቢ ናቸው። ዉሃቢ ደግሞ ተስፈንጣሪ ሃይማኖት ነው። ኤርትራ ውስጥ ደግሞ ክርስትናና እስልምና እኩል ለእኩል ነው። አሁን ውሃቢዎቹ በሚገቡበት ጊዜ እኩል ለእኩል የነበረውን ሚዛን ሊዛባ ይችላል። ቅርብ ጊዜ እንደሰማሁት ከኤርትራ ደግሞ የሚሰደዱ ክርስቲያኖቹ ናቸው። ስለዚህ ኤርትራ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስላማዊ ሪፐብሊክ ልትሆን ትችላለች። ይሄ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ይኖረዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራን መለየት በጣም አስቸጋሪ ነው።

እናም የነዚህ የአረቦች ኤርትራ ውስጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያንም የሚመለከት ጉዳይ ነው። በዚህ አይነት ሁኔታ ኢትዮጵያም ኢኮኖሚዋ ትልቅ ችግር ውስጥ ነው። ደህንነቷም ሉአላዊነቷም፣ ደህንነቷም አደጋ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል።በኢኮኖሚ ደግሞ ወደብ የሌላቸው አገሮች ወደ ውጭ የሚልኩት ምርት ከ33 እስከ 40 በመቶ ሊቀንስ ይችላል።

ሸገር ታይምስ ፡- የኢትዮጵያ መንግስት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል መሆኑን የዲፕሎማሲ ስኬት አድርጎ ይቆጥራል። በኢንቨስትም ስለመሸለሙንም ያነሳል። በመንግስታቱ ድረጅት በርግጥ ተለዋጭ አባል መሆን በዲፕሎማሲ ቋንቋ ጉልበቱ ምን ያህል ነው?

ዶክተር ያዕቆብ፡- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል መሆን ምንም የሚያመጣው ነገር የለም። ለኢትዮጵያ ምንም የሚጨምርላት ሃይል የለም።ይሄ ብዙ አገራት በተራ እየተለዋወጡ የሚያገኙት ነገር ነው እንጅ ሃይላቸውና አቅማቸው ተመዝኖ የሚሰጣቸው አይደለም። ብዙ አባል አገራት እንደ አጋጣሚ በየተራ የሚፈራረቁበት ነገር ነው። እንጂ ኢትዮጵያ ባላት ተጽዕኖ ምክንያት አይደለም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የሆነችው። ይሄ ተራ በተራ የሚደረግ ነገር ነው። ብዙ አገሮችም በተራ ያደረጉት ነገር ነው።

ሸገር ታይምስ ፡- ከላይ እርስዎ ያነሷቸው ስጋቶች አሉ። አሰብ የማናት በሚለው መጽሃፍዎን የጠቀሱት ነገር አለ ግን አገሪቷ ምን ብታደርግ ይሻላታል?

ዶክተር ያዕቆብ፡- እንግዲህ በዘላቂነት መጽሃፌም ላይ ያቀረብኩት ሃሳብ ምናልባት ብዙ አማራጮች አሉ።

አንደኛ ከኤርትራ ጋር ተደራድሮ አሁንም ለሰላም ሲባል ምናልባት እንደገና መካለል ። አሰብን ወደ ኢትዮጵያ የሚያደርግ ማካለል ስምምነት ማድረግ አንዱ ነው። እና በዚህ ማለት ኤርትራ የእርሻ መሬት ያስፈልጋታል፣ ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል። እዚህ ላይ ተደራድሮ አንዱ ከአንዱ መግባባት ላይ መድረስ።

ሸገር ታይምስ ፡- አሁን እርስዎ ስለመደራደር አነሱ። በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ አስመራም ሄጄ ለመደራደር ፈቃደኛ ነኝ ይላሉ። ግን አሁን ላይ ያለው የኤርትራ መንግስት በሰጥቶ መቀበል መርህ ያምናል ብለው ያስባሉ?

ዶክተር ያዕቆብ፡- ልክ ነው አሁን ጥሩ ነገር አነሳህ ። ሁለቱም መንግስታት ለድርድር የሚያመቹ አይደሉም። በሁለቱም በኩል ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እስካልተመሰረተ ድረስ ለድርድር ቀና መልስ አይሰጡም። ዴሞክራሲያዊ አገሮች እኮ አይዋጉም። ሁለት ዴሞክራሲዎች አይዋጉም። ግን ዴሞክራሲ በሌለበት ሁኔታ በኢትዮጵያም በኤርትራም በጠረንጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ለሃገር የሚጠቅመውን ነገር በድርድር ሊግባቡ አይችሉም። ስለዚህ ይሄ የአሁን ጥያቄ አይደለም ማለት ነው። ምናልባት በሁለቱም አገራት ዴሞክራሲ በሚመሰረትበት ጊዜ ራሽናል በሆነ መንገድ የአገራችን ጥቅም ምንድነው ብለው ሊደራደሩ ይችሉ ይሆናል።

አሁን ያቀረብኳቸው ሃሳቦች እኮ በአሁኑ ጊዜ ይፈጸማሉ ሳይሆን ምናልባት በሁለቱ አገራት መካከል ዴሞክራሲ በሚመሰረትበት ጊዜ ሁለቱ ቁጭ ብለው አይ እንደገና እንካለል ኤርትራ የእርሻ መሬት ያስፈልጋታል፣ ኢትዮጵያ የእርሻ መሬት ትሰጣለች አሰብ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ይካለል የሚል አንዱ አማራጭ ሊሆን ይችላል።
ሌላው አማራጭ ደግሞ ፊት እንዳልኩት ሁለቱም በጋራ እንዲጠቀሙበት አሰብ ራሱ ራስ ገዝ ሆኖ በነገራችን ላይ የኤርትራ አካል አልነበረም። በደርግ ዘመን አሰብ ራስ ገዝ ነበር። በአጼ ሃይለስለሴ ዘመን ደግሞ አሰብ የወሎ ክፍለ አገር አካል ነበር። ስለዚህ ወደዛ ለመመለስ ሁለቱም በጋራ እንዲጠቀሙበት ራስ ገዝ ሆኖ አስተዳደሩ በዚያው በአሰብ አካባቢ ተመስርቶ ወደቡን በመጠቀም ላይ ግን ሁለቱም በጋራ የሚጠቀሙበት መንገድ መሻት ይቻል ይሆናል። ለዚህ ግን በሁለቱም አገራት ውስጥ በእውነት ለህዝብ የቆመ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የገነባ አይነት መንግስት ያስፈልጋል።ዴሞክራሲያዊ መንግስት ካልሆነ መንግስት ጋር መደራደር አስቸጋሪ ነው። አይሆንምም። ይሄ እንግዲህ ጊዜ የሚፈልግ ነገር ነው ማለት ነው።

ሸገር ታይምስ ፡- አሰብ የኢትዮጵያ ነበር አሉኝ ። ታዲያ አሰብን የኤርትራ ግዛት ያደረገው ማነው?
ዶክተር ያዕቆብ፡- እንግዲህ ፌዴሬሽኑ በሚፈርስበት ጊዜ አሰብ ወደዛ ወደ ኤርትራ ታጠፈ። ፌዴሬሽኑ በ1952 ዓመተ ምህረት ነበረ የተቋቋመው ከዛ በኋላ ፌዴሬሽኑ ሲፈርስ አሰብ የኢትዮጵያ አካል ሆነች። ኢትዮጵያ በዚያን ጊዜ ሁለት ወደቦች ነበሯት ማለት ነው ምጽዋና አሰብ። ኤርትራ ስትገነጠል አሰብን ይዛ ነው የሄደችው ። ይሄ ደግሞ በዓለም አቀፍ ህግም ትክክል አይደለም። አሰብ የኢትዮጵያ ነበረች ኤርትራ ነጻ በወጣችበት ጊዜ እና ኤርትራ ነጻ ስትወጣ የያዘችውን ግዛት ብቻ ነበር ይዛ ነጻ መውጣት የነበረባት። ይሄ በህግ በያዝከው እርጋ ማለት ነው። እና ኤርትራውያን ሲገነጠሉ የያዙትን ብቻ ነበር ይዘው መውጣት የነበረባቸው።

አሰብ የኤርትራ ግዛት የኤርትራ አካል አልነበረም። ወደ ኢትዮጵያ መቅረት ነበረበት። ግን ጠያቂ አልነበረም። ማንም ጠያቂ አልነበረም። እንዲያውም ኤርትራና ኢትዮጵያ ህወሃትና ወይንም ኢህአዴግና ሻዕቢያ በሚደራደሩበት ጊዜ አደራዳሪ የነበረው የአሜሪካው የአፍሪካ ክፍል ሃላፊ ኢትዮጵያ እንደት ወደብ አልባ ትሆናለች በሚልበት ጊዜ መለስ ዜናዊ አንተ ይህንን የሚመለከትህ ጉዳይ አይደለም፣ እኛ የምንነጋገርበት ነገር ነው አንተን አይመለከትህም አለው። እንጅ አሜሪካኖችም ኢትዮጵያ ወደብ እንደሚያስፈልጋት አሰብ የኢትዮጵያ አካል መሆኑን በድርድሩ ጊዜ አውቀው አጽድቀው ነበር። መለስ ዜናዊ ነው ይህንን አያገባችሁም ብሎ እንዳውም በዘለፋ መልክ ነው ኮኸን የተባለውን ሰውዬ መልስ የሰጠው ይባላል።

ሸገር ታይምስ ፡- እርስዎ በሃገራት መካከል የተፈጠሩ የድንበር ግጭቶችን በህግ ዳኝተዋል። ከዛ ልምድዎ በመነሳት ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ፊት የመዋሃድ እጣ ይኖራቸው ይሆን ብዙዎች የዚህ ግምት ባለቤት እየሆኑ ናቸው?

ዶክተር ያዕቆብ፡- እንግዲህ የሁለቱ አገሮች እጣ ፋንታ አሁን የምንነጋገረው በአሁን መንግስታት ሳይሆን ወደፊት ዴሞክራሲ በሚመሰረትበት ጊዜ የሁለቱ እጣ ፋንታ የተሳሰረ ነው። በምንም መለየት አይቻልም። እኔ ምስራቅ አፍሪካም ምዕራብ አፍርካም ሰርቻለሁ ኖሬባቸዋለሁ። በእውነት። እንዳው ሁለት ተመሳሳይ ህዝብ እንደ ኤርትራና ኢትዮጵያ ህዝብ ተመሳሳይ ህዝብ አይቸ አላውቅም። በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት በሁሉ ነገር ሁለቱን ለይቶ ማየት አይቻልም። እና ወደፊት የሰከኑ መሪዎች በዴሞክራሲ እምነት ያላቸው ለህዝብ የቆሙ መሪዎች በሚኖሩበት ጊዜ የሁለቱ ዕጣ ፋንታ የተሳሰረ በመሆኑ ወይ ፌዴሬሽን ወይ ኮንፌዴሬሽን ይመጣሉ የሚል እምነት አለኝ። አሁን በእውነት እነዚህ ሁለት አገሮች የኢትዮጵያ 100 ሚሊዮን ህዝብ የኤርትራ ታታሪ 5 ሚሊዮን ህዝብ የኢትዮጵያ ሰፊ ገበያ ለኤርትራውያን ክፍት ሆኖ ኢትዮጵያ ሁለት በጣም ስትራቴጂክ የሆኑ ወደቦች ቢኖራቸው እነዚህ ሁለቱ ቢዋሃዱ ወይንም ፌዴሬሽን ቢፈጥሩ በእውነት በጣም ከባድ የሆነ ጠንካራ አገር ሊወጣቸው ይችል ነበር። በአካባቢው ሱፐር ፓወር ሊሆኑ ይችሉ ነበር።

ግን አርቆ ማየት የተሳናቸው መሪዎች በሁለቱም በኩል እነኝህ መከፋፈል የሌለባቸውን ህዝቦችን በጣጠሷቸው። አሁን በህዝቡ በኩል ውይይት እየተካሄደ ነው። እንዳውም ቅርብ ጊዜ የካቶሊክ ሃይማኖት ጳጳሳት ኤርትራ ሄደው ከኤርትራ ባለስልጣናት ጋር ሰላምን አስመልክቶ እየተነጋገሩ ነው። በነገራችን ላይ የካቶሊኩ ጳጳስ አቡነ ብርሃነየሱስ ኤርትራ እንዳይገቡ ታግደዋል።እርሳቸው እንዳውም የቡድኑ ሊቀመንበር ነበሩ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ግን ታግደዋል። እነዚህ ከአፍንጫቸው አርቀው ማሰብ ያልቻሉ ኢሳያስም ሆነ መለስ እንዳው አርቀው ቢያስቡ ኖሮ በጣም ትልቅ የዳበረ ከባድ ትልቅ ጫና ሊያደርግ የሚችል አገር ሊፈጥሩ ይችሉ ነበር።

ሸገር ታይምስ ፡- ኢትዮጵያና ኤርትራ ቢዋሃዱ በቀይ ባህር አካባቢ ሚናቸው ምን ያህል ይሆን ነበር ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ያዕቆብ፡- ትልቅ አገር ሊሆኑ ይችሉ ነበር በእውነት።

ሸገር ታይምስ ፡- ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአሰብ ቁጭትዎን በደብዳቤ ስለመጻፍዎት በአሰብ የማናት መጽሀፍ ላይ አስፍረውታል። ለአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትርስ ደብዳቤ ጽፈዋል ወይም ለመጻፍ አስበዋል?

ዶክተር ያዕቆብ፡- እኔ በአሁኑ ጊዜ ብዙም ለውጤት የሚበቃ ነገር አይሆንም ያው እንግዲህ ጊዜውን መጠበቅ ያስፈልጋል። ትንሽ አርቀው ሊያስቡ የሚችሉ መሪዎች እስኪመጡ ድረስ ምናልባት መቆየት ያስፈልግ ይሆናል። በአሁኑ ሁኔታ ላይ ለአቶ ሃይለማሪያም ተጻፈ ለኢሳያስ ተጻፈ ምንም ለውጥ የሚያመጣ ነገር የለም። አቶ ሃይለማሪያም በተደጋጋሚ ተናግረዋል፣ ኤርትራ ሄደን ለመነጋገር ፈቃደኞች ነን ብለዋል። ሆኖም ግን አቶ ሃይለማሪያም ራሱ በአንድ ወቅት አሰብ የኤርትራ ግዛት ነች፣ ኢትዮጵያ በምንም ሁኔታ አሰብን የምትጠይቅበት ምንም ምክንያት የለም ብሎ ተናግሮታል። እዛ መጽሃፍ ላይ እንዳውም ኮት አድርጌዋለሁ። እና በአሁኑ ጊዜ የኢህአዴግ መንግስት የኢትዮጵያን የባህር በር መብት ያስከብራል የሚል በበኩሌ እምነት የለኝም መጠበቅ ይኖርብናል።

ሸገር ታይምስ ፡- በአገሪቷ ግጭቶች ተበራክታውል፣ በመንግስት ላይ ኩርፊያዎች ታይተዋል፣ ከ2007 ዓመተ ምህረት አገር አቀፍ ምርጫ በኋላ በተለይ ገዥው ፓርቲ 100 በ100 አሸነፍኩ ባለ ማግስት ይህ መሆኑ ምንን ያሳያል?

ዶክተር ያዕቆብ ፡- በአገራችን መናቆር የተፈጠረበት ምክንያት አገሪቱን በብሔር ከፋፍሎ አንዱን ብሔር ሌላውን ጨቋኝ አድርጎ መንግስት ባዋቀረው ፌዴሬሽን ምክንያት እንዳውም የኢትዮጵያ ህዝብ ጨዋ ህዝብ ሆኖ ነው እንጅ አንዱ ጨቋኝ አንዱ ተጨቋኝ ተብሎ ሲሰበክ የነበረ ህዝብ ነበር።እና የኢትዮጵያ ህዝብ ጨዋ ሆኖ ነው እንጅ በዛ በስብከቱ መሰረት ቢሆን ኖሮ ወደ መጥፎ ሊያመራ ይችል ነበር። እና በብሔር ትምህክተኛ ጠባብ እየተባለ ተከፋፍሎ ህዝቡ ትምክተኛው አንተን ይንቅሃል በዝብዞሃል እየተባለ ሲሰበክ የኖረ ነው። እና አሁን ለተፈጠረው መናቆር ዋናው ምክንያት በብሔረሰብ ሰበጣጥሮ ያንን ፌዴሬሽን የሚባለውን በብሔር መከፋፈሉና አንዱን ብሔር የሌላው ጠላት አድርጎ በማቅረብ የተፈጠረ ሁኔታ ነው። ይሄ ግን እኔ በእውነት በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጭቆና አለ ብዬ አላምንም አልነበረም። ምናልባት ኢህአዴግ እስኪመጣ ድረስ እንዳውም የብሔር ጨቆና አልነበረም። እርግጥ ነው አሁን ኬንያ ውስጥ ኪኩዩ፣ አካምባዩ ፣ የሚባሉ አሉ።

ኪኩዮች ትንሽ የበላይነት ይሰማቸዋል። ኡጋንዳ ውስጥ ባጋንዳ የሚባሉት የበላይነት ይሰማቸዋል። ሶማሊያ ውስጥ እንኳን ብትሄድ መሪሃን የሚባሉት ትንሽ የበላይነት ይሰማቸዋል። ኢትዮጵያም ውስጥ አንዳንድ አባሎች የበላይነት ይሰማቸው ይሆናል።ግን በህግ በፖሊሲ ተደንግጎ በፖሊሲ ተቀርጾ አማራ እንዲህ ነው። አማራ የበላይ ነው አማራ ይሄን ይሄን ያገኛል። ሌላው የማያገኘውን ለአማራ ይሰጣል የሚል ነገር ተሰምቶ አያውቅም። እንዳውም ብዙ ሰዎች ባጠኑት መሰረት በገጠሩ ብንሄድ የድሃ ድሃው አማራው ነው። እና አማራው የተለየ ዕድል የተለየ ፕሪቪሌጂ ተሰጥቶት አያውቅም። ማነው ማንን የጨቆነው፣ ማንም የተጨቆነ የለም። እርግጥ በሁሉም አገር ያለ ነው አንዱ የበላይነት ሊሰማው ይችል ይሆናል።ግን በፖሊሲ ተቀርጾ ያ ብሔር ልዩ ጥቅም ካልተሰጠው የብሔር ጭቆና አለ ማለት አይቻልም።

ሸገር ታይምስ ፡- ሰሞኑን ህዝባዊ ምክክሮች በክልሎች መካከል እየተደረጉ ነው። የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች በባህርዳር፣ የአማራና ትግራይ ደግሞ ጎንደር ላይ ምክክር አደርገዋል። ይህ ምን ትርጉም ይኖረዋል?

ዶክተር ያዕቆብ ፡- አሁን በኦሮሚያና አማራ ክልሎች መካከል የተጀመረው የሚያዘልቅ ከሆነ በጣም ደስ የሚል ነው። በእውነት እኔ እንደ አብዮት ነው የቆጠርኩት፣ እና በጣም ደስ የሚል ነው ወደነበረው ተመለሰ። በሌለ ነገር በሌለ ምክንያት አማራ ኦሮሞ እየተባለ ሲያጋጩ የነበሩ ካድሬዎች አሁን ባዷቸውን ወጥተዋል። አሁን የሚታየው ከወጣቱም፣ ከምሁራንም፣ አካባቢ ኦሮሞዎች የወሰዱት አቋም ትክክልኛ ነው። መሆንም የነበረበት ነው። የነሱን መተባበርና የማይፈልጉ ሰዎች የነዙት የነበረ ጠላትነት ነበረ እንጅ በኦሮሞ ህዝብና በአማራ ህዝብ መካከል ጥል ኖሮ ወይንም ጥላቻ ኖሮ አያውቅም። እርግጥ ነው ብዙ አማሮች ከየቦታው ተባረዋል።

ለመባረራቸው ምክንያት የፖለቲካ ካድሬዎች ናቸው እንጅ ህዝቡ አይደለም። ለምሳሌ ጉራፋርዳ አማሮች ተፈናቀሉ፣ ሲፈናቀሉ የአገሬው ህዝብ ተሰብስቦ ሸኝቷቸው ስንቅ እያስቆጠረ ነው፣ ህዝቡን የሸኘው እንጅ በህዝቡ መካከል የነበረው፣ ግጭት አልነበረም። አንዳንድ ካድሬዎች የፈጠሩት ነገር ነው እንጅ በህዝቡ መካከል ምንም ጊዜ ግጭትና ጥላቻ ኖሮ አያውቅም። በእውነት የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ ሊመሰገን የሚገባው ነው።

ሸገር ታይምስ ፡- አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ክልሎች ለአስተዳደር እንዲመቹ የተቋቋሙ አይመስሉም። በሀገሪቷ ብዙ አገሮች ያሉ ነው የሚመስለው ፣ ክልሎችም ዓላማቸው ክልላዊ መሆን እንጅ በኢትዮጵያዊ ጉዳይ ላይ እያተኮሩ አይደለም ይባላል። ይሄን ነገር አስጊ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ?

ዶክተር ያዕቆብ ፡- አንዳንድ ክልሎች ልክ ሌላ አገር እንደሆኑ አድርገው ነው የሚወራውና የሚሰበከው ስለወሰን ነው የሚናገሩት፣ በአንድ አገር ምን ወሰን ይኖራል? መካለል አለብን ይባላል፣ በአንድ አገር ውስጥ እኮ መካለል አያስፈልግም። እስከዚህ ድረስ ከብት ልታስግጥ ትችላለህ፣ እስከዚያ ድረስ ልታርስ ትችላለህ ይባላል እንጅ መካለል ።ልክ እንደሌላ አገር ከኬንያ ጋር እንደሚደረገው ወይንም ከኤርትራ ጋር እንደሚደረገው ስለመካለል ያወራሉ። እና ይሄ ክልሎች የሚለው በእውነት በጣም ኢትዮጵያ የምትለዋን ዋናውን ሃሳብ እያደበዘዙ እየመጡ ነው። ኢትዮጵያ የሚለው እየደበዘዘ ክልሎች እየገነኑ እየመጡ ነው። እርግጥ አሁን በህዝቡ ውስጥ የተፈጠረው በጣም ደስ የሚል ነው። ግን መሪዎቹ ናቸው ይህንን የሚያመጡት የመሪዎቹ እንጅ የህዝብ ችግር አይደለም። የክልል መሪዎች ራሳቸውን እንደ ንጉስ ቆጥረው ልክ እንደ ሌላ አገር ክልላቸውን እንደ ሉአላዊ አገር ቆጥረው፣ ስለመካለል ከአንዱ ክልል ወደ አንዱ ክልል እኮ ፈቃድ እንደሚያስፈልግ ነገር እኮ ነው።
በህገ መንግስቱ ደግሞ እንዳውም ይሄ ከአጼ ምኒልክ ጀምሮ አጼ ምኒልክ አንዱ አዋጃቸው ዜጋዬ በፈለገበት ይቀመጥ ፣ ከአንዱ ቦታ ወደ አንዱ ቦታ ማፈናቀል ክልክል ነው። ይህንን ብታደርግ አልምርህም ማሪያምን ብለው አውጀው ነበር። እና አሁንም በህገ መንግስቱ አለ። ማንም ኢትዮጵያዊ በፈለገበት መኖር ይችላል። የመዘዋወርና የመኖር ነጻነት ኦለው። እንዳውም ይሄ ደግሞ ዓለማቀፍ ድንጋጌ ዩኒቨርሳል ዲክላሬሽን ኦፍ ሂዩማን ራይትስ ይህንኑ ይደግመዋል። ማንም ዜጋ በአገሩ ውስጥ በፈለገበት ይኖራል፣ ተዘዋውሮ ሊሰራ ሊኖር ይችላል ይላል።

የኢትዮጵያ እንዳውም ከዛም የተራመደ ነው። ይሄ መብት ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ህግን ተከትለው የገቡ የውጭ አገር ዜጎችንም ነው። አንድ የውጭ አገር ዜጋ ህግን ተከትከሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ከገባ በፈለገበት ሊኖር ይችላል፣ በፈለገበት ሊዘዋወር ይችላል። እና አሁን በክልሎች መካከል ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንዱ ክልል ወደ አንዱ ክልል ለመሄድ አስቸጋሪ እየሆነ ነው። ብዙ ሰዎች በተለይ አማሮች በብዛት በብዛት ከየቦታው እንደተፈናቀሉ ይሄ የሚታወቅ ነገር ነው ይሄ ፍጹም ህገ ወጥ ነው፣ እንዳውም ይሄ ዓላም አቀፍ ወንጀል ነው። አንድ ሰው በዘሩ፣ በቋንቋው፣ በሃይማኖቱ፣ ምክንያት ካለበት ማፈናቀል፣ ዓለም አቀፍ ወንጀል ነው።

ሩዋንዳ እንከሳቸው ከነበሩ ሰዎች / ዶክተር ያዕቆብ በሩዋንዳ ተከስቶ ከነበረው የእርስ በእርስ ግጭት በኋላ ጉዳዩ በህግ ሲያዝ አቃቤ ህግ ነበሩ/ አንዳንዶቹ ቱትሲዎቹን ከየቦታው ያፈናቀሉ ሰዎች በዓለም አቀፍ ወንጀል ተከሰው ነው። ይሄ በሰው ፍጥረት ላይ የሚሰራ ወንጀል /Crime against humanity/ የሚባል በጣም በጣም ከባድ ወንጀል ነው። ምናልባት ከዘር ማጥፋት ወንጀል /Genocide/ ቀጥሎ ያለ ወንጀል ነው ልትለው ትችላለህ ።

ሸገር ታይምስ ፡- ግን ይሄንን በክልሎች መካከል ያለ ግጭት ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ይላሉ
ዶክተር ያዕቆብ ፡- ይሄ ክልሎች የሚባለው ነገር ከመጠን በላይ ማክረር አስፈላጊ አይደለም። ክልል ለአስተዳደር ብቻ ነው እንጅ ክልል ራሱን እንደ አንድ መዋቅር ወይንም አገር የሚቀመጥ ነገር አይደለም ለአስተዳደር እንዲመች ብቻ ነው እና እንዳውም እኮ በአንዳንድ አገሮች አንድ ብሔር ማካለል ክልክል ነው። ብሔሮች ተደበላልቀው ነው መካለል ያለባቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ብሔር ብሔር የሚል ነገር ተፈጥሮ በቃ ከብሔር ሌላ ነገር ማሰብ አይቻልም እና ይሄ አገር ማዳከም ነው። ኢትዮጵያዊነትን ማዳከም ነው። ብሔሮችን ማጠናከር ማለት ብሔሮቹ ከአስተዳደር ውጭ ሌላ ምንም ዋጋ መኖር የለበትም። እና በህገ መንግስቱም የማይገባቸው መብት ነው የተሰጣቸው ብሔሮች። ከውጭ አገር መንግስታት ጋረ ውል ሊፈራረሙ ይችላሉ ይህም በፍጹም ህገ ወጥ የሆነ ነገር ነው። ኢትዮጵያ ብቻ ናት ሉዓላዊና ከውጭ አገር መንግስታት ጋር ውል ልትፈራረም የምትችለው በህገ መንግስቱም እንደገና ደግሞ ሌላም የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ባለቤቶች ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው። ይሄ በእውነት በፍጹም ሊዋጥ የሚችል ነገር አይደለም።

ሸገር ታይምስ ፡- ለምን?
ዶክተር ያዕቆብ ፡- እንደ ብሔረሰቦች እንደት ሉዓላዊ ሊሆኑ ይችላሉ? ሉዓላዊ አገር ነው እንጅ ብሔረሰብ አይደለም። እንግዲህ ሁለት ብሔረሰቦች ቢገነጠሉ ኢትዮጵያ የለችም ማለት ነው? ምክንያቱም ሉዓላዊነቱ የብሔረሰብ ነው ይሄ በእውነት እንዳው በቶሎ መታረም ያለበት ነገር ነው። እርግጠኛ ነኝ በሂደት ይታረማል። ሉዓላዊነት ሁልጊዜ የህዝብ ነው። የአገር ነው። የአሜሪካ ህገ መንግስት እኛ የአሜሪካ ህዝብ ነው የሚለው፣ የደቡብ አፍሪካ ህገ መንግስት እኛ የደቡብ አፍሪካ ህዝብ ነው የሚለው ህዝቦችም አይልም። የኛ ግን እኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሉዓላዊነት ባለቤት ነን ይላሉ። ይሄ በፍጹም በህግም የሌለ ነገር ነው በእውነት። አንድ ብሔረሰብ ሉዓላዊ ሊሆን አይችልም፣ ሉዓላዊነት ሁል ጊዜ የአንድ አገር ነው እንጅ የአንድ ጎሳ ምናምን አይደለም።
ሸገር ታይምስ ፡- በኢትዮጵያ ህገ መንግስትን ስለማሻሻል ማንሳት ብዙም አይደፈርም ነበር ይባላል። አሁን ግን የኢፌዲሪን ህገ መንግስት ስለማሻሻል ፍንጮች እየተሰሙ ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎችም እየተደራደሩ ናቸው ይህም ጉዳይ አንዱ ነው እየተባለ ነው። እርስዎ ከመንግስታቱ ድርጅት ጀምሮ ብዙ የህግ አዋጆችንና የአገራትንም ህጎች ያውቃሉና ምን አስተያየት አለዎት?

ዶክተር ያዕቆብ ፡- የኢትዮጵያ ህገ መንስት መሻሻል ያለበት ነው።
በመጀመሪያ አንቀጽ 3 ነው 2 የመጀመሪያው እሱ ነው። የሉዓላዊነት ባለቤት ብሔር ብሔረሰቦች ናቸው የሚለው ። ብሔር የሚል ቃል እኮ የለም ኢትዮጵያ ውጥ ነው እንጅ ኬንያ ውስጥ ኪኩዩ ብሔር ነው አትለውም፣ ጎሳ ነው የሚባሉት እንዳውም ብሔር የሚለው ቃል ኢትዮጵያ ውስጥ ነው እንጅ ሌላ ቦታ የለም እንዳውም። እና አንድ እሱ ነው መሻሻል ያለበት። ሌላው ሁሉን ሰው ያጨቃጨቀ አንቀጽ 39 ነው። እርግጥ ነው በዛሬው ጊዜ ማንም ብሔር ብሔረሰብ የራሱን ቋንቋ መናገር ባህሉን፣ ማበልጸግ ይሄ መብት ነው፣ ዛሬ በዓለማቀፍ ህግ የታወቀ መብት ነው፣ መገንጠል የሚባል መብት ግን የለም።በማንኛውም ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች አንድ ብሔረሰብ ከአንዱ ጋር ሊገነጠል ይችላል የሚል የለም። በማንኛውም ሰብዓዊ መብት ደንጋጌ እንዳውም የአፍሪካ ህብረት መመስረቻ ጹሁፍ አንቀጽ 3 ምን ይላል የአፍሪካ ህብረት ከዓላማው ዋነኛው የአባል አገራት ሉዓላዊነትና አንድነት ማስጠበቅ ነው ይላል። እና የአፍሪካ ህብረት እንኳን መገንጠልን ይከለክላል።ማንም የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ህብረቱ የተቋቋመው ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ነው ይላል።

ስለዚህ መገንጠል የሚባል ነገር የለም፣ የትም የለም ። እና ይሄ በእውነት አንቀጽ 39 በጣም አሳፋሪ አንቀጽ ነው። ይህንን አላስፈላጊ የሆነ አስተሳሰብ ህዝቡ ላይ መቅረጽ እንዴ አሁን እኮ የአንዱ ክልል አስተዳዳሪ ወይም ርዕሰ መስተዳድር ውሃ ቀጠነ ብሎ እገነጠላለሁ ሲል ነበር። ከጥቂት ሰዎች ጋር ተጣላና እገነጠላለሁ ይላል ሁሉም እየተነሳ እንገነጠላለን ይላል መገንጠል አይቻልም አንደኛ ኢትዮጵያ አንዲነቷን የመጠበቅ መብት አላት፣ ህጋዊ አካል ነች፣ ውል ልትዋዋል ትችላለች፣ ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ጋር ልትዋዋል ትችላለች፣ ህጋዊ አካል ነች፣ እና አንድነቷን የመጠበቅ መብት አላት፣ እንዳትፈርስ ራሷን የመጠበቅ መብት አላት፣ እና ይሄ እስከ መገንጠል የሚለው አሳፋሪ ነገር ነው፣ እና በህዝቡ ላይ አላስፈላጊ የሆነ ሃሳብ መቅረጽ ነው። እና አሁን በየቦታው የሚደመጥ ነገር ነው። እንገነጠላለን ለቀልድም ቢሆን እንገነጠላለን ይባላል፣ ከየት መጣ ይሄ ነገር ኢትዮጵያ ውሰጥ ብቻ ነው ይሄ ነገር ፣ እገነጠላለሁ እንድህ አይነት ህገ መንግስት መገንጠል የሚል ህገ መንግስት በዓለም የለም፣ድሮ ራሺያ ውስጥ ኮሚኒስቶች አስገብተውት ነበር፣ በኋላ ግን አስወጡት፣ አሁን በራሺያ ህገ መንግስት ውስጥ የለም፣ መገንጠል እችላለሁ የሚል የለም።

ሌላስ
ሌላም መሻሻል ያለበት የዚህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደ ህግ አውጭም ነው እንደ ህገ መንግስት ተርጓሚም ነው። ይሄ በፍጹም መሆን የሌለበት ነገር ነው። ህገ መንግስት ተርጓሚ ነጻ መሆን አለበት ከፖለቲካም ፍጹም ነጻ መሆን ያለበት ነው። በሌሎች አገሮች የህገ መንግስት ፍርድ ቤት ይቋቋማል። ያ የህገ መንግስት ፍርድ ቤት ሃላፊነቱ ምንድነው፣ በህገ መንግስቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች መተርጎም ነው፣ ኢትርዮጵያ ውስጥ ግን በህገ መንግስቱ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች ተመልሰው ወደ መንግስት ይመለሳሉ፣ ይሄ ህገ መንግስት ፍርድ ቤት ከመንግስት የተለየ መሆን አለበት ነጻ መሆን አለበት። ነጻ ፍርድ ቤት መሆን አለበት፣ መሻሻል ከሚገባቸው አንዱ ነው። ሌሎችም አሉ፣ ህገ መንግስቱን ለማሻሻል በጣም በጣመ አስቸጋሪ ነው እንዳወ አይቻልም ማለት ይቻላል፣ ይሄም ራሱ ቀለል መደረግ አለበት።
ሸገር ታይምስ ፡- ዶክተር ያዕቆብ ሃይለማሪያም ከሸገር ታይምስ ጋር ስላደረጉት ቆይታ እናመሰግናለን።
ዶክተር ያዕቆብ ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.