በአፋር ክልል ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ቱሪስቶች አንዱ ተገደለ

 

BBN news December 5, 2017

በአፋር ክልል ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ቱሪስቶች መካከል አንዱ መገደሉ ተገለጸ፡፡ የክልሉ ፖሊስ እንዳስታወቀው፣ ግድያው የተፈጸመው በአፋር ክልል አፍዴራ በተባለው ወረዳ ሲሆን፣ ግድያውን የፈጸሙት ግለሰቦች ማንነትም እስካሁን ድረስ አልታወቀም ተብሏል፡፡ ማንነታቸው ባልታወቀ ሰዎች ተፈጸመ በተባለው በዚሁ ጥቃትም፣ ከሟች በተጨማሪም አንድ ሰው በጥይት ተመትቶ መቁሰሉን የክልሉ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በተጠቀሰው ስፍራ ሲንቀሳቀሱ በነበሩት ቱሪስቶች ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው እሁድ ኅዳር 24 ቀን 2010 ሲሆን፣ ጥቃቱ የተፈጸመበት ሰዓትም ከምሽቱ 4፡30 ተኩል እንደነበርም ተነግሯል፡፡ እንደ ፖሊስ ገለጻ ከሆነ፣ በተከፈተው ጥቃት ህይወቱ ያለፈው የውጭ ዜጋ ሲሆን፣ የመቁሰል አደጋ ደርሶበት የተረፈው ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ወደ ስፍራው ያቀኑት ቱሪስቶች ሁለቱ ብቻ እንዳልነበሩ የሚገልጸው መረጃው፣ ነገር ግን ሟች እና የቆሰለው ግለሰብ ፎቶ ለማንሳት ከሌሎቹ ተነጥለው በሔዱበት ሰዓት ጥቃቱ ሊፈጸምባቸው እንደቻለ መረጃው ያክላል፡፡

የጥቃት አድራሾቹ ማንነት እስካሁን ድረስ እንዳልታወቀ የገለጸው የክልሉ ፖሊስ፣ ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝም አክሏል፡፡ ቱሪስቶቹ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው የእሳት ባህር የሆነውን ኤርታሌን ለመጎብኘት በሄዱበት አጋጣሚ ሲሆን፣ ሆኖም ጨለማን ተገን ባደረጉ ሰዎች ጥቃት ሊሰነዘርባቸው ችሏል ተብሏል፡፡ ቆስሎ ተርፏል የተባለው ኢትዮጵያዊ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የታወቀ ነገር የለም፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.