የቤተ ክህነታችን ‹ሠለስቱ አርእስተ ኃጣውእ› (ዳንኤል ክብረት)

ፎቶ፡- ሐራ ተዋሕዶ

ቤተ ክህነቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የመከራ በር እየሆነ ነው፡፡ ወደ ሁለት ሺ ዘመን ለኖረችው ቤተ ክርስቲያን ስድሳ ዓመት የማይሞላው ቤተ ክህነት ሊመጥናት አልቻለም፡፡ እርሷ ወደፊት ስትራመድ እርሱ ከኋላ ተቸክሏል፡፡ የራሳችን ጳጳሳት እንዲኖሩንና የራሳችን ቤተ ክህነት እንዲያስተዳድረን እስከ መሥዋዕትነት የታገሉትን ቀደምት አበው ሳስብ ኀዘን ይወረኛል፡፡ ያ ሁሉ የደከሙለት ቤተ ክህነት በሙስና፣ በብልሹ አስተዳደርና በወገንተኝነት አዘቅት ወድቆ ሲዛቅጥ ቢመለከቱት ምን ይሉ ይሆን? ከዘመነ ንጉሥ ሐርቤ እስከ ዘመነ ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች የሚመራ የራሷ ቤተ ክህነት እንዲኖራት የታገሉት ነገሥታት በዐጸደ ነፍስ ሆነው ሲመለከቱ ምን ይሰማቸው ይሆን? የአንበሳ ደቦል፣ የወርቅ እንክብል፣ ቀጭኔ ግልገል ተሸክመው ጳጳስ ለማምጣት እስክንድርያ ድረስ የተጓዙ መልእክተኞች ዐረፍን ባሉበት ዘመን ይህንን በራስ ሕዘብ ላይ የሚሠራ ግፍ ሲያዩ ከፈጣሪያቸው ጋር ምን ይነጋገሩ ይሆን?

ልጆቻቸው ፍትሕ ፍለጋ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን በር ሲያንኳኩ፡፡ በረከት ለማግኘት መምጣት የነበረባቸው ምእመናን ሙስናን ለማስቆም የፓትርያርኩን ደጅ ሲጠኑ፡፡ መስቀል ለመሳለም መምጣት የነበረባቸው ምእመናን ዘረኛነት አንገፍግፏቸው ለቅዱስ ፓትርያርኩ እግዚኦ ሲሉ፤ ቃለ በረከት ለመስማት መምጣት የነበረባቸው ምእመናን መልካም አስተዳደርን ፍለጋ ቤተ ክህነቱን ሲለምኑ፣ እንደ ሰብአ ሰገል አምኃ ይዘው መምጣት የነበረባቸው ምእመናን የአቤቱታ ደብዳቤ ይዘው ሲመጡ ሲያዩ ምን ይሉ ይሆን?

መስቀል ትተው የጦር መሣሪያ የሚታጠቁ፣ ቤተ ክርስቲያን ትተው ሱቅ የሚገነቡ፣ ገዳማትን መርዳት ትተው የከተማ ቦታ የሚቸበችቡ፣ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት ትተው ሙስናን የሚያስፋፉ፣ በጎችን ማሠማራት ትተው ዘመዶቻቸውን በየሥራ መስኩ የሚያሠማሩ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን አደኽይተው እነርሱ በብልጽግና የሚንፈላሰሱ ምንደኞች በቤተ ክህነቱ መሠማራታቸውን ቢያውቁ እነዚያ አበው ምን ይሉ? ለሀገሪቱ ችግር መፍትሔ ትሆናለች ብለው ያሰቧት ቤተ ክህነት እርሷ ራሷ የችግሩ አካል ሆና ቢያዩዋት የሚለብሱት ማቅ፣ የሚነሠንሱትስ ዐመድ ምን ዓይነት ይሆን ይሆን?

እነሆ ማርቲን ሉተር ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የወጣበትና የፕሮቴስታንት እምነትን የጀመረበት 500ኛ ዓመት በመላው ዓለም እየታሰበ ነው፡፡ በኛም ሀገር የሚገኙ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት የመታሰቢያ መርሐ ግብር ማዘጋጀታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በኦክቶበር 31 ቀን 1517(እኤአ) ማርቲን ሉተር በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያነሣቸውን 95ቱን ጥያቄዎች በዊተንበርግ ካስል ቤተ ክርስቲያን (Wittenberg Castle church) በር ላይ ለጠፈ፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ያጠኑ ሊቃውንት እንደተስማሙበት አብዛኞቹ የማርቲን ሉተር ጥያቄዎች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በወቅቱ የገባበት አረንቋ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ የቫቲካን ቤተ ክህነት ችግሩን ከመፍታት ይልቅ በችግሩ ውስጥ መዋኘትን መረጠ፡፡ ከዝናብ ቶሎ ካልወጣህ ዝናቡ ይሞቅሃልና፡፡ አስተዳደራዊና ሙስናዊ ችግሮች እያመረቀዙ ሲሄዱ ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ መልክ እየያዙ በመምጣታቸው ምእመናኑ በቤተ ክህነቱ ላይ የነበረውን ምሬት ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲያዞር አደረጉት፡፡ እንክርዳዱ ሲነቀልም ስንዴውም አብሮ ተነቀለ፡፡ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚያወሳውም እንግሊዞች በ16ኛው መክዘ የካቶሊክ ቤተ ክህነትን መጥረቢያ አንሥተው ያባረሩት ቅንጡ ቤተ ክህነታውያን በድኻ ምእመናን ላይ ይሠሩት በነበረው በደል ተንገፍግፈው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክህነት ሙስና የሚስፋፋበት መደላድል በመፍጠር፣ አስተዳደራዊ ብልሹነትን በማስፈንና መንደርተኛነትን በማስፋፋት በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ የምእመናኑ ቅሬታ ወደ ቁጣ፣ ቁጣቸውም ወዳልተፈለገ መሥመር መሄዱ አይቀሬ ታሪካዊ እውነት ነው፡፡ እስካሁን ምእመናኑን እያስመረሩ የሚገኙት ነገሮች ከቅዳሴው፣ ከጸሎቱ፣ ከጾሙ፣ ከትምህርቱና ከሥርዓቱ የሚመነጩ አይደሉም፡፡ ሠለስቱ አርእስተ ኃጣውእ ተባብረው የፈጠሯቸው እንጂ፡፡ ሠለስቱ አርእስተ ኃጣውእም ሙስና፣ የአስተዳደር ብልሹነትና መንደርተኛነት ናቸው፡፡

ዛሬ የአዲስ አበባ አብዛኞቹ ካህናት የመኖሪያ ቤት የላቸውም፡፡ እንዲያውም አዳዲስ በሚሠሩ ቤቶች የኋላ ክፍሎች ውስጥ (ሰርቪስ ቤቶች) ተጠግተው ዕቃ እየጠበቁ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ካህናቱ ልጆቻቸውን የተሻለ ትምህርት ቤት መላክ አይችሉም፤ የአንዳንዶቹም ደመወዝ በየወሩ አይከፈላቸውም፡፡ በሌላ በኩል በአስተዳደር የሚመደቡት አካላት ቤትና መሬት የሚሸጡ፣ የንግድ ተቋማትን የሚያስተዳድሩ፣ መኪና የሚቀያይሩ፣ በውስኪ የሚራጩ፣ በሥጋ የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ዛሬ የብዙዎቹ ካህናት ልጆች አባቶቻቸው በቤተ ክህነቱ የሚደርስባቸውን በደል ስለሚነግሯቸው በእግራቸው ተተክተው ካህናት መሆን አይፈልጉም፡፡ አባቶቻቸው ለመቀጠር፣ ለማደግ፣ ለመዛወር፣ የደመወዝ ጭማሪ ለማግኘትና ለመሾም ጉቦ መስጠት ግዴታቸው መሆኑን ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ ታድያ እነርሱ ምን በወጣቸው እዚህ ምሬት ውስጥ ይገባሉ?

የምእመናኑ ዕውቀትና ንቃት አደገ፤ የቤተ ክርስቲያኒቷ ሀብትና ንብረት ተትረፈረፈ፣ የካህናቱና አገልጋዮቹ ቁጥር ጨመረ፤ የዘመኑ ጥያቄዎች እየተቀየሩና እየበዙ መጡ፡፡ ይህን ማስተዳደር የነበረበት ቤተ ክህነት ግን እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ ይሄዳል፡፡ መንግሥት እንኳን ሲቪል አስተዳደሩን ለማሻሻል በየዘመናቱ የአሠራር ማሻሻያዎችን ሲያደርግ ቤተ ክህነት ግን ላለፉት 40 ዓመታት ባለችበት እየረገጠች ነው፡፡ በደንባራ በቅሎ ቃጭር ተጨምሮ እንደሚባለውም በዚህ ችግር ላይ ደግሞ ሠለስቱ አርእስተ ኃጣውእ ተጨመሩበት፡፡

ዘመኑ የመረጃ ዘመን ነው፡፡ እንደ ጥንቱ ግመል ሰርቆ አጎንብሶ መሄድ አይቻልም፡፡ በየሠፈሩ የሚሠሩት ሕንጻዎች፣ በየገበያው የሚገዙት አክስዮኖች፣ በየሆቴሉ የሚረጩት ውስኪዎች፣ በየፓርኪንጉ የሚቆሙት መኪኖች፣ በየባንኩ የሚገቡት ገንዘቦች፣ በየአንገቱ የሚንጠለጠሉት ወርቆች ሙሰኛ ቤተ ክህነታውያን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ምን እየሠሩ እንደሆነ ይነግሩናል፡፡ ገዳማቱ ተቸግረው፣ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እየተዘጉ፣ የአብነት መምህራን እየተራቡ፣ የአብነት ተማሪዎች ቁጥር እያሽቆለቆለ ሄዷል፡፡ የሙሰኞች ሆድና ሀብት ግን እየጨመረ ነው፡፡

ብልሹ አስተዳደሩ ለሙሰኝነቱ የረሰረሰ መሬት ፈጥሯል፡፡ ሙሰኞች ሲጋለጡ ደግሞ መንደርተኝነቱ ይከላከልላቸዋል፡፡ ትግሬ ስለሆነ ነው፣ ሸዋ ስለሆነ ነው፣ ጎንደር ስለሆነ ነው፣ ጎጃም ስለሆነ ነው፣ ወሎ ስለሆነ ነው ይባላል፡፡ ሙስናው፣ ብልሹ አስተዳደሩና መንደርተኛነቱ እንዲህ ተጠላልፎ ከጠቅላዩ እስከ አጥቢያው ተሠናስሏል፡፡ በአንድ ወቅት ለሥራ ወደ ገጠር የሚሄዱ የአንድ ሀገረ ስብከት ሰዎች አደጋ ይደርስባቸውና ሕይወታቸው ያልፋል፡፡ እጅግ የሚገርመው ነገር ግን ከአንዱ በቀር ሁሉም የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ ዘመዶች ናቸው፡፡ ‹ኀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ› ነበር የሆነው፡፡ አንዳንዶቹ አህጉረ ስብከት ‹እንትናና ቤተሰቡ› እስኪመስሉ ድረስ በቤተ ዘመድ ተሞልተዋል፡፡ እዚያ ቦታ አቤቱታ ሲመጣ ‹አብ ሲነካ ወልድ ይነካ› ይሆናል ነገሩ፡፡ ተከሳሽ አጎት፣ አጣሪ የአጎት ልጅ፣ ዳኛ ወንድም ይሆንና ትራጄዲው ይመደረካል፡፡ ምእመናኑ ፍትሕ ሲጠብቁ ሥጋ የሚበሉት ይነሡና አጥንት የሚሠብሩት ይተካሉ፡፡

ወሎ ውስጥ ነው አሉ ታሪኩ የተፈጸመው፡፡ዐፄ ምኒልክ ከወይዘሮ ባፈና የወለዷቸው ወይዘሮ ማናለብሽ የምትባል ልጅ ነበረቻቸው፡፡ ለመሐመድ ዓሊ ተዳረች፡፡ ወይዘሮ ማናለብሽ ባሏንና አባቷን ተማምና በልጇ ላይ በደል ያደረሰችባት አንዲት ወሎዬ እንዲህ ዘፍናው ነበር፡፡

እናትሽ ባፈና ምኒልክ አባትሽ

ባልሽ ማመድ ዓሊ አንቺ ማን አለብሽ

በየትኛው ዳኛ አቤት ልበልብሽ፡፡

ቤተ ክህነቱም እንዲህ ነው የሆነው፡፡

ቤተ ክህነቱ፣ በተለይ ደግሞ ለእውነትና ለእምነት የቆሙ አባቶች በጊዜ ነቅተው እንክርዳዱን ራሳቸው ካልነቀሉት፤ ጊዜ የሚያመጣው አጫጅ እንክርዳዱን ከነ ስንዴ መንቀሉ አይቀሬ ነው፡፡ ከ500 ዓመታት በፊት መንፈሳዊነታቸውን ሁሉ ትተው የኃጢአት ማስተሥረያ ወረቀት ለድኾች እየሸጡ ሀብት ሲያደልቡና በአስተዳደር በደል ሕዝቡን ሲያሰቃዩ የነበሩት የካቶሊክ ቤተ ክህነት ሰዎች የገጠማቸውም ይኼው ነው፡፡

የጨው ገደል ሲናድ ብልህ ያለቅሳል ሞኝ ይስቃል እንደተባለው ችግሩ የገባቸው አባቶችና ምእመናን እያለቀሱ ነው፡፡ ፍሬውን እየበሉ ከላይ የተቀመጡበትን ዛፍ እየቆረጡ ያሉት ሙሰኞች ደግሞ ይስቃሉ፡፡ መንፈሳዊ ኀዘን ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍትሕ ይጠይቃልና ተገቢ ነው፡፡ ከዚሁ በተጓዳኝ ግን ‹አላህንም አምናለሁ፣ ከብቴንም እጠብቃለሁ› የሚለውንም ብሂል መርሳት አይገባም፡፡ ከዘመኑ መናፍቃን ጋር ተባብረው በሠለስቱ ኃጣውእ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመግደል እያሤሩ የሚገኙትን የቤተ ክርስቲያን የውስጥ መዥገሮች ለመንቀልና ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የሚተርፍ የእፎይታ ዘመን ለማምጣት ምእመናን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ የጀመሩትን ገድል መቀጠል አለባቸው፡፡ መንግሥታዊ አካላትም ከቤተ ክህነቱ የሚደርሳቸውን የስልክ ጥሪ ብቻ ሳይሆን የምእመናንንም ሮሮ መስማት አለባቸው፡፡ ያለበለዚያ ግን የቤተ ክህነቱ ዳፋ መንግሥትንም እንዳያዳፋው ያሠጋል፡፡ በተለያዩ የእምነት ተቋማት መካከል የሚፈጠረው ግጭት ዋናው መንሥኤ በእምነት ተቋማቱ ውስጥ የሙስና፣ የአስተዳደር ብልሹነትና የመንደርተኝነት መሠልጠን ነውና፡፡ ለኃጥኣን የመጣ ለጻድቃንም መትረፉ እንደማይቀር የማገናዘቢያው ጊዜ አሁን ነው፡፡

ሜልበርን፣ አውስትራልያ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.