ኢትዮጵያ፡ ቀስ በቀስ በሚፈላ ውሃ የምትቀቀለው እንቁራሪት (አስፋው ገዳሙ)

በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ19ኛው ክፍለ ዘመን እንደተገኘ የሚነገርለት የቤተ ሙከራ ውጤት ከሳይንሳዊ ጭብጦቹን ይልቅ ዛሬም ድረስ ነባራዊ ሁኔታዎችን ቅልብጭ አድርጎ በማሳየቱ በኩል ጎልቶ የሚታወቅ ተምሳሌታዊ ወግ ሆኗል፡፡ፈረንጆቹ የምትቀቀለው እንቁራሪት(The boiling frog) ይሉታል፡፡መነሻ ሃሳቡ አንዲት እንቁራሪት ፈልቶ በሚንፈቀፈቅ ውሃ ውስጥ ብትከታት ወድያው ተስፈንጥራ ትወጣለች፤ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ ከተህ በተቻለ መጠን ውሃው ቀስ በቀስ ብታሞቀውና ብሎም ብታፈላው ግን የግለቱ አደገኛነት ስለማታስተውለው ተቀቅላ እስክትሞት ድረስ እዛው ትቆያለች የሚል እንአድምታ አለው፡፡

የዘመናችን የስነ ህይወት ተማራማሪዎች ትርክቱ ሳይንሳዊ እውነታ እንደሌለው አረጋግጠናል ቢሉም ከጊዜ ወደ ጊዜ በለሆሳስ እየተባባሱ ሄደው የጋራ ጥፋት የሚያስከትሉ ማህበራዊ ቀውሶችን ከሚያስረዱ ዘይቤያዊ አነጋገሮች አንዱ ለመሆን ግን ያስቆመው የለም፡፡የፖለቲካ፣ማሕበራዊና ባህላዊ እሴቶች መላሸቅ ለመተንተን እንደ መንደርደርያ ከሚያገለግሉ ምሳሌዎች ቀድሞ የሚጠቀስ ነው፡፡የምዕራቡ ዓለም ልሂቃን የአየር ንብረት ለውጥና የኢኮነሚ መንኮታኮት ለመተቸት ተጠቅመውበታል፡፡

እኔም የሃገራችን ፈርጀ ብዙ ችግሮችን ባስተዋልኩ ቁጥር እምዬ ኢትዮጵያ ቀስ በቀስ በሚፈላ ውሃ የምትቀቀለው እንቁራሪት መስላ ትታየኛለች፡፡በየጊዜው የሚከሰቱት ችጋሮች ቀስበቀስ ከርሃብነት ወደ ጠኔ እስኪሸጋገሩ ድረስ የሚያስተውላቸው የለም፡፡የወሎ ርሃብ ወደ ጠኔ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ያስተዋለው አልነበረም፡፡ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ከሆኑ በኋላ ግን ደርግ እንደ ትልቅ የፖለቲካ ውድቀት አድርጎ በማራገብ ንጉሳዊ አገዛዙን ለማብጠልጠል ተጠቅሞበታል፡፡

እነ ጥላሁን ገሰሰም
‹‹ዋይ! ዋይ! ዋይ! ሲሉ
የርሃብ ጉንፏን ሲስሉ›› እያሉ በለቅሶ የታጀበ ዜማ አዚመውበታል፡፡ዘፈኑም ሆነ የፖለቲካ ውዥንብሩ ግን በወቅታዊ ግለቱ ፈልተው ከመንፈቅፈቅ ውጪ የችግሩ ምንጭ ለይቶ በመምታት ለወደፊት እንዳይከሰት ያደረጉት ጥረት አልነበረም፡፡ለዛም ነበር ሃገራችን በ1977 ዓ.ም ሌላ አስከፊ ርሃብ ለማስተናገድ የተገደደችው፡፡በንጉሳዊው አገዛዝ ሲያላግጥ የነበረው ደርግ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› ከሚለው ባዶ መፈክሩ በስተቀር ያመጣው ለውጥ አልነበረም፡፡‹‹መሬት ላራሹ›› የሚለው የ1960ዎቹ ልሂቃን ጥያቄ መልሻለሁና የእኔ መፈክሮች ከማስተጋባት አልፎ ሌላ አስተሳሰብ የሚያራምድ ካለ ነፃ እርምጃ ይወሰድበታል ብሎ አወጀ፡፡አዋጁ ቀይሽብርን አስከተለ፡፡ሃገርና ህዝባችንን በቁሙ ተቀቀለ፡፡

በመፈንቅለ መንግስት የስልጣን ኮርቻ ተቆናጥጦ ሃገርና ህዝባችንን ሲያተራምስ የኖረው ደርግ በሌላ ጡንቻም ከመንበረ ስልጣኑ በሃይል ተወገደ፡፡አሁን ሃገራችንን በመግዛት ላይ ያለው ኢህአዴግስ ከርሱ በፊት ከነበሩ ስርዓቶች የተማረው ምን ይሆን?የሃገራችን ፈርጀ ብዙ ችግሮች ምንጭ ምን እንደሆነ ለይቶ ያውቃል?ያለንበት ነባራዊ ሁኔታስ በትክክል ተገንዝቦት ይሆን?በእኔ እይታ መልሱ አይደለም የሚል ነው፡፡ከታሪካችን እንደምንረዳው የሃገራችን ችግሮች ምንጭ ለዘመናት ታሞ ሲማቅቅ የኖረውና አሁንም በጠና መታመሙን የሚያውቅለት ያጣው ምስኪኑ ፖለቲካችን ነው፡፡የኋላ ቀርነታችንና ድህነታችን መንስኤ ፖለቲካችን ነው፡፡ፖለቲካችን ያመጣብን ችግሮች የሚቀረፉት ‹‹ፖለቲካና ኮረንት በሩቁ›› ብለን ራሳችንን በማግለል ሳይሆን የሃገራችን ችግሮች ምንጭ መሆኑን አውቀን በጋራ ስንረባረብበት ብቻ ነው፡፡

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከፖለቲካ ጫናዎች ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡በህይወት ለመኖር የሚያስፈልጉ ሰው ሰራሽ ነገሮች ሁሉ የፖለቲካ ውጤቶች ናቸው፡ የጤና፣የፍትሕ፣የማጓጓዣ፣የውሃ፣ የመኖርያ፣ የመብራት፣የስልክ፣የትምህር ወዘተ አገልግሎቶች እንዳለ የፖለቲካ ውጤቶች ናቸው፡፡ የእነዚህና መሰል አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ሽፋንና ጥራት የሚወሰነው በፖለቲካ ነው፡፡

ወደ ስራ ስንሄድና ከስራ ስንመለስ ጉልበታችን እስኪብረከረክ ድረስ ታክሲ ለመጠበቅ የምንቆመው በፖለቲካችን አማካኝነት ነው፡፡ መብራት በጠፋ ቁጥር የጨለማ ማቅ የምንለብሰው፣ ሻማ ለመግዛት የምንሯሯጠው ፖለቲካችን ባመጣው ጣጣ ነው፡፡ ውሃ ድንገት ሲጠፋ በግማሽ ሻወር የምንቋረጠው፣ ዓይናችን ሳሙና እያቃጠለው በጨርቅ አድርቀን ለመውጣት የምንገደደው፣ ፖለቲካችን ባመጣብን በሽታ ነው፡፡የምንጠጣውና ምግብ የምናዘጋጅበት ውሃ ጠፍቶ በጣም የምንቸገርበት ምክንያትም በፖለቲካችን ደካማነት ነው፡፡ ወር ሙሉ ሰርተን ካገኘናት ደሞዛችን ግማሽ ለቤት ክራይ እንድንከፍል የምንገደደውም በፖለቲካችን ምክንያት ነው፡፡በአጠቃላይ የድህነታችን ምንጭም ሆነ የድህንነታችን እንቅፋት ፖለቲካችን ነው፡፡

የእነዚህና መሰል አገልግሎቶች የተደራሽነትም ሆነ የጥራት መጓደል አለ ማለት የፖለቲካ ችግር አለ ማለት ነው፡፡የፖለቲካችን መታመም የሃገራችን መታመም ያመለክታል፡፡ይህ የኢትዮጵያውያንን የመኖር ተስፋ በማጨለም የሚወዱት ወገናቸውንና ሃገራቸውን ትተው እንዲሰደዱ እያደረገ ያለው በሽታ ሊስተካከል የሚችለው ታድያ በእኛ በዜጎች ንቁ ተሳትፎ ነው፡፡በፖለቲካችን ያገባናል ብለን በሰለጠነ መንገድ ስንወያይ፣ስንመካከር፣ ስንከራከር፣ የሐሳብ ልዕልና እንዲያሸንፍ የሐሳብ ፍጭት ስናደርግ ነው፡፡

ኢምክንያታዊ አስተሳሰቦችና ልምዶች በምክንያታዊ አስተሳሰቦችና አምሮች መቀየር የሚችሉት የብዙሐን ድምፅ ከጫፍ እስከጫፍ ሲያስተጋባ ነው፡፡ፖለቲካችን የእናት ሃገራችን እጣፈንታ የሚወሰንበት ሃገራዊ ጉዳያችን በመሆኑ በቸልተኝነት የምንመለከተውና ፈርተን የምንሸሸው አይደለም፡፡ሃገራዊ ስሜታችን ገንፍሎ ከአራቱም የሃገራችን አቅጣጫዎች ሆ ብለን የምንነሳው የውጭ ወራሪ ሃይሎች ዳር ድንበራችን ጥሰው በገቡ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዷ ፖለቲካዊ ውሳኔም ጭምር መሆን አለበት፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ይቅርና በፖለቲካ ላይ ያላቸው ፍልጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ ሄዶ እንደ ነውር የሚቆጥሩት፣ እንደ ኮርንት ከርቁ የሚሸሹት፣ በሽኩሹክታ የሚያወሩት አስፈሪ ነገር ሆኗል፡፡ብዙ የሃገራችንና የውጭ ሊህቃን‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጊዜው ጠብቆ እንደሚፈንዳ የተጠመደ ፈንጅ ነው›› ይላሉ፡፡ ገዢው መንግስት(ኢህአዴግ)ና ተቃዋሚዎች ለአንዲት ሃገር እድገትና ብልፅግና ስለተሻለው ዘዴ አይደለም የሚከራከሩት፡፡የእኛ ዘዴ ይሻላል ሳይሆን እኛ እንበልጣለን፣ እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ትጠፋለች፣ እነ እንትና ምንትስ ናቸው፣ ሃገር መምራት አይችሉም ወዘተ የመሳሰሉ ናቸው፡፡ ይህ በአስተሳሰብ ልዕልና ሳይሆን በግለሰቦች ማንነትና በጉልበት ላይ የተመሰረተው ፖለቲካችን በሁለት ፅንፎች ተወጥሮ ለመበጠስ የተቃረበ ይመስላል፡፡ኣንዴ እየተቋጠረ በሌላ ጊዜ ድሞ እየተበጠሰ፣ አንዱ ዘመናይ ሌላውን እየገነደሰ፣ አምባገነን ተወግዶ በሌላ አምባገነን እየተተካ፣ ሁሌም የነበረውን በማውደም ‹‹ሀ›› ብለን እየጀመርን እንሆ ለዚሁ ደረስን፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ በህዝብ ይሁንታ ተመርጦ ለህዝብ የቆመ ህዝባዊ መንግስት አልነበረም፣የለም፡፡ሁኔታው በጣም አስጊና አሳዛኝ የሚያደርገው ደሞ ህዝባዊነቱን ማር በተቀቡ ቃላት እያሽሞነሞነ ለ24 ሰዓታት ከመለፈፍ አልፎ በተግባር የሚያሳይ መንግስት እውን የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ መሆኑን ስንገነዘብ ነው፡፡አሁንም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተስፋ ያለው አይመስልም፡፡ በገዢውም ሆነ በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፉ ዜጎች በዘመነ የፖለቲካ አምርና በሐሳብ ልዕልና ለማሸነፍ ወይም ለመሸነፍ ሳይሆን በማንኛውም መንገድ ለማሸነፍ ብቻ የተዘጋጁ ናቸው፡፡

በዢው ፓርቲ የተሰለፉ ወገኖች እነሱ ከሚያስቡትና ከሚያደርጉት ውጪ እውነት ያለ አይመስላቸውም፡፡ በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፉም ቢሆን የተሻሉ ናቸው ለማለት ያን ያህል አያስደፍርም፡፡ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በስልጣን ለመቆየት ሲል ማንኛውም መንገድ እንደመፍትሔ ሲከተል ይታያል፡፡ተቃዋሚዎችም እንዲሁ በማንኛውም መንገድ ስልጣን ለመጨበጥ ሲፍጨረጨሩ ይስተዋላል፡፡ይሁን እንጂ በማንኛውም መንገድ በስልጣን መቆየትም ሆነ የስልጣን ኮርቻ ለመቆናጠጥ መሞከር ኢህገመንግስታዊና አፍራሽ ውጤት የሚያስከትሉ ተግባራት ናቸው፡፡ህገ መንግስቱ የሚያትተው ሉዓላዊው የስልጣን ባለቤት ህዝብ እንደሆነ ነው፡፡ህዝብ ይሾማል፣ ህዝብ ይሽራል፡፡ከዚሁ ውጪ ስልጣን አይገኝም ይላል፡፡ይህ ተግባራዊ የሚሆነው ግን በሃገሬ ፖለቲካ ያገባኛል ብሎ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርገውን ሁሉ በአሸባሪነት ፈርጆ በማሰር፣ሃገሩን ለቆ እንዲሰደድ በማስገደድ፣ ኢህአዴግን የሚቃወም ሁሉ በጠላትነት በመፈረጅ አይደለም፡፡

በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የ1960 ዎቹ አብዮት ተከትሎ የተከሰተው እልቂትና የ1997 ምርጫን ተከትሎ የደረሰው የህይወትና የንብረት ውድመት እንዲሁም የፖለቲከኞቹ ተደጋጋሚ መፍረክረኮችና ክህደቶች ተስፋ ስላስቆረጡት ከማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ራሱን ለማግልል ተገድዷል፡፡ ‹‹ፖለቲካና ኮረንት በርቁ›› በሚሉት ፈሊጥ ስለፖለቲካ አለመተንፈስ የመረጠው በጣም ብዙ ነው፡፡
የመገናኛ ብዙሐንና ጋዜጠኞቻችን ይህንኑ የሞት ሽረት ጉዳያችን ችላ ብለው ጥዋት ማታ ስለአውሮፓ ክለቦች የሚደሰኩሩትም ሊዚሁ ነው፡፡ዝግጅቶቻቸው ስለሃገራችን ወቅታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች ሳይሆን ስለምዕራባውያን ታዋቂ ሰዎች ውሎና አዳር ነው የሚደሰኩሩት፡፡
እንደ ሽሻቤቶች፣ጫትቤቶችና መጠጥ ቤቶች የወጣቱ አእምሮ ለማደንዘዝ የሚሰሩ ነው የሚመስለው፡፡የወጣቱ ንቃተ ህሊና የሚያዳብሩ አመራማሪ ፅንሰሐሳቦች አያቀርቡም፡፡

ስለሃገራዊ ፖለቲካታችን ማሰብ፣መመራመር፣መከራክርና መወያየት የተከለከለ፣‹‹አደገኛ›› የሚል ምልክት በደማቅ ቀይ ቀለም የተፃፈበት ይመስላል፡፡በአጠቃላይ የሃገራቸን ልሂቃን ትውልድን በመግራትና አቅጣጫ በማሳየት አርአያ ባለመሆናቸው አገሪቱ በመጠቁ ፅንሰሓሳቦች ድርቅ ተመትታለች፡፡ይህ የአስተሳሰብ ድርቅ ነው ከፖለቲካችን እንደንሸሽ ባንሸሽም በኋላ ቀርና የላሸቀ ፖለቲካ እንድንዘፈቅ ያደረገን፡፡

ይሁን እንጂ፣ከፖለቲካ ሸሽቶ ማምለጥ እንደማይቻል ማህበራዊ ንሯችን ቋሚ ምስክር ነው፡፡ፖለቲካ ኮረንቲ እንኳን ቢሆን ያለኮረንቲ መኖር እንደማይቻል መታወቅ አለበት፡፡ኮረንቲ የሚያስከትላቸው አደጋዎች ፈርተን በኮረንቲ ፍሰት የሚገኘው መብራት መጠቀሙን እንዳላቆምነው ሁሉ ፖለቲካ ያስከተላቸው ታሪካዊ ጥፋቶች ፈርተን ከፖለቲካ ራሳችንን ማግለል የለብንም፡፡ጥፋቶቹን አስወግደን ጥቅሞቹን ብቻ ለማጉላት እንችል ዘንድ የፖለቲካው ባህሪና የአጨዋወት ዘድየው አውቀን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንደገለፅነው ሌላ አማራጭ የለንምና ነው፡፡

በዛሬው የፖለቲካ መቀዛቀዝ ተሸውደን ነገ ቀስ በቀስ እየጋለ ሄዶ የነበረንን ሁሉ በእሳት ማግዶ በማውደም እንደገና ከዜሮ ለመጀመር እንዳንገደድ ከወዲሁ መንቃት አለብን፡፡የፖለቲካ ድህነታችን እስካልተቀረፈ ድረስ ከኋላ ቀርነትና ምጣኔ ሃብታዊ ድህነት ልንላቀቅ አንችልም፡፡የስልጣን መሪውን ተረክበው ሃገራችንን ወደ ጥፋት ገደል ሲያሽከረክሯት እያየን ዝም ማለት ከማንወጣው አዘቅት ወስጥ ይከተናልና አቅጣጫቸውን እንዲያስተካክሉ ምልክት ልንሰጣቸው ይገባል፡፡ምክንያቱም ተጎጂዎቹ እኛ እንጂ እነሱ አይደሉም፡፡አምባገነኖች በሌላ አምባገነን ከስልጣናቸው ሲወገዱ የሚጎዳው ህዝብ ብቻ መሆኑን ከደርግ ስርዓት መማር እንችላለን፡፡ከ400 ሺ እስከ 1.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እንደፈጀ የሚነገርለት መንግስቱ ሃይለማርያም ያለአንዳች ችግር ነው በዝምብባዊ ዓለሙን እየቀጨ የሚገኘው፡፡

ተፃፈ በ ህዳር 10 ቀን 2007 ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.