ትዝብት! (ጌታቸው ሺፈራው)

 

መኳንንት ካሳሁን አያሌው፣ ብስራት አቢ ጥሩነህ፣ አበበ ይማም አበጋዝ እና ይማም መሃመድ አደም ታህሳስ 2/2010 ዓም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት አንድ የዓቃቤ ሕግ ምስክር ተሰምቶባቸዋል። ምስክሩ በፓርቲ አባልነት አብሯቸው ሲሰራ የነበረ፣ ከእነሱ አንድ ቀን ቀድሞ የታሰረ ሰው ነው። ከእስር ቤት ውጭ መጥቶ እንደመሰከረ ቢገልፅም የተከሳሽ ቤተሰቦች አሁንም ማዕከላዊ ታስሮ እንደሚገኝ አረጋግጠናል ብለዋል። ብዙውን ጊዜ ተገዶ የሚመሰክር እስረኛ በተፈለገው መንገድ መመስከሩ እስኪረጋገጥ በእስር ላይ ይቆያል። ምስክሩ በተከሳሾች ጠበቃ መስቀለኛ ጥያቄ ሲቀርብለት ይርበተበት ነበር። ፍርድ ቤቱ “ይረጋጉና ይመልሱ” እያለ ለማረጋጋት ሞክሯል። ለቀረበለት ጥያቄ “አያስፈልግም” የሚል መልስ ሲሰጥ ፍርድ ቤቱ “የተጠየቁትን ይመልሱ” እያለ በተደጋጋሚ ትዕዛዝ ሰጥቶታል)

የምስክሩ ቃል ከሞላ ጎደል:_

~ ስም?

ይመር ሰይድ ሀሰን

~ዕድሜ ?

32

~ስራ?

መምህር

~አድራሻ?

ደቡብ ወሎ ደሴ ……

~ለምን መጡ ዛሬ?

ለምስክርነት

~የሚመሰክሩባቸውን ሰዎች ያውቋቸዋል?

አዎ! (ተከሳሾቹ የተቀመጡበት ድረስ ሄዶ እስከ አባት ስም እየጠራ ለፍ/ቤቱ አሳይቷል)

(ዐቃቤ ሕግ ዋና ጥያቄ):_

ዐሕ:_ የት ነው የምትተዋወቁት?

ምስክር:_ የምንተዋወቀው ደሴ ነው። ጓደኛዬ ካሳሁን ብስራት ከአግአዴን አመራሮች ጋር አባል በመመልመልና በማደራጀት እየሰራ ነው አብረን እንስራ አለኝ።

ዐ ሕ:_ምን ለማድረግ?

ምስክር:_ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ነው። ከውጭ የሚመጡ መመርያዎችን፣የአግአዴን ሰነዶች ይላኩልናል።

ዐሕ:_ ምን የሚሉ ናቸው መመርያዎቹ ?

ምስክር:_ ስለ አግአዴን አባል አመላመል፣ አደረጃጀት እና ዓላማ ፣ የ1ለ5 አደረጃጀት አባላት ከሌላው ጋር አይገናኙም፣ አመራሮቹ ብቻ ናቸው። የአሻጥር ስራዎች እንዴት እንደሚሰሩ የሚያስፈልጉ ነገሮች ተብሎም ተልኳል። ዳዊት የሚባል እንግሊዝ የሚኖር የአግአዴን አመራርም የህወሃት ድርጅቶች ላይ ሰላም ባስ፣ቴሌ፣አብቁተ፣ ኖክ ሌሎችም እንዴት ጥቃት እንደምንፈፅም ነግሮናል።

ዐሕ:_ ከብስራት ጋርስ?

ምስክር:_ ብስራት ከመኳንንት ጋር ሆኖ ዳዊትን በስልክ አገናኝቶኛል

ዐሕ:_በምን ሰዓት ነው የምትገናኙት?

ምስክር:_በሳምንት አንድ ቀን በአካል ሌላውን በስልክ

ዐሕ:_ እርስዎ ታስረው ነበር?

ምስክር:_አዎ። እኔ የታሰርኩት ጥር 27/ 2009 ነው። እነሱ ጥር 28 እና 29 ታሰሩ።

መስቀለኛ ጥያቄ:_

ጠበቃ:_ ስምህ ማን ነው?

ምስክር:_ይመር ሰይድ

ጠበቃ:_ሌላ ስም የለህም?

ምስክር:_ ስለማምር ነው ቤተሰቦቼ ይመር ያሉኝ። እንደሙስሊምነቴ ኡመር ሰይድ ነው ስሜ

ጠበቃ:_ መታወቂያዎ ላይ ማን ይላል?

ምስክር:_ ይመር! መጠራት ያለብኝ ግን ኡመር ተብዬ ነው።

ጠበቃ:_ መታወቂያ አለዎት ?

ምስክር:_ አዎ
ጠበቃ:_አሁን ይዘዋል?

ምስክር:_ አልጋ ይዠበታሉ። አልያዝኩትም

……
……

ጠበቃ:_ዛሬ ከየት መጡ?

ምስክር:_አልጋ ከያዝኩበት

ጠበቃ:_ መቼ ተፈቱ?

ምስክር:_ መንግስት ወይንም ፖሊስ……

ጠበቃ:_ መቼ ተፈቱ? (በድጋሚ)

ምስክር:_ 2009 ሰኔ

ጠበቃ:_ቀኑስ?

ምስክር:_ ረስቸዋለሁ

ጠበቃ:_በየትኛው ቀን እንደሆነ አያስታውሱም?

ምስክር:_አላስታውስም

ጠበቃ:_ከ1 እስከ 30 ባለው ቀን መቼ እንደተፈቱ አያስታውሱም?

ምስክር:_አላስታውስም

ጠበቃ:_ ብስራትን በአካል አግኝተውት ያውቃሉ?

ምስክር:_ አላውቅም

ጠበቃ:_ብስራትን ከ2007 ምርጫ በፊት ሰማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤት ሄደው አላገኙትም?

ምስክር:_ አላገኘሁትም

ጠበቃ:_ ከምርጫ በኋላስ ቢሮ ሄደው አያውቁም?

ምስክር:_አላውቅም። ከዛ በፊት ደሴ እያለ አውቀዋለሁ።

ጠበቃ:_በተከሰሰበት ጉዳይ በአካል አውርታችሁ ታውቃላችሁ?

ምስክር:_በስልክ ነው

ጠበቃ:_መኳንንትን በአካል አግኝተውታል?

ምስክር:_2008 ዲኤስ ቲቪ ቤት አግኝቸዋለሁ

ጠበቃ:_2008 መቼ?

ምስክር:_አላስታውሰውም

ጠበቃ:_ ወሩንም?

ምስክር:_ አላስታውሰውም

ጠበቃ:_ከመኳንንት ጋር ስትገናኙ ቀድሞ የተዋወቀ ማን ነው?

ምስክር:_እሱ

ጠበቃ:_ ምን አለዎት?

ምስክር:_ከአግአዴን ጋር አብረን እንድንሰራ፣ ስለ አግአዴን የሽብር ጥቃት፣ አብረን እንድንደራጅ

ጠበቃ:_ እርስዎን በምን መረጠዎት?

ምስክር:_ስለሚያውቀኝ

ጠበቃ:_መኳንንት ከአግአዴን ጋር በምን ይገናኝል ነው ያሉኝ?

ምስክር:_በማህበራዊ ድረገፅ

………

……

ጠበቃ:_ የአግአዴን አባል እንዲሆኑ የጠየቀዎት መኳንንት ነው?

ምስክር:_ አዎ

ጠበቃ:_እሱም አባል መሆኑን በማስረጃ አሳይቶዎታል?

ምስክር:_አላሳየኝም

ጠበቃ:_ታዲያ እንዴት አወቁ?

ምስክር:_ስለነገረኝ

ጠበቃ:_ ብስራት መቼ ደወለልዎት?

ምስክር:_2009

ጠበቃ:_ ምን ወር?

ምስክር:_ከጥቅምት በኋላ

ጠበቃ:_ የስልክ ቁጥሩን ያዉቁታል?

ምስክር:_ በ83 ቤት ስልክ ነው

ጠበቃ:_ መመርያዎቹ ለአበበ ተላለፉ ብለዋል?

ምስክር:_ አዎ

ጠበቃ:_ በቃል ነው በፅሁፍ?

ምስክር:_በፅሁፍ

ጠበቃ:_ ሰነዶቹ መላካቸውን እንዴት አወቁ?

ምስክር:_አብረን ፕሪንት አድርገን አንብበናል

ጠበቃ:_ ይህ የሚሉት ፅሁፍ በፖሊስ ተይዟል?

ምስክር:_አልተያዘም

ጠበቃ:_የት ነው ፕሪንት ያደረጋችሁት?

ምስክር:_ስፔስፊክ ቦታውን ባላውቀውም፣ አይጠገብ ካፌ አጠገብ

………

ጠበቃ:_ የአበበን ኢሜል ያውቁታል?

ምስክር:_ አላውቀውም

……

ጠበቃ:_ መመርያው የአግአዴን የሚል የተለየ ምልክት አለው?

ምስክር:_ስለ አግአዴን ከማውራቱ ውጭ የተለየ የማውቀው ነገር የለም

………

………

……

ጠበቃ:_የፋይናንስ ድጋፍ መጣላችሁ?

ምስክር:_አልመጣም

ጠበቃ:_ምን ቃል ተገባላችሁ?

ምስክር:_አራት ኮምፒውተር፣ ለድርጅት ስራ፣ ለበጎ አድራጎት፣ ለቤንዚንና ማቀጣጠያ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን አቅደናል

……

ጠበቃ:_ በድርጅቶቹ ላይ ምን ለማድረግ አቀዳችሁ?

ምስክር:_ለማጥቃት

ጠበቃ:_ እጃችሁ ላይ ምን ነበር?

ምስክር:_በእቅድ አስቀምጠናል

ጠበቃ:_ የተገዛ ነገር የለም?

ምስክር:_ተወያይተናል። አልተገዛም።

ጠበቃ:_የማህበራዊ ድረገፅ ይጠቀማሉ?

ምስክር:_አልጠቀምም

ጠበቃ:_ የስልክ አፕልኬሽን ይጠቀማሉ?

ምስክር:_አልጠቀምም

ጠበቃ:_ምንም አይጠቀሙም?

ምስክር:_አልጠቀምም

የፍርድ ቤት ማጣሪያ ጥያቄ:_

ፍ/ቤቱ:_ ከመኳንንት ጋር ትውውቃችሁ እንዴት ነበር?

ምስክር:_ እንደማንኛውም ሰው

ፍርድ ቤቱ:_እንደማንኛውም ሰው ከሆነ እንዴት ይህን ሚስጥር አወራችሁ?

ምስክር:_ ከዛ በፊት ብዙም አንቀራረብም

ፍርድ ቤቱ:_ከመኳንንት ጋር በደንብ ካልተዋወቃችሁ እንዴት ይህን ሚስጥል ልታወሩ ቻላችሁ?

ምስክር:_ ስለምንቀራረብ

ፍ/ቤተ:_ እንዴት ወደ አግአዴን ገባህ?

ምስክር:_በአካባቢያችን ባሉ ችግሮችና የማንነት ጥያቄ ምክንያት

ፍ/ቤቱ:_በእናንተ አካባቢ የማንነት ጥያቄ አለ እንዴ?

ምስክር:_ጎንደር አካባቢ የወልቃይት

ፍ/ቤቱ: _ አሻጥርና የሽብር ጥቃት አንድ ነው?

ምስክር:_ሽብር እንዳለ ሆኖ ጥቃት ማድረግ

ፍ/ቤቱ:_ምንድን ነው ልዩነቱ?

ምስክር:_አሻጥር በድብቅ መስራት ነው

ፍ/ቤቱ:_ የድርጅቱ ነው ያሉት ፅሁፍ ለምን በፖሊስ አልተያዘም?

ምስክር:_እንደምንያዝ ስላወቅን አበበ ስልኩን አስወግዷል

ፍ/ቤቱ: _የቀረበብዎት ክስ አለ

ምስክር:_የለም

ፍ/ቤቱ:_ያኔም “የሽብር ጥቃት” እያላችሁ ቃሉን ትጠቀሙበት ነበር?

ምስክር:_አዎ

ፍ/ቤቱ:_የሽብር ጥቃት፣ መንግስትን በኃይል ለመጣል እያላችሁ?

ምስክር:_አዎ

ፍ/ቤቱ:_ኢትዮ ቴሎኮም፣አብቁተ እና ሌሎችም የህወሃት ብለው ነበር የሚያውቋቸው?

ምስክር:_ አላውቅም

ፍርድ ቤቱ:_ አሁንስ

ምስክር:_የህዝብ ነው

ፍ/ቤቱ:_እንዴት አወቁ

ምስክር:_መንግስት ምህረት ካደረገልኝ በኋላ

ፍ/ቤቱ:_እንዴት ልትያዙ ቻላችሁ

ምስክሩ:_ወደ ብዙ ተግባሮች እየገባን ባለንበት ወቅት መንግስት ይዞናል

(ተከሳሾቹ ላይ ሶስት የዐቃቤ ምስክሮች አሉ ተብሏል። አንዱ ፈርሞ አልመጣም በመባሉ ፖሊስ አስሮ ለቀጣይ ቀጠሮ ያቅርብ ተብሏል። ሌላኛው መጥርያ አልደረሰውም ስለተባለ መጥሪያው ደርሶት ይቅረብ ተብሏል። ሁለቱም ምስክሮች አዲስ አበባ የሚገኙ ሲሆን ተከሳሾቹ ቃላቸውን ሲሰጡ ታዝበዋል የተባሉ የደረጃ ምስክሮች ናቸው። በቤተሰብ በኩል ማረጋገጥ እንደቻልኩት ተከሳሾቹ ቃላቸውን ሲሰጡ የታዘበ ሰው አልነበረም። ሆኖም ይቀርባሉ የተባሉት ምስክሮች ተከሳሾቹ ቃል በሰጡበት ወቅት ነበርን ብለው የሚመሰክሩ ናቸው። ተከሳሾቹ ሁለቱን ምስክሮች ለመስማት ለጥር 4/2010 ዓም ተቀጥረዋል)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.