አርቲስት ታማኝ በየነ በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ መፈታቱ ተገለጸ

Posted by Dereje Clearphoto on Tuesday, December 12, 2017

ዘርይሁን ሹመቴ

የሰብአዊ መብት ጥሰት ህመም የሚሆንበትና የአገር ጉዳይ ፍቅር የሆነበት አርቲስት ታማኝ በየነ ዛሬ በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ተዘገበ።

አፍሪቃውያን በየአገራቸው ያለውን የአምባገነን ስርአትና ይህ ስርአት የፈጠረውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ቀውሶችን ለመሸሽ በሚያደርጉት ስደት በሊቢያ እየደረሰባቸው ያለውን የባሪያ ንግድ ለመቃወም በተዘጋጀው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተገኘው አክቲቪስት ታማኝ በየነ ለአምባሳደሩ የተዘጋጀውን ደብዳቤ እንዳይሰጥ በመታገድ በቁጥጥር ስር ውሏል።

በሊቢያ በባርነት እየተሸጡ ያሉትን አፍሪቃውያንን ጉዳይ ለመቃወም ይህ ሰላማዊ ሰልፍ እንደተዘጋጀ እና በሊቢያ መንግስት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ የሚገልጽ ደብዳቤ በዋሽንግተን ዲሲ የሊቢያ አምባሳደር ለሆኑት ለማቅረብ የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ለአምባሳደሩ የተዘጋጀውን የተቃውሞ ደብዳቤ በአካል ወደ ኤምባሲው ገብተው መስጠት እንደማይችሉ ለታማኝ በየነ እና ለሌላኛዋ የሰልፉ ተወካይ የኤምባሲው የጸጥታ ሃይል ሲነግራቸው የተቀሩት ሰልፈኞች ቁጣቸው በመገንፈሉ የተነሳ ከዋሽንግተን ዲሲ ፖሊሶች ጋር ንትርክ ውስጥ ገብተው ታይተዋል።

አክቲቪስት ታማኝ በየነ የተቃውሞውን ደብዳቤ በቢጫ ኢንቨሎፕ እንደያዘ ከሌላኛይቱ የሰልፉ ተወካይ ከሆነች ግለሰብ ጋራ በቁጥጥር ስር ውሎ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።

በአሁን ሰአት አክትቪስት እና አርቲስት ታማኝ በየነ ከፖሊስ ቁጥጥር ነጻ ወጥቷል በእስራቱ ለተበሳጩትና ለተጨነቁት ኢትዮጵያውያን ምስጋናውንም በመልክቱ አስተላልፏል።

በስደት አለም የተለያዩ ስቃዮችና ግፍ የደረሰባት ኢትዮጵያዊት የሊቢያው አምባሳደር በሚረዱት በአረብኛ ቋንቋ አገራቸው የአፍሪቃ ስደተኞችን እንደ እቃ በባርነት እየሸጠች መሆናን በመጥቀስ በጎላ ድምጽ ስትቃወም ታይታለች።

በሰልፉ የተገኙት ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በእንግሊዘኛ፣ በፈረንሳይኛ እንዲሁም በአማርኛ ቋንቋዎች ንዴታቸውንና ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል።

በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የሊቢያ ኤምባሲ የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ከተለያዩ የአፍሪቃ አገራት የተውጣጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ውለዋል።

በዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ላይም ኢትዮጵያኖች በመሳተፍ በኢትዮጵያ ለ25 አመታት የነገሰው የተበላሸ ስርአት ያመጣውን የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበረሰባዊ ቀውስን በመሸሽ ለስደት የተዳረጉትን ዜጎቻችን በሊቢያና በሌሎች አገራት የሚደርስባቸውን ግፍ ሲያወግዙ ቆይተዋል።

በሊቢያ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪቃ አገራት ስደተኞች የሚደርስባቸውን ግፍና የባሪያ ንግድ በመቃወም በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ፣ በደቡብ አፍሪቃ እንዲሁም በእስራኤል ቴላቪቭ ከተማ አለም አቀፋዊ የተቃውሞ ሰልፎች ሲደረጉ ውለዋል።

ከ 25 አመት በፊት ኢትዮጵያኖች በማይታወቁበት ለእንደዚህ አይነት ውርደት፣ ስደት እና ስቃይ መዳረግ ከሁለት አስርተ አመታት በላይ በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ሙሉ ሃላፊነቱን መውሰድ አለበት የሚሉ አስተያየቶች ተበራክተው ይሰማሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.