ቁልፍልፍ። (ሥርጉተ ሥላሴ)

ከሥርጉተ ሥላሴ 13.12.2017 ከጭምቷ ሲዊዘርላንድ።

ሥርጉተ ሥላሴ
ሥርጉተ ሥላሴ

„እግዚአብሄር ለሰው ሁሉ ባለጠግነትን እና ሀብትን መስጠቱ፣ ከእርሷዋም ይበላና ዕድል ፈንታውን ይወስድ ዘንድ በድካሙ ደስ ይለው ዘንድ፤ ማሰልጠኑ ይህ የእግዚአብሄር ሥጦታ ነው።“ (መጽሐፈ መክብብ ምዕራፍ ፭ ቁጥር ፲፱።)

ለኢትዮጵያ እናቶች እና የዕንባ ማህበርተኞች ወገኖቼ።

በቅድምያ በአዶልፍ ዶር. ደብረጽዮን ገብረሚኬኤል አመራር በትግራይ፤ በወልደያ እና በጨለንቆ ደማቸው ለፈሰሰው ቀንቦጦች፤ ህጻናት እና አረጋውያን እግዚአብሄር አምላክ ነፍሳቸውን በአርያመ ገነት ያስገባልኝ። አሜን። ለቤተሶቦቻቸውም አብዝቶ መጽናናቱን ይስጥልኝ – መዳህኒተዓለም አባቴ። አሜን።

ይድረስ ለሰብዕዊ መብት ተሟጋች ጋዜጠኛ ለጸሐፊ ዬኔታ ሙሉቀን ተስፋው።
<ul>
<li>የዛሬ ጹሑፍ የመነሻዬ ተነሳሽነት።</li>
</ul>
በማስተዋልህ ውስጥ።

በአምክንዮ ቀረቤታ።

ወቅታዊነት እና አስፈላጊነቱ።

ጤና ይስጥልኝ የኔታ ሙሉቀን ተስፋው እንዴት ሰነበትክ እናትዬ። ደህና ነህ ወይ። እርግጥ አሁን ያለው አዬር የእኔን መልእክት በጥሞና ታዳምጠዋለኽ ባልልም ግን እኔ ያልተመቸኝን ሃስብ ቋጥሬ ከማስቀምጠው ብገልጥልህ የተገባ ነው ብዬ አስቤ ነው። መዘግዬትም የለበትም። ለደከምክበት ጉዞ ደጋፊ አቅም ማግኘት የመፍትሄ አንድ ደረጃ እርከንም ስለሆነ እንዳስተውለው ለማሳሰብም ፈልጌ ነው። አሁን ደግሞ እንደ ቀደመው ጊዜ በጋራ ሞት ከተፈረደበት መንፈስ ጋር በደም መተሳሰሩም ግድ ይላል። ብቻ ተሩጦ ከግብ አይደረሰም – ለዛውም አማራዊ መንፈስን የሚያስተናግድ ቅንጣት ቅነነት ያለው ሰማይ ቤት ብቻ ነው። እግዚአብሄር ወዶ – ፈቅዶ – ህሊናን አሰናድቶ ወደ እኛ የሚመጣን መንፈስ ከላከልን ደግሞ ለእኛ ብርቅ እና ሽልማታችንም ነው – ለቅኖች። በመንፈሳችን ህሊና ውስጥም በፍጹም ቅንነት እና ትህትና አንጥፈን፤ ጎዝጉዘን ልንቀበለው ይገባል ባይ ነኝ። ከቶ ከፈጣሪ በታች ለነገረ አማራ ማን አለውና? የሚሞትበት ታሪኩን ባለቤትነቱን እንኳን ዘጋቢ አላገኘም።

እናትዬ …

ባልጠጋነትህ እና ሃብታምነትህ ያለው በህሊናህ ውስጥ ነው። ይህን የሰጠህ ደግሞ አማኑኤል አባታችን ነው። ስለሆነም ጸጋህን አወቀህ በመክሊትህ ዙሪያ ትትርናህን፤ ጥረትህን፤ የምትከፍለውን መስዋዕትነት እጅግ አድርጌ አከብራለሁ። አብዝቼም ድንግልዬ ትጠብቅህ ዘንድ የአቅሜን እጸልይልሃለሁ። አደንቅህም አለሁ። ለዚህም ነው ቤተሰቦቼ እንኳን „አማራ ነን“ ብለው የማያወቁትን ማንነቴን አንገቴን ሳልደፋበት አማራ ነኝ ብዬ የወጣሁት። ለዚህም ነው የአማራ ተጋድሎ ትጉሃንን የኔታ የምለው። ብዙ ሰዎች የአማራ ተጋድሎ ከሰመ የሚሉ አሉ። በመንፈሳችን ውስጥ ያለውን ቋያ ስለማያውቁት ነው። ችግኝ አይደለም አሁን አማራነት ሰብል ነው። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ላይበቃ የነፃነት ትግሉ መንፈስ በአማራ የህልውና ተጋድሎ ላይ ሲዘምትበት አማራነቴ ካልነሸጠኝ፤ የተሰነዘረበት ቅስም የሚሰበር፤ ፍጹም አግላይ ቡድናዊ ሂደትን ፊት ለፊት ወጥቼ ካልሞገትኩት እኔ „ስለ ሰብዕዊነት“ ከራሴ መብት ካልጀመርኩት ይህን የቤት ሥራ ከቶ ማን እንዲሠራልኝ እሻ ነበር? እኔ ሥርጉተ – ሥላሴ አማራነቴን የእኔ ብዬ ካልተቀበልኩት ከቶ ማን ሊቀበልልኝ ይችል ነበር? እኔ ያላከብርኩትን የወላጆቼን ደም ማን አለሁኽ ሊለው እፈልጋለሁ? አማራነቴ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት ማንፌሰቶ ፈቃድ በፍጹም ሁኔታ በላይ ነው። ምክንያቱም ከወላጆቼ የዘር ሐረግ በላይ አይደለም እና። ከወረቀት ደሜ ተፈጥሮዬ ይበልጥብኛል። ስለዚህም የተጋድሎ ትርፍ ሊመዘን፤ ሊለካ ከቶውንም ወቄት ሊበጅለት አይችልም። አንቴናዬን ቀጥ አድርጌ ነው ግራ ቀኙን እማዳምጠው። „ከራስ በላይ ንፋስ“ ስለሆነ። ወደ እኔ የሚመጣውን የፍቅር መንፈስ ደግሞ እጄን ዘርግቼ፤ የመንፈሴን በር ቧ አድርጌ ከፍቼ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ አስተናግደዋለሁ፤ በበዘ ቅንነት እና ሰላማዊነት። ኢትዮጵያን አውዳታለሁ ስል ወደ እኔ እዬገሰገሰ ያለውን ቅን የኢትዮጵያዊነት መንፈስን ሳልገፋ፤ በቅድመ ሁኔታ ትብትብ ሳላስር የመንፈሴ ባለርስት ሳደርገው ብቻ ይሆናል የኢትዮጵያዊ ዜግነቴ ትርጉም ሙሉዑ የሚሆነው። ምክንያቱም የአማራነት ጥቃቴ ኢትዮጵያዊነቴን ጽላቴ በማድረጌ ነው እና። „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ለእኔ የመንፈስ መኖዬ ነው። ለእኔ ኮለል ያለ ውሃዬ ነው። ከሰው አንደበት የወጣ ስለሆነ ፍጽምና አልጠብቅበትም፤ እኔም ፍጹም አይደለሁም እና። እኔም ከስህተት ነፃ አይደለሁም እና። ለዚህ ጥበቃ የሚያደርግ አቅም ያለው ንጽህና እንዳለ ግን አምናለሁ። በኦህዲድ አዲሱ ካቢኔ በሦስተኛው ደረጃው አካል አምመሰከረው ለጊዜው የለኝም። ግን ነገር ግን የዶር. አብይ አህመድ መንፈስ „ለኢትዮጵያዊነት ሱስ ነውን“ ቤተኛ መንፈስ ጥበቃ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ። ይህ እኔ ስላልኩት ሳይሆን ተፈጥሮው ስለሆነ ነው። ስለሆነም የራህባችን ሚዛን፤ ጸጥታውን የሚንከባከቡ ወታደር፤ የሰላም አማካሪ ጠባቂ ባለሟል በቅርበት አለው ብዬ በጽኑ አምናለሁ።

ጥሞና።

እናትዬ አሁን ሰሞኑን በአቶ ለማ መገርሳ ዙሪያ አንድ መረጃ አውጥተህ አይቸዋለሁ። በጥቂት ደቂቃዎችም 1000 ወገኖችን ቀልብ ስቧል። አዬህ ያ ሰንጠረዥ ከፈላስፋው ከዶር. ዳኛቸው አሰፋ ቅኔያዊ ቅኝት አምክንዮዋ አቅሙ በልጦ አይደለም። ያ መረጃ በእስር ከሚሰቃዩት የዕንባ መረጃ ቋት አይመጣጠንም። ኢትዮጵያዊነትን ውስጡ ላደረገ መንፈስ ዕሴቱ የዶር. ዳኛቸው ቃለ ምልልስ ሆነ የእስረኞችን ሁኔታ የሚዘግበው የሰብዕዊ መብት ተሟጋች ጋዜጠኛ የአቶ ጌታቸው ሽፈራው ሚዛን ይመታል። ለኢትዮጵያ ህዝብ እና ለዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ የቀረበ የድረሱልን ጥሪ! (በእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ 38ቱ ተከሳሾች) <a href=”https://etzena.com/amharic/archives/42669″>https://etzena.com/amharic/archives/42669</a> አስከ ዛሬ ድረስ 63 ወገኖች ብቻ ነው ሸር ያደረጉት።

በ16 እስረኞች ላይ በምርመራ ወቅት የደረሰ ጉዳት – ጌታቸው ሽፈራው 134 Shares ብቻ ነው በውስጡ ለማስቀመጥ የፈለገው። <a href=”https://etzena.com/amharic/archives/41771″>https://etzena.com/amharic/archives/41771</a> አሁን ይሄ የአዶልፍ ሂትለር ሥርዓት የሚፈጽው ኢ-ሰብዐዊነት ቢያንስ ለአማንያን እንዴት ከውስጥ አይገባም። የእግዚአብሄር ፍጡር በምድሪቱ እንዲህ ሲንገላታ፤ እንዴት የእኛ አይባልም። እንዴት በቂ አድማጭ አያገኝም?

አዬህ ታናሼ፤

ፍላጎታችን ከምን ላይ እንዳለ ያሳያል። መስታውት ነው። ራዕያችን ይህን ሰቆቃ ማዕከሉ ያደረገ አይደለም „ሰውን“። በሴራ ፖለቲካ በቅናት እና በምቀኝት፤ እንዲሁም በበቀለ የዘለበ ራዕይ ነው ያለን። ከዚህ ጸላዬ ሰናይ መንፈስ ወጣቶች በፍጹም ሁኔታ መውጣት አለባችሁ። እናንተን ለሚተኩትም ተጋድሏችሁ በዚህ ላይ ካልተመሰረተ የአደራ አውጪ ቤተኞች መሆን አትችሉም። ስለምን ነው በፍጥነት ያን አህል አንንባቢ ያገኘው ብለህ መርምረው? ለማን ነው ያ ሰንጠረዥ የትርፍ ቋት የሆነው? የማንን ቤትስ ይሠራል – ያደራጃል – ያዋቅራል?

መልስ።

ለኢትዮጵያዊነት ትንሳኤ ቀብር፤ ለታላቋ የትግራይ ሥርዎ መንግሥት የ200 ዓመት ህልም፤ ለኢጎ አርበኞች፤ አቅም ብቅ ባለ ቁጥር ለሚብተከተኩ አቅመ ቢሶች፤ አዲስ ሃሳብ የማፍለቅ አቅማቸው ተሟጦ ላለቀባቸው የግራ ፖለቲካ ሊሂቃን ህልም እና የሥልጣን ሱስ ወረርሽኝ የሚፈልጉትን ብልቱን የእኔ ብለህ ያውም በአንተ በሥምህ ስላወጣህ ነው። ይህም መብትህ ነው። ግብረ ምላሹ ግን የአንተ በፍጹም ሁኔታ ሊሆኑ ያልቻሉ መንፈሶች፤ ሲታገሉኽ የቆዩ መንፈሶች ሁሉ የድል መባቻ ነበር። አቅም ፈጠርክላቸው። ይህ አቅመ ቢሱ የትም የተበተነው ያ እንግልተኛ መንፈስ ደግሞ በጥርጣሬ እንዲታይ በቀጥታ ያደርገዋል። ቂምም ያስቋጥራል። እናንተ የህልውናው ተጋድሎ አብሪ ኮከቦች ናችሁ እና። ለምታጣፉትም ሆነ ለምታለሙትም ከተጋድሎው ታሪክ እና ውጤቱ ጋር በፅኑ የተሳሰረ ነው። በስተጀርባችሁ „የሚሊዮን የህልውና የአደራ ተስፋ“ አለባችሁ። ነገ ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም። ለነገ ዛሬ የአቅም ጎጆ በብልህነት መቀለስ ያስፈልጋል። የነፃነት የተጋድሎ የመፍትሄ መንገድን ትንፋሽ የሚቃረን ከሆነ ስለምን ትደክማለህ? አንድ ፖለቲከኛ ወቅትን፤ የሃይል አሰለላፍን ማድመጥ የቅደሚያ ተግባሩ ህጉም ሊሆን ይገባል። በዚህ ሂደት ገዥ መሬት ላይ ያለው የመንፈስ አቅም ሙት መሬት ላይ ላለው የመንፈስ አቅም ያለው አትራፊነት በግብር ይውጣ የሚወራረድ የቁጥር ፎርሙላ አይደለም። የህልውና ተጋድሎ ጉዳይ የከረንቡላ ጨዋታ አይደለም። የህልውና ተጋድሎ አደራም ብቻ ሳይሆን የኪዳን ድርብ፤ ንብርብር የትውልድ ዕዳ ነው።

የሆነ ሆኖ ወቅታዊ ባይሆንም ይህን የኔታ አቻምየለህ ታምሩ ወይንም የእኔታ ሙሉነህ ዮሖንስ ቢጽፉት አይደንቀኝም። ምክንያቱም እነሱ ጎን ለጎንም በነገረ ኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ አትኩሮት ስላላቸው። አንጻራዊ በሆነ ሁኔታ የኔታ አያሌው መንበሩም ቢጽፈው በተወሰነ ደረጃ በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ የሚያቀነቅኑ መንፈሶች በጹሑፎቹ ላይ ስለምመለከት አይደንቀኝም። አንተ ስታደርገው ግን ለምን በአሁን ሰዓት ይሄን አመክንዮ መረጠ በማለት እራሴን ጠዬኩት? ጹሑፎችህን በውስጤ አነባለሁ፤ ቃለ-ምልልሶችህን በሙሉና በተረጋጋ መንፈስ ከመንፈሴ አዳምጣለሁ በራዲዮ ፕሮግራሜ ተጠቅሜበታለሁ። „ብራና ራዲዮንም“ ቃለ- ምልልሶችን እከታተላለሁ። የአማራ የህልውና ተጋድሎ ቆመሶች ሁላችሁም ቀለማችሁ የተለያዬ ነው። እንደ ቀለማችሁ ተፈጥሮ ከውስጤ አስቀምጬ አዳምጣችኋዋለሁ። ቀለማችሁን እማስተናግድበት መንገድ በወጥነት ሳይሆን እንደ ቀለሙ ዓይነት ነው ውስጤ የማደርገው። አሁን ያንተ ቀለም አረንጓዴ ነው። የዬኔታ አቻምየለህ ታምሩ ቀይ ነው። የዬኔታ ሙሉነህ ዮሖንስ ቢጫ ነው። ዬዬኔታ አያሌው መንበሩ ደግሞ ሀመራዊ ነው። እነኝህ ቀለሞች በግል ህይወቴም ምርጫዎቼም ናቸው።

ክህሎት።

እኔ እንደምለው ብቻ ሳይሆን፤ አንተም ነፍስህ የሰከነችበትን አሳምረህ፤ አደላድለህ ታውቀዋለህ። እኔ እንደሚረዳኝ እና እንደ ተረጎምኩህ ምሰጣህ ሙሉ ለሙሉ የምጽዕተ አማራ ተኮር ላይ ነው – የምትሠራው። ሙሉ ጊዜህን የሰጠኸው ጥግ ባጣው ተገፊ ማንነት ላይ ነው። የማይቻለውን በመቻል መስጥረኽ ነው እዬኖርክበት ያለኸው። ይህም ለፕሮፖጋንዳ ሸቀጥነት፤ ወይንም ለአፍቅሮተ ማንፌስቶ፤ ወይንም ለኢጎ፤ ወይንም ለዝና እና ለከንቱ ውዳሴ ከንቱነት ብለህ ሳይሆን በእያንዳንዱ የአማራ ጉዳት ላይ አቧራ ለብሰህ፤ በጭቃ ተለወስኽ፤ በህመሙ – በስቃዩ – በመከራው – በዕንባው – በዕንግልቱ – በሞቱ – በሚሰቀጥጠው ዜና፤ በተስፋው ውስጥ „ሰው“ በሚለው ታላቅ የከበረ ፍጡር የደረሰውን ያልተቋረጠ፤ በተለያዬ መልክ እና ይዘት ፖለቲካዊ ሴራ የአማራ ማህበረሰብ ሆነ አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪውንም ጨምሮ ያሰተናገደውን ሀገራዊ ጭካኔ፤ አረመኔነት፤ የዘር ጥፋት እና ፍዳውን፤ ሰቀቀኑን ከውስጥህ አስቀምጠህ የእኔ ብለህ፤ ኧረ ከራስህም በላይ ካለ ቋሚ ማህያ ቤተሰቦችህን ለበለሃሰቦች አሳልፈህ ሰጥተሃል። በነገረ አማራ የጥናት እና የምርምር ተግባርን የከወንክ የተግባር ጀግና በመሆኑህ ከዚህ በላይ የምታስቀድመው አጀንዳ ለአንተ ሊኖር ባለመቻሉ ነው። እኔም ብሆን እንደ አንተ አልተፈቀደልኝም እንጂ ጸጋውን ሞልቶ ሰጥቶኝ ቢሆን ሰው በሀገሩ፤ ሰው በቀዩ፤ ሰው በባዕቱ በራሱ ሥጋ እና ደም፤ ግን በዘሩ ብቻ ተነጥሎ መገለል፤ ጭቆና – ሞት – እልቂት እንዲህ ሳያባራ ሲታወጅበት ዘመን ይቅር የማይለው የአሳር ዓይነት – በዓይነት ከመጠን አልፎ ሲጎመዝዝ አንተ የወሰድከውን፤ አንተ የደረስክብትን አቋም የማልወስድበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ህይወቱን አይተኸዋል – ኑረኽበታልም። በራስህም ህይወት ችግሩ እዬተፈራረቀ በደሉ ደርሶብሃል።

ስለሆነም ሙሉ ጊዜህን ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ሃብትህንም ሳትሰስት ለዚህ አብይ በኽረ ሰብዕዊ፤ ተፈጥሯዊ ጉዳይ መስጠትህ ከሰማይ የተሰጠህ፤ በእናትዬ ማህጸን ስትጸነስ የተቀባኸው መክሊትህ ነው። እያንዳንዱ ልጅ ሲወለድ መክሊት ይዞ ይወለዳል። አባታችን ቅዱሱ አቡነ ተ/ሃይማኖት፤ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ፤ አባታችን አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባም ገና በጽንሳቸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ መክሊት ነበር። ቅዱሳኑ ልክ እንደ እኛ እንደ ሰው ተፈጥረው ግን በምድር ላይ እዬኖሩ የቅዱሳን፤ የጻድቃን፤ የሰማዕታትን ገድል ፈጽመው ሰማዕት፤ ቅዱሳን የተባሉት። ታቦት የተቀረጸላቸውም። አሁን አቡነ ተ/ ሃይማኖች ግብጽ ሳይቅር ቅድስናቸውን እና ሰማዕትነታቸውን ተቀብላ መታሰቢያ ሠርታላቸዋል። ስለሆነም ቅድስና በዬትኛውም ሁኔታ እና መስክ ሊከሰት ይችላል። መንፈሱ አዛኝነት ነው። መንፈሱ ተቆርቋሪነት ነው። መንፈሱ አርቲፊሻል ያልሆነ ርህርህና ነው። መንፈሱ የሌላውን ችግር የራሴ ብሎ ከውስጥ መቀበል ነው። መንፈሱ ሰዋዊነት – ተፈጥሯዊነት ነው። እናታችን ቅድስ ክርሰቶስ ሰምራ ፈጣሪዋን፤ አምላኳን ስለምን ከሰይጣን ጋር አትደራደርም፤ ስለምንስ ከሞት በኋዋላ ገሃነም ነፍሳት ይቀቀላሉ ብላ ሞግታዋለች። አዬህ እናታችን ቅድስናዋን ያገኘችው በሰብዕዊነትና በተፈጥሯዊነት ወስጥ ነው። በሥጋ ከእኛ ለሚለዩት ሁሉ አሰበች፤ ተቋርቋሪ ተሟጋች ሆነች። በምድርም ሲኖሩ የሚያሳስታቸው፤ ሃጢያት የሚያሠራቸው ዲያቢሎስ ነው፤ ከእርሱ ጋር እርቅ ፍጠር ብላ ነው አማኑኤልን አባታችን ፈጣሪዋን ሥልጣነ አምላክነቱን እያወቀች ነበር የሞገተችው። ስለዚህ ለእኔ እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ቅድስት ብቻ ሳይሆን የሰብዕዊ መብትም፤ የተፈጥሯዊነትም ደፋር ተሞጋችም ናት። ይህ ደግሞ ስትፈጠር ቅብዕዋ ነበረ።

መፍትሄ እና መንገዱ።

አዬህ እናትዬ መልካምነት፤ ደግነት፤ የሰውን ችግር የእኔ የራሴ ብሎ ከራስም በላይ አድርጎ ውገዘትን ከመቀበል በላይ፤ መገለልን ከመፍቀድ በላይ፤ ዕውቅና ከመነፈግ በላይ ለእኔ የምድራዊ ጽድቅነት፤ የሐዋርያዊነት ተግባር የለም። አዬህ የእኔ ልጅ ችግርን ማጥናት ለመፍትሄ መንገድ ጠራጊ ነው። ግን በራሱ መፍትሄ አይደለም። መፍትሄዎችንም ማፍለቅ በዛ ላይ መሥራት እጅግ ያስፈልጋል። ይህም ማለት ወደ መፍትሄ የሚወስዱ ማናቸውንም ነገሮች ሁሉ አቅሞችን አላማበከን ማለት ነው። አቅሞችን በዬትኛውም ሁኔታ እና ጊዜ በፈቀድነውም ይሁን ባልፈቀድነው መንገድ ይከሰታሉ። ጠጋኝ አቅሞች አትኩሮትን ሆነ አክብሮትን እንደ ማንኛውም ክስተት ይሻሉ። አብሶ የመንፈስ አቅም ደንዳና አንጀት የለውም፤ መከፋት ከገጠመው መሬት የያዘ አቅም ሳይፈጥር ህልም እልም ይሆናል። አቅም የተግባር የማሸጋገሪያው መንገድ የመሆኑን ያህል፤ ትእግስቱን የሚፈትኑ ሁነቶች ከተፈጠሩበት ሸብረክ ይላል። ስስ ነው sensitive፤ ሲሳዩንም ላከበረው ለሌላ ይሸልማል። ሐሴቱንም ሎተሪ ለወጣለት ያስረክባል።

አቅም የሚፈልቀው ከዬትም ወገን፤ ቡድን፤ ድርጅት፤ ግለሰብም ሊሆን ይችላል። ቅድሚያ ወደ አንተ የመጣልህን አቅም ማክበር ያስፈልጋል። ያን አቅም ከውስጥ መቀበል ያስፈልጋል – ብልህነትን ሰንቆ። ፖለቲካ ከላይ እንደገለጽኩልህ ወቅትን ማድመጥ በአጽህኖት ይሻል። አቅሙን ወደ አንተ ለመምጣቱ ምልክት ካገኘህ ወይንም ደወሉን ከሰማህ፤ ግማሽ መንገድ ተጉዘኽ „እንኳን ደህና መጣኽ“ ማለት ይኖርብሃል። ለዛውም አንተ ያልደከምክበት፤ ያለሰብከው አንተ መንፈስህን ሌላ ላይ አሳርፍኽ በዛ ላይ እዬደከምክ፤ መንገዱ እዚህ ነው ሲልህ ፈጣሪህ ያን የባትሪ ጨረር መከተል አለብህ። ሙሉ ለሙሉ ከጨለማ ባያወጣህ እንኳን፤ የመንገዱን ድቅድቅነቱን ይቀንስልሃል። ፍጽምና ከማንም፤ ከዬትኛውም ፍጡር የለም እና። ፍጹም የሆነ ደስታ መሬት እራሷ አልታደለችበትም። ለዛውም ፍቅርን ያህል የመቻቻል፤ ዕውቅና የመስጠት፤ አመስግናለሁን የሚሸለም፤ የድንገቴን ሰናይን የሚያስረከብ አደራ ያለበት ልዩ ተፈጥሮ። ይህም ቢቀር ቢያንስ አቅሙን በቅንነት ከውስጥ መደገፍ ያስፈልጋል። አየህ እናቱ አቅም በራስ መተማመንን ይፈጥራል። በራስ መተማመን ደግሞ ጉልበትን እና ሃይልን ያመነጫል። ጉልበት እና ሃይል ደግሞ „አደርጋለሁ! እችላለሁ!“ ማለትን ጸንሶ ይወልዳል። ጉልበትና አቅም ሆኖ የማይቻለውን ችሎ ከወጣ ደግሞ ከማናቸውም ጥቃት ይከላከላል። ጉልበት የአንቱ አቅም ከሆነ ጥላ ከለላ ይሆናል። ጉልበት ያለው ሳቢ ሃይል የአንተ ለመሆን ከፈቀደ የህልውና መጠጊያ ይሆናል። በዛ አቅም ውስጥ ያንተም ጎጆ ማህበርተኛ ናት። ቤተኛ ናት። የአንተ የቤት ሥራ ይህ ወደ አንተ የመጣውን አቅምን ችግርህን ዘንበል ብሎ ያደምጥ ዘንድ መንከባከብ አለብህ። በጥንቃቄ መያዝ አለብህ። እንክብካቤውን ለማግኘት ደግሞ ምስባክ መሆን ይኖርብሃል፤ አንተ ውስጥህን አሸንፈኽ ስርክራኪውን ጠረገህ ማውጣት። አዬህ አባትዬ ጉልበት፣ አቅም ካለም ሌላ ተጨማሪ አዲስ አቅም ይፈጥራል፤ ተጨማሪው ጉልበት በሚፈጥረው የግፊት እና የስበት መጠን የችግሮች መፈልፈያዎች መካች፤ ረጂ መንፈስ እያገኙ ይሄዳሉ።

ከምንም ነገር በላይ የአቅም ሥጦታ ከሁሉም በላይ ነው። ለዚህ ነው የፖለቲካ ሊቃናት አንድ ሰው ዝናው ከመውጣቱ በፊት የት እንደ ወደቀ፤ የትም እንዳለ አያውቁም። ትዝ አይላቸውም ያ ሰው ከነመፈጠሩም። ዜጋቸው ስለመሆኑም አይረዱትም። ጌጣቸው ስለመሆኑም አያስተዋሉትም። ሚዲያዎች እራሳቸው የሰው ልጅ ሰው መስሎ የሚታያቸው እውቅና ሲያገኝ ብቻ ነው። „አንድ ጹሑፍ አንብቤ ነበር በአንድ ውቅት በአርበኛ ዘመነ ካሴ ዙሪያ በነበረው እሰጣ ገባ “እናንተ ማን ናችሁ እነእከሌን እናውቃቸዋለን“ የሚል። እኛ ከዜግነት ውጪ ነን። ሌላው አያገባውም፤ ቤተሰቡ ሳይቀር ከቁጥር የለም – ተሰርዟል። ቤተሰቡ አስተያዬት መስጠት የት ደረሰ ብሎ መጠዬቅ አይፈቀድለትም። ስለ እኔ ማንነት ዳኛው ፈራጁ ቀዳጁ ወሳኙ ሌላ መንፈስ ነው። አፌ ቃል እንዳያወጣም የዕውቅና ሰሌዳ ከግንባሬ ላይ „መናገር ተከልክሏል!“ ተብሏል። ስለዚህም መዳህኒተ ዓለም አባቴን ቢያንስ በነፃው መሬት እናገር ዘንድ እንዲፈቅዱልኝ ስውር ጌቶቼ እንዲያማልደኝ መለመን አለብኝ። ሱባኤ መግባትም። በስተቀር የሰው ማህበረተኛ አይደለሁም እኔ። “It’s pure Discrimination!” የሆነ ሆኖ „ሰው መሆን ማለት ዕውቅና ማግኘት ማለት ነው።“ ስለሆነም ያ ሰው አድናቂ ሲያፈራ ፖለቲከኞች፤ ሚዲያዎች ይረባረቡበታል። የራሳቸው ለማድረግ፤ ለማያውቁት ተፈጥሮ የድል አጥቢያ አርበኛ ይሆኑበታል። እንዲያውም ተቆርቋሪ ተሟጋች ሆነው ያርፋሉ። ስለምን ይመስልሃል? ድልድይ፤ መሰላል የመንፈስ አቅም ስለሚያስፈልጋቸው። ሁሉም ያን አደባባይ ፈክቶ የወጣውን አቅም ይሟሟትበታል፤ ቢችል የራሱ ለማድረግ ባይችል ዝንባሌው ወደ እርሱ እንደያጋድል፤ እንዲጠጋጋም ተግተው ይታትራሉ። ማሸነፍ የሚገኘው በተሟላ አቅም መሆኑን ያውቃሉ።

ስለሆነም አቅም ለዛውም ፈቅዶህ የመጣን አቅም የራስ ለማድረግ መፍቀድ፤ ቅንነትን መቀለብ አውዱን – ጠረኑን – መንፈሱን የራስ ማድረግ ፖለቲካዊ ብልህነት ነው። መቼም አንተ ወጣት ሙሁር ነህ፤ በሰው ልጆች ጥቃት ላይ ጥናት እና ምርምር ያደረክ ድንቅ ትጉህ ብላቴና ነህ። በዛ ላይ በሥነ – ልቦና ላይ ያተኮርክ የስብዕነት ውስጣዊ የስሜት መንፈስ አጥኚም ነህ። በተጨማሪም ጸሐፊም ጋዜጠኛም የሆንክበት መስመር ፈተናው ያዬለ ሰብዕዊነት ነው ምርጫህ። ለእኔ የሰብዕዊ መብት ጋዜጠኛ ነህ። አማራም ሰው ነው እና። አማራም የእግዚአብሄር ፍጡር ነውና። ይህን ተጋድሎ የምትመራበት መንፈስህ ደግሞ መሳጭ ነው። ጨዋነት፤ አስተዋይነት የታከለበት ነው። ህግ አትተላለፍም።

ሙሉ መክሊት ከአስተዋይነት ጋር ነው እኔ የምታዘበው። እንደ ሰው፤ እንደ ወጣትነትህ በዕድሜ ለጋነት የሚመጡ ባህሪያቶችም እንደ ተጠበቁ ሆነው። ግድ ስለሚል። በአንተ ዙሪያ ያለው የሰብዕዊ መብት ተሟጋችነት መንፈስ ፍትሃዊ ነው። አንተ የምትፈልገውን ነፃነት ሌሎችም እንዲኖራቸው ትሻለህ። ይህን በቅማንት ማህበረሰብ ላይ ባለህ ጻዕዳ አቋም በፍጹም ሁኔታ ተረድቸኽአለሁ። „ስለ እሜቴ አይከል“ ጉዳይ ያነሳሳኸው ነገር ደስ ብሎኝ ነበር ያነበብከት። ጎንደርም በዋቄፈታ የሚያምኑ ሰዎች በመከባባር የሚኖሩበት ቦታ ስለመሆኑ ያመሳጥራል። አሜቴ አይከል ሳትከስም መኖሯን ስስማ እራሱ መንፈሴን ደስ ብሎታል። ብዙ ሰው ቅቤ እንደሚቃባት ስለማውቅ። እንደ ተስፋም ነው የሚያያት። ያ ጹሁፍህ የመጀመሪያ የሥራ ቦታዬ የጭልጋ መንፈሱን በምልሰት ቃኝቼ የቅማንት ማህበረሰብ ውስጥነት አስቃኝቶኛል። በሰላሙ ጊዜ ብታዬቸው የሚደንቅ ሰዋዊ ተፈጥሮ ያላቸው ለሰው ልጆች ሁሉ እኩል አፍቅሮት የነበራቸው ናቸው። እኔ በመደበኛ ፕሮግራም ብቻ አይደለም በዬመንደሩ እሄድ የነበረው ለዛቸው፤ ጠረናቸው ሽው ባለኝ ቁጥር ወገቤን በመቀነቴ ሸብ አድርጌ ምርኩዜን ይዤ እረፍት ጊዜዬን ሁሉ ከእነሱ ጋር አሳልፍ ነበር፤ እንደ ወላጆቼ ነበር የማያቸው። „እሙሃይ“ ብለው መጀመሪያ ሥም ያወጡልኝ የጭልጋ ገበሬዎች ነበሩ። ቋንቋቸውን በተወሰነ ደረጃ እማርም ነበር ከእነትሸት። አይከል፤ ሰራባ፤ ገለድባ፤ ጮንጮቅ ከተሞች ሁሉ ይነገር ነበር በደረግ ጊዜ። እኔም ለመነሻ የሚሆኑ ነገሮችን 10ኛ ክፍል እያለሁ የሠራሁት ነገር ነበር ጎረቤቶቻችን ቅማንቶች ስለነበሩ። እዛ ስሄድ ቋንቋውን በነፍሱ አገኘሁት። ስለሆነም በዚህ ዙሪያ ሳታዳላ፤ ለራስህ የበለጠውን እጅ ሳትሰጥ፤ የሰጠኸው ቅን መንፈስ እንዴት እንደ መሰጠኝ፤ የፍትህ አሰጣጥ ዘይቤህ በአንተ ያለኝን ዕምነት እንዴት እንዳጎለበተው ልነግርህ አልችልም። ያ አቋምህ የዕውነት ጉልማ ነበር። ጨዋ ልጅ ነህ። ተባረክ።

ጹሑፉን እያነበብኩኝ በእግሬ የተጓዝኩባቸውን፤ ሜዳዎች፤ ጋራዎች፤ ሸንተረሮ፤ አቀበቱ፤ ቁልቁለቱ ወንዙ፤ ሁሉ በተመሰጠ ትዝታ እቃኛቸው ነበር። የአዝማራው ወቅት የመንገዱ ጠረን፤ የተኛሁባቸውን ክምሮች – የሳሩ ሽታ፤ ያነጥፈኳቸውን አጎዛዎች፤ የጠጣሁባቸውን አንኳላዎች እና ፋጋዎች፤ የበለሁባቸው በትናንሽ ገበቴዎች የእርጎ፤ የአጓት ፍትፍቶች ሁሉ እልም አድርገህ፤ ጭልጥ አድርገህ በትዝታ ወሰድከኝ። ናፍቆቴን ያገኘሁበት ጹሑፍ ነበር። እኔ ሆንኩ ቤተሰቦቼ የከተማ ሆነን ግን የገጠርን መልካም ማዕዛ የኖርኩበት በዚያ አጋጣሚ ነበር። ምርቃቱ፤ አክብሮቱ፤ የፍቅሩ ድንግልናው ወቄት አልነበረውም። አቀባበሉ፤ አሸኛኘቱም እንዲሁ። የልማት ሠራተኛው እራሱ ከመላ ኢትዮጵያ የተውጣጣ ነበር። ኦሮሞዎች፤ ወላይታዎች፤ ትግሬዎች ሁሉ ነበሩ። ግን ጎንደር ላይ አንተ ማነህ? ሃይማኖትህ ምንድ ነው? ተብሎ ተጠይቆ የማያውቀው ከድንበር እስከ ደንበር ነበር። ዛሬ ቅማንት እና አማራ መባሉ ብቻ ሳይሆን የጦርነት ቀጠና እንዲሆን መፈለጉ ያ ተዝቆ የማያልቀው የአብሮነት የፍቅሩ፤ የመቻቻል ልቅናው፤ የአስተሳሰቡ መቅድምነት መስጫነቱ ነው ጠላትን እንዲህ ያፈረባት። ኢትዮጵያን በመንፈስ አንድ የማድረግ ሙሉዑ አቅም የተፈጠረበት ባዕቱ ነበር ጎንደር። ስለሆነም በቅማንት ማህበረሰብ ውስጥ ሆነህ፤ ስሜታቸውን ለማድመጥ የሄድክበት መንገድ እጅግ ድንቅ ነበር። ስመትህ ተደራሽም ነው። ውስጣችውን ስለማውቀው የተገባ ድንግል ቅንነት ነው። እጅግ አድርጌም አመሰግንሃለሁ።

ይህን ማስተዋልህን የተቀናቀነ የጹሑፍ መረጃ ነበር ሰሞኑን የለጠፍከው። አንተ በአማራነት መንፈስ ውስጥ እንደ ሰመጥከው አቶ ለማ መገርሳም በኦሮሞነት መንፈስ ውስጥ የሰመጡ ናቸው – የቁቤ ትውልድ ቤተኛ ናቸው። በሳቸው ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊነት በአንተ በራስህ ውስጥ ብታዬው መልሱን ታገኘዋለህ። አዬህ ብሄርተኝነት ቀላል የአዕምሮ ፍልስፍና አይደለም። አብሶ አሉታዊው መንፈስን ምራኝ ካለ እጅግ ከባድ ነው። አዶልፍ ሂትለርን የተጋሩን ባለስልጣኖች በዚህ ውስጥ ማዬት ይቻላል። ከዚህ ለመውጣት ከራስ ጋር አብዝቶ መታገልን ይጠይቃል። ፍልሚያው እጅግ ቁልፍልፍ እና ፈታኝም ነው። በተሎ ካልተነቃበት እንዲያውም የማይደን በሸተኛ የሥነ- ልቦና ተጠቂም ያደርጋል – ከአረመኔነት ጋር። አውሬ ነው የሚያደርገው። መለወጥ „ሀ“ ሲባል ደግሞ አድማጩ ጊዜ እና አደብ ሊሰጠው ይገባል። አድማጩ ታጋሽነትን ስንቅ ማድረግ ያስፈልገዋል። የማከብረው ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ያለው ጥሩ ፍልስፍና ነው። ከሊቅ እስከ ደቂቅ ይህን በልባችን ውስጥ ብንጽፈው ምርጫዬ ነው። እጅግ ያደገ፤ የሰለጠነ መሪ መርኻዊ መንፈስ ነው „<strong>አናአስደንግጣቸው!“</strong> አሁን ብንገርህ ይህን ስሰማ ምነው ፈጣሪዬ ይሄን መሪ ቃል ከእኔ አንደበት የወጣ አድርገኽልኝ በነበረ አልኩኝ። አውንታዊ ቅናት አይነት – የምር። ረቂቅ አስተሳብ ነው መቻችልን ለማድመጥ በንጽህና የፈቀደ።

ማያያዣ።

አዬህ የአማራ ተግድሎ ፏ ብሎ በአምክንዮ አቅም ጎልብቶ ሲወጣ የፖለቲካ ሊሂቃን፤ ሚዲያዎች፤ የኢጎ መናጆ አደረጉት፤ በግራ በቀኝ ወጠሩት፤ አስደነገጡት እናም ተሸበሸበ። አዬኽ በጥንቃቄ መንፈሱን ልንጠቀምበት ሲገባ፤ ዘላቂ መንፈሱን የጊዜያዊ ፕሮፖጋንዳ ሰለባ እንዲሆን ተፈረደበት። ለሁሉም ሳይሆን አቅም ባክኖ ቀረ። አሁን ደግሞ በእኛ አቅመ ቢስነት ሌላ አዲስ መንፈስ አሰባሳቢ ተፈጠረ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው።“ ከፉከክር ወጥቶ ዘመኑን የሚተረጉም የተስፋ ብልህ ፖለቲከኛ አላገኘም የአማራ ህልውና ተጋድሎ። ከቃላት አጠቃቀም ጀምሮ ውድድር / ፉክክር ፍልሚያ ላይ ነበሩ፤ የአንበሳው ድርሻ የእኔ / የእኔ መባባልን ነበር የታዘብነው። አርበኛ ጎቤ በሰማዕትነት ሲያልፍ ጸጥ አለ – ሁሉም። ተስፋ በዚህ ማህል ጥግ አጣ። ተዉ ሲባሉም አይሰሙም። ያቆጠቆጠ አዲስ አቅምም ያፍራል፤ ይሸማቀቃል በዘመቻ ሲቀጠቀጥ። ስለዚህም ነው አማራጫችን ሰጥቶን ልንጠቀምበት ባለመቻላችን መዳህኒተዓለም አባታችን ሃዘኑን የገለጠበት መንገድ „ከኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ጋር ራህባችን ማዕዶተኛ ያደረገው። ጠንቃቃነት ያተርፋል እንጂ አያከስርም። የአቅም አያያዝ እና አድማጭነት ጥበብ ክው ብሎ የደረቀ ነው በኢትዮጵያ የግራ የፖለቲካ ሊሂቃን የተምክሮ ታሪክ። ይሄ ፖለቲካዊ ስልት ጉልበታዊነትን እንደ ስትራቴጅ የያዘው ሆኖ ነው የሚታዬው። ፖለቲካ ብልህ ሙያዊ አማካሪም ያስፈልገዋል። ወቅቱን በአክብሮት የሚያደምጥ፤ ያደመጠውን የአሸናፊነት አቅም እንዲያገኝ የሚያደራጅ፤ የሚመራ። የነፃነት ራህብተኛ ከስሜታዊነት መውጣት አለበት። አቅምን ከሚበትኑ፤ ከሚያሸሹ፤ ከሚያሸማቅቁ ነገሮች በእጅጉ መታቅብ አለበት። ሰሚ ቢገኝ።

መቅሰም።

የሞራል ፖለቲከኛው አቶ በቀለ ገርባ ከአሜሪካ የ አማርኛው ድምጽ ጋር በነበራቸው የቃለ ምልልስ ቆይታ „እንደ ኦሮሞ ብሄርተኝነቴ“ ብለው ነበር ቃለ ምልልሱን የጀመሩት። ይህን የሰማው የጎንደር የአማራ ተጋድሎ አብዮት ግን ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ አላገለላቸውም „በቀለ ገርባ መሪዬ ነው ብሎ ነበር ፎቷቸውን በትልቅ በክብር ሰርቶ የተነሳው“ ይህም ብቻ አይደለም የኦሮሞ ንቅናቄ ይዟቸው የሚወጡትን መሪ መፈክሮች ጎንደር አዳምጧል፤ አይቷልም። የራሳችሁን ብቻ ጥያቄ ይዛችሁ ስለወጣችሁ የእኛ አይደላችሁም አላለም። የአማራ የህልውና የተጋድሎ አብዮት። „የኦሮሞ ደም ደሜ፤ የጋንቤላውም/ የኮንሶ ደም ደሜ ነው“ ነው ብሎ ነበር የወጣው። „የድምጻችን ይሰማ“ ሰላማዊ ንቅናቄ የእስልማና ሃይማኖት በኢትዮጵያ እንደ ተፈጥሮው እኩልነቱ ይረጋገጥ ብሎ ተነሳ እንጂ፤ ቅድስት ተዋህዶ ተሰደደች ብሎ አልነበረም የወጣው፤ ኢትዮጵያዊነት ጌጤ የሚሆነው እስልምና ሃይማኖት የውስጡ ሰላም ሲጠበቅ ነው በማለት የአርባራቱ መንደር „ድምጻችን ይሰማ የእኛ ነው“ ብሎ ነበር ነፍሱን ለበለሃሰቦች አሳልፎ የሰጠው። የወልቃይት እና የጠገዴ ወረራ ብቻ ነው ለእኔ ለጎንደሬው ወይንም ለአማራ የሚመለከተው አላለም „ሉዕላዊነታችን ይከበር፤ ዳር ድንበራችን ይጠበቅ“ ብሎ ነበር የወጣው። ለነፃነት የሚደረጉ ትግሎች ሁሉ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ከሻብያ ጋር እያለካለከ ወደ እስር ቤት የሚግዛቸው ወገኖቹንም ስሜት ያ ገድለኛ የአማራ ተጋድሎ አብዮት በተደሞ አዳምጧል። „አሻባሪ የምትሏቸው የእኔም ወገኖቼ ናቸው“ በማለት ነበር „የሻብያ ተላላኪ ወያኔ እንጅ እኛ አይደለነም፤ ፍቅሩ ለእናንተ ነው የሚቀርበው“ ብሎ ነበር ፊት ለፊት ወጥቶ የትግራይ ሥርዎ መንግሥትን የሞገተው። ይህን የቅኔው መንደር ዝም ብሎ አላለፈውም፤ አነበበው፤ ተረጎመው እና አመሰጣረው ጎጃም ዋርካው። በደሙ ውስጥ አድምጦ ደም ገበረበት። በምልሰት በግርድፍ ሳይሆን ሂደቶችን ልቅም አድርጋችሁ አብሶ የአማራ ተጋድሎ ትጉሃን በውስጣችሁ አስቀምጧቸው። መንፈሱን እኔን ይምራኝ ብላችሁም ፍቀዱለት። ድንጋጌ ነው። አናም ተጋድሎው ምን እንደሚፈልግ ያመሳጥራላችኋል። የአቶ ለማ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ሳይሆን ያኦነግን መሥራች የአቦ ሌንጮ ለታ መንፈስ የገዛ ነበር ያ ተደሞ ህሊና ልቦና ላለው። ምላሹን በበለጸገ ሁኔታ ከአዳማ እስከ ሀረር በተደሞ ውስጡን ውስጥ አድርጎታል ብዙሃኑ – ከነተጋሩ በስተቀር።

በመሃል የጠቢቡ ቴወድሮስ ካሳሁን ኢትዮጵያን ከዓለም ፈጣሪነቷ ጋር በቅኔ ጠልፎ፤ በድጓ አስጊጦ፤ በጸመ ድጓ ወርቦ፤ በዜማ ቃኝቶ ሚስጢር አሰብሎበት – አስብኳል። ሁለት ስንኞችን ለይተን ብንመለከት ይህ ዓዋጅ እንኳንስ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ከዛም በላይ ረቂቅ መንፈስ ወላድ ቢሆን አይደንቀኝም። „የጀግኖች ሐገር ያዳም እግር አሻረ ፈለገ ግዮን ያንቺ ስም ሲጠራ እንኳን ሰማይ ላይ ባንዴራሽን አይቶ ስምሽ ሲጣራ፤ ኢትዮጵያ ሲባል ማን ዝም ይላል ከቶ“ „የፍጥረት በር ነሽ የክብ ዓለም መግቢያ ዙሮ መጀመሪያ።“ እንግዲህ „የጣና ኬኛ“ ዘመቻ መሰረቱ ተዋራራሽ ነው። የሥነ ልቦና አቅሙን ያገኘው ከፕሮፖጋንዳ ሸቀጥ ሳይሆን ከሰብሉ ዘር ነው። „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነውም“ ምንጩ ያ ነው። የሁሉም የወል መነሻ ምንጭ ደግሞ አለ ልክ እንደ ግዮን። „የፈራ ይመለስ“ ይህ ድንቅ መንፈስ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርን „ሰውን“ ማዕከሉ ባደረገው ትንታጉ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መርህ መሰረትነት ተነስቶ አቶ ሞላ አስገደሞን የሞገተው „የፈራ ይመለስ“ የ500 የጎንደር ወጣቶች ወላዊ የ2015 የአባ ታጠቅ ንቅናቄ ነበር። ይህ ነበር የጎንደር የአማራ ተጋድሎ አብዮት የመንፈስ ሃብቱ ሙሉ ምርት። ከዚህም ባለፈ በንዴት የጦፈው የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ የኢትዮጵያን ሱማሌዎች በኦሮሞ ማህበረሰብ ላይ ሲያነሳሳ፤ እና ግፍም ሲፈጽም እዛ የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ከግፈኞች ጋር አብረን አንቆም በማለት ማናቸውንም መስዋዕትነት አብረው ከፍለዋል። በዛው ሰሞናት በጎሬ፤ በመቱ፤ በከፋ አማራ ላይ ያነጣጠረው ጥቃትም ቂሙ የተቋጠረው በዚህ ምክንያት ነው። ያበደ ውሻ ነበር ያደረጋቸው። ከዛ ከጥፋት ማህበር ጋር መንፈሱን ያለዳበል ጽዱቅ የአማራ መንፈሳዊ ንጽህና ጋር የነበረው ቂም ወለድ ጥቃት ነበር። ግን መዳህኒተ ዓለም በጥበቡ ገመናውን ገለጠው። የተጋሩ አባላት ከነጉዳቸው ነበር በመቱ በጎሬ እጅ ከፍንጅ የተያዙት። ይህ ሁሉ እድንማርበት እንጂ የትም እንድንበትነው አይደለም አባታችን በዬቀናቱ አዎንታዊ መልዕክት የሚሰድልን። ስለሆነም ተያያዥ መንፈሶችን፤ ተወራራሽ ፍላጎቶችን፤ መደማመጦችን ከልብ ሆኖ መቀበል ያስፈልጋል። አንድ በፖለቲካ ህይወት ለመኖር የፈቀደ ጋዜጠኛ መልካሙ ነገር በአውንታዊ ነገሮች ላይ አቅምን ማፈስስ ነው ለፍሬ እንደሚያበቃው ማወቅ ያለበት። ለዘር የሚያበቃ ቅንነት ብቻ ነው።

„<a href=”http://www.satenaw.com/amhara-oromo-forum-debrebrehan-university/”>http://www.satenaw.com/amhara-oromo-forum-debrebrehan-university/</a>

Amhara Oromo Forum in Debrebrehan University

እንደ ታላቅ እህትነቴ በግልጽ ልገልጽልህ የምፈልገው ቁም ነገር „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርገው አማራውን ነው። ምክንያቱም የአማራ ፍዳ፤ መከራ፤ አሳር የሚመነጨው ኢትዮጵያን የእኔ ስላለ ብቻ ነው። መንፈሱን ለጣሊያን ባንዳነት እንደነታጋሩ ስላልሸለመ ነው። አማራ ለጣሊያን ባንዳዊ መንፈስ ለደቂቃ ለመስገዛት የማይፈቅድ ቁርጥ ያለ ሃሳብ እና አቋም ያለው፤ የጽናት ተምሳሌነት ነው። አማራ በማድረግ፤ በመፍጠር፤ በመፈላሰፍ አቅሙም አንቱ የሆነ ማህበረሰብ ነው። ይህን መንፈስ የቀድሞው ኦነግ፤ ሻብያ እና ወያኔ መቼውንም ቢሆን ሊሰሙት የማይፈልጉት ካንሰራቸው ነው። „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ለእኛ ደግሞ ትንሳኤያችን ነው። ኢትዮጵያን በጥርሳቸው ይዘው የሚቀኑባት ሁሉ መስማት አይፈልጉም ይህን ስንኝ። እኔ ደግሞ ቃለ ህይወቴ ነው።

ዛሬ ለመንፈሱ መጠለያ፤ መጠጊያ፤ ማደሪያ አልባ ለሆነው አማራ „አማራ ታስፈልገኛለህ፤ ወደ አንተ መጣሁ“ ሲባል ከደስታ በላይ ሐሤት ነው። ለእኔ ሁነኛ ነህ በማለት ያገለለው፤ የተጸዬፈው መንፈስ ሲመጣ አማራ ይህን አቅም መግፋት፤ መናቅ፤ ማጠውለግ አለበትን? አንተ ወይንስ እኔ ነን ኦሮምያ በሚባለው ክልል ያሉትን የአማራ ነፍሳት መታደግ የምንችለው ወይንስ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው?“ ለመሆኑ አማራው ከፈጠረው ከአምላኩ/ ከአላህ፤ ከእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም በስተቀር ማን አለው? የአማራ ሊሂቃን? ወይንስ ህብረ ብሄር የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚባሉት? ወይንሰ በአማራ ስም ከኢህአፓ ወደ አማራ ድርጅት ተቀዬርን የሚሉት ኤርትራዊው አቶ በረከት ስሞዖን፤ ጉራጌው አቶ ንጉሱ ጥላሁን ወይንስ ተጋሩው አቶ አለምነህ መኮነን? ከቶ ማን ነው አለው – ለአማራው በቅርብ። „ሰው“ ማዕከል አድርጌያለሁ የሚለው የሰብዕዊ መብት ተሟጋች እንኳን የአማራን ጥቃት ለመግለጽ አለተቻለውም። አማራ በተሸፈነ ወይንም በተጠቀለለ መርዝ ውሰጥ መንፈሱ ተቀብሮ እንዲቀር ነው የሚፈለገው። ቀልፍልፉ ይሄው ነው።

ባለፈው አንድ ጹሑፍ ጽፈህ አንብቤ ነበር። የጽጌ ፆም መፍቻ ቁስቋምን በጅማ አካበቢ ችግር እንዳለባቸው። ታነበው አታነበው አላውቅም ከሥር ጽፌልህ ነበር። ስለምን ይሄዳሉ? ከጎንደር ከ2009 በዕለ መስቀል ይመሩ ብዬ። ሰው ሰላም ከሌለው እንዴት ነው የቤተክርስትያን ሥርዓትን ሊፈጽም የሚችለው። ቤተክርስትያንስ እንዴት ነው ልትኖር የምትችለው? አዬህ ቅዳሴ ሲዳላ ነው። ቅዳሴ ሲመችህ ነው። ሳይመችህ ቤትህን መቅደስ አድርገህ ማሳለፍ ነው። ክፉ ጊዜ የሚያልፈው አደብ ገዝቶ በመሬትን ላይ በጥንቃቄ በመራመድ ነው። በዚህ ውስጥ ያለ አማራ በዬደረሰበት የሚጨፈጨፍ አማራ። ጭፍጨፋው ዜና እንዳይሆን የሚፈለግ አማራ። ተጋድሎው እራሱን ችሎ እንዳይወጣ የሚፈለግ አማራ። መደራጀቱ እንደ ጦር የሚፈራ አማራ በአስገዳዩ፤ በአስጨፍጫፊው፤ በአግላዩ በባህርዳሩ እንኮሸሽሌ በብአህዴን መድረክ ላይ ነው „ስለምናስፈልጋችሁ ብቻ ሳይሁን ስለምታስፈልጉን“ „ጣና ኬኛ! አማራ ኬኛ!“ ይህ የተጋድሎ እንብርት መሆን ካልቻለ ምን ሰማይ ላይ እንደምትጠብቁ በውነቱ አላውቅም። የጋረዳችሁ ነገር አለ። አዲስ መንፈሶችን አዲሶቹ ትውልዶች መቀበል ካልቻላችሁ ምን የሰማይ ቁርባን እንዲቀርብላችሁ ትሻላችሁ? እንደ ተመራማሪነትህ፤ እንደ የሥነ – ልቦና ባለሙያነትህ፤ „ሰውን“ ማዕከል እንደ አደረገ ጸሐፊነትህ እና ጋዜጠኝነትህ ይህን መንፈስ ማስጠጋት ወይንስ ማግለል? ሳንክ እየፈለጉ መፎካካር ወይንስ የውስጡን ሰላም መጠበቅ? ይህን ጤነኛ መንፈስ ማቀፍ ወይንስ ከፎቅ አውርዶ መፈጥፈጥ፤ ወይንስ አቅሙን ተጠራጣሪ ማድረግ፤ ወይንስ በአቅሙ ውሰጥ ጥግ ያጡ ነፍሶች ጥጋቸው ይሆን ዘንድ የተደራጀ፤ ተከታታይነት ያለው ተግባር መፈጸም የቱ ነው ለአንተ አቋራጭ መንገድህ? የቱ ነው የሚቀድምብህ? የቅንጦት የቦታ ምሪትና ፖለቲካ ወይንስ የህልውና ማስቀጠያ እራፊ ጊዜ? እኮ የቱ ነው ቅርብ ስሜትህ?

ለንጽጽር ያወጣኸው መቼ ነው የአማራ በሚባለው ክልል የአማራ ሆኖ የሚያወቅ ከ50 ሺህ በላይ የወልቃይት የጠገዴ የአርማጭሆ መሬት ላይ ስለምን ይመስልሃል የትግራይ ሰዎች እንዲሰፍሩበት የተደረገው? የሰሞናቱ የግጨውስ ጉዳይ? ለዛውም በትጥቅ ትግል ህይወታቸው በተመክሮ የኖሩ ናቸው የሰፈሩበት? በመግደል በአራዊትነት የሰለጠኑ – የተጋሩ አውሬዎች። በሴራ በሳጥናኤልነት የተመረቁ – ጫካዎች። ስለምን ይመሰልሃል መተከል ለቤንሻጉል ጉምዝ የተፈጠረው? የትኛው የአማራ ባለሃብት ነው አቅሙን ጉልበቱን አማራ በሚባለው መሬት ጎልብቶ እንዲወጣ የሚፈቀድለት? ለትግራዮች በሚያመች መልኩ ነው ጥሪው መተላለፍ የነበረበት። ምክንያቱም ከላይ አስከታች አማራን በጠላትነት የፈረጁት ነው ቦታውን ሁሉ የወረሩት። እውቅና ለራሳቸው ለዘራቸው መስጠት አለባቸው። ኢትዮጵያ በብሄራዊ ደረጃ በጸጥታው፤ በኢኮኖሚው፤ በማህበራዊው፤ በድህነንቱ የትግራይ ሥርዕወ መንግሥት ነው የገነነው። ብሄራዊ አይደለም። አይደለም ኢትዮጵያዊ መሬት ላይ በአህጉራዊ ሆነ በዓለም አቀፍ ክፍት የሥራ ቦታዎች ብሄራዊ አይደለም – ምደባው። ሥርዕወ – ትግራይ ነው በአፍሪካ አህጉራዊ ድርጅቶች ሆኖ ኢትዮጵያን አሳታፊ ባደረጉ ዓለምዐቀፍ ሁነቶች ሁሉ ያው ነው፤ የትግራይ ሥረዎ መንግሥት ነው ያለው። ብሄራዊ መንፈስ ያለው እንዲሆን የሚፈለገው አማራው ክልል ብቻ ነው። ስለምን የታላቋ ትግራይ ህልም በአማራ መቃብር ላይ መሆን ስላለበት። ተወልጀው በተወለደበት ቀዩ የባለቤትነት ስሜቱን ለመግደል።

የሁለም የተጋድሎ መንፈስ እኩል አቅም አለው። ነገር ግን የፖለቲካ ሊቃናት፤ ሚዲያዎች ቃለ – ምልልስ ሲያድረጉ ግን የኦሮሞ ተጋድሎ ብቻ ነው ጎልቶ እንዲወጣ የሚደረገው። የሚፈለገው። አማራው የተጋድሎ ታሪኩን እንኳን ቅስሙን እንዲሰበር፤ ተቅብሮ እንዲቀር በትጋት እዬተሠራበት ነው። በውጭም በሀገር / ውስጥም፤ በሚታይም / በማይታይም የክስተት አምክንዮ ትግሉ ያነጣጠረው በአማራ የህልውና ተጋድሎ ላይ ነው። የወያኔ ሃርነት ትግራይ የሚ/ር ማዕረጉን ሹመቱን በ2009 ሲያነቆጠቁጠው 9ኙ ከኦሮሞ ነበር። የአማራ ሊቃናት ደግሞ ይህ በደል፤ ይህ ቅበር እርምጃ፤ ይህ መገለል ቸል ብላችሁ ተኙ እያሉ ይሰብካሉ እንደ ዶር. ተስፋዬ ደመላሽ ዓይነቶች። አማራውን አማራው እራሱ እዬጨቆነው፤ አማራውን እራሱ አማራውን ቅስሙን እዬገደለ፤ አማራውን እራሱ አማራው እያሳደደው እያስገለለው ነው ያለው። በዚህ ውስጥ ነው „ኢትዮያዊነት ሱስ ነው“ ሊታይ፣ ሊመረመር የሚገባው። አዬህ አንድ ዕጣ ነፍስ ኦሮምያ ክልል ጥግ፤ የህግ ከለለ ካገኘ ለእኔ ትርፍ / የሰማይ ጽድቅም የምለው ይሄው ነው። ቤት – ቦታ – የቅንጥ – የቅንጦት ነው። ለሞቴ ኬክ ቁረሱልኝም ነው። መጀመሪያ „ሰው“ ናችሁ እናንተም እንደ እኛ አለን የምትሉት ወገን ክልል እንዳላችሁ ተመልክተናል፤ የአማራ ህዝብ ፍቅር ስለመሆኑ አስተውለናል። እስከዛሬ የተጓዝንበት መንገድ ትክክል አይደለም። እንዲያውም ይህን ሥርዓት ለማምጣት ሰፊውን መስዋዕትነት የከፈለው አማራ ሆኖ ሳለ ሚዳያቸው ስለምን ዝም አለ እያሉ ነው ነው አሁን የኦሮሞ ሙሁራኑ። ይህ የመንፈስ ልዕልና አብዮት እኛ የሠራነው ሳይሆን ሰማይ ቤት በማይመረመር ጥበቡ የፈጸመው ነው። እኛማ ገና አዛኝ መንፈስ ብቅ ሲል ቅንጡን ነው የምናበረው። ቅንነት የሚከፈልበት ሆኖ። „<a href=”https://www.youtube.com/watch?v=xrUhwyeK0J8″>https://www.youtube.com/watch?v=xrUhwyeK0J8</a>

የምሁራን ውይይት ስለ አማራ እና ኦሮሞ ህዝቦች ግንኙነት-በአማራ ቴሌቪዥን“

የሁለቱን ማህበረሰቦች እትብታዊ መንፈሱ ዘመናት አይሽረውም። አሁን እነሱ ገብቷቸዋል። የዓጼ ሱስንዮስ አጽመ ርስት ጣና ገዳም ያረፈ ስለመሆኑ፤ የንግሥና ባዕታቸውም ጎንደር መሆኑ እስከ ልጅ ልጆቻቻው እና ሥነ – ልቦናቸው ከምድር በላይ ብቻ ሳይሆን ከምድርም በታች ትውፊቱ በደም ተገምዶ፤ በዘር አስብሎ ህያዊነቱን እና ተፈጥራዊነቱን ተመሰጥውበታል። በነገራችን ላይ የኔታ ሙሉነህ ዮሖንስ አንድ ጹሑፉ ላይ „የኦሮሞ መሬት“ ሲል በትርጉም አቃንቶ በጥንቃቄ የጻፈው ነበር። አዎን ኦሮሞ ጎንደር ላይ ባለርስት ነው። ምን አልባት ጎንደር ላለ ሰው ጠንቃቀው የኔታ ሙሉነህ ዮሖንስ በጻፈው መልክ ቃሉ ላይገባው ይቻላል። እሱ ግን የንትርክ አንባ እንዳይሆን በማለት፤ የወገኖቹ መንፈሳቸው፣ ስሜታቸውን የሚገርፍ እንዳይሆን እንደ አንድ ዕድሜ ሙሉ ጎልማሳ ነበር በማስተዋል የጻፈው። ስለምን? ደስ በሚያሰኛቸው አገላለጽ፤ ጥሩን ባሉት እንጥራቸውም በሚል ከወጣት የማይታሰብ ዕድሜ ጠገብ ትህትና እና አክብሮት በተሞለበት ነበር የጸፈው። ቢያንስ በዘመናት ውስጥ ሽግግሩ በመንፈስ ዝንባሌውም እርሸው አለ።

በለፈው ሰሞን የኔታ አያሌው መንበሩ የጻፈው ነገር ነበር። የኦሮሞ የባህል ማዕከል ባህርዳር ላይ የመሬት የመረካከብ ጉዳይ የከፋው ይመስላል። አንድ ሰው ጋብቻ ሲፈጽም የሚሰጠው እና የሚቀበለው ተቻችሎ የሚያኖረው ጥበብ አለው። የውስጥ ሃዲዱ መቻቻል ነው። ይህ ለ27 ዓመት ተስብሯል። ይህን በአዲስ መንፈስ መስምር ማስያዝ የሚቻለው መተዋወቅ፤ መቀራረብ ሲቻል ብቻ ነው። ውስጠን ስትፈቅድ። ለዛም ይህን መሰል መሬት የያዘ ተግባር ሲከውን ነው። መወሰን ነው ፍቅርን ጋብቻ የሚያደርገው። መፍቀድ ነው ጋብቻን የህብረተሰብ መሰረት የሚያደርገው። ትውልድን የሚፈጥረው። አሁን ይህ ይበል የሚያሰኝ ነገር ነው። የወያኔ ሃርነት ትግራይ ስንት መሬት ነው ለታላቋ ትግሬ ከአማራ መሬት ላይ በግፍ፤ በጭካኔና በወረራ የወሰደው? እንኳንስ መንፈስን በአዎንታዊነት በፈቃድ የሚያለማ ተቋም ቀርቶ። ምን ያህል ጋሻ መሬትስ ነው ማዕከሉ የሚፈልገው? ባህል የነፍስ የአውቀት ተቋም ነው። ይልቁን እዛ ያሉ የአማራ ቤተሰቦች የሚያስፈልጋቸው እጅግ በርካታ የመንፈስ ጥበቃ አለ። ለዛ እንትጋ። ፍቅር ሳይሰጥ ፍቅር መቀበል አይቻልም። ፍቅርን የቅድመ ሁኔታ ህግ አይገዛውም። አብሮ መኖርንም የቅድመ ሁኔታ ዶግማ አያስተዳድረውም። መፈቃቀድ ድርጊትን ማብቀል አለበት። በማብቀል ውስጥ ነው ፍቅርን ለልጅ ልጅ የሚበቃው። እናንተ በቀለም ዕውቀት ትብልጡኛለችሁ። እኔ ደግሞ በዕድሜም፤ በፖለቲካ ህይወት ተመክሮም ከእናንተ ብብልጫ ባልሄድም እሻላለሁ። ስለሆነም እንደ አማራ ባህል እታለም እምትናገረውን ከልብ ሆናችሁ አዳምጡ። ፈጽሙም – ትእዛዝ ግን አይደለም።

ከአቅም ብክነት ጋር ፍቅር በፍቅር አትሁኑ፤ አትወዳጁ።

አቅም አታባክኑ። አቅም ባላበት ቦታ ሁሉ አንቴናችሁን ዘርጉ። አቅም ባላበት ቦታ ሁሉ የንባችሁ ጉዞ የአቅምን አበባ ማዕዛ እንድትቀስም ፍቀዱላት። ወያኔ የሚፈልገው እና የማይፈልገውን፤ የአማራ ተጠቂ መንፈስ ጥግ ማግኘት፤ የሚፈለግውን የማይፈልገውን መንፈስ በውል ጊዜ ወስዳችሁ አጥኑት። ቁጭ ብላችሁ ጊዜ ሰጥታቸውሁ አስቡት። አስቡት። አስቡት። ማሰብ ጊዜ ይፈልጋል። ጊዜውን ከመከራው ጋር አድምጡትም። ወጣትነታችሁ የሚያስገድዳችሁን ስሜታዊነትን ቆዬኝ ብላችሁ ስክነትን ለተጋድሏችሁ አውሉ – አሁንም ትዕዛዝ አይደለም፤ አስተያዬት እንጂ። ስሜታዊነት ሆነ ግብታዊ አትሁኑ እንደ ማለት። ከሁሉ በላይ ከጀግና ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጽናትን ተማሩ። በጥቂት ጹሑፎች የሽልማት ዓለም ዐቀፍ ድርብድርብ ተቀባይነት ማግኘት አስተውላለሁ። በሌሎቹ ዘንድ ዕውና እና ክብር ተገኝቷል። ሰው ስላላቸው። ጋዜጠኛ ተመስገን ግን ወ/ሮ ፋናዬ ደሳለኝ መንፈስ ደስ እንዲላት እንኳን ለሽልማት መቅረቡ ቀርቶበት አንድም ቀን የዓመቱ ታላቅ ሰው ሳይባል ነው ከእስር ቤት የወጣው። ግን እሱ ወጣትነቱን ለበለሃሳቦች አሳልፎ የሰጠ፤ ጤናውን ለኢትዮጵያዊነት መስዋዕት የሰጠ ታላቅ ሰው ነው። እንደ እሱ ጠቃሚው እና የማይጠቅመውን ለመለየት ድፈሩ። ግን በጥበብ፤ በብልህንት እንዲሆን መንገዳችሁን ፍቀዱለት።

በምንም መልኩ ቢሆን ቅንነትን የሰነቀ፤ ከጥላቻ ወደ ፍቅር የሚያመጣ መንፈስን ተቃራኒ፤ ተጠራጣሪ ሆኖ መቅረብ የተገባ አይደለም። ያለፈውን የባህርዳር የፍቅር ሰሞናት በሆነ ባልሆን መመልምል፤ መልምሎም ማድረቅ ለአማራ ህልውና ከሚታገል መንፈስ የሚጠበቅ አይደለም። ሌሎች ያድርጉት፤ እኛ ግን ተባባሪ መሆን አያስፈልግም – ለሳንክ ቁፋሮ። ጠንቃቃነት ያተርፋል እንጂ አያከስርም። የትኛው መንፈስ ነው አቅም ያለው ሰው ለግለግ ብሎ፤ ተደማጭ ሆኖ በልጦ እንዲወጣ የሚፈለገው። አፈር ላይ ትቢያ ላለነው እንኳን አይፈቀደም እንኳንስ ላይ ላሉት። እኔ እኮ በስንት የሞት የሽረት ትግል ነው አሁን አባ ቅንዬ ሳተናው ጹሑፌን እያወጣልኝ ያለው። እንግዲህ የእኔም ብዕር ተፈርቶ ማለት ነው። ሃቅም፤ ዕውነትም፤ ነጻ መንፈስም፤ የሚፈራበት ዶክተሬኑ የሶሻሊዝም የህብረተሰባዊነት የሴራው ውቅያኖስ የግራው ፖለቲካ ነው። አዲሱ ትውልድ ውርሱን መጸየፍ አለበት። የኔታ አያሌው መንበር አንደ አማራ ልንጸዬፈው ይገባል ትል የለ። አዎን ከእናንተ መጀመር አለበት። ቅን መንፈሶችን መንከባከብ አለባችሁ እንደ አማራ የፍቅር ሰውነት። በቅን መንፈሶች ጋላሪ ውስጥ ለመክተም መፍቀድን የሚያሳጣ አንዳችም ነገር የለም፤ ከቲፎዞ ብዛት ከማጣት በስተቀር። ቲፎዞ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ደግሞ ጤዛ ነው። ቲፎዞነት ፈጣሪ የሰጠውን የማስተዋል ጸጋ፤ ሚዛናዊነትን፤ ዕውነት ፈላጊነትን ድርቅ የሚያስመታ ከተፈጥሮ ጋር የተጣላ ግልብ ስንቅ ነው። የሚታጡ ነገሮችን ፈቅዶ ግን አትራፊ ነገሮች ላይ አትኩረት እና አክበሮት መስጠትን አድምጡት። ሁኑበት። ህይወቱን ለመኖር ፍቀዱት፤ ውደዱት። ቅንነት ጸጋ ነው። ጸጸት አይመትራችሁም ቅኖች ከሆናችሁ። ፈጣሪም/ አላህን አይከፋም። ድንግልም ሐሤት ታደርጋለች።

ለቅኖች።

ሌላው የሄሮድስ መለስ ዜናዊ የሙት መንፈስ ያደናበረው ሃይልም እዬሠራው ያለው ነገር አለ። „አብሮነታች“ ይህም „አማራ እና ኦሮሞ እሳትና ጭድ ነው“ „አማራን እና ኦርቶዶክስን እንዳይነሳ አድርገን ምሰን ቀብረነዋል ወዘተ ወዘተ“ የት ሄደ እና ነው አሁን የወያኔ ሃርነት ትግራይ „ የአብሮነት ልሳን“ የኖኽ መረከብ እኔ ነኝ እያለ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው? ሊታገለው የፈለገው አንድ አቅም አለ። የአማራ እና የኦሮሞ የመንፈስ ትስስር፤ ውይይት፤ መደማመጥ፤ መግባባት። ይህ ለኢትዮጵያም የመዳኛዋ ዋዜማ ነው። እራሱ የትግራይ ሥርዎ መንግሥት በሰሞናቱ ንግግሮች ላይ ተዘውትሮ „እኛ ኢትዮጵውያን“ የሚሉ ሃይለ ቃሎች ጎልተው እዬወጡ ነው። መሬት ላይ ያለው እውነት ግን ይህ አይደለም። የአማራና የኦሮሞ የመግባባት ሂደቶች ከተጀመሩበት ዕለት ጀምሮ ያሉ ሁለገብ ያላባራ የሰው ልጅ የጥፋት መስኮች ምንያህል እንደሆነ ቅኖች መመዘን ያለባቸው ይመስለኛል። ስለዚህ አቅምን ሰብስቦ አቅም በታኙን በመንፈስ መታገል ዓራት ዓይናማ መንገዳችን ሊሆን ይገባል።

አሁንም አቅሙ ኑሮት፤ አዲስ ሃሳብ፤ አዲስ መንፈስ፤ አዲስ ራዕይ፤ አዲስ ተነሳሽነት፤ ተቆርቋሪ ችግርን የሚያደምጥ ቢያንስ በራሱ ህሊና ውስጥ ለመናገር፤ ለመጻፍ፤ ለማንበብ፤ ለመተቸት ፈቃድ ሰጥቶ ነፃነት ለሚያውጅ ኢትዮጵያዊ ቅኖች፤ ልቦናቸውን ለቅንነት መሸለም አለባቸው ብዬ አምናለሁ። ልቦናቸውን ውስጣቸውን መስጠት ብቻ ሳይሆን አቅሞችን የሚቀናቀኑ ትክ … ትኮችንት በእንጭጩ እዬቀጩ ፈውስ ለመሆን መትጋት ያስፈልጋል። ወጣቱ ለቅንነት ቅርብ ያለሆነ ማን ይሁን?

ልቦና።

አዬህ እናትዬ ከአንተ በፊት አንድ ሰው በአቶ ለማ መገርሳ ዙሪያ አንድ የቪዲዮ ክሊፕ ለቆ ነበር። ያ ድምጽ እስልምና ሞት፤ እና የእድሜ ልክ እስራት ሲፈረድብት አልነበረም። አሁን ግን እኔ አለሁኝ ብሎ ተነሳ ። ቪዲዮው ላይ ለማመሳካሪያነት ያቀረበው የስብዕዊ መብት ተሟጋቾችን ቀልብ ለመሳብ ለሃይማኖቱ አርበኛ የሆነውን አህመዲ ጀብልን ፎቶ አያይዞ ነበር ያቀረበው። ይህ ማለት „ኢትኦጵያዊነት ሱስ ነው“ „ለድምጻችን ይሰማ ቤተሰቦች“ ባዕድ ከሆነ፤ ለድምጻችን ይሰማ ትጉሃን ያለንን አክብሮት እንድንሸረሽር ታስቦ ሲሆን፤ መንፈሱ ለእኛ ለ እስልምና አማንያን ዕድ ነው ዓይነት ነው። በሌላ በኩልም „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ዙሪያ መንፈሳቸው የተሰባሰበውን ቅን የእስልማ እምነት ተከታዮች መንፈስ ለመተርተር ታስቦ ነበር – አባ አዋጉ። ነገር ግን እግዚአብሄር ይስጠው እና ሳተናው ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህምድ ከኢትዮጵያ ያሉ መንፈሶችን በስልክ በቀጥታ ደውሎ እያነጋገረ ዕውነታውን መሰረት አስያዘው። እንዲያውም የሄሮድስ መለስ ዜናዊን ፎቶ ሰው እዬገነጠለ „ኢትዮጵያዊነት መንፈስን ነውን“ ከፍ እንዳደረገ ነበር ቃለ ምልልስ አድራጊዎች የገለጹት። በውነቱ ጋዜጠኛ ሳዲቅ የወሰደው እርምጃ እጅግ የሚያረካ ነበር። ይህ ሁሉ ለተስተካከለ ፍትሃዊ ሥርዓት የሚበጅ አልነበረም ሰውዬው የሠራው። አቅም ከዬትም ይምጣ፤ በዬትኛውም ሁኔታ ይቅረብ እንደ አቅምነቱ ከቀደመው አቅም ጋር ቤተኛ መሆን አለበት። ዕውን እስልማናም ነፃነትን ያልም ከሆነ። መዳኛ ስለምን ይሆን እንዲህ ቅድመ ሁኔታ የሚበዛብት? ይገርማል።

ክወና

ባተሌው ታናሼ የእኔ ሙለቀን ተስፋው የትኛውም የግራ ፖለቲካ ሊሂቅ ከእግዚአብሄር ወይንም በድንገተኛ አደጋ በሞት ካልተለዬ ሥልጣን መልቀቅ ባህላቸው አይደለም። ፊልም ላይ አክተር አይሞትም። የግራ ፖለቲካ አክተሮችም ከሞት በስተቀር ከሥልጣን ምኞት ጋር አይፋቱም። ለዚህ ነው ሁሉንም ቅን ሃሳብ የሚተናኮሉት፤ የሚያወግዙትም። አሁን በኢህአፓ ስንት ወጣት በተጋድሎው አለቀ ግን የኢህአፓ መሪ አቶ መርሻ ዮሴፍ አሉ፤ የኦነግ ማንፌስቶም ባላበራ ሁኔታ አሁንም የኦሮሞ ልጅ ይሞታል፤ ይታሰራል ይሰደዳል፤ የ ኦሮሞ እናትም እዬወለደች ስንቅ አቅራቢ ናት። አሁን አቦ አቦ ሌንጮ ለታ የአገር አድን ተባባሪ መሪ ናቸው። ሥልጣን ይፈልጋሉ፤ የታላቋ ትግራይ ሥር ዕዎ መንግሰት የቀድሞው ጠ/ሚር ሄሮድስ መለስ ዜናዊውም በእግዚአብሄር ሞት ባይሄዱ የቤተሰብ ማህበር ያደርጉት ነበር ሥልጣኑን። የሻብያው ፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂ ይሄው እንደ ተደላደሉ ነው ከዘውዱ ጋር ሙጭጭ ብለው። በሶሻሊዝም ዋናውን ካራክትር የሚጫወቱት አክተሮች ኑ እስኪላቸው ደርስ ስልጣናቸውን ለሌላ አያካፍሉም፤ በማን ደም? በምስኪኑ፤ በደሃው ደም መስዋዕትነትን፤ በፕሮፖጋንዳ አዝማችነት የሥልጣን ህልም የእድሜ ልክ ነው። ሌሎች ሐገሮችም እንዲሁ ነው። በኪዮባ፤ በግማሿዋ ኮሪያ፤ በቻይን በራሽያ አንባገነንነት፤ ሥልጣን አንድ ላይ መማከል መለያ ምልክታቸው ነው የሶሻሊስት ርዕዮት አራማጆች።

ይሄም ብቻ አይደለም። ጥክክሎች፤ ፍትሃዊዎች፤ ዲሞክራቶችም እነሱ ብቻ ናቸው። ከ እኛ ወዲያ ላሳር ባዮች ናቸው። እኛ ነን የመፍትሄ መሠረቶች፤ የራዕይ መንገዶች ብለው ስለሚያምኑ ምንም አዲስ ሃሳብ የማስተናገድ የአምክንዮ አቅም የላቸውም። ማፍለቅም አይችሉም የዘመኑ ባህሪ አልፏቸው ጥሏቸው ሄዷል። ደርግም ለዘር ሳይበቃ በዚህ ግትርነቱ ነው ተበትኖ የቀረው።

ስለሆነም ይህን የሚጻረር መንፈስ ሁለ ያለ ርህራሄ በተገኘው መንገድ በወበራ ያጭዱታል፤ ይቀናቀኑታል።

ሰብዐዊነት የለም ተፈጥሯዊነት የለም። በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ያልሆነ ያፈነገጠ መንፈስ ደግሞ ብቅ ካለ ያልተስማሙት ጊዜያዊ ስምምነት ያደርጉ እና አቅሙ አፈር አስኪቀምስ፤ ግብዕተ መሬቱ እስኪጠነቀቅ በግራ በቀኙ ዱላ ነው። የአማራን ተጋድሎ የገጠመው ፈተና ይሄ ነበር። የነፃነት ራዕይ አለን የሚሉት፤ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ የሚጸዬፉት፤ የኢህአፓው ዝንጣፊ ብአዴን ሊሂቃን የወልዮሽ ህልማቸው የሥልጣን ዘላለማዊነት ነው። ቢግባቡ ግን 40 ዓመት 8/8 ዓመት እንኳን ቢፈቃቀዱት፤ በፈረቃ ሥልጣኑን መያዝ ይችሉ ነበር። ትውልድም በዬዘመኑ እንዲህ አይመተርም ነበር። ኢትዮጵያም የእልቂት አንባ አትሆንም ነበር። አድጋ ከፍ ብላ ትታይ ነበር።

ስለሆነም ታታሪ የነጻነት ፈርጦች፤ ወጣቶች በይዘት ከእነሱ በተለዬ ሁኔታ ዘመናችሁ በፈቀደው ዘመናዊነት እና ሥልጣኔ የመለወጥን ጉዳይ በመንፈስ ውስጥ ለውስጥ የመደራጀት/ የማደራጀትም ሃላፊነት አለባችሁ። ግራ ፖለቲካ ለትውልድ ግራ ነው። መንገዱ ሴራ እና ምቀኝነት፤ ቅናት ብቻ ነው። ገደል ነው። ቋያ ነው ዙሪያ ገባው። ስለዚህም ምርጫችሁ ሊሆን አይገባም።

በተረፈ ከሰነበትኩኝ ዛሬ የጻፍከት ዘሃውን ነው። ፈትሉን ደግሞ በቀጣይ ስለምመለሰብት ከልብህ ሆነህ እንድታዳምጠው አደራዬ የምር ነው። አዬህ እናቱ መንፈስ ቅዱስ የቀረበው ሰው ከተጋፋ ህዝብ ጎን ቆሞ ፍቅሩን የሚገልጽበት ቅኔያዊ ጎዳናው የተለዬ ነው። ይህን በማስተዋል ሁነህ ትምረመረው ዘንድ፤ በቀጣይ ጹሑፌ ታዳሚ ትሆንም ዘንድ በትሁት መንፈስ አሳስብሃለሁ። ሰው ሰውን የሚለካበት የራሱ የሆነ ቀለም፤ ሚዛን አለው። እኔ ያን ንጽንህናን ያዬሁበት፤ የተረጎምኩበት መንገድ ምን አልባት እንደ ተፈጥሮዬ ወጣ ያለ ሊሆን ይቻላል። ብቻ አማክልልህ መጨመሪያ አለኝ – በቀጠሮ። እርግጥ ጽፌ ካስቀመጥኩት ከወር በላይ ነው። ቢሰነብትም ዕሴቱ አይቀንስም።

ከአክባሪህ እና ከምትሳሳልህ ታላቅ እህትህ።

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር።

እግዚአብሄር ይስጥልኝ። ጥንካሬውን፣ ብርታቱን፣ ጽናቱን፣ መጽናንቱን ለሁላችን ይስጠን አምላካችን። አሜን።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.