ትራምፕ የኦባማን ላይብረሪ መጸዳጃ ቤት ለማጽዳት እንኳን ብቁ አይደሉም ተባለ

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 4/2010)

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኦባማን ላይብረሪ መጸዳጃ ቤት ለማጽዳት እንኳን ብቁ አይደሉም ሲል በአሜሪካ የሚታተም አንድ ታዋቂ ዕለታዊ ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ አሰፈረ።

ዩ ኤስ ኤ ቱደይ የተሰኘው ይህ ጋዜጣ ጠንከር ያለ ትችት በመሰንዘር የሚታወቅ ጋዜጣ ባይሆንም ትላንት ማክሰኞ ይዞ የወጣው ርዕሰ አንቀጽ ግን በአሜሪካ በሚገኙ ሌሎች መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኗል።

የጉዳዩ መነሻ የሆነው የፕሬዝዳንት ትራምፕ ትላንት በቲውተር ገጻቸው ያሰፈሩት ጽሁፍ ነው።

ትራምፕ በገጻቸው የኒዮርክ ሴናተር የሆኑትን ክርሲት ጂሊብራንድ ለምርጫ ዘመቻ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የማያደርጉት ነገር የለም፣ ግለሰቧ የምትጠየቀውን ሁሉ ለመፈጸም ወደ ኋላ አትልም በማለታቸው ነው።

ይህ አስተያየት ግለሰቧን በሴትነቷ የሰደበ በመሆኑ ፕሬዝዳንቱ ሊወገዙ ይገባል ሲል ጋዜጣው ጠንከር ያለ አቋም ይዟል።

ጋዜጣው በርዕሰ አንቀጹ ፕሬዝዳንቱ ሴናተር ጂሊብራንድን ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ የጾታ ግንኙነት ከመፈጸም ወደ ኋላ አትልም የሚል ትርጉም የያዘ ነገር መናገራቸው ለያዙት ቦታ ብቁ አለመሆናቸውን ያሳያል ብሏል።

ጋዜጣው ሲቀጥልም ፕሬዝዳንቱ በየጊዜው በቲውተር ገጻቸው የሚለቁት እጅግ የወረደና የሰዎችን ክብር የሚነካ ንግግር ማቆሚያ የሌለው እየሆነ መቷል ብሏል።

እንዲህ አይነት የሰውን ክብር የሚነካ ንግግር የሚናገሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የባራክ ኦባማን የላይብረሪ መጸዳጃ ቤት ለማጽዳት ወይንም የጆርጅ ቡሽን ጫማ ለመጥረግ ብቁ አይደሉም ብሏል።

ጋዜጣው ሲቀጥልም በኦባማና በቡሽ ላይ ያለው የፖሊሲ ልዩነት እንደተጠበቀ ነው ብሏል።

ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች በብዙ መንገድ የገቡትን ቃል አልጠበቁም።ነገር ግን የጨዋነታቸው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ አያውቅም ብሏል።

በአሜሪካ የሕዝብ ተመራጮችና ታዋቂ ጋዜጠኞች በሴቶች ላይ የፈጸሙት ጾታዊ ትንኮሳና መድፈር በሰሞኑ ሲጋለጥ ተመራጮቹ ወንበራቸውን እንዲለቁ ጋዜጠኞቹም ከስራቸው እንዲሰናበቱ ምክንያት ሆኗል።

ይህ ክስተትም ባለፈው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት በርካታ ሴቶች በፕሬዝዳንት ትራምፕ ጥቃት ተፈጽሞብናል ብለው ያቀረቡት አቤቱታ እንደገና መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል።

ሌሎቹ ተጠያቂ ከሆኑ ፕሬዝዳንቱም ሊጠየቁ ይገባል ባይ ናቸው የፕሬዝዳንቱ ተቃዋሚዎች።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.