የቋሚ ሽፍቶቹ ስርአት እና ከዳር እስከ ዳር የተቀጣጠለው ህዝባዊው ተቋውሞ (ኤድመን ተስፋዬ)

ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ህዝባዊነት ሽው ያላለበት ህወሀት ኢህአዴግ ከምስራቅ እስከ ሰሜን የተነሳውን ህዝባዊ ቁጣ እንደለመደው በጠብመንጃ አፈሙዝ ለመመለስ እየተሯሯጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ በፊት በሀገራችን ከታዩት ህዝባዊ ቁጣዎች በተለየ አሁን ላይ ከሀገራችን ሰማይ ስር የተቀጣጠለው ህዝባዊ ቁጣ የህወሀት ኢህአዴግ የሀያ ሰባት አመት የግፍ፣የዘረኝነት እና የሽፍታነት አገዛዝ የወለደው ከመሆኑም በላይ ሀገራዊው ተቋውሞ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ አንባገነኑን እና ዘረኛውን ህወሀት-ኢህአዴግ ማስወገድ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው፡፡

ከበረሀው ትግል ጀምሮ ህዝባዊ ባንኮችን በመዝረፍ የሚታወቀው ህወሀት-ኢህአዴግ ስልጣን ይዞ ታላቋን ኢትዮጲያ ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የስርአቱ መገለጫ ከሆኑት ውስጥ ከአናቱ እስከ ጥፍሩ በመንግስታዊ በሌብነት መነከር እና በህዝብ ዘንድ አመኔታ ማጣት ነው፡፡  ለመንግስታዊ ሌብነት ሲባል ብቻ ህዝብን ከቀየው ማፈናቀል፣ ህዝብን እና የሀገር መሬትን መቸብቸብ፣ በሀገር ሀብት እና ንብረት መነገድ እና ለግለሰብ አገልግሎት ማዋል  በስርአቱ የተለመዱ ሆነዋል፡፡ ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት በህዝብ የጋራ እንቅስቃሴ የሚመጣ መሆኑን ያስተዋለ ሰው ህወሀት-ኢህአዴግ ህዝብን እያጉላላ ፣ህዝብን እያስለቀሰ ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት አመጣው ማለቱን ሲሰማ የህወሀት ኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ ቢያስቀው የሚገርም አይመስለኝም፡፡

በዘመነ ህወሀት-ኢህአዴግ ከታዩት መንግስታዊ ቅሌቶች ውስጥ አንዱ ለልማት በሚል የዳቦ ስም ህዝብን ከቀየው ማፈናቀል ነው፡፡ አንድን ሉአላዊት ሀገር የሚመራ መንግስት ከሚጠበቅበት ግዴታ ውስጥ የህዝብን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር በማስጠበቅ እና በማጎልበት በሀገሪቷ ላይ የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊ ስርአት መፍጠር አንዱ ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካት ደግሞ ቀጣይነት እና ዘላቂነት ያለው የተቀናጀ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፓሊሲ መንደፍ ተገቢ ነው፡፡ ህወሀት-ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት እለት ጀምሮ የህዝቡን ማህበረሰባዊ እሴቶች በመናድ ህወሀት-ኢህአዴግአዊ እሴቶችን በህዝቡ ላይ ለመጫኑ ብዙ ማመላከቻዎች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ ለዘመናት በአንድ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማፈናቀል እና የነሱን ይዞታ ለልማት በሚል የዳቦ ስም በአንድ የፓለቲካ አስተሳሰብ ለተቃኙ ጥቂት ግለሰቦች ማከፋፋል አንዱ ነው፡፡ ይህ የፓርቲው አካሄድ በእኔ እምነት አሁን ላይ ለታየው ህዝባዊ ቁጣ መንስኤ  ከመሆን ባለፈ እና ፓርቲውን ወደመቃብር ከመክተት ባለፈ ለሀገሪቷም ሆነ ለህብረተሰቡ የሚፈይደው ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ህዝብ ያላመነበት፣ያልመከረበት እና በህዝብ ተቀባይነት ያላገኘ ልማት መጀመሪያውኑ ለሀገርም ሆነ ለህዝብ የመጥቀሙ ነገር ጥያቄ ምልክት ውስጥ የወደቀ በመሆኑ ነው፡፡

ኢኮኖሚያዊ ልማት ማለት ቁሳዊ ብቻ ሳይሆን ሰዋዊውም ጭምር ነው ፡፡ የሰውአዊ ልማት መገለጫው ደግሞ የግለሰብንም ሆነ የማህበረሰብን ሰዋዊ መብት በማክበር እና በማስከበር ግለሰብንም ሆነ ህብረተሰብን ለምርታማነት በማዘጋጀት እና አምራች በማድረግ ሀገራዊ ኢኮኖሚን ማሳደግ ነው፡፡ በእኔ እምነት ህወሀት-ኢህአዴግ ከየትኛዎችም የቀድሞ የሀገራችን መንግስታት በተለየ መልኩ ሰውአዊ ልማትን የረገጠ መንግስት ብቻ ሳይሆን ለሰውአዊ ልማት ትኩረት ሳይሰጥ ኢኮኖሚውን በተከታታይ አሳደኩት በማለት በድፍረት የሚናገር መንግስት ነው፡፡ እንዴት እና በምን መልኩ ነው ቤቱን አፍርሰህ አውላላ ሜዳ ላይ የጣልከውን ህዝብ ለልማት የምታነሳሳው ?   እንዴትስ ነው በማዳበሪያ እዳ ናላውን ያዞርከውን አርሶ አደር አስተባብረህ ህዝቡን የሚቀልብ ብሎም ለውጪ ምንዛሬ አምጪ የሚሆን የግብርና ምርት እንዲያመርት የምታደርገው ? ከወሬ እና ከፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ያለፈ ነባራዊ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለመምጣት ሰዋዊ ልማት ላይ ማተኮር ብቻም ሳይሆን ሰውአዊ ልማትን የሚያቀላጥፉ ነፃ እና ገለልተኛ የፍትህ እና የኢኮኖሚ ተቋማትን መገንባት እና መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ እንደ እኔ እምነት በምንም ስሌት በአንድ ፓለቲካ አስተሳሰብ ብቻ የተሰባሰቡ ግለሰቦች በሞሉበት የህወሀት -ኢህአዴግ የፍትህ ስርአት ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ስርአት ሊገነባ አይችልም ፣ በምንም መልኩ ወገንተኛ በሆነው የህወሀት ኢህአዴግ ስርአት ውስጥ እውቀት እና ብር ያለው የግል ባለሀብት በነፃነት በኢኮኖሚ ስርአቱ ላይ ተሳታፊ ሊሆን አይችልም ?

ወገንተኛነት እና መንደርተኛነት የተጠናወተው ስርአት የጥቂት ስብስቦችን ኑሮ እና ኪስ ከመሙላት ባለፈ    ሰዋዊ እና ቁሳዊ ሀብትን በማስተሳሰር የብዙሀኑን ህዝብ ኑሮ ሊያሻሽል ስለአለመቻሉ ከህወሀት-ኢህአዴግ ስርአት በላይ ማሳያ ያለ አይመስለኝም፡፡ ህግ አውጪ፣ህግ ተርጓሚ እና ህግ አስፈፃሚ የፍትህ ተቋማት መሆናቸው ቀርቶ ግለሰቦች በሆኑባት ሀገራችን በምንም ተአምር ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል ሊኖር አይችልም፣  የቀድሞዎቹ ታጋዮች የአሁኖቹ ሀገር አስተዳዳሪዎች ሀገር ከማስተዳደር ባለፈ በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ስርአት ላይ በነጋዴነት፣በአምራችነት፣ በህንፃ አከራይነት በአስመጪ እና ላኪነት ተሳታፊ በሆኑበት ሁናቴ በምን ተአምር ነው የግል ባለሀብቱ ሀብቱን እና እውቀቱን ሀገሪቷ ላይ ለማፍሰስ ተነሳሽነት ሊኖረው አይችልም፡፡

ወገንተኝነት፣ዘረኝነት በነገሰበት ስርአት የሚዘወር ኢኮኖሚ ብዙሀኑን ለዘርፈ ብዙ ድህነት በማጋለጥ ጥቂቶች ብቻ የተዳደለ ህይወት እንዲኖሩ መንስኤ የሚሆነው፡፡ የዚህ አይነቱ ስርአት አስከፊ ውጤት ደግሞ የቱንም ያህል ህዝቡ በኢኮኖሚያዊ ችግር ቢተበተብ የህዝብን ችግር ከመፍታት ይልቅ በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት እንዲሉ ስርአቱ ሙሉ ትኩረቱ ዘረፋ እና ስልጣንን ማስጠበቅ ላይ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ በሀገራችን አሁን ላይ እንደሚታየው አይነት ህዝባዊ ቁጣ እንዲነሳ መንስኤ ይሆናል፡፡

ከምስራቅ እስከ ደበቡብ፣ከደቡብ እስከ ምእራብ ያለው የሀገራችን ህዝብ የህወሀት ኢህአዴግ ስርአት የሌብነት ስርአት ስለመሆኑ፣ የህወሀት ኢህአዴግ ስርአት የቋሚ ሽፍቶች ስርአት ስለመሆኑ አሁን ላይ ነጋሪ ሳያስፈልገው የገባው ይመስለኛል፡፡ አሁን ላይ በሀገራችን ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ የሚታየው የኦሮሚያ ህዝቦችም ሆነ የአማራ ህዝቦች ጥያቄ የህወሀት ኢሃዴግ ቋሚ ሽፍታነት ባህሪ የፈጠረው እና የወለደው ነው፡፡ የጥቂት ሽፍቶች ስብስብ የሆነው ህወሀት-ኢህአዴግ  ለዘረፍው ሀገራዊ ሀብት መንስኤ የሆነውን ስልጣኑን ለማስጠበቅ እና ዘለቄታዊነቱን ለማረጋገጥ ህዝቦችን ማጋጨት፣ማፈናቀል ዋነኛ ተግባሩ ለመሆኑ ነጋሪ የሚያሻን አይመስለኝም፡፡ ይህ ሙት ስርአት እንደለመደው የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ህዝብን መግደል ስራዬ ብሎ ተያይዞታል፡፡ የአለም ታሪክ እንደሚነግረን ህዝብን ያሸነፈ ስርአት ስለአመኖሩ ነው፡፡ በመሆኑም  የህወሀት-ኢህአዴግ የቋሚ ሽፍትነት እና  የዘረኝነት ባህሪ  አንገፍግፎት በሀገራችን  ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ቁጣውን እየገለፀ ያለውን የህዝባችንን ጥያቄ እና ብሶት በጠብመንጃ  እና  በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስቆም መሞከር ጅልነት ነው፡፡ መፍትሄው የህዝቡን ጥያቄ መመለስ ነው፡፡ የህዝቡን ጥያቄ ለመመስ ደግሞ ቋሚ  ሽፍትነት እና  ዘረኝነት መገለጫው ለሆነው ህወሀት ኢህአዴግ ከቶውንም አይቻለውም ምክንያቱም ህዝቡ አምርሮ እየተቃወመ ያለው የህወሀት-ኢህአዴግን ቋሚ ሽፍትት፣የህወሀትን የበላይነት፣ የህወሀት-ኢህአዴግን የዘረኝነት አገዛዝ ነውና፡፡

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.