የኦሕዴድና ብአዴን የፓርላማ አባላት ስብሰባ አንሳተፍም አሉ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 11/2010)

በኢትዮጵያ ፓርላማ የኦሕዴድና ብአዴን አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በምክር ቤት ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ካልሰጧቸው በመደበኛ ስብሰባዎች አንሳተፍም አሉ።

የኦሕዴድና የብአዴን የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ሀገሪቱን ስጋት ላይ በጣላት ብሄር ተኮር ግጭትና የፖለቲካ ቀውስ ላይ አቶ ሃይለማርያም ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርበዋል።

አባላቱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በተወከሉባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ውይይት ካካሄዱ በኋላ ነው።

በኢትዮጵያ ያለው ቀውስ ከፖለቲካ ፓርቲ ሽኩቻ ወደ ፓርላማ አባላትም ተሸጋግሯል።

የወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታ ያሳሰባቸው የኦሕዴድና የብአዴን ተወካይ የሆኑ የምክር ቤት አባላት በመደበኛ ስብሰባ ማሳተፍ ማቆማቸውን ነው የገለጹት።

ምክንያታቸው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ሃገሪቱን ስጋት ላይ በጣለው ብሔር ተኮር ግጭትና የፖለቲካ ቀውስ ላይ መጀመሪያ ማብራሪያ ይስጡን በሚል ነው።

እናም የምክር ቤቱ አባላት ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ እስኪገኙ ድረስ መደበኛ ስብሰባዎችን አንሳተፍም ብለዋል።–የኦሕዴድና የብአዴን ተወካይ የፓርላማ አባላት።

አባላቱ ላቀረቡት ጥያቄ ከምክትል አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም ባለፈው ሳምንት ሀሙስና ትላንት ማክሰኞ መካሄድ የነበረበት የፓርላማው መደበኛ ስብሰባ አለመካሄዱ ነው የተነገረው።

በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባልነት ስነምግባር ደንብ መሰረት የፓርላማ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩን በወር አንድ ጊዜ ጠርተው ማብራሪያ መጠየቅ ይችላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ደንብ መሰረት በአመት 2 ጊዜ ዝርዝር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ የማቅረብም ግዴታ አለባቸው።

በፓርላማ አባላቱ ጥያቄ መሰረት አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ምላሽ ባይሰጡ ስለሚከተለው ሁኔታ በሕጉ የተቀመጠ ነገር የለም።

ጉዳዩን በተመለከተ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.