መውረድ ወይስ መዋረድ?

 

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሕዝብን ጥያቄ ተቀብሎ  በክብር ከሥልጣን የወረደ ንጉሥም ሆነ መንግስት አልታየም::  አለመታየቱንም ለማስረዳት ወደ ሁዋላ ሂዶ ያለፉትን ነገሥታትንና መንግስታትን አወራረድ ማውሳት አያስፈልግም::  ምክንያቱም ሁሉም እስከመጨረሻዋ ዕድል ድረስ ቆይተው ፍጻሜአቸውን ማበላሸታቸው ለኢትዮጵያ  ሕዝብ አዲስ ታሪክ ስላልሆነ::

ዛሬ ወያኔ በሕዝብ ስልጣን ላይ ሆኖ  በስብሻለሁ:: በክቻለሁ እያለ እንደገና እራሱ አገግሞ  እስኪመጣ ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከነብስባሴው እንዲሸከመው ይፈልጋል:: የበሰበሰ ነገር ደግሞ ይከረፋል:: ይገማል:: ይጠነባል::  እንኩዋን ሊሸከሙት ሊጠጉት እንኩዋን የማይቻል ነው:: ሽታው እራሱ በሽታ ነው:: ይህን ያልተረዳ ወያኔ ከነ ምናምኑ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ አልወርድ ብሎ እየታገለ ነው:: ያለፉትን ሥርዓቶች አወራረድ አይቶ የራሱን አወራረድ እንዲያሳምር እየተመከረ ነው:: እየተለመነም ጭምር::  የወያኔ ጆሮ ግን መስማት የሚፈልገውን ብቻ መስማት ስለሚፈልግ ሕዝብን ለማዳመጥ እየተቸገረው ይገኛል:: እንዲያውም በሽታውን  ኖርማል ለማድረግ እና ከሕዝቡ እንዲጋባም ጭምር  የሚያደርገው ጥረት የባሰ አዘቅት ውስጥ እየሰመጠ ነው::

ወያኔ እጅግ በጣም  የከፋ እና የከረፋ ታሪክ ባለቤት ነው:: የሰው ልጅ ነፍስን በጅምላ የጨፈጨፈ ሥርዓት ነው:: ነፍስ ግድያ ቀላል ወንጀል አይደለም::  ከሥልጣን ከወረድኩ ሕግ አይለቀኝም::  ስለዚህ ሥልጣንን እንደ የመጨረሻ ዋስትና አድርጌ መቆየት አለብኝ:: የሚፈታተነኝ ካለ  በኃይል ተረግጦ ይገዛል:: ብሎ ዘርፈ- ብዙ ወንጀል መሥራት የእራስን መቃብር በገዛ እራስ እንደመቆፈርና እራስን በእራስ እንደመቅበር  ጭምር ነው::ወንጀልን ያስብሳል እንጂ አይቀንስም :: ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ  በዘር ተዘርዝሮ ሲነታረክ ለወያኔ  ዕድሜ አይሰጥም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ በጎሣ እየተጎሠሠ ለወያኔ የሥልጣን ዘመን አያራዝምም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ወያኔ የአባሎቹን የደጋፊዎቹን እና የተባባሪዎቹን ፎቅ እያሳየ ለምተናል ሲባል አምኖ አይቀበልም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ  የወያኔን የመሠረተ ድንጋይ ንጣፍ እያየ  የህልም ተስፋ በመመገብ ሌላ የግፍ አገዛዝ  ዘመን አይፈቅድም::

በአጠቃላይ የወያኔ የማጨናበሪያ እና የማደናገሪያ መሣሪያዎች በሙሉ ተበላሽተዋል:: እንደከዚህ ቀደም አገልግሎት አይሰጡም:: እንደዚሁም ወያኔ ሕግ አስከባሪና ኃላፊነት የሚሰማው ድርጅት አድርጎ ለማስመሰል   በአባላቶቹ ውስጥ ጠጥረውብኛል ብሎ የሚያያቸው አባሎቹን ጭዳ በማድረግ እራሱን የሚያተርፍበት ስልትም  ጭንጋፍ ከሆነ ቆየ :: አይሠራም:: ወያኔ በሁሉም  ነገር ሲያቅተው በጉልበት የለየለት አምባገነን ሆኖ ለመቀጠል ከመመኘቱ የተነሳ ሠራዊቱን በመላው የኢትዮጵያ ክልል እያሰፈረ ነው::

መስሎት ነው እንጂ እራሱ ሠራዊቱ አፈሙዙን ወደ እራሱ እንደሚያዞር የጠረጠረው አይመስልም ::

ስለዚህ ወያኔ ልብ ከገዛ ከሥልጣን ለመውረድ እራሱን ዝግጁ ማድረግ አለበት:: ከሥልጣን አወራረድን ማጥናት ይኖርበታል:: ይህን ካላወቀበት መዋረድን አሜን ብሎ መቀበል  ግድ ይለዋል :: የማይቀረው አጋጣሚ ይኸው ነው::

ደምለው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.