አዲስ አበባ የኦሮሞ ካልሆነች የማን ልትሆን ነው ታድያ?። (ከተማ ዋቅጅራ)

አዲስ አበባን ለኦሮሞ እንሰጣታለን በማለት የከሰረ እና ያረጀ የማስፈራሪያ የፖለቲካ አካሄዳቸውን ወያኔዎች ከሰሞኑ መምዘዛቸው  እየተነሳባቸው ያለውን አገራዊ ይዘት ያለውን  ተቃውሞ እናስቀይራለን ብለው ነው። በዚህች የወያኔ ካርድ ማንም አይደሰትም ማንም አይደነግጥም። ታድያ አዲስ አበባ የኦሮሞ ካልሆነች የማን ትሁን? የየመን? ወይንስ የሱዳን? ወይንስ የኬንያ? ምን አይነት የወረደ እና የበሰበሰ ሃሳብ እንዳላቸው ድንቅ ይለኛል። አዲስ አበባን 45 አመት ሙሉ ኦሮሞው ኃይለ ስላሴ ቤተ መንግስት አድርጓት ተቀምጠዋል። አዲስ አበባን ኦሮሞው  መንግስቱ ኃይለማርያም 17 አመት ነግሶ ተቀምጦበታል። ታድያ ያኔ ለምን የኢትዮጵያ ህዝብ ስጋትና ፍርሃት አልገባውም? ዛሬስ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ቤተ መንግስት ገብቶ ቢያስተዳድር አልያም ለማ መገር  አልያም  በቀለ ገርባ  ወይንም ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ነግሰው ቢያስተዳድሩ ኢትዮጵያኖች እኮ ናቸው። አዲስ አበባን ለኦሮሞ እንሰጣለን ብሎ ማስፈራራቱ አማራው ማህበረሰብ አዲስ አበባን ለኦሮሞ ከምትሰጡ እኛ አማሮች ከወያኔጋር በመሆን ሊያጠፋችሁ የመጣውን የህዝብ ቁጣ ከጎናችሁ በመቆም የወያኔ ስልጣንን እናስቀጥለዋለን እንዲላችሁ ነውን? አንዱን ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ፣ አንዱን ገዳይ  ሌላውን ተገዳይ፣ አንዱን አጥፊ ሌላውን እንደተጠፊ፣ አንዱን ነዋሪ ሌላውን መጤ፤ በማድረግ የሚሰራው የፖለቲካ አካሄድ  በሁለቱ ህዝቦች ዘንድ ውድቅ ከተደረገ ቆየ። የኢትዮጵያ ህዝብ ትግል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት  ብሎ ሳይሆን በነጻነት የመኖር የህልውና  ጉዳይ እንደሆነ መሬት ላይ የሚደረገውን ትግልን አይታችሁ ወደ ልቦናችሁ መመለስ አለመቻላችሁ እኔ ከሞትኩኝ ሰርዶ አይብቀል እንዳለች አህያ መሆን ነው።

ወያኔ እየሄደበት ያለው እጅግ አደገኛ አካሄድና ለስልጣኑ ማራዘሚያ ብለው የሚቀምሙት መርዝና በየቦታው በሚያጠምድ ዘግናኝ ፈንጅዎች ማን ለዘላለም እንደሚጎዳበት የመያስፈራ ጉዳይ ነው።  አሁንም አሁንም ደግሜ እና ደጋግሜ የማዝነውና የምፈራው ለምስኪኑ እና ምንም ለማያውቀው በስሙ ለሚነገድበት ለትግራይ ህዝብ ነው።

ወያኔ ስልጣኔን ከማጣ ቤንዝን ላይ ክብሪት በመለኮስና ይሄንንም በከፍተኛ ሁኔታ የሚያቀጣጥሉ ካድሬዎችን በሰፊው በመመልመል ከፍተኛ ብር እየከፈላቸው በማህበራዊ ሚዲያ በሚባሉት እንደ  ፌስቡክ ባሉት እና እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ ጥፋትን የሚያስፋፉትን በማሰማራት የመጣብኝን መከራ እሻገራለው ስልጣኔንም ባነደድኩት እሳት ሌሎች(ብሔር) ሲጠፋፉ ወያኔ ከመሃል ወጥታ እራሷን ይጠብቁኛል ባለችው ጦር ተከባ ጥግ በመሆን እመለከታለው ስልጣኔንም በዚህ ስልት እስከመጨረሻው አስጠብቃለው የምትለው አደገኛ አካሄድ በህዝብ ላይ የሚጫወቱት  ቁማር በመሆኗ በመላው ኢትዮጵያ እየመጣባቸው ባለው የህዝብ ቁጣ ወገባቸው ድረስ የቀበራቸው እንደሆነ እና የተደገፉት ምርኩዝ ብአዴን እና ኦህዴድ እየከዳቸው እንደሆነ ቢረዱም ቅሉ እንደአበደ ውሻ መክለፍለፍ ማቆም ባለመቻላቸው ከአደገኛነቱ ባሻገር የትግራይን ህበረሰብ በቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ እጅጉን እንዲጠሉ በማድረግ ሆድ እና ጀርባ እንዲሆኑ በመሰራት  ላይ ናቸው።

እንግዲህ የትግራይ ህዝብ ሆይ ከነቃችሁ የመንቂያችሁ ሰዓት አሁን ነው። ጀንበሯ ልትጠልቅ 11፡45 ሰዓት ላይ ነው። ወያኔ በአዲስ አበባ ዙሪያ መለኮስ የፈለጉት እሳት በደረቁ ሲተረገም፦ አዲስ አበባን ለኦሮሞ ሰጥተን ነው የምንሄደው የምትለው፦

አዲስ አበባ ለኦሮሞ ከተሰጠ የአማራና የኦሮሞየ ማህበረሰብ  ይጋጫሉ። ያም የኔ ናት ያም የኔ ናት በማለት ይጣላሉ እርስ በእራስ ሲጠፋፉ ወያኔውያን ግን ምንም አይነት አደጋ ሳይደርስበት የስልጣን ዘመናችን ይረዝማል የሚል የከሰረ እሳቤ ይዘው ነው።
ወያዎች እንዳሰቡት ቢሆን  የትግራይ ህዝብ በአዲስ አበባ እና በመላው ኦሮምያ እንዲሁም አአማራ እና በተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት በተለኮሰው እሳት አለመቃጠላቸው ምን ያህል እርግጠኛ ሆነው ነው? እሳቱ ከተነሳ እኮ ከፊት ያገኘውን በሙሉ እንደሚያጠፋ መገንዘብ የተሳናቸው ስለምን ይሆን ? ምንም የማያውቀውስ ሰፊው የትግራይ ህዝብን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ተቃርኖ እንዲኖር መፍረድስ ስለምን አስፈለጋችሁ? በትግራይ ህዝብ ላይ የተደበቀ ቂም አልያም ህዝቡ የማያውቀው ደባ ይኖራቸው ይሆንን? ይሄን መመርመር ያለበት የትግራይ ህዝብ ነው። ስለዚህ አዲስ አበባን ለኦሮሞ የምትለዋ መርዝ ቀድማ  የምታጠፋው ወደዳችሁም ጠላችሁም ዋሻችሁም ደበቃችሁም ወያኔንና ተከታዮችን ነው። ይሄንን ለማወቅ ነብይ መሆን አይጠበቅብኝም። ለሁሉም ግዜ አለው አይደል ያለው መዝሙረኛው ዳዊት። ይሄንን የምለው ለትግራይ ህዝብ ካለኝ ክብር እንጂ ኮካዎች እንደሚሉት  የትግራይን ህዝብ ስለምጠላ አይደለም።  በመዋሸት አልያም በማስፈራራት አልያም በመሸፋፈን የምናልፍበት ግዜ አይደለም።  ወደድንም ጠላንም እውነትን ፊት ለፊት የምንጋፈጥበት ግዜ ላይ ነው ያለነው።

ስለዚህ ከአሁን በኋላ ወያኔ ስልጣኑን ለማራዘሚያ በሚያደርገው መርዘኛና አደገኛ አካሄድ የኦሮሞ እና የአማራ ማህበረሰብ ለደቂቃም አይጣሉም። እንደውም ቀጤማ ተጎዛጉዘው… ዘንባባ ነስንሰው….. አበባ በትነው…… ያንተ ስልጣን የኔ…… የኔ ስልጣን ያንተ፣ የኔ አገር ያንተ…..ያንተ አገር የኔ፣ ያንተ ህዝብ የኔ……የኔ ህዝብ ያንተ፣ የኔ ደም ያንተ….ያንተ ደም የኔ፣ በመባባል በፍቅር የሚኖር  ህዝብ ነው። አንተም ግንድ እኔም ግንድ ተከባብረን፣ ተዋልደን፣ ተፋቅረን፤ እንኖራለን እንጂ ለወያኔ የተንኮል ደባ በምንም መልኩ እነዚህ ህዝቦች ተጋላጭ ልጣን ማራዘሚያ አይሆኑም። አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት የምትለዋ አነጋገር የአማራ ማህበረሰብ በማስደንገጥ የወያኔ ስራ የሚሰራበትም ሆነ የሚሰማበት አካሄድ በሁለቱ ማህበረሰብ ተቀባይነት አይኖረውም። ይልቁንም ኮካዎችን መስማት በማቆም ይሄንን አደገኛ የወያኔን አካሄድ በአደባባይ መቃወም ያለበት የትግራይ ህዝብ ነው። ጨው ለራስህ  ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ ድንጋይ ነህ ተብለህ ትጣላለህ የሚለው ተረት ተፈጻሚ እንዳይሆን በጥልቀት ይታሰብበት።

ለማ መገርሳ በተናገረው ነገር ጽሁፌን ልቋጭ። “አዲስ አበባ የኦሮሞ፣ የአፍሪካ፣ የመላው ኢትዮጵያና የአለም መንግስታት መቀመጫ መዲና ናት” በማለት የወያኔን ፈንጂ እጃቸው ለይ አፈንድቶታል። ከአሁን በኋላ ወያኔ የምታጠምደውን ፈንጂ እያመከንን እንሄዳለን እንጂ ፈንጂ ላይ የሚራመድ ማንም ኢትዮጵያዊ አይኖርም። አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት ለሚለው ለወያኔ ቁማር የኛ ምላሽ፦ እንኳን አዲስ አበባ ጎንደር የኦሮሞ ናት። እንኳን አዲስ አበባ ባሌ የጎጃም ናት። ነው።

ከተማ ዋቅጅራ
22.12.2017
Email- waqjirak@yahoo.com

Attachments area

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.