የህወሓት መሪዎች በመቀለ ግምገማ ሂደትና የውጭ ተቃዋሚው ግብዝነት (ገብረ ለማ)


ህወሓት ከመቀለ ስብሰባ መሰረታዊ ለውጥ ይመጣል ብሎ ማሰብ ኣይቻልም። በፊትም በስብሰናል ብለዋል። በስብሰው ስንቱን ህዝብ እንደበደሉ ኣልተጸጸቱም። እንዲያውም ሙሱና እንዳይነካባቸው ተጠንቅቀው የሽግሽግ ለውጥ ብቻ ነው ያደረጉት።
ኣንድ ኣወንታዊ ስራ ግን ሰርተዋል። ለጥፋታቸው ተስማምተዋል። ኣብረው ለመዝለቅም ቃል ገብተዋል። በኣዲሱ ኣመራር ታችኛውም እንደሚሰፈር ኣጽድቀዋል። መስፈርቱ ግን የሙሱና፣ ክራይ ሰብሳቢ፣ ተለጣፊ መሆን ወዘተ ናቸው።

ሃገር ቤት ያሉ ተቃዋሚዎች በኢሕአዴግ ስልለላ፣ ክትትል፣ እንግልት፣ እስራት፣ ግድያ፣ ኣካልን ማጉደል፣ ቤተሰብን ማሰቃየት፣ ወዘተ ስር ሁነው የተቻላቸው እየሰሩ ናቸው፣ ይመሰገናሉ። የውጪው ተቃዋሚ ነው የሚገርመው። የስንት ኣመት ተመኩሮ ኣለኝ እያለ፣ የተማርኩ ነኝ እያለ፣ ተሰባስቦ ኣወንታዊ ስራ መስራት ግን ኣልቻለም። ህወሕት/ኢሕአዴግ ተሰባስበው የወሰኑት እቅድ ይፈጹሙታል። ኢሕአዴግ ካሁን በኃላስ እንደዛ ይቀጥላል ወይ በሂደት እናየዋለን። ኣሁንም የእንግሊዙ/የጣልያን የከፋፍለህ ግዛ፣ የሃገራችን መሪዎችም ሲጠቀሙበት የነበረ፣ ወያኔም በሕገ ደንብ ኣጽድቆ የሰራበት፣ እኛም እሱን ተከትለን የኦሮሞ የኣማራ የጎንደር የትግራይ የዓፋር የደቡብ የቤኒሻንጉል የሶማሌ እያልን ለእናት ሃገራችን ኢትዮጵያ ሁለተኛ ምድብ ኣድርገን ስንሰራ ቆይተናል። ያመጣነው ለውጥ ግን የለም፣ ጭራሹን በዘር፣ በመንደር፣ በቓንቓ ተለያየን።

ስለዚህ ህወሓት መቀለ በ35 ቀናት እንደተስማሙ፥ የውጭ ተቃዋሚ ሁሉ ለ 7 ቀናት ተሰባስቦ ሃገራዊ መስፈርት ኣስቀዶሞ መስማማት ብቻ ነው መፍትሄው። እኔ ልቅደም ይሀው ከንቱ መሆኑን እመን። የት ነበር ሳይባል፣ እንዲህ ነበር ሳይባል ሁሉም እኩል ኣንድ ድምጽ መነሻ ኣድርጎ ኣብላጫ ድምጽ ያገኘው ይጸድቃል፣ በዚህ መስፈርትም ኣላሰራ ያለ ይባረራል። እስካሁን የተሰባሰቡት ኦነግ፣ ግንቦት ፯፣ የኣፋር፣ ሸንጎ፣ ሰማያዊ፣ ኣንድነት፣ ህብረት፣ የሶማሌ፣ ሌሎችም ሁሉ ይካተታሉ። መንግስቱ ሓይለማርያምም እሳተፋለሁ ካለ ይሳተፋል፤ ቤተሰቦቼ የጨረሳቸው ቢሆንም። ምክንያቱም ሃገራዊ ቢሄራዊ ስርኣት ለመትከል ነው፣ ሕግ የበላይነት። ሕጉን ተቀብለን ሁሉም በሕጉ መሰረት ከተስተካከለ በሕጉ ሁሉም ይፈተሻል።

ማስተዋል ያለብን በሃገር ቤት ኣዲሱ ትውልድ የኣከባቢውን ድጋፍ እያገኘ ያመራር ቦታውን የሚረከብበት እድል እየፈጠረ ነው ስለዚህ የውጭ ተቃዋሚዎች ተቀባይነትም ላይኖራቹሁ ይችላልና። “በዚህም ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የኦሕዴድና የብአዴን አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ተገኝተው ወቅታዊ ግጭቶችንና የፖለቲካ ቀውሱን አስመልክቶ እንዲያብራሩ፣ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎችም ዝርዝር ምላሽ እንዲሰጡ አቋም ይዘው ጥያቄ ማቅረባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡” http://www.ethiopianreporter.com/index.php/article/5278 እንደዚህ ማለት የጀመሩት የነሱ መበርታት፣ ከኣካባቢያቸው ድጋፍ እና እምነት ማነጻቸው፣ የህወሓት መላላት ያረጋግጣሉ። ከዚሁ ጋር መጣጣም የሚቻለው የነሱን ያህል የሥነ ልቦና ጥንካሪ ሸምተን ስንተባበር እና በተግባር ልናሳያቸው ከቻልን ነው። ሚዲያዎች፣ ቪዥን ኢትዮጵያ፣ ሲቪል ማህበሮች የመሳሰላቹሁ ሙሉ መብት ኣግኝታቹሁ በሃገር ቤት መሳተፍ የምትችሉት ሕግ የበላይነት ስርዓት ሲኖር ብቻ ነው ስለዚህ የማንም ኪስ ሳታዩ በቅንነት መስራት ከናንተ የሚጠበቅ ነው። ስለሆንም ላልፉት 27 እና 42 ኣመታት መስራት ያቃተን ባህሪ በራሳችን ከራሳችን ኣውጥተን ተከባብረን ኣብረን ለመስራት ስብእና ይኑረን። መጠላልፉን ትተን፣ ለስልጣን ሩጫ ትተን፣ እኔ ልምራ ትተን…. ለህዝብ መርህ ኣስቀድመን ተቻችለን በተግባር መስራት ስንጀምር ነው። የዩሮፒያን ኣዲስ ዓመት 2018 በኣዲስ መንፈስ ልባችን ከፍተን ለህዝባችን ስንል ተከባብረን ኣብረን ለመስራት ሁላችን እንነሳ። እስካሁን ያመጣኸው ለውጥ የለም፤ እንደዚህ ብሎ መቀጠሉ ለውጥ ኣይመጣም።

ከጠላጥ ኣብረህ ለመስራት ለህዝብ ስትል ተነስ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.