በመሰረታዊ ወታደሮችና መስመራዊ መኮንኖች አማካኝነት ከፍተኛ አመጽ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት በከፍተኛ አዛዦች መያዙን ታወቀ

የጸጥታ ኃይሎች እና ማህበረሰብ
የጸጥታ ኃይሎች ዜና (ታህሳስ 14, 2010 ዓ.ም)

(ኢሳት ዜና ) በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የሚካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ በመከላከያ ውስጥ ያሉ የሰራዊቱ የታችኛው እርከን አባላት አማካኝነት አመጽ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት እንዳለ ለማወቅ ተችሏል። በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የሚደረገው ተቃውሞ መከላከያ ውስጥ ባሉ የሰራዊት አባላት ዘንድ ቀልብ መሳብ መጀመሩ ከፍተኛ የጦር አዛዦችን ለስጋት እንደዳረገ በመከላከያ ውስጥ ያሉ ወኪሎቻችን ይገልጻሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሰራዊቱ ስብሰባዎች ላይ ከመብት ጥያቄዎች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች መነሳት መጀመራቸው በመከላከያ ውስጥ ያለው ሰራዊት ላይ እምነት ማጣት መጀመሩን ከፍተኛ የሆኑ የጦር አዛዦች ሲገልጹ ተስተውሏል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለያየ አጋጣሚ የሚከዳው የሰራዊት ብዛት በከፍተኛ ቁጥር መጨመሩ በመከላከያ ውስጥ ያለውን የስጋት መጠን ከፍ እንዲል አድርጎታል። በሰራዊቱ እና በመስመራዊ መኮንኖች ዘንድ በአዛዦች ላይ የሚያነሱት ቅሬታዎች እያደጉ መምጣታቸውና ይህንንም ቅሬታ በሰራዊቱ ስብሰባዎች ላይ መገለጽ መጀመሩ ሰራዊቱ በአዛዦቹ የሚወርድን መመሪያና ትዕዛዝ አልቀበልም ወደሚል ሊያመራ ይችላል የሚል ምልከታ እየተያዘ መምጣቱን መረጃውን ያቀረቡልን ወኪሎቻችን ይገልጻሉ። በወታደራዊ መረጃ ዋና መምሪያ ስር የሚገኘው የጸረ መረጃ መምሪያ ጉዳዩን ተከታትሎ የመፍትሄ ሃሳብ እንዲያቀርብ ታዟል።

ሰራዊቱ ለጠላት ፕሮፓጋንዳ ተጋላጭ ሆኗል የሚለው ሃሳብ በወታደራዊ ከፍተኛ አዛዦች ዘንድ በስፋት መያዙን የገለጹት ወኪሎቻችን ይህን ሁኔታ ለመቅረፍ የሚያስችል መጠነ ሰፊ ስራዎች መሰራት ካልቻሉ በሰራዊቱ ዘንድ ከፍተኛ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል በርካታ የጦር አዛዦች እያሳሰቡ ይገኛሉ። የኦሮሞና የአማራ ብሄር ተወላጆች የሆኑ የሰራዊቱ ከፍተኛ የጦር አዛዦች ካሉባቸው ሃላፊነቶች እየተነሱ ምንም ሚና ወደሌለው የሃላፊነት ቦታ እየተመደቡ መሆኑ በሰራዊቱ ዘንድም አንዱ የቅሬታ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ለማወቅ ተችሏል። ይሄም መደረጉ በሰራዊቱ አዛዦች መካከል ያለው ያለመግባባት እንዲሰፋ ምክንያት ሆኗል። የህወሃት አባል በሆኑና በሌሎች የሰራዊቱ የጦር አዛዦች መካከል ግልጽ የሆነ የሃሳብ ልዩነት እየመጣ መሆኑን በመከላከያ ውስጥ ያሉ ወኪሎቻችን ይገልጻሉ። ለህወሃት ታማኝ አይደሉም ተብለው የሚታሰቡ የጦር አዛዦች ከሃላፊነት ቦታቸው እየተነሱ መሆናቸው ይታወቃል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.