የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት አቤቱታ ውድቅ ተደረገ (በጌታቸው ሺፈራው)

~ በአቶ መብራቱ ጌታሁን ዓለሙ ስም ላይ ሊሰጥ የነበረው ብይን ለቀጣይ ቀጠሮ ተላልፏል


የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት የሆኑት እነ መብራቱ ጌታሁን “የወልቃይት ጥያቄ በታሪክና ህገ መንግስት”በሚል በፃፉት 46 ገፅ ፅሁፍ ወልቃይት የትግራይ ነው የሚል አቋም ይዘዋል ያሏቸው ዳኛ ዘርዓይ ወልደሰንበት ከችሎት እንዲነሱላቸው ያቀረቡትን አቤቱታ ፍርድ ቤት ውድቅ አድርጎባቸዋል።

ተከሳሾቹ አቤቱታ የቀረበባቸው ዳኛ ጉዳዩን በግድ እዳኛለሁ ስለማይሉ ራሳቸውን ያነሳሉ የሚል ግምታቸውንም ያስቀመጡ ሲሆን ዳኛው በአቤቱታው ላይ ከችሎት መነሳት እንደሌለባቸው የሚገልፅ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በዚህም መሰረት በፅሁፉ ያንፀባረቁትን አቋም ሀሳብ በነፃነት የመግለፅ መብቴን ተጠቅሜ ነው፣ ከተከሳሾቹ ጉዳይ ጋርም አይገናኝም የሚል መልስ የሰጡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ዳኛው መነሳት የለባቸውም የሚል ብይን ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ጨለማ ቤት የሚገኙት አቶ መብራቱ ጌታሁን ስለሚገኙበት የጤና ሁኔታ አቤቱታቸውን በፅሁፍ ለፍርድ ቤቱ ያስገቡ ሲሆን በመዝገቡ 2ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ጌታቸው አደመም በህመም ምክንያት አልቀረቡም።

ከዚህ ባሻገር ዛሬ ታህሳስ 18/2010 ዓም ፍርድ ቤቱ በአቶ መብራቱ ጌታሁን ስም ጉዳይ ብይን ይሰጣል ተብሎ የነበር ቢሆንም ዐቃቤ ሕግ አስተያየቱን ባለማካተቱ ለቀጣይ ቀጠሮ ተላልፏል። ፍርድ ቤት አቶ መብራቱ ጌታሁንን “መብርሓቱ” እያለ ሲጠራ ተከሳሽ ስማቸው ” መብርሓቱ” ሳይሆን “መብራቱ” እንደሆነ በመግለፅ እንዲስተካከል ሲጠይቁ ቆይተዋል።

አቶ መብራቱ ስሜ ይስተካከል ብለው ሲጠይቁ የግራ ዳኛው አቶ ዘርዓይ ወልደሰንበት “እስከመጨረሻው በዚሁ ስም እንጠራዎታለን” ቢሉም መሃል ዳኛው አቶ ዮሃንስ ጌሲያብ አቤቱታው እንደሚታይ ገልፀው መረጃ እንዲያመጡ መጠየቃቸው ይታወሳል። አቶ መብራቱ መረጃቸውን ያቀረቡ ሲሆን በመረጃው ላይ ዐቃቤ ሕግ አስተያየቱን በፅሁፍ ባለማስገባቱ ዛሬ ሳይበየን ቀርቷል።

በሌሎች መዝገቦች የስም ስህተት ሲፈጠር እና ተከሳሾችም ሌላ ተጨማሪ መረጃ ሳያቀርቡ በችሎት ሲያመለክቱ ፍርድ ቤቱ ለዐቃቤ ሕግ እንዲያስተካክል ገልፆ የተስተካከለባቸው ሁኔታዎች ታይተዋል።

ፍርድ ቤቱ አቶ መብራቱ ጌታሁን በፅሁፍ ያቀረቡትን አቤቱታ አይቶ፣ በአቤቱታው ጉዳይ ላይ እንደአስፈላጊነቱ ቀጠሮ ሊሰጥ እንደሚችል ሲገልፅ፣ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 30 ቀጠሮ ይዟል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.