አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር አብይ አህመድ ፍርድ ቤት ቀርበው ሊመሰክሩ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 18/2010)

በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ በመከላከያ ምስክርነት የተጠቀሱት አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር አብይ አህመድ ፍርድ ቤት ቀርበው ሊመሰክሩ እንደሚችሉ ተገለፀ።

ባለስልጣናቱን በአካል አግኝቼ አነጋግሬያቸዋለሁ ያሉት የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ሌሎችም በችሎት ተገኝተው ሊመሰክሩ እንደሚችሉ ገልጸውላቸዋል።

በሌላ በኩል የበቀለ ገርባ የመከላከያ ምስክር የሆኑት አቶ አንዱዓለም አራጌ በከባድ ወንጀል የተከሰሱ ናቸው በሚል ማረሚያ ቤቱ ችሎት አላቀርብም ማለቱ ተሰምቷል።

በእነ ጉርሜሳ አያኖ የክስ መዝገብ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያሉት ተከሳሾች በመከላከያ ምስክርነት እንዲገኙላቸው ጠይቀው የነበሩት አቶ ለማ መገርሳን፣ ዶ/ር አብይ አህመድን፣ ወ/ሮ ጫልቱ ሰኒንና አቶ አባዱላ ገመዳን ነበር።

ለምስክርነት የተጠሩት ባለስልጣናት ግን ለሁለት ጊዜ ያህል ስብሰባ ላይ ሆነን ነው በሚል ለምስክርነት መቅረብ አለመቻላቸው ታውቋል።

ታዲያ አሁን ላይ የተከሳሾቹ ጠበቃ አቶ አብዱልጀባር ሁሴን ለችሎቱ ለምስክርነት የተጠሩት ባለስልጣናት ችሎት ቀርበው ሊመሰክሩ ይችላሉ የሚል መረጃ አቅርበዋል።

ፋይል

ይህን ደግሞ እራሴ በአካል አግኝቼ አነጋግሬያቸዋለሁ።በቃላቸውም ይህን ምላሽ ሰጥተውኛል ብለዋል ጠበቃው አብዱልጀባር።

ከዚህ በፊት ያልተገኙትም በስብሰባ ምክንያት መሆኑን አረጋግጠውልኛል ብለዋል።

እንግዲህ ግለሰቦቹ እንዳሉት ከሆነና በቃላቸው መሰረት ፍርድ ቤት ቀረበው የምስክርነት ቃላቸውን የሚሰጡ ከሆነ ለነገ ታህሳስ 19/2010 በችሎት ቀጠሮ ተይዞላቸዋል ይላል ኢሳት ያገኘው መረጃ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በፖሊስ ተይዘው ይቅረቡልኝ ያሉት አቶ በቀለ ገርባ ሌላኛው ምስክራቸው አቶ አንዱአለም አራጌም ችሎት ቀርበው ምስክርነታቸውን እንዳይሰጡ ተደርገዋል።

ይህን ያደረገው ደግሞ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት በራሱ ስልጣን እንደሆነም ታውቋል።

ማረሚያ ቤቱ ለዚህ የሰጠው ምክንያትም አቶ አንዱአለም ከባድ ፍርደኛ ናቸው በዚህም ምክንያት በችሎት ቀርበው መመስከር አይችሉም የሚል ነው።

ይህን የሰማው ፍርድ ቤትም ማረሚያ ቤቱ አቶ አንዱዓለም አራጌን በነገው ችሎት ላይ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ከዚህም ሌላ ፍርድ ቤቱ እስከ ታህሳስ 19/2010 ለምስክርነት በሰጠው የሶስት ቀን ቀጠሮ መሰረት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ችሎት ቀርበው መመስከር ካልቻሉ በቀጠሮው መጨረሻ ላይ ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ገልጿል።–ትዕዛዙ ምን እንደሆነ ባይታወቅም እንኳን።

የግራ ዳኛው ዘርአይ ወልደሰንበት እኛን የመዳኘት መብት የላቸውም እኛም በሳቸው መዳኘት አንፈልግም በሚል የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ መደረጉ ተሰምቷል።

ወልቃይት የትግራይ ነው የሚል አቋም ይዘዋል በሚል ቅሬታ የቀረበባቸው የግራ ዳኛው ዘርአይ በሕጉ መሰረት ጉዳዩን በግድ እዳኛለሁ ማለት እንደማይችሉ ተከሳሾቹ አንቀጽ አጣቅሰው ቢያቀርቡም ሰሚ ግን ማግኘት አልቻሉም።

ዳኛው ራሳቸው መልስ ሰጪ ራሳቸው ወሳኝ በሆኑበት በዚህ መድረክ ላይ የተከሳሾቹ በግለሰቡ አንዳኝም ጥያቄ ውድቅ እንዲሆን መደረጉ ታውቋል።

ሌላው በፍርድ ቤቱ ውሎ አንተ ይዘህው በመጣህው መጠሪያህ ሳይሆን እኔ በምሰጥህ ስም መጠቀም አለብህ የተባሉት የአቶ መብራቱ ጌታሁን ዓለሙ ጉዳይ ነው።

የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ መብራቱ ጌታሁን ስሜ መብራቱ እንጂ መብርሓቱ አይደለም ስለዚህ ይስተካከል በሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ የሚሰጣቸው አላገኙም።

የግራ ዳኛው ዘርአይ በዚሁ ስም እስከመጨረሻው እንጠራሃል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋቸዋል።

ቀደም ሲል የመሃል ዳኛው ስምህ እንደዛ ስለመሆኑ ማስረጃ አቅርብ ያሏቸው አቶ መብራቱ ማስረጃቸውን ቢያቀርቡም አቃቢ ሕግ አስተያየቱን በጽሁፍ አላስገባም በሚል ለዛሬ ተይዞ የነበረው ብይን ሳይሰጣቸው ቀርቷል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.