እንኳን አባ ዱላን ለማና ገዱንም ስለአመናቸው ሳይሆን ጥሩ አጋጣሚ ስለፈጠሩልን ነው (ሰርፀ ደስታ)

እኔን እንደገባኝ ሌላው ሌላው እንዳለ ሆኖ ብዙ ጊዜ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ መሆናችን ብዙ ልንራመድበት ከምንችልበት እያንሸራተተ እዛው ይመልሰናል፡፡ በአሁን ጊዜ ነገሮች እየጋሉ ትልቅ ትኩረት እንዲሰጣቸው እየተሰራጩ ያሉትም በትክክል እውነታዎችን በሚረዱና በሳል አስተሳሰብ በአላቸው አደለም፡፡ የመገናኛ ብዙሀን ነን ብለው በውል ከተቋቋሙት እስከ ተራ የፌስቡክና ዩቱብ ድምጾች የሚነገረው ነገር ለወደፊትም እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ብዛታቸውን ጨምሮ ውዥንበር ከመፍጠር ሌላ በውል የታመነ መረጃ የሚሰጡ ስንት እንደሆኑ አላውቅም፡፡ አሁን የያዘን አባዜ አንድ ሰሞን በሚሰጠን የወሬ ቀለብ እያጋጋልን እንቆይና ያ ወሬ ደግሞ ሌላ ሆኖ ሲገኝ እንገና ሁለተኛ ዙር ወሬ ይሆነናል፡፡ አባዱላና በረከት መልቀቂያ አስገቡ ተብሎ እንደተዓምር ተወራ፡፡ በረከትን እንኳን ማንም ከቁብ አልቆጠረውም አባዱላ ግን የለቀኩበት ምክነያት የድርጅቴና ሕዝቤ መብትና ክብር አልተጠበቀም በሚል ነበር፡፡ ይህን ስላለም በብዙዎች ለአባ ዱላ ትልቅ ቦታ ተሰጠው ትልቅም ወሬ ሆነ፡፡ እንደ እውነቱ እንዲህ ያለውን ነገር አይተን ስላላወቅን ብርቅ ሆኖብን እንጂ አባ ዱላ ከአንጀቱ ብሎት እንኳን ቢሆን የዛን ያህል ልናጋንነው ባልተገባ፡፡ ወደልቦናህ ተመልሰህ ከሆነ ይቅርታ ልትጠይቀን ይገባል ሊባልም በተገባ ነበር፡፡ አባዱላ ለአለፉት 26-7 ዓመት በሕዝብ ላይ ብዙ ወንጀል እየሰራ ባለ ቡድን ውስጥ ከዋነኞቹ አንዱ ሆኖ ሲሰራ እንደቆየ ልንረሳለት ሳይሆን በይፋ አምኖ ይቅርታ ከጠየቀን ይቅር በማለት ምህረትን ልናስተምረው ነው የሚገባን፡፡ ሆኖም ሕልውናችንን ሳይቀር የተፈታተኑንን ጠላቶቻችንን ትንሽ ወደ እኛ የቀረበ የሚመስል ንግግርም ይሁን ድርጊት ሲያደርጉ ጠላቶቻችን እንሆኑ ዘንግተን ይሁን ፈረተናቸው አላውቅም ግን ትልቅ ክብር እንሰጣቸዋለን፡፡ እነሱም እኛ ያለንበትን የመንፈስ ልዐልና በዚህ ደረጃ እንደወረደ ስለተረዱ እየሸነገሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወጥመዳቸውን ያጠነክሩብናል

በሟቹ መለስ መጨረሻ ዘመን ሰውዬውን ያላደነቀ የለም፡፡ ለምን ብለን ስንጠይቅ ግን ከላይ የጠቀስኩት በራስ የመተማመን ልዕልናችንን ማጣታችንና በቀላሉ የመሸንገላችን እውነትን ነው የሚመሰክረው፡፡ እንጂማ መለስ እኮ የኢትዮጵያ ጠላት እንደሆነ ማንም አእምሮ ያለው ሊያስበው የሚችል ፍጥጥ ያለ ድርጊቱ ማስረጃ ነበር፡፡ አሰብን አሳልፎ መስጠት፣ በሕዝቦች መካከል በተለይም አማራና ኦሮሞ መካከል የማይታረቅ ቂም ለማኖር ማሴር፣ ለአገርና ሕዝብ የተናገሩ ማሰርና መግነደል (ልብ በሉ የሽብር ሕጉን ማን እንደወጠነው)፣ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት መክፈትና ሆን ብሎ ብዙ ኢትዮጵያውያን እንዲያልቁ ማድረግ፣ በዚሁ ጦርነት ኢትዮጵያ መልሳ አሰብን የመያዝ አጋጣሚውን ሆን ብሎ ማጨንገፍ፣ አያሌ ወገኖችን በመግደልና በማሰር በማሰቃየት፣ ወሳኝ የሆኑ የአገሪቱን መዋቅሮች በወያኔ ትግሬዎች ሙሉ በሙሉ በሚያስብል መልኩ ማስያዝ (ምሳሌ መከላከያ፣ ውጭ ጉዳይ፣ አየር መንገድ)፣ ሌሎችም፡፡ ይሄን ሁሉ ያረገ የኢትዮጵያ ሕዳሴ መሪ ተዋናይ በሚል ትልቅ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ሁሉንም ትተን እሱን እየሰማን ደነዘዝን፡፡ አፍዝ አደንግዝ ይልሀል ይሄ ነው፡፡ በመጨረሻም  የህዳሴ ግድብ በሚል አዲስ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፈተልን ብዙ ተጃጃልን፡፡ ከህዳሴው ግድብ በፊት ሌላ የህዳሴ ድልድይ የሚል ያችን አባይ ላይ የተንጠለጠለች መሻገሪያ ትልቅ አድርገን እንድናያት ብዙ አወራብን፡፡ ልብ በሉ መቼም ብዙ ኢትዮጵያውያን በብዙ አገር ይኖራሉ አነሰም በዛም በሚኖሩበት አገር ያለውን ቴክኖሎጂ ያያሉ፡፡ ዓለም ላይ ዛሬ በመቶ ኪሎሜትሮች የሚለኩ ድልድዮች የሚሰሩበት ዘመን ነው፡፡ ብዙዎቻችንም የመቶዎቹ ኪሎሜትሮችን ድልድይ ባንሻገርም አነስተኞቹን እስከ 5ኪሜ የሚደርሱትን ተሸግረናል፡፡ አዎ ለአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የአባይ መሸጋገሪያ ርብራብ ተዓምር ነው፡፡ አዲስ አበባ ጎተራ ማሳለጫ ለምን ያህል ጊዜ የእድገቱን ማማ እየወጣንበት መሆኑን ለማሳየት በመለስና ቡድኑ ፕሮፓጋንዳ እንደተነዛ አስታውሱ፡፡ ሒሳቡ ለኢትዮጵያውያን ከዚህ ያለፈ ነገር አያስፈልጋቸውም የሚል ንቀት ከአልሆነ እንዲህ ያሉ ሥራዎችን ተጠናቀው መከፈታቸውን ዜና ከመናገር ያለፈ ያን ያህል ባልተዘፈነላቸውም ነበር፡፡ ራዕያችንን እንዲህ አኮስሰው እንደ ሕጻን ልጅ  መጫወቻ ነገር በመስጠት እንድናደንቅ ያደርጋሉ፡፡ ከነቃን ግን ይገድሉናል፣ ያስሩናል ወይም ከአገር እንድንሰደድ ያደርጋሉ፡፡ በአጠቃለይ አንደም ራዕይ ያለው በአገሪቱ እንዳይኖር በማድረግ እነሱ ብቻ የሚደነቁ ሆነው እንዲኖሩ ነበር ሥራቸው ሁሉ፡፡ ዛሬ ላይ ሕዳሴ የተባለው ግድብም ስንት የህዝብ ገንዘብ ከተደፋበት በኋላ መደራደሪያ ነው፡፡ ግድቡ ሕዝብ ገንዘብ የገፈግፋል የእነሱ ሥራ ምክነያት እየፈጠሩ ግድብ ለመጎብኘት በሚል በእኛ ብር ይጨፍሩበታል፡፡ ከአንጀትማ ቢሆን ግድቡ ዛሬ ላይ አልቆ ነበር፡፡ የሆነው ሁሉ ግን …. መለስ ሲሞት አዲስ እንድናመለከው አዲስ ፕሮፓጋንዳ ጀመሩበን፡፡ የመለስ ራዕይ፣ የመለስ ሌጋሲ፣ ምናምን በሚል አዲስ ጆሮ ጭው የሚያደርግ ፕሮፓጋንዳ፡፡ ታች ቀበሌ ሳይቀር መለስን ከአላመለካችሁ የሚል ማስጠንቀቂያ ተላለፈ ሁሏም  እንዳቅሟ መለስን እንደ አምላክ የምትዘክርበትን ትንሽ ጓሮም ቢኆን የመለስ ፓርክ ብላ መዘክር አኖረች፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ዘርዘር ለማረግ የፈለኩት ወያኔና አባሮቿ ማለት  ምን ማለት እንደሆኑ በዚህኛው ምልኩም እንድታስተውሉት እንጂ ዛሬ ላይ ሴራቸው ፈጦ ወጥቷል

ሰሞኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ፓርላማ ሥብሰባ ሰረዘ ተብሎ ብዙ ስናወራ ነበር፡፡ አሁንም እናስተውል ዛሬ ላይ ኦፒዲዮ ሆነ በዐዴን ወደው ሳይሆን በግዳቸው ከሕዝብ ዘንድ መቆም አለባቸው፡፡ በቀደም በፓርላማ ስብሰባ መሰረዝ ያረጉት ከሚጠበቅባቸውም በጣም ጥቂቱን ነው፡፡ አይተን ስለማናውቅ ልናደንቃቸው አይገባም፡፡ ከአሁን በኋላ ደግሞ መብታቸውን ነው ሕዝብ ትኩረት ሰጥቶ እየተባበራቸው ያለው ውስጣቸው የያዙትንም ቢይዙ በተግባር የሚሰሩት መልካም እስከሆነ ጊዜ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከአሁን በኋላ አንዲት ቦታ ቢሰናከሉ አደጋው ለራሳቸው ነው፡፡ እርግጥ ነው አሁንም የሆነ ቦታ ድረስ ህዝቡን በመምሰል ሕዝቡ አመኔታ ሙሉ በሙሉ ከጣለብን በኋላ የሴራ ቀለበታችን ውስጥ እናስገባውና ሸርተት ብለን ወደነበርንበት እንመለሳለን ብለው አስበው ሊሆን ይችላል፡፡ የለማና የገዱ ቡድን አንድ ነገር አምጥቷል ቢያንስ ብሕዝቦች መካክል መቀራረቡ በተለይም በአማራና ኦሮሞ መካከል መቀራረቡ የሚኖረውን ጠቀሜታ ሕዝቡ እንዲረዳውና በይፋም ይሄንኑ መቀራረብ በተግባር በሚታዩ ኩነታት እየቀየረ መሆኑ፡፡ ሁላችንም ቁልፍ ጉዳያችን እዚህ ጋር ነው መሆን ያለበት፡፡ በሕዝቦች መከፋፈል ምክነያት ምን ያህል እየተጎዳን እንደሆነ ተገንዝበን የተጀመረውን ወደፊት ማስቀጠል አዲስ ሀሳብና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ወደ አንድነትና ሕብረት የሚያመጣ መንፈስ እንዲጎለብት ማድረግ፡፡ ያኔ ኢትዮጵያውያንን የሚመነዝር ሴራ የሚያቆም ኃይል አይኖርም፡፡

ዛሬ አባ ዶላ በነበረበት ሊቆይ መስማማቱ ትልቅ ጉዳይ አድርገን አላስፈላጊ ጊዜ መስጠት የለብንም፡፡ ነገ ለማና ገዱም ተመሳሳይ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አባ ዱላ ከሕዝብ ይልቅ የቡድኑ ጉዳይ እንደሚበልጥበት ከፈለገ ምርጫው ነው፡፡ የእኛ ትኩረት በነዱት መነዳት አይሁን፡፡ አሁን የለማና ገዱን ቡድን ለእኛ እስከጠቀመን ጊዜ ድረስ እንጠቀምበታለን፡፡ በዚሁ እሳቤ ከወዲሁ አንድ ቀን ሊንሸራተት እንደሚችል ተገንዝበን በኋላ ቢንሸራተትም እንኳን  የጠበቅነው ስለሆነ ብዙም መደናገር አይፈጥርብንም፡፡ አንድ ቀን የተጠራቀም መደናገር ለመፍጠር እየሰሩ እንደሆነ እየጠረጠርናቸው በእኛ መስመር ውስጥ እስካሉ ድረስ እንጠቀምባቸው ነው መልዕክቴ፡፡ በዚህ እሳቤ ለዘለቄታውም ከሕዝብ ጎን ከቆሞ እሰዬው ወደፊትም ሕዝብ እንደውለታቸው አክብሮ ያኖራቸዋል ከተንሸራተቱም ድሮም አንትን አምኜ ሳይሆን ልጠቀምብህ ነው ብለን ከእኛ ሰልፍ አውጥተን ጥለናቸው እኛ ወደፊት እንቀጥላለን፡፡  እነ ለማ ዛሬ ትልቅ ጉልበት እያላቸው የጠበቅንውን ያህል እየሄዱ አደለም፡፡ ሆኖም ጥንቃቄም እያደረጉ ሊሆን ይችላል፡፡ ቢያንስ ግን አሁን ላይ የሽብር ሕግ ወጥቶ በሴረኞች የታሰሩ የፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞችና ደጋፊዎቻቸው አለምንም ቅድመሁኔታ አስፈላጊው ካሳ ተከፍሎአቸው እንዲፈቱና  አላግባብ እንዲታሰሩ በአደረጉ ቡድኖችም ይሁን ግለሰቦች የሚጠየቁበትን ሊያስቡ ይገባል፡፡ ቀጥሎ የኦሮሚያ ባለስልጣናት እንደመከላከያ ምስክር ተጠርተዋል፡፡ እዛም ላይ በሚናገሩት ገና ብዙዎቹን እናያለን፡፡ ልብ በሉ ሲጀምር ከየክልሉ በሽብርተኝነት ሥም የተያዙ ሰለባዎች ከክልሉ አሳልፎ ለሌላ መስጠት በራሱ ወንጀል ነው፡፡ ፌደራሊዝም ከተባለ ይሄው ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የሚመጣ ሕግም በሉት ሥልጣን ወንጀለኛ ነበር የሚሆነው፡፡ ከአማራው ክልል ኢትዮጵያዊነትን በይፋ በማወጃቸውና ኢትዮጵያውያንን ወደ አንድነት ራዕይ የጋበዙትን እነ ንግስትን አሸባሪ ብለው ከጎንደር ሲያፍሱ አማራ ክልል ተብዬው የት እንደነበር ሊጠየቅ በተገባው፡፡ እስካሁን የማዕከላዊው ገዳይና አሳሪ ቡድን ወኪል እንጂ እንደተለየ የምናያቸው የሰሩት ብዙም የለም፡፡ የሰሞኑ የጉደና ለማ ቡድን ሕዝብን ከሕዝብ ማቀራረቡም ጅምር እንጂ ገና ነው፡፡ ከአሁን በኋላ ደግሞ  እናያለን፡፡ በየክልላቸው ምን ያህል ዜጎች ለወያኔ ገዳይ ቡድን እንደሚሰጡና እነደማይሰጡ፡፡

ሌላው ውዥንብራችን ተቃዋሚዎች ላይ ያለን አመለካከት ነው፡፡ እስካሁን በምናየው ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ አስቦ የመጣ ተቃዋሚ ቡድን ለማግኘት አልቻልነም፡፡ ያለምክነያት እየደጉ ያለምክነያት የሚቃወሙ በፍጹም ዛሬ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የሚፈልጓቸው አደሉም፡፡ አብዛኞቹ ተቃዋሚዎችም በ60ዎች ጭንቅላቶች ስለተመሰረቱ ዛሬም ድረስ ያው ስንዳክርበት ከሰነበትነው የጥፋት አስተሳሰብ ሳይላቀቁ ነው የኢትዮጵያ አሳቢና ፍትህ አስፋኝ የሆኑት፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ በብሔር አስተሳሰብ የሚመጣ አማራጭ አትፈልግም፡፡ ሰሞኑን አንዱ ትኩረት አግኝቶ መነጋገሪያ የሆነው ቻርተር እናረቃለን ብለው የተነሱት ራሳቸውን ንቅናቄ ብለው በሚጠሩ የብድን ስብስብ ነው፡፡ እንደእውነቱ እኔን ገርሞኛል፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ በተመሳሳይ የኦሮሞ አክቲቪስት ነን ብለው የተነሱ ቻርተር በሚል ውዥንብር እንደፈጠሩ እናስታውሳለን፡፡ አሁን ደግሞ እነዚህ፡፡ አላማቸው ግን እውን ምንድነው? ለመሆኑ ዛሬ ቻርተር እናረቃለን የሚሉ ራሳቸው ከወያኔ በምን ያህል የተሻለ አስተሳሰብ ውስጥ ናቸው? አንዳነዶቹም ከወያኔ ጋር አገርንና ሕዝብን በመበታተን ቁልፍ ሚና የነበራቸው ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ የዘረኝነትና ጥላቻ ፖለቲካ በይፋ በተወገዘበት ዘመን ራሱን ግንቦት 7 ብሎ ያቋቋመውን እንኳን ስናይ ያው ሌሎቹ እንደሚሉት ዋነኛ ጉዳዩ የብሄር ጉዳይ ነው፡፡ ላዩ ግን በአንድነት ተከፍኗል፡፡ አማራና ትግሬ ለዘመናት ሲገዙ ኖሩ አሁን ደግሞ ተራው ለኦሮሞና ለደቡብ የሚል አስተሳሰብ ያለበት ቡድን በምን መስፈርት ነው ከዘር ነጻ ሆኖ ኢትዮጵያዊ የሚሆነው፡፡ ኦሮሞን ማካተት የተፈለገው ለገበያ እንጂ ድርጅቱ ጭርሱንም ከኦሮሞ ጋር ግንኙነትም ፍቅርም የለውም፡፡ እንዲህ ባለ ቀመር ወደ ሥልጣን የሚደረግን ሕልም እዛው ባለበት ማምከን ግዴታችን ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በብዙ አማራ በሆኑ ሰዎች የሚቀርብበት በትክክለም የተንኮል ቀመር አንደሆነ የሚታሰበው ይሄው ግንቦት 7 የተባለው በፓርላማው ከአንድ በላይ ቋንቋ የሚናገር ይላል፡፡ በአለው እውነት ብዙዎች አማርኛና የተወለዱበትን ቋንቋ ስለሚችሉ አይመለከታቸውም ግን የአገሪቱ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው የአፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ የሆነው የአማራ የተባለው ሕዝብ ግን በግ7 ቀመር የመወከል መብት የለውም፡፡ ምን ያለብት ዝላይ አይችልም ሆነና ነገሩ ያችንው የውስጥ መርዝን ለይምሰል እንኳን መደበቅ አልተቻለም፡፡ ልብ በሉ ግ7 የተመሰረተው በ1960ዎቹ ሳይሆን ከ10 ዓመት ወዲህ የመጣ ነው፡፡ ሰዎቹ ግን የ60ዎቹ ናቸው፡፡ ደጋፊዎችም በጭፍን ከመደገፍ በችፍንም ከመቃወም ይልቅ ምክነያታዊ እንሁን፡፡ የእኔ ብሔር ድርጅት ወይም እኔ ብሔር በበላይነት የሚሳተፉበት ድርጅት በሚል መደገፍ የትም አያደርሰን፡፡

ትኩረት አሁን አነሰም በዛም አዋጭው የገዱና ለማ ቡድን ነው፡፡ በይሆን የገዱና ለማ ቡድን ውልፍት እንዳይል በቁጥጥር ሥር አውሎ መጠቀሚያ ማድረግ ነው፡፡ ተሳክቶ እነ መረራና በቀለ ከእስር ቢፈቱ ዛሬ ላይ ትልቅ ጉልበት የሚሆኑበት እድል ይኖራል፡፡ ጥረታችንም ይሄው ነው መሆን ያለበት፡፡ ለወያኔና አጋሮቿ ምንም አይነት እድል መስጠት አያስፈልግም፡፡ የለማና ገዱ ቡድን ለሕዝብ የሚኖረውን አመኔታ ከሚያጠናክርባቸው አንዱም በእስር የሚገኙ ወገኖችን በይፋ እንዲለቀቁ ማድረግን ሲጀምር ነው፡፡ ሌላው በወያኔ የሥለላ መረብ መሰለል ሳይሆን የወያኔን የሥለላ መረብን ጨምሮ ወያኔዎችን ራሳቸውን በልዩ የስለላ መረብ ውስጥ ማጥመድ ነው፡፡ እንደ አስፈላጊነቱም እርምቻ መውሰድ፡፡ከወያኔ ትግሬ ውጭ ከሆኑ መከላከያና የየክልሉ ፖሊሶችም አንዱ ሥራቸው ወያኔንና የሥለላ መረቧን ኢላማ ያደረገ እንቅስቃሴ ማረግ ነው፡፡  እንደ ድሮው እሰለላለሁ ማለት ሳይሆን ራስ ሰላይ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ይህን ሁሉ ሕዝብ ይዞ ነገሮች በአጭር ጊዘይ የማይሳኩበት ምክነያት አይኖርም፡፡ ለማይረቡ ጎዳዮች ራሳችንን አናባክን፡፡ ትኩረታችን በአንድ አቅጣጫ ይሁን፡፡ ሁሉም ሊያውቀው የሚገባ ጩኸታቸው እየተሰማ ያለው በአብዛኛው የተንኮለኞች ነው፡፡  ከእነዚህ ተጠንቅቀን አሁን በነለማና ገዱ እየተፈጠረ ያለውን አጋጣሚ ወደ ፍጻሜ ለማድረስ መፍጠን ነው፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይታደግ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.