ክፍል – አምስት፤ አብይ ኬኛ! ለቅኖች ብቻ።  አብይ ክስተት ነው ለመቅድመ – ጠፈር   (ሥርጉተ ሥላሴ )

ክፍል – አምስት፤ አብይ ኬኛ! ለቅኖች ብቻ።

 አብይ ክስተት ነው ለመቅድመ – ጠፈር 

      ሳይንቲስቷ ለኢትዮጵያም!

 ከሥርጉተ ሥላሴ 01.01.2018 (ከአደብማዋ ሲዊዘርላንድ።)

„የሰው ልጅ መንገድን ያዘጋጃል፤ እግዚአብሄር ግን አካሄዱን ያቃናለታል።“ (ምሳሌ ምዕራፍ ፲፮ ቁጥር ፱)

„ፍቅር በማካፈል ሰላምና ፍቅራችን በዝቶልን መኖርን እንፈልጋለን። እናንተም እንደ ኦሮሞ ህዝብ ለጋሽ ህዝብ ስለሆናችሁ ብር ብቻ ሳይሆን ሳቃችሁን እና ፍቅራችሁን እንድትልግሱን እንጠይቃለን።“ (ዶር. አብይ አህመድ።) „እንጠይቃለን?“ ይገርማል የትህትናው ርስት ዕሴት አዱኛው የልብ ነው፤

 • ቀኒት ቀን ወጣላት።

አንዲህና እንዲያ ስትባትል ኗራ

ተለቅልቃ በነጭ በጋራ ተራራ

ተመርምራ ሳታውቅ በዕውቀት ተፈርፍራ

ተጠቅልላ ነበር ክስተቷን ተወራ።

ስለተመስጌንም ዛሬ እንዲህ ስገራ

በተስፋ ብርሃና ነባቢት ሲደራ

ዋልድባ ቦረና በአብይ አርጎ በራ

ጉማጉም ተገፎ ይሄው ሆነ ብራ!

 • አለኝ።

እንሆ ሙሉ ወርዴን በመቀነት አደግድጌ ለጥ ብዬ አጅ ነሳሁ ለቤተ – መንግሥቱ ጋዜጠኛ ለማስረሻ አለሙ። ስለምን? ትንሳኤን ይዞ በአዲስ ዓመት በድል ኮሮጆ አንቀጻትን ሊያሰቆጠርኝ ስንቅ ስለቋጠረልኝ። ለዛውም በርህሩህ ልቦና እና በኮስታራ ሃሞት፤ እኔንም አማራውን ለዛውም ጎንደሬዋን ሊያቅፈኝ፤ ሊደግፈኝ አለሽ ብሎ ዕውቅና ሊያሳፍሰኝ በተስፋ አሹልኮ መፈክር ሊያረገኝ ስለሆነ።

 • ቢከፈት።

ወንድም ጋዜጠኛ ማሰረሻ አለሙ አንተ ባትኖር በውስጤ ክስተት ገፋ አድርጌ አልሄድበትም ነበር። ስለ አቶ ለማ መገርሳ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ስጽፍ ብዙ አልተጻፈላቸውም፤ አልተነገረላቸውም እንጂ ከጎናቸው ዶር. አብይ አህመድ መኖራቸውን እሰቡት በማለት ለበስ አድርጌ ነበር ያለፍኩት። ካሰኘህ ሙግቱን ግን ተአባቶቼ፤ ተጥንተ – ተጠዋቱ  በተጠዬቅ ደሜ ተኑረንበታል። ተንጠባጣቢ ውራጅ ሳይፈልግ በነጠረው ንጥሩ ሙግቱ ሆነ መርታቱ ተዚህም አለ። እንዲህ የተከደነው ሲሳይ ተከፍቶ ይገለጥ መዝገቡ ይነበብ ተባለለት፤ እልሃለሁ አቶ ወንድም የቤተ- መንግሥቱ ሊጋባ። ከቶ „ወንድም“ ማለት ካለደረጃዬ ተንጠራራሁ ይሆን? እንደ መዳፈርስ ትቆጥርብኝ ይሆን፤ ከሆነ ለጥ ብዬ ይቅርታ እላለሁ … ነገ መግቢያ የለኝም እና፤ የዜግነት ርቦና ሲሶ … እያመሰን ተዚህም። ህም።

አዬህ 40 ዓመት ሙሉ ዜግነትን መሰረት ያደረገ የመንፈስ የውሃ ልክ ውቅር አልነበረንም። እርሾ አልቦሽ ነበር። በደርግ ጊዜ ጨቋኝና ተጨቋኝ የሚል ነበር። ጨቋኞች እኛ ነን የሚሉ አማራዎች ሳሉት ባለ ሁለት አፉን ማረጃውን – ለራሳቸው። አሁን ደግሞ ጨቋኙ የአማራ ብሄር እሱን በማጥፋት ነው፤  አሁንም ከዛ መሠረተ ሃሳብ ተነስቶ አንድ አናሳ ብሄረሰብ ዘለግ አድርጎ ሌሎችን በአጃቢነት አሰልፎ ተነሳ፤ ወያኔም ዲሞክራሲ አብዮት በጎሳ ዶክተሪን ነው፤ ደርግም ያራምደው የነበረው በመደብ ላይ አንቱ የሆነ ዴሞክራሲያዊ አብዮት። ልዩነቱ ይሄኛው ትግራዊ ዜግነትን ይዞ አሸናፊ አድርጎ መውጣት፤ በሂደቱ ሌሎችንም አቅም እያሳጣ እስከ አስኬደው መንገድ ድረስ መጓዝ፤ ካላዋጣውም ወደ ተነሳበት ተመልሶ የታላቋ ትግራይን ሪፕብሊክ መመሰረት። ይህን ለማድረግ „ኢትዮጵያ“ እያለ የሚነስተውን አማራን ጥርግ አደርጎ ማጽዳት። ዛሬ ካለንበት ደረስን።

 • የአደራ ማህደር።

ለእኔ ውጪ ሐገር ሁለት ተቋማት ብቻ ከዚህ የወጡ ናቸው። ማለት ዜግንነትን መሰረት ያደረጉ ለናሙና የሚጠቀሱ።  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ስደተኛው ቅዱስ ሲኖዶስ እና የስሜን አሜሪካ ስፖርት ድርጅት። ታስታውሳለህ አይደል? የዘንድሮ የስሜን አሜሪካ የስፖርት ፌስታ ላይ የብዕሩን ለዛ የምወድለት የህግ ባለሙያው አቶ ተክለሚኬኤል አበበ እንደ እብድ ነበር ያደረገው። በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ማለት ሆነ በጠቢቡ ቴወድሮስ „ኢትዮጵያ እና  በአጤ ቴወድሮስ የጎንደር የግጥም ስንኛት።“ ወልድያ በጥጋባቸው የተጋሩ ኮበሌዎች በፈጠሩት ችግር የመቀሌ ወጣቶች ምሽቱን ቀውጢ ሲያደርጉት፤ አዲግራት ላይ ዩንቨርስቲውና ማህበረሱ አደራውን በልቶ ታሪክ ይቅር የማይለው ግድፈት ውስጥ ሲጨመሩ፤ ትዝ ያለኝ ልጅ ተክሌም አጋጣሚውን ቢያገኝ ጠቢቡን ቴዲን ሆነ ተከታዮችን ምን ሊያደርግ ይችል ይሆን ያሰኝም ነበር። ልጅ ተክሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ በሚመለከት በ2013 የጎንደሬዎች „ማህበር“ አድርጎ በዘለፋ ነበር የፃፈው። ግን አባቶቻችን ባለፈው ዓመት በነበረው የሃሳብ ጉስጉስ ዘው አሉን? አላሉም። የእነሱ ተልዕኮ የእግዚአብሄርን የሰማዬ መንግሥት ህግጋት ማስፈጸም ነው። ስለሆነም ልጅ ተክሌ የተነሳባት የጥላቻ መንፈሱ መቅኖ አጥቶ ቀረ። ይህ የአደባባይ ሚስጢር ነው። አባቶቼ ዶግማቸው የሰማይ እንጂ ምድራዊ ሆኖ በገሃዱ ዓለም እንደምንተራመሰው የሃሳብ ልቃቂት በዝብርቅነት የሚዘፈቁ አይደሉም። የእኔን ሃሳብ ይዘው ባለመነሳታቸው፤ ያን ሃሳብ ወግነው የተሰጣቸውን ሰማያዊ ጸጋ ባለመዳፈራቸው እነሱን በጠራ ሰማይ ላይ የሚያበሩ ክዋክብት ሆነው እንዳያቸው አድርጎኛል። ይሄ ነው ቅድስና። ይሄ ነው መንፈሳዊነት። ይሄ ነው የተዋህዶ ሚስጢር ድንበር አልቦሽ፤ ወሰን አልቦሽ መክሊትን በትጋት መከወን ማለት። ስለዚህም ነው ዛሬ በሁለተኝነት እነሱን ያከልኩት። ዝንፍ አላሉም። በፍጹም። በዚህ ጽናታቸው እንዲቀጥሉም መንፈስ ቅዱስ ይርዳልኝ። አሜን! እንደ ገሃዱ ዓለም ሰወች እንደ እኛ እንዲሆኑ ፈቃዴ አይደለም እና። ምድራዊ ቤት ምናቸውም አይደለም? ተመስገን!

እነኝህ አካላት ውጪ ሐገር ሆነው ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ዜግነት አጥፍቶ ቢቻል ትግራዊነትን ባይቻል ደግሞ „ድህነትን“ ዜግነቴ ነው ብሎ እንደ ተነሳው ወጣት ጦማሪ በፍቃዱ ሀይሉ ማድረግ ነበር። ተሳከቶለትማል። ውሉ ጠፍቶ ድክረቱም ይሄው ነው። ስጋት፤ ፍርሃት ተናኝቷል። ነገር ግን ኢትዮጵያ አምላክ አላት እና አንድ ነብይ አስነሳ አብይ የሚባል። የመጀመሪያው ተቋም በ40 ዓመቱ የኢትዮጵያዊነት ዜግነት የጨለማ ዘመን፤ ዜግነትን ማዕከል አድርጎ የተነሳ ህላዊነት። ልቅናው ከዛሬ ላይ የተነሳ አይደለም ከመነሻው የተነሳ ነው። እያንዳንዷ ጥቃቅን ነገር በትርጉሙ ውስጥ ቤተኛ ናት እንኳንስ ኢትዮጵያዊው ሰው፤ ኢትዮጵያዊው ጫካ፤ ዱር ገደል፤ ሸለቆ፤ አየር፤ ገዳማት፤ ቅርሳት ዜጋ ነው ለዶር አብይ አህመድ። ማዕከሉ ሰው፤ ሩጫው ሰውን ሰው በማድረግ ኢትዮጵያን አኩል ማድረግ – ከሰለጠኑት። እኩል ለማድረግ ከስንት ሺህ ዓመታት በፊት የሥነ – ክዋክብት፤ የሥነ ቀን አቆጣጠር የጠፈር ጥበብ ተማራማሪዋን፤ ሞጋች ሳይንቲስነቷን፤ ፈላስማዋን ኢትዮጵያን ውስጥ በማድረግ ነው ዶር. አብይ አህመድ ፈለግ ህይወት የሆኑት። ወደ ኦህዲድ ዶር አብይ አህመድ ሲሸጋገሩ  የተሰጣቸውን ሰማያዊ ጥሪ በመያዝ ስንቁን አዳጉሰው፤ አደራጅተው ነው። በአጭር ጊዜ ነው የተሳካው። ልክ እንደ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መሠረት። የእልፎች የመንፈስን የደም ማዘዣ ጣቢያ ማግኘት ቻሉ።

አግልሎ፤ ጠልቶ፤ ወግኖ የተነሳውን መንፈስ ሁሉ ተጸዬፉት። ያን ፈራጅ ለይ ስንኩል መንፈስ ማድመጥን ነፈጉት። አንተ እዬተዋጋህ ያለኸው በአምሳሉ ለሌላ 27 ዓመት በማግገለ ላይ ቁጭ በሉ እያልከን ነው የምትሰብከው። አትችልም። „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ የእንደ ገና መወለድ ጽኑሱ ከታማኙ ቤት መምህራዊ የማሳመን አቅም መርጌታነትን ከዶር አብይ መንፈስ ፈቅዶ መስተዋድድ በመሆኑ ነው።

„ሰው ከሌለው በደመቀው ከተማ በቀትር ብትጓዝ ይጨለምሃል፤ ትፈራልህ“

ይልሃል የአብይ መንፈስ። አንተ የምትከተለው የተማረና ያልተማረ፤ ሴትና ወንድ፤ አማራና ትግሬን አግለህ ነው እሱ ደግሞ ይዟት የመጣት ሊቅ „ሳይንቲስት ለመሆን ሰው መሆን ብቻ ይበቃል“ የምትል ነፍስን ነው።

ራሳችን ስንጠይቅ ስንመለከት ምን ይታዬናል? ድመት ሆነን አንበሳ ነው የሚታዬን? ወይንስ አንበሳ ሆነን ድመት ይታዬናል? ወይንስ ሰው ሆነን ሰው ይታዬናል፤ ስለሳይንስ ስናወራ፤ ሳይንቲስት ለመሆን ሰው ብቻ  መሆን በቂ ነው።“ የአብይ ክስተታዊ መንፈስ እንዲህ ዓይነቶችን ሊቃናተ አንስትን ለማድመጥ ይፈቅዳል። የእናንተው ለብዕር ምርት እንኳን አስቁሙ፤ እገዱ፤ እንዴት እንዲህ ዓይነት ጹሑፍ ታወጣላችሁ ወዘተ ወዘተ … ለዛውም በሞፈር ዘመት ሄዳችሁ … ሁሉንም መጠቅላል ትሻላችሁ። ከቤተኞቻችሁ ማን ድርሽ ሲል። በሰው ቤትም አራጊ ፈጣሪ መሆንን ታልማላችሁ።

የዶር. አብይ አህመድ የህሊና ምናባዊ ጉዞ እና የዛሬ 40 ዓመት ከቆማችሁበት ፈቅ ለማለት ላልተፈቀዳችሁ የግራ አራማጆች ልዩነታችሁ የዛሬ 200 ዓመትም አይገናኝም። ድልድዩ ተሰብሯል። የማዝንው አንተ ከዛ የተረፍክ የዛሬው ትውልድ ሆነህ በዛ ውስጥ መሆንህ ነው። እኔ ደግሞ ስላዬሁት፤ ስለሰለጠንኩበት፤ ስለመረመርኩት፤ ስለሰራሁበት፤ በተሰበረ ድልድይ ወይንም ባለቀ ባትሪ ውስጥ እዬዳክርክ መሆንህ ማሳዬት ትውልዳዊ ድርሻዬ ነው። ዝም የምለው የነፃነቱ ትግሉን ሞራል ለመጠበቅ እንጂ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በሻብያ ልብ ተገጥሞለት ሂደቱን የጀመረው በአማተር ጫካዊ ትውና ነው። አሁን ዘመን ተገልብጦ በእውቀት ላይ በተመሰረት ጊዜ እዬጠበቀ በሚፈነዳ አስደንጋጭ ቦንብ፤ በሰለጠነ ብልጣዊ ዘዴ ያልተከለሰ ሂደቱን እያስተዋልን ነው። ከዚህ አፈንግጦ ብርሃን ጨረሯን ስትልክ ግርዶሽ ያሰኛል ካል ግን በልክህ፣ አቅምህን አውቀህ ትራመድ ዘንድ ይህ የብዕር ቦንብ ይላክልሃል፤ አልሆነም ካልክ ደግሞ በሰነድ፤ በድምጽ የተደገፉ አመክንዮችን ይዘን እንሞግትሃለን፤ አዬህ በችሮታ የሚገኝ ዜግነት የለም። ዛሬ ዜግነቴን ከትግራይ ሥርዕዎ መንግስት እለምናለሁ፤ ነገ ደግሞ በበታችን ስሜት ከሰመጠ፤ ሁሉንም ሥልጣን ከውኖ በአንድ የሃሳብ የበላይነት ባሰላ እጅግ አናሳ ቁጥር ካለው ብሄረሰብ ተንበርክኬ እኔም መለመን፤ ወጣቶቼም በዛ ሥር ወድቀው እንዲማቅቁ ስለማልፈቅድ እሞግተሃለሁ።

ለዚህ እኮ ነው ዶር. አበባ ፈቃደን የምትፈሯቸው። ባለፈው ከአቶ እያሱ አለማዬሁን ቃለ ምልስ አድርጋችኋዋል፤ ዶር ነገዴ ጎበዜን ግን አላደረጋችሁም። ለዛውም መንፈሳቸው ቤተኛ ነው የሚልም ሰምቻለሁ፤ የሆነ ሆኖ ዶር. አሰፋ ነጋሽን ግን ስለምን አትሞግቱትም፤ ለምን? አቶ እያሱ አለማዬሁ ጉራጌ፤ ዶር ነገዴ ጎበዜ እና ዶር. አሰፋ ነጋሽ አማራ ስለሆኑ ብቻ። ለዚህ ሌላ ሎጅክ ላምጣ ብትል አሁንም እሞግትሃለሁ ፋክት ከእጄ አለና። አዬህ አሁን እኔ የምጽፈው ለሳተናው ሙሉውን ተመችቶት አይመስለህ። የማይመቸው አለ፤ ግን ዴሞክራሲ የማይመችህንም ለማድመጥ መፍቀድ ነው። ዴሞክራሲ ሰሌዳ ላይ መጻፍ አይደለም። ከራስህ ነው የሚጀመረው። ሌላው ጋዜጠኛ ሰውን ማዕከል፤ እውነትን መሪህ ብታዳርግ ይህ የሚያቅት አስፈሪ አይሆንም ነበር። እማንታዘብ ይምስለሃልን? የማናይ ይመስልሃልን? የማናስተውል ይመስልሃልን? ሦስቱንም በአካል እኔ አውቃቸዋለሁ። ለሚያምኑበት ዓላማ አቅማቸው አይበላለጥም። በጽናታቸው ውስጥ ሙላት በመጣ ቁጥር ዘንበል ቀና የሚሉም አይደሉም። እውነቱን ብነግርህ ድፍረት ያንሳችኋዋል። ደፋሮች ብትሆኑማ እንደ ጋዜጠኛና ሰብዕዊ መብት ተሟጋቹ  እንደ ሙሉቀን ተስፋው እንደ አደረገው ጦማሪ በፈቃዱ ሀይሉን መድረኩን ከፍታችሁ በትህትና ትሞግቱ ነበር። ድፈረት አይሸመት በሶሻሊዝም ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የዛር አዟሪት። መጫን – መጨፍለቅ – መዳጥ – ማፈን፤ ወያኔ ሃርነትን በመተቸት አምክንዮ ሚዛን ውስጥ መስታውት አልቦሽነቱ ስልስልም ድርቅ የመታውም ለዚህ ነው። በራስ ላይ ምን ጎደለ ጉድፌ ምንድን ነው ማለት ማን ይድፈራት? በነፃነት ሀገር ነፍስ ነፃነት አግኝታ በቅላ ማደግ አትችልም። በዬአመቱ ጉግስ።

ከዚህ እንድትወጡ ባለፈው ዓመት በተከታታይ ጹሐፎችን ጽፌያለሁ። ሃብት የመንፈስ እንጂ የከረባት ወይንም የገበርዲን አይደለም። ዛሬ ምንያህሉ መንፈስ እዬሸሸ፤ እዬቀነሰ፤ ተስፋ እያጣ፤ ጥግ እዬፈለገ ስለመሆኑ „ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው“ ከለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደ ደገፈ ሌላ ማሰረጃ ማቅረብ አይቻልም። በላፈው ዓመት ስጽፍ ዲሞክራቶች መሸነፋቸውን ያወቁት ዘግይተው፤ ከተሸነፉ በኋዋላ ነው ብዬ ሁሉ ነበር። ግን ትቢያ ላይ ያለች ሴትን ማን ያድምጥ? የወረቀታችሁ ማህበርተኛ ስላልሆነች የምታመልኩት ዲግሪም የላትም፤ በዛ ላይ አማራ ጎንደሬ። እንሆ „ሰው የዘራውን ያፍሳል።“ የሰሞኑ ስብሰባዎች የወንበሮች እንጂ የሰው አልነበሩም የሆላንዱንም የሙንሽኑንም ተመልከተው። ለዛውም ሙንሽን ዜግነትን ማዕከሉ ያደረገ የቅኖች፤ የተግባር አንበሶች መንደር ነው። እነሱንም በአካል አውቃቸዋለሁ – የተግባር ሰውነታቸውን እመሰክርላቸዋለሁ። ቦታ ጠፍቶ ተሳታፊ እንዳልተመለሰ፤ ያን ያህል ክፍት ቦታ ሳይ ደንግጫለሁ። ያ ሁሉ የመንፈስ ሃብት በአመራር የስልት፤ የጥበብ፤ የተመክሮ አያያዝ ማነስ ተናዳ …. አዝናለሁ … የሚያሳዝነው ይህ መንገድ አሁንም ያዋጣናል ተብሎ መቀጠሉ ነው። ውጪ ሀገር የአቅም ጥገኝነት ልመና፤ ሀገር ውስጥ የአቅም ጥገኝነት ልመና፤ ለመሆኑ የአንተ፤ እምተኮራበት፤ ደረትህ ነፍተህ በዬዓመቱ በዙር እምትፎክርበት አቅምህ አድራሻው የት ላይ ነው? የሃሳብ የበላይነት ከኖረህ የሰበሰብከውን እያፈሰስከው ሳይሆን እዬጨመርክበት፤ እያሰበልክ ድል ላይ መሆን ነበረበት … በስተቀር „ማሰሪያ የሌለው ልጥ“ ነው የሚሆነው … በአቅሙ ውስጥ ሌላ ያልታቀደ ሃሳብ አቅም እያገኘ ሲመጣ አንተን የበጠበጠህ ይሄ ነው። „ወትሮ ነበር እንጂ ….“ አዬህ ያን ያህል የተራራ ያህል ንቀት አያተርፍም። ትዕቢተኛውን ወያኔን እዬታገልን ሌላ ትዕቢት ለመሸከም መታቀድ አይገባም ነበር። በችግር ውስጥ የችግርህን አቃላይ መስመር እንጂ የችግር አጣብቂኝ ማቀድ የተገባ አዋጪ መንገድ አይደለም። ይህ ነው ያልገባህ የወርቅ እንክብል ፍሬ ነገር። ያን ጊዜ ካስተውስከው ትእግስት ሲያልቅ ፍቅር ይሰደዳል ብያለሁ። የወያኔ ሃርነት ትግራይ የሰሞኑ የዝባዝንኬ ድሪቶም ይህንኑ ያዬሁበት። በዛ ውስጥ ፍሬና እንክርዳድን መለዬት የዶክትሬት ማዕረግ ባለድግሪነት አይጠይቅም። ቅንነት ብቻ እንጂ።

 • ክስተት።

ጋዜጠኛ ማስረሻ አለሙ የነገ የ4ኪሎ መንበር ባለሙሉ ሥልጣን፤ ካለ ትንሽ ራፊ ጨርቅ የጠቀጠቃቸው ዶር. አብይ አህመድ የሀረርን ተፈጥሮ ተክነውበታል። መቼስ አይካድ ነገር ሐረር ኢትዮጵያ መሆኗ። ኢትዮጵያም የሐረር፤ ሐረርም የኢትዮጵያ የፍቅር ነፍስ። ስለፍቅር ኢትዮጵያ መምህርነቷ ሥረ – ትውፊት እንዳለው፤ በፍቅርም ተፈጥሮ፤ በፍቅር መርህ አፈጻጸም፤ በፍቅር ዶግማ እናት ኢትዮጵያ አብነቷ ዝልቅ ሰለመሆኗ ዶር. አብይ አህመድ የገለጹበት ትሁታዊ፤ ክብረታዊ፤ ሰናያዊ፤ አትኩሮታዊ፤ እራስን ዝቅ ያደረገ መሳጫዊ ንግግር ለማዕልቲት ማህሌት ትቆም ዘንድ እንዲህ ወደድኩኝ።

አንዱን አቅርበህ አንዱን አርቀህ፤ አንዱን ቤተኛ አድርገህ አንዱን የእንጀራ ልጅ አድረገህ፤ አንዱን ንቀህ ሌላውን አልቀህ፤ ለአንዱ ትውልድ የሥነ – ልቦና ጤንነት ተጨንቀህ እና ተጠብበህ ለሌላው ደግሞ ጠቅጥቀህና አጎሳቁለህ፤ አንዱን የደም ፍርፋሪ  እንጥብጣቢህን አጠራቅመህ አጠጋግተህ ሌላውን ደግሞ በባይተዋርነት ገፍተህ – ገፍትረህ – ገርፈህም ኢትዮጵያ ማለት ከፓስተርነት አያልፍም። አንተ ጋዜጠኛ ማስረሻ አለሙ እራስህ የፖስተር ፍቅረኛ ስለሆንክ በሰውኛ ቋንቋ ባልፈተሽክው፤ ወይንም ባልመረመርከው፤ ወይንም ሂደቱን በጥሞና ልትታደምበት ባልፈቀድከው አግላይ፤ ወጋኝ ፖለቲካ አንደበተ መንበር ላይ ሆነህ „በሰው ቁስል እንጨት“ እንዲሉ ታቆስለናለህ፤ ከዛም ባለዘመኖች፤ ከዚህም „የመላዕክታን ጉባኤ“ የሚሰልቁን፤ እንዲሁም ሥነ – ልቦናችን በዬአመቱ በቤንዚን አርከፍክፈው የሚያነዱት አልበቃ ብሎ። መቼስ አዘኔታ አልፈጠረልህም። እስቲ ትንሽ ብንስቅ ምንህ ይቀነሳል? ደስ ቢለን ተስፋ ብንደርግ፤ ዜግነታችን መለኪያ ሲሆንልን እንይ ብለን ብናስብ ምን ይገድህ ነበር? አለመማር ወንጀል ሆኖ ስታጣጥሉት፤ ስታብጠለጥሉት፤ ወልቃይት መወለድም ውሽክ ማድረጊያ የማቃለያ ቅመም ስታደርጉት የላሊበላን ውቅር ፍልፍል ድንጋይ ውጤት መስህብነት አታስታውሱትም? የአድዋን ድል ትዝ አይላችሁም? ስንቱ?

አዬህ … መሪነት ምንጩ ከንጹህ ልብ ይቀዳል። ርህርሄ ስላልከው ሳይሆን ስትሆንበት አንተነትህን ያስነብባል። ርህራሄ ቤተኛ እና ገረድ ሠርተህ አይደለም። መሪነትን ውስጥህን በውስጣቸው በፍቅር ተሸሙኖ፤ በማህባዉ ጸዳል የፊት ጸዳላቸው ወጋገን በያለንበት የተስፋ ማህጸን እንዲሆኑልን የፈቀደንላቸው ዶር. አብይ አህመድን ገጻቸውን ብቻ ዛሬ ለመነሻ በመረጥኩት ርዕሰ ጉዳይ ላይ እያቸው። „ ዛሬ ታምራላችሁ“ በማለት የሊቀ – ሊቃውነቱን የምርምር፤ የርቀት ምናባዊ ምልሰትና የወደፊት ትልም የሆነውን የልቅና ጉባኤ ሲፈክቱ አስተውለው። „https://www.youtube.com/watch?v=5bzcyojnaMY Science Conference (የሳይንስ ጉባኤ)“

ከልብህ ሆነህ። የሚነግርህ፤ የሚያጫውትህ፤ የሚስብህ ማዕዛና ጣዕማዊ መልዕክት አለው … ዜግነታዊ ሰውኛ አለው። ውስጠህን በፍቅር ጥሪኝ ይደባብሳውል፤ ያበባብለዋል፤ ያቆላምጠዋል፤ መካራው ጠንቶበት ትራስ ውስጥ ተንተርሰኸው እንዳደረ ጨርቅ ኩፍትርትር ያለውን ነፍስ ውስጡን ፈቅዶ ቧ አድርጎ ከፍቶ ፏ እንድትል፤ ስጋት እንዳይኖርብህ፤ ጥርጣሬ እንዳያባዝትህ ዕድሉን በአዲስ ብሥራት ይከፍታል። ግን ይህ የሚታይህ የቅንነት ቤተኛ መሆን ሲቻልህ ብቻ ነው። ለማንፌስቶነት ማህበርተኝነት ሞትም ጉዳያችሁ አይደለም። መጋጋሉን ብቻ ነው የምትፈልጉት። ሥልጣን ወንበር አሁኑኑ! ይህም ድሃ ወገንህን አስፈንጥረህ ሳይሆን የእኔ ሃብት ስትለው። ያለተማረውን ሥጋህን አቅርበህ እንደ ተፈጥሮው ስታጣጥመው፤ ለዛው እንዲስብህ ስትፈቅድለት፤ እንደ አቅሙ ስተቀበለው ነው። አካለ የታመመ፤ በሽተኛ ቢሆን ሥጋህ – ደምህ – ነፍስህ  -መንፈስህ ስለመሆኑ ስታቀፈው፤ ልብሱ ቆሻሻ መሆኑን ሳትጸዬፈው ነው፤ ይህንም ታደልኩበት ስትለው ብቻ ነው። ነገ ድምጹን እኮ ታልማለህ አይደል በቀጥታ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፤ ስለህዝብ አክብሮት ፍቅር እንዲህ ይላሉ ዶር. አብይ አህመድ … እነሆ …

„ወደ ሐረርጌ የመጣነው በአሁኑ ጊዜ ዓለም እያጣች ያለችውን ፍቅር እናንተ ዘንድ በብዛት እያመረታችሁ ስለሆነ እንዳታክፈሉን ብለን ነው። ምክንያቱም ባሁኑ ጊዜ ፍቅር ማጣት የአገር ችግር ስለሆነ። በአለም ሆነ በአገራችን ችግር እንዲፈጠር ምክንያት እዬሆነ ያለ የእርስ በርስ ፍቅር ማጣት በሐረርጌዎች ዘንድ በብዛት እያመረተ ነው። ወደ እኛ እንድታስላልፉልን፤ ኤክስፖርት እንደታደርጉልን እንፈልጋለን። ምክንያቱም እዬበላን ተርበናል። እዬጠጣን ተጠምተናል። ያለውን ፍቅር በመካፈል ሰላምና ፍቅራችን በዝቶልን መኖር እንፈልጋለን። እናንተም እንደ ኦሮሞ ህዝብ ለጋሽ ህዝብ ስለሆናችሁ ብቻ ሳይሆን ሳቀችሁን እና ፍቅራችሁን እንድትለግሱልን እንፈልጋለን።“

https://www.youtube.com/watch?v=rZj7KffGJa8

Dr Abiy Ahmed Called for UNITY in Oromiyaa Oct 18, 2017

ኢትዮጵያ የፍቅር ትምህርት ቤት ናት ነው የሚሉት። ፍቅርን ከእናቴ ጠብቼ ግን አልሆንኩበትም እርቦኛል፤ ጠምቶኛል እና እባካችሁን አጥቡኝ እያሉ ነው። እኔም በ2015 በዚህ ላይ አትኩሮት ያለው መልዕክት ነበር ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የላኩት። ፍቅርን በትምህርት ቤት እንደ ቁጥር፤ እንደ ቋንቋ ትምህርት ልጆች በት/ ቤት መማር አለባቸው ነበር ፕሮጀክቴ፤ በዶር አብይ አህመድ ህሊና ዕውቅና ይሄው አግኝቷል። ያን ጊዜ የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ጸሐፊ መልሱን ሲጽፉልኝ እስኪ ለሀገርሽ መንግሥት አማካሪያቸው ብለውኝ ነበር። ለማን? ለዬትኛው መንግሥቴ? አንድ ቀንጣ ነፍስ ለመንፈሴ ይሄ ነው የምለው አለነበረም። እግዚአብሄር ይመስገን ፍቅር የራበው፤ ፍቅር የጠማው፤ የፍቅር ናፋቂ ለዛውም የፖለቲካ ሊሂቅ ተገኘ በሀገሬ መሬት  በኢትዮጵያ። ስለዚህ ከዚህ በላይ ለዓለም ፈዋሽ መንፈስ አለ አላልም። ህልሜን ለዛውም በሥጋና በደሜ ውስጠት እነሆ አዬሁት። አገኘሁት። ተስፋዬ ተንሰራፋ ትንሳኤ ይሄ እንጂ የኮሮጆ ቁጥር ልመና ደጅ ጥናተኛ አይደለም። ፍቅር በመታመን ማህጸን እንጂ በቃላት ካብ አይሸመትም። ፍቅር የገቡትን ቃል በመፈጸም እንጂ በኪዳኑ ዝግ ስበስባ አይመጣም። ለዛውም እኔን ተጸይፈህኝ?

 • የምርምሩ ምጡቅ ጥበብ የቅኔ ጉባኤ ብርቅ አቀራረብ።

https://www.youtube.com/watch?v=AyY1kbD3MG8

Tech Science TV Program Episode 39

የእኔ ቅኖች አጅግ የምናፍቃችሁ የሐገሬ ማሮች … ይህ የኢትዮጵያዊ ሥነ – ምርምራዊ አመክንዮዊ ጉባኤ ከሰርከኛው፤ ከወትሮኛው ዘዬ በእጅጉ የተለዬ ነበር። ውስጠ – መቅደሱ የታደመበት ሥነ – ጥበብ መጥምቁ ዮሓንስን ተከትሏል። እኔን ያግባባኝ መንገድ የዚህ ጉባኤ የዕልፍኙ ስፋት፤ የግድግዳው የቀለም ጸጥታዊ ስበት፤ የወለሉ ንጽህና ውበትና ማራኪነት፤ የወንበሩ ምቾትና ደልዳላነት፤ የድምጽ ማጉያው ጥራት፤ ድምቀትና ዘመናዊነት አልነበረም። እኔን የማረከኝ ወይንም እኔን ሳብ ያደረገኝ ብልህ ብሂል አለ። ህንፃውማ ተዚህም አለ። አዳራሹም እንዲሁ። ቀለማም ውበቶችም አሉ በአይነት ተዚህ ተሲዊዚዬ። ቤቴም ቤተ መቅደሴም በራሴ የቀለም ውበት ንድፍ የተጠበበች ስለሆነ ከጸጥታዋ ጋር ልኳን ጠብቃ ግን ተናፋቂነቷ ልባዊነት ነው። ስለዚህ ማርኮቴ ሌልኛ ነው። ቀደምቷ ሐገር ኢትዮጵያ የጠፈር ቀደምት ሳይንቲስትነቷ ተባ፤ ኢትዮጵያ ዛሬም አንደ ትናንቱ በጥበብ አውደ ምህርት፤ በልቅና ሠረጋላ የአደራን ዕዳን በአደራ ጥራት ለማሰቀጠል የጉባኤው ባልድርሻ የሆነው ዜግነታዊነት ሳይንስና ቴክኖሎጂ የተነሳበት ዓላማ እና ግቡ፤ የነገ የትውልዱ በኸረ ጭንቀቴ ስለሆነ ድርጁነቱ በመሪነት በህብሬነት መስከኑ ነው ትንፋሼ የሆነው። እርግጥ ዛሬ ዶር አብይ አህመድ ከድርጅቱ ውስጥ የሉም። በነበራቸው አጭር ቆይታ ግን ኢትዮጵያዊ ዜግነትን በጽኑ አለት አማካሉት ለመጀመሪያ ጊዜ ከ27 የእንግልት ዘመን። ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ታቦት ቀረጹለት። ኢትዮጵያዊ ዜግነት መፍሄነቱን በተጋድሎ አበሰሩት። መሰረትን በህሊናቸው ሰንቀው፤ ሃሳብን ዕውን አደረጉት፤ የአባቶቻቸውን አደራ በአደራ አበቀሉት በንጽህና ቅንነት። በሌላ በኩል ይህ ብቃት ታሪካችን ስለሆነ በቅጡና በወጉ የህሊናቸው ለምነት በቅኝት ዘክርን ነገን በውል አናስበው ዘንድ የተስፋ ኪዳናችን ጽንሰት ስለሚያፋፋልን ነው የመረጥኩት። ጥቂት የአትኩሮት አውደ ምህረቶችን ለመነሻነት ባነሳሳስ?

 • ዓላማው ሆነ ግቡ ኢትዮጵያ ከጥንት አስተዛሬ በኢትዮጵያ የመንፈስ ጥሪት ከመነሻው ብቻ የተነሳ መሆኑ ዕጹብ ነው። ኩረጃ የለበትም። ወይንም ቅጂ አይደለም!

የጥብብ ልቅናው አወቃቀር ለመጀመሪያ ጊዜ ታላቅ ብሄራዊ ጉባኤ በቅኔ ውበት፤ በሥነ – ግጥም ነግሦ፤ ውስጥን አናቦ፤ ከተልዕኮው ጋር ተናቦ፤ ከህሊና ተደርሶ – ለህሊና አድርሶ፤ ባንጎል ታስቦ – ተሰልቶ – ተደራጅቶ – ተሰብሎ፤ ሊሂቅንን ከእውነት ከልባዊነት አብቅሎ አህዱን … ክለቱ እያለ ርቱ ሲል እጬጌውን ኢትዮጵያዊነትን በውስጥ ስለወስጥ፤ ስለተስፋ ሆንክን ስለማለት አብሥሮ፤ ችሎት በማሆን ማለሙ ሲሳላ መቸቱ ልዩ ነው፤

https://www.youtube.com/watch?v=wY3b3nsOGJ0&t=129s

Ministry of Science and Technogy(MOST), Leadership and Motivation Program

 • በወንዶች ዓለም ሴቶች ያላቸውን ዕምቅ ሃብት አናይ ዘንድ ዕውቅና ሰጥቶ ለዚህ ስላበቃን፤ የሰማዮዋ ጠሐይ መሬት ላይ ወርዳ ሃብታችን እንደትሆን፤ የእኛ እንድንላት፤ እኛም አለንበት፤ ቤተኛ ነን እንል ዘንድ ለዚህ ስላበቃን የሰማይ ታምር ነው፤ ክብሩ ይስፋ አማኑኤል አባቴ። አሜን!
 • የኢትዮጵያ የሳይንቲስትነት አቅም ጥልቅነት የመነሻውን ቀደምትነት ይህ ጉባኤ ስለ አጰጰሰው፤ ኢትዮጵያዊ ትውፊትን መርጆ ህላዊነቱ እንዲሆን ስለፈቀደ ከገድል በላይ ነው – ለእኔ።

የዶር. አብይ ትርጉም የህሊናቸው ልሳነ – መሬት፤ የነባቢነታቸው ሥናዊ – አምክንዮ፤ ክህሎትን በልቅና፤ ልቅናውን በኪናዊ እኛነት፤ እኛነቱን በነጠረ ማግስታዊነት ባዘቶ፤ ወርቅና ፈትሉን አስማምቶ በምለስት ቃኝቶ አሸምነ። ስለሆነም ሙቀት ፈጥሮ ሙቀት እንዲሆነን ቅኖች ከልባችን ፈቅደን። ስለምን? ነፍስ ፈጥሮ፤ ነፍስ ሆኖ፤ ነፍሳችን ስለመለሰልን – የቅኖችን። መሪትነት በዚህ መስመር ይመጣል ተብሎ ብዙም ባይታሰብ „ጊዜ ገቢረ ለእግዚአብሄር“ እንሆ ሆነ። ተመስገን! ጊዜ ታሪክን ይሠራል።

„ከእርምጃ ወደ ሩጫ አብረን አንሩጥ!“  ነው የሚለው መራሂ ግብሩ ወይንም የማዕዶቱ እልፍኝ ማህንዲስ። ለዚህም ጥልቀታችን በልቦና ሙሉዑነት፤ በደምና በሥጋችን ውስጥ ዘልቀን እናይ ዘንድ ሲፈቅድልን፤ አደብ ገዝተን፤ በተደሞ ሆነን፤ አርምሞን አስብከን ለውስጣችን ውስጣችነን አንተርሰን፤ በሚስጢራችን ረቂቅ ተሰጥዖ መፈረሽ የኛ ፈንታ ነው። የቻላችሁ፤ የወደዳችሁ ሚስጢርነታችን፤ ረቂቅነታችን ስለምን ስለመሆኑ ጊዜ ወስዳችሁ ታዳምጡት ዘንድ በታላቅ ትህትና እጠይቃችኋዋለሁ። ዶር. አብይ አህመድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አቅምን በአቅም አደራጅተው እርግጠኛ የሆነ ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያደረጉትን ጥረት በዚህ ውስጥ ማዬት ይቻላል። የቤት ሥራውን ለእናንተው ለእኔዎቹ ለቅኖቹ እሰጣለሁ። የተወያዮችን መንፈስ በምን ሁኔታ፤ በአክብሮት አንደ ተቃኙትም መጨረሻ ላይ የሰጡትን ጥቅል የማጠቃለያ ሃሳብ፤ በህሊና የቃለ ጉባኤ ጸሐፍትነታቸውን ስተመረምሩት የአዳምጭነታቸውን፤ የአትኩሮታቸውን የማሰብ አቅማቸውን፤ የማወራረስና የማዛማድ ተደሟዊ ጸጋቸውን ማዬት ትችላላችሁ፤ ደጋግማችሁ ስታዳምጡት። ፍሬዘሩን፤ ፍሬ ነገሩን መስህብ ውሉ ይገለጥላችኋዋል። ስለሆነም ዛሬ እኔ በዚህ ዙሪያ ከዶር. አብይ አህመድ ጥቂት ነገር ብቻ አንስቼ በልዕልቴ፤ በመራሂተ በወ/ሮ ጽዮን ተክሎ የመንፈስ ቅድስና ላይ ትንሽ እልና የሚያሰጋኝን ነገር አንስቼ ዕለቱ በርቱ ይከዋናል።

 • „ሳይንቲስት ለመሆን ሰው ብቻ መሆን በቂ ነው።“  ከመራሂተ ወ/ሮ ጽዮን ተክሉ።

ይሄ ነው የዶር. አብይ ጥልቅ ሚስጢር። በወንዶች ዓለም የሴችን አርቆ የማሰብ፤ የማስተዋል፤ የምርምር ማዕክልነት የማዬት፤ ሴቶች በምናብ ተጉዞው ከለምንም የመገናኛ ዘዴ በስሜት ለስሜት ሃዲድ የመዘርጋት ቀያሽ ርቁቅ ተፈጥሯዊ የግንኙነት ብቃት እዳላቸው፤ መጠበብን አስመልክቶ ከውስጣቸው የተቀበሉበትን ምልከታ፤ ለማስረጃነት መሬት ላይ ክንውኑን ማዬት ያስችላል። ሴቶችን ከውስጥ መቀበል አትራፊ ብቻ ሳይሆን፤ ትውልድንም አጽዳቂ ስለመሆኑ ያሉትን በመሆን ቃላቸውን ያከበረቡት መታመንን ያበለጸጉ ብቸኛ ታላቅ ሰው መሆናቸውን ማዬት ያስችላል። ለሴቶች አቅም ዕውቅና መስጠት፤ የሴቶችን የእውቀት ሃይል ማመን። ውስጣቸውን መውደድ። ምናባቸውን ማፍቀር በተጨባጭ ያሰዬናል ይህ የዶር አብይ አህመድ እርምጃ። ስለሆነም ከዶር. አብይ አህመድ መንፈስ ውስጥ የእኩልነታችን፤ የአቅማችን፤ የብቃታችን፤ የማድረግ ተስጦዖችን፤ የመፍትሄ አመንጭነታችን ትንሳኤ እንዳለንም ቅኖች በድፈርት እንዲህ እንናገራዋለን። እንሰብከዋለን። የሴቶች የሰማይ መንፈሳዊ ባለጸግነት በታማኝነት በማብቀል የመጀመሪያው ሐዋርያችን ናቸው እና የእኛ ዶር. አብይ አህመድ። በህልም አለም መኖር ለገለማን፤ ላንገሸገሸን ግዕፋን ሴቶች አብይ ብሌናች! አብይ ህሊናችን! አብይ ክስተታችን ነው! አብይ አዲስ ቀናችን ነው! አብይ አዲስ ዘመናችን ነው! አብይ አውራችን ነው! ተመስገን!

የእኔ የተግባር ልዕልት ወ/ሮ ጽዮን ተክሉ ተወዳጅ የሚያደርግ የአቀረረብ ልቅና፤ የልሳን ጣዕም፤ የሰብዕና ክህሎት፤  የአገላለጽ ውበት፤ የድምጽ ቅኔዊ ቃና ዜማዊ ምትሃቱ ማረከኝ እና ሙሉውን እንዲህ አቀረብኩት። ስታዮዋቸው ደግሞ ተመስገን ትላለችሁ። እርጋታቸው አንዳች ሳቢ ነገር አለው። አዎን በርግጥም ሙሉዑ አቅም ሀገር ቤት አለ። ትውስት የማይፈልግ። እንዲህም ይላሉ መራሂተ ቅኔ ወ/ሮ ፅዮን ተክሉ …

„ራስን መገምገም በምን አንጻር ማደረግ አለባችሁ፤ በእነዚህ ኢንተሌጄንስ ውስጥ እራሳችሁን የቱ ጋ ታገኙት አላችሁ?  ማናችንም አድገን አልጨረስንም! የትዮኞቻችንም ፉሊ ዴቮሎፕ አላደርግንም! ሁልጊዜ ፐርሰናል ዴቨሎፕመንት የሚቀጥል ነገር ነው! ስለዚህ እኔ ሳዬው የትኛው ነው ሚሲንግ ፒስ ከእኔ ውስጥ የጠፋው ነገር ምንድን ነው? ከባጠቃላይ ሲብል ሰርቨንት ውስጥ ምንድን ነው የጠፋው? ከኢትዮጵያኖች ምን የጎደለ ነገር አለ? አሁን ወደ ራሳችን እንድንመለከት እፈልጋለሁ፤ አስተማሪዎች ነን፤ ለምንድነው ልጆቻችን ማብቃት ያቃተን፤ ተማሪዎችን። አለቆች ነን ለምንድነው ሰራተኞቻችነን ፉሊ ማድረግ ያቃተን፤ ያልቻልነው። እነዚህን ነገሮች አንድንጠይቅ፤ ራሳችን ስንጠይቅ ስንመለከት ምን ይታዬናል? „ድመት ሆነን አንበሳ ነው የሚታዬን? ወይንስ አንበሳ ሆነን ድመት ይታዬናል? ወይንስ ሰው ሆነን ሰው ይታዬናል? ስለሳይንስ ስናወራ፤ ሳይንቲስት ለመሆን ሰው ብቻ  መሆን በቂ ነው። ማሰብ፣ ሃሳብን ማደራጀት፤ በምክንያት ማስቀመጥ፤ ከዛ በኋዋላ ደግሞ ማስተላለፍ።“ ይሄ በዬትኛውም መንገድ ብትሄዱ፤ ሳይንቲስት ያደርጋችኋዋል። Max Black የሚባል ሳይንቲስት / ፈላስፋ/ ስለሳይንስ ሲናገር ምን አለ? ሳይንቲስቶች፤ ንጹህ የጠራ ምናዐብ አላቸው አለ። ማለት ያልተዛባ፤ ያልቆሸሸ፤ ያልዘገጠ ታውቃላችሁ ቆሻሻ የሌለበት፤ ያነን የጠራ ምናዐብ አዲስን ሃሳብ ለማፍለቅ ካለው የሚቀንሱ ሳይሆኑ፤ ጥበባዊ የፈጠራ ምንዐብ ያላቸው ሰዎች ሳይንቲስቶች ናቸው። እና አብረን እንዴት ነው የምንሮጠው? ስንሮጥስ መሮጥ ብቻ ነው የምንፈልገው? ወይንስ መድረስ የምንፈልገብት ቦታ አለ? ለመሮጥ ምን ኢኪዩብመንት ያስፈልገናል? ሰው አንድ ቦታ ለመድረስ ሲፈልግ፤ መጀመሪያ ራሱን ማዘጋጀት አለበት፤ ስለዚህ ርምጃችን ወደ ሩጫ አንዲቀየር፤ ሩጫውም ዝም ብሎ መንገድ ላይ ማህል ላይ የሚቀር ሳይሆን እስከምንፈልግበት ድረስ መሮጥ እንድንችል የሚያደርግ ነገር ያስፈልገናል፤ ማለት ነው። ስለዚህ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ጉዳይን ቀለል ካደረግነው ችግር የመፍታት ጉዳይ ከሆነ፤  እጃችን ላይ ያሉት ትሎች እኛ ራሳችን ሰው መሆናችን ማሰባቸን አይምሯችን፤ ይሄ ሃርድ ዌር የተባለው ነገር ኢንባይሮመንታችን ያሉት  ያላቸው ነገር ለመፍጠር ለመፈልሰፍ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለመሮጥ በቂ ናቸው።“ 

ቢስ አይይብን። እያንዳንዱ አረፍተ ነገር ልዩ አቅም፤ ሃይል ይሰጣል። ተስፋን ያፋፋል። ያነሳሳል። ሙቀት ይሰጣል። አይዛችሁ ይላል። በተለይ በዝምታ ውስጥ ማሰብ ለሚወዱ፤ በጸጥታ ውስጥ ማግስት ለሚያሳስባቸው፤ በመመሰጥ ውስጥ ደርሻ ለሚሞግታቸው አጽናኝ ነው። „ድመት ሆነን አንበሳ ነው የሚታዬን አንበሳ ሆነን ድመት? ወይንስ ሰው ሆነን ሰው ይታዬናል?“ ይገርማል። ይደንቃል። እንኳንም የኔ ሆኑ። „ሰውነታችን ማዕከል አድርገን እንነሳ ነው“ ቢሆንማ ነበር ግን አልተቻለም። ለመሆኑ ሰው ስስ ወይንስ ድርብ ነው?

„ሳይንቲስት ለመሆን ሰው ብቻ  መሆን በቂ ነው።“ ይህ አገላለጽ የቀስተዳመና ፓርቲ የተመሠረተበትን፤ በኋዋላም ቅንጅት ያዘከረውን፤ ከዛም ግንቦት 7 የቆመሰበትን፤ አሁን አሁን ደግሞ ኢሳትም የተጋባበትን ሰውን በዲግሪው ብቻ የመለካት የፕ/ መስፍን ወልደማርያም ከፋይ ዕሳቤ የናደ ብቻ ሳይሆን የደረመሰም ነው። የኢትዮጵያ ሳይንቲሰት፤ ፈላስፋ ዓራት ዓይናማ የሀገር መሪዎች፤ የሃይማኖት መሪዎች የነበራት ሐገር ናት። ምስክሮቹ እኛው ራሳችን መኖራችን በቂ ነው ኢትዮጵያዊ ተብለን። ኢትዮጵያ ተብላ። እንኳንስ „መጸሐፈ ፈውስ“ እነ ፋሲል፤ ላሊበላ፤ አክሱም፤ በርካታ ገደማት እያሉ። አባቶቻችን በዲግሪያቸው ተለክተው፤ በሰርትፊኬት ተመዝነው ሳይሆን በሥነ – አዕምሯቸው የልቅና ብቃት እስከ 500 ዓመት ብንቆይ እንኳን እንሱ የሠሩትን ዕጹብ ድንቅ ተግባር መከወን ቀርቶ የእውቀት ዓውደ ምህረቱ ሳይቀር ዛሬ ወርዶ ቁልቁል የጦርነት ቀጠናው ምክንያታዊነት ሆኗል፤ ለሰሚውም ግራ ግራር።

ያ  የአባቶቻችን ልቅና ትውፊት፤ ዕሴት፤ አስተምህሮት ዛሬ በለጸጉ፤ ለሙ፤ አደጉ ከሚባሉት ዩነቨርስቲዎች ተመርቀውበት አይደለም። አልነበረምም። ዛሬ ካለ ወረቀት በራስ እራስ አስተዳደር የመሳተፍ ዕድሉ የለም። ስንቱ ህዝብ ተምሯል ሲባል ደግሞ አንኳንስ ኢትዮጵያ ውጪ ሐገርም ዕድሉ ከሌለ የለም ነው። ስለዚህ ይህ ማህበረሰብ ባለቤት አልቦሽ ስለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ሥነ – ልቦናው ስበብ አስባብ እዬተፈለገ ተቀጥቅጧል። ይህን ቅጥቅጥ ነው ወ/ሮ ጽዮን ተክሉ በመንፈስ ልዕልና ህክምና የፈወሱት። ብሩክ ነፍስ። „ማናችንም አድገን አልጨረስንም!“

ይህ የወ/ሮ ጽዮን ተክሉ ፍልስፍና እያዳመጥኩ አንድ ነገር ሞገተኝ። ለመሆኑ „የመጀመሪያው ኮንፒትር በማን ተሰራ?“ ብዬ አሰብኩኝ። ለእኔ የመጀመሪያው ኮንፒተር ፈጣሪ አምላክ ነው ብዬም ተቀበልኩት። „እንዴት?“ ብዬ አሁንም እራሴኑ ሞገትኩት? ሰውን እንደ አምሳሉ አድርጎ ሲፈጥረው ተፈጠረ ብዬ መደምደሚያ ላይ ደረስኩኝ። አሁንም „በምን ሂሳብ?“ ብዬ ተጠዬቅ አልኩት እኔኑ፤ አዎን ትልቁ ኮንፒተር የሰው ጭንቅላት ነው ወ/ሮ ፅዮን ተክሉ እንዳሉት። ትልቁ ኮንፒተር በሥነ – ዕዕምሮ ዋና ማዘዣ ጣቢያ ሆኖ ሌሎች ደግሞ አሉ ብዬም በመለጠቅ አሰብኩኝ። ልክ ሂሳብ ማስያ፤ ትኬት መቁረጫ፤ የስኳር ደም መጠን መለኪያ፤ ሞባይል፤ የሙቀት መጠን መለኪያ እነዚህ ሁሉ እኮ እንደ አቅማቸው ኮንፒተር ናቸው። ስለዚህም ልብ አንድ ኮንፒተር አለው፤ ሳንባ፤ እንኩላሊት፤ አንጀት፤ ማህጸን፤ ጨጓራ፤ ጣፊያ እያልን ስንሂድ ሰው በብዙ ተፈጥሯዊ ኮንፒተር ተገነባ ነው ብዬ አሰብኩኝ። እነኝህ የሰው አዕምሮ የሠራቸው ሳይሆኑ በፈጣሪ ረቂቅ ጥበብ የተሠሩ ናቸው፤ በእጃችን ያሉት ሞባይል ኮንፒተር ግን የሰው ልጅ የሥነ – ዐዕምሮ ሁለተኛ ደረጃ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው። የሚያገናኛቸው ለእኔ ሁሎችም ሃይል ሰጪ/ ደጋፊ የሚስፈልጋቸው ስለመሆኑ ሲሆን፤ ባትሪ፤ ኤለትሪክ ሃይል፤ ምግብና መጠጥ ንጹህ አየር፤ ሲበላሹ/ ሲታመሙ በሂደት የመጠገን፤ ሲያበቁ ደግሞ ወይንም ከአግልግሎት ውጪ የመሆን፤ የማራጀት እጣቸውም በተመሳሳይነት ማዬት ይቻላል። ስለዚህ ወ/ሮ ጽዮን ተክሉ ያሉት ነገር ከልብ የሚገባ ነው። ሰው ሥነ – አዕምሮውን ማሰራት ከቻለ ሳይንቲስት፤ ፈላስፋ መሆን ለመቻል የሚያገተው አንዳችም የሰርትፌከት ማነቆ ነገር የለበትም። በዚህ መስተጋብር የቅርብና የሩቅ ወገንተኛ እና ነጣይ አስተምኽሮችን መፍጠር ከሰውነት ፍልስፍና ከፈጣሪ ሰውን የመፍጠር አቅም ጋር መፈታታን ይሆናል። ማኽከነ!

 • „ዋልድባና ቦረና የጠፈር ምርምር መሰረተ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን፤ እጅግ ሞጋች አምክንዮ ባለሀብቶች ናቸው።“

„ካለንደር ስል በሥነ ፈለክ ሳይንስ Astronomical Science በቦረና እና በወላድባ አካባቢ የተገኙት መረጃዎች አንደሚያመለክቱት፤ ኢትዮጵያም ከራሽያም፤ ከአሜሪካንም በፊት በስፔስ ሳይንስ የጠለቀ እውቀት ያላቸው ወላጆች የተሻለ ዕውቀት እንደነበራቸው የሚያመላክቱ መረጃዎች እዬተገኙ ነው። ለምሳሌ በቦረና ተማርን የምትሉ ሰዎች የውለደት ቀናችሁን የምታከብሩት ተሳስታችኋዋል፤ ግንቦት ስምንት ዛሬ እና ግንቦት ስምነት በሚቀጥለው ዓመት የተለያዩ ስታሮች፣ ጋላክሲዎች፣ ኮኮቦች የሚያርፉበት ስለሆነ በፍጹም ቀኑ አንድ አይደለም። የሚል ተማርን የምንል ሰዎችን የሞሞግት /ቻሌንጅ/ የሚያደርግ ሃሳብ ያነሳሉ።“

የዶር. አብይ አህመድን ሃሳብ ለማጠናከር ትንሽ የመጀመሪያው አብርንታት ዋልድባ ገደም የተመሰረተበት ዘመኑ ቀደምትነትን በጠረፍ ምርምር ዕይታ ጉልበት ይሰጠዋል ብዬ አስባለሁ። ቅደመ ዓለም፣ ማዕከለ ዓለም፤ ድህረ ዓለም የሁሉ ጌታ መዳህኒተ ዓለም ሥልጣን ነው። ዋልድባን በሚመለከት አባታችን የገደመው ገዳም ነው የሚል ቃለ ህይወት ነው ያለው። እከሌ በሚባል ንጉሥ ተገደመም የሚል ታሪክ የለም ይላሉ የቤተክርስትያን ሊሂቃን። በሁለተኛ ደረጃ የኢትዮጵያን ህላዊነትንም አመክንዮ አባቶቻችን እንዲህ ነው የሚገልጹት ..

„አትዮጵያ በ፫ ሺህ 3000 ዘመን ነፃነቷን ጠብቃ ተቀምጣለች እዬተባለ የሚነገረው ፩ኛ (1)ከሰብታህ ጀምሮ እስከ ጲኦረ ድረስ የነበረውን ፭፻፰ (508) ዘመን፤ ፪ኛ (2) ከትንሹ ሳባ ጀምሮ እስከ ንግሥት ሳባ ወይም እስከ ንግሥት ማክዳ ድረስ የነበረውን ፰፻፶፪ (852) ዓመት በድምሩ ፩ሺ፬፻፲፪ (1412) ዓመት ሳይጨምር ከቀዳማዊ ሚኒሊክ ጀምሮ አስከ አሁን ያለውን ጊዜ ብቻ በማሰብ ነው እንጂ፤ ኢትዮጵያ የምድሯና የባህሯ የአዬሯ ዳር ድንበር ታወቆ መንግሥቷ ተቋቁሞ ነፃነቷን ተጥብቆ መኖር ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የአለው ዘመን ፬ሺ፫፻፺፫ ነው (4393) ነው“

በዬትኛውም ንጉሥ ሥም ወይንም ፈቃድ ተገደመ የማይባለው አብርነታት ዋልድባ ገዳም ቀደምትነቱ በፈጣሪ በራሱ እንደተገደመ ነው አባቶቻችን ያቆዩልን። „ይህ ገደም የተገደመው ፬፻፹፭  (485) ዓ.ም ስለሆነ ይህ ገዳም የሚለው ቃል የተነገረው ገዳሙ ከመገደሙ ፬፻፹ (480) ዓ.ም በፊት  ነው ማለት ነው።“ አባቶቻችን በአጽህኖት ይህን ጽፈውታል።

ጋዜጠኛ ማስረሻ አለሙ ከዚህ ጥልቅ ሚስጢር ለመነሳት የፈቀዱትን ዶር አብይ አህመድን ስትዘነጥል ስንት ነገር እናዳናጋህ ማዬት አለብህ፤ በማንፌስቶ ፍቅር ብቻ ሰው አይለካም። ሰው አይመዘንም። በጣም ተለላለፍክ – በድፍረት።

የኔዎቹ ቅኖቹ ከላይ ያነሳኋቸው የዶር አብይ አህመድን መሠረተ ሃሳብ ለማፋፋት የተጠቀምኩበት ማስረጃ ግማሹን በድምጽ ስለሰራሁት እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ በዚኸው በሳተናው ማሳ አቀርብላችሁና ፈቅዳቸሁ፤ ወዳችሁ የማንነታችን ጥልቅነት የራሳችሁ ለማድረግ ትተጋላችሁ ብየ አስባለሁ። ጉዳዬን ስከውን። ይሄ ነው የዶር አብይ አህመድን የአዲስ ዘመን ልዩ ክስተት እንድንላቸው እምንፈቅደው። ይሄ ሚስጢራዊ እራስን የማዬት ማሾነት ነው ተቀናቃኝ ሆኖ የወጣውን የጋዜጠኛ ማስረሻ አለሙ ሃሳብ ልሞግተው ያነሳሳኝ። ኢትዮጵያ ቀደምት የሥነ – ጠረፍ ሳይንቲስት መሆኗ፤ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ሳይንቲስቶች ያልደረሱበት ግን በኢትዮጵውያን ቀድሞ የተሠራ የህሊና ተግባር መሆኑን እናያለን። በዬአመቱ ቀኖች ሲመጡና ሲሄዱ፤ የክዋክብቶች ተጽዕኖ በአፈጣጠራችን፤ በባህሪያችን በብቃታችን ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዖኖ እነሱ ቀድመው አይተውታል። ጠፈርን እጅግ በሚገርም ምጥቀት በመንፈስ ቅዱስ ሃይልም ተማራምረውታል። ምርምሩ ደግሞ መሬት በራሷ እንዝርት ስትዞር የሚያመጣውን ቀናዊ፤ ወራታዊ፤ ወቅታዊ ሁኔታ ደግሞ በሌላ መንገድ አይተውታል። ይህ ኢትዮጵያን የእኔ ያለ ሁሉ አንጡራ ሃብቱ ነው። አንገቱን የማይደፋበት፤ እሱነቱን በርግጠኝነት በደም ማህተም የሚትምበት። ገና አለም ተመራምሮ ያልደረሰበትም ቅምጥ የምርምር ቅርስ  በእጃችን አለን ነው የሚሉት ዶር አብይ አህመድ። ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ያመጣው ጉርፍ ነው የምትለው ዕሳቤ በዚህ ወድቆ እንዳይነሳ ሆኖ አቧራ ለብሷል ጋዜጠኛ ማስረሻ አለሙ።

ይልቅ አሁንም በእኔ መንፈስ ውስጥ የሚመላለሱብኝ፤ የሚሞግቱኝ አብይ ጉዳዮች አሉ። የኮከብ ባህሪያትን ማጥናት አትኩሮት አለኝ። ይሄን ዛሬ ስለተነሳ ሳይሆን ሀገር ቤት እያለሁ „አዕምሮ“ ጋዜጣ ላይ „ ጋዜጠኛ አብርሃም ጉዝጉዜ“ የሚባል ዬዩንቨርስቲ መምህር ይመስለኛል የሊንዳን የኮከብ መጸሐፍ ይተረጉመው ነበር። ቅዳሜ ጥዋት ከድል ገብያ ገብርኤል ሜክሲኮ አደባባይ የሚቀድመኝ አልነበረም። ሂጄ እምገዛው ለኮከብ ትንተናው ፍቅር ስለነበረኝ ነው። የእኔን ኮከብ „ንጹሃን“ ብሎ ነበር የጀመረው። ዝርዝሩ ውስጥ „ቤት መቀመጥ አይወዱም“ ይላል። ይሄ ደግሞ የእኔ ሰብዕና አይደለም። የማይስለቸኝ ነገር ቢኖር ቤት መቀመጥና ጸጥታ ነው፤ ዘም ማለት። በጸጥታ ማሰብ እፈልጋለሁ። ሰው ቤት መሄድ አልደፈርም፤ በሁኔታዎች አስገዳጅነት አልፎ አልፎ ስሄድ ሲጨንቀኝ እዛው ሆኜ መጸዳጃ ቤት ከፍቼ ለረጅም ጊዜ በመስኮት እቆማለሁ። ስለሆነም ከእኔ ሰብዕን ጋር በፍጹም ሁኔታ የማይመስል ነበር። ጋሼ አብርሃምን ሞገትኩት ያን ጊዜ ሥርጉት እርቂሁን ይባል ነበር የብዕር ሥሜ፤ በለገዳዲም ጹሑፎች ይቀርብ ነበር በዚህ ሥም፤ እርቂሁን የአርበኛው የእሚታዬ ሥም ነበር። እና አንዲህ ብዬ ጻፍኩለት „ዟሪ“ አይደለሁም። ከሰው ጋር ቀጠሮ ከኖረኝ ራሱ ምክንያት ፈልጌ ነው የምቀረው። ሳስበው እኔ በተወለድኩበት ወራት የተወለዱ ልጆች የሰዓት ልዩነትም አለው። ስለዚህ በወል እምንጋራው ባህሪ ሲኖር የተወለድንበት ሰዓት፤ በውስጡ ባሉ ሰከንዶችም የተጠጋጉ ፕላኔቶች፤ ኮከቦች ተጽዕኖ ልዩነት ያመጣል ብዬ ነበር የጻፍኩለት። በአንድ ቀን ውስጥ እንኳን 24 ሰዓት አለ። በ24 ሰዓት ውስጥ ደግሞ ወደ 440 ሰከንዶች አሉ። በስከንዶች ውስጥም ልዩነት አለ። በአንደኛው በሶስተኛው እያለ ስለዚህ ምርምሩን አንዳለ መቀበል ብቻ ሳይሆን፤ አንደ መነሻ ወስዶ ክፍልፋዮች የሚያመጡትንም የለውጥ ድምፆች በጥልቀት መርመርምር አስፈላጊ ነው ብዬ ስለማምን ነበር ለጋሼ አብርሃም የጻፍኩለት። እሱ በእውነተኛው ስሜ አግኘቶ ሊያወያዬኝ ፈልጎ ነበር፤ እኔ ደግሞ ቁጥብነቴ ቃላት የለውም። አልደፍረውም እንደዚህ ዓይነቱን ነገር። እንኳን ያን ጊዜ በወጣትነት ዛሬም በሙሉ ዕድሜ ችግር አለብኝ። ስለዚህ ሳንገናኝ ቀረን። እሱ ፈልጎ ነበር ክርክሩን፤ እኔ ደግሞ ፈቃድ አልሰጠሁትም።

የሆነ ሆኖ የዶር አብይ አህመድ ራስን ማዬት፤ ራስን ማስጠጋት፤ ራስን መዋጥ፤ ራስን እንደ ንጹሕ አዬር መማግ፤ እንደራስ ለመኖር መደሰት። አንዳለኝ ለመኖር መሆንን መወሰን። በመሆን ውስጥ ራስን በመቀበል በውስጡ መጽደቅ ከተፈቀደ በራስ መተማመን አቅሙ በራሱ መንገድ ሙሉዑ ሰብዕናን ያጎናጽፋል። የተመጣጠነ ስብዕና ደግሞ እንዲህ መሬት ይዞ በጽናት እንዲቆም ያደርጋል። ሌላ የተመሰጥኩበት የሀገር የአደራ ባለ ዕዳ ከፋይነት፤ ከእናታቸው ለሰፈር ከሚልኩት የቅመሱልኝ፤ ከጎረቤት በመልስ ከሚጣው የሐሤት ቅብብል ጋር እንዴት እንዳወደዱት ከታምር በላይ ነው። ይኑርልን። አትኩሮታቸው አጅግ መጠነ ሰፊ ነው። በዚህ መሃል ግን  ስጋት አለብኝ … እንዳይነጥቁን …

 • ሰለስጋት።

መቼም ይህን ብቃት ኤርትራዊው አቶ በረከት ስምዖን ለደቂቃም ከጥቃት ሳት አይሉለትም። የሳይንቲስት ኢንጂነር ቅጣው እጅጉ ሞት፤ የአቶ አንዱ ዓለም አራጌ የዕድሜ ልክ እስራት፤ የአርበኛ አንዳርጋቸው ተላልፎ መሰጠት፤ የአቶ በቀለ ገርባ እስር፤ የዶር መራራ ጉዲና እስር፤ የአቶ አሰፋ ጨቦ ሞት ከአቶ በረከት ስምዖን ኢትዮጵያን ከመሰለል ተልዕኮ ጋር የተዋዋለ ነው። ስለምን? ኢትዮጵያ በበቀሉ ብቁ ልጆቿ መብቀል፤ ማበብ፤ መለምልም ይህን ማዬት አይፈቅዱትም። የሻብያ ሰላይ ናቸውና።

ታዲያ ይህን ብቃት እንዲህ በቸልታ የሚታይ ይሆናልን? አይመስለኝም። አሁን ደግሞ ጠቢቡ ቴወድሮስ ካሳሁን ኤርትራ ናፈቀችኝ እያለን ነው።  „አይጥ ለሞቷ የድመት አፍንጫ ታሸታለች“ በሰላም ቢመለስ እንኳን የአንጀት በሽታውን ተሸክሞ ነው። ትዳሩም – ፍቅሩም – ህይወቱም ምስቅለቅል ነው የሚለው። ፕ/ ኢሳያስ አፈወርቂ ሌላ በሽታ የለባቸውም። ኢትዮጵያ ናት በሽታቸው። በዶር አብይ አህመድ የህይወት ጉዳይ ያንዣበበው አደጋ ከኤርትራ አስከ ኢትዮጵያ መረቡን የዘረጋ ነው ብዬ ነው እማምነው። እንዲህ አላሰቡትም የሴራ መርበኞች ዶር. መራራ ጉዲና፤ አቶ በቀለ ገርባ ሲታሰሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ልቅናው ጎልቶ፤ ተደማጭነቱ ደምቆ የሚወጣ ወጣት ብቁ ኢትዮጵውያን ይኖራል ተብሎ አልታሰበም። አሁን ባልተሳበ ሁኔታ፤ ባልተሳበ ፍጥነት በዬደቂቃው የመንፈስ ጥሪቱና ለውጡ ከተገመተው እና ከተጠበቀው በላይ ነው። ሂደትን የሚጠበቁ የሁለመና ማስከኛ መቋጠሪያ ውሎችም በትቅቅፍ በአዎንታዊነት ችግኛቸው ለምለም ነው። ነገ ለሚያስፈራን አብሶ መከላከያ ውስጥ በራሱ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ውስጥ የዶር አብይን መንፈስን ለመጠበቅ የፈቀዱ ወገኖች መኖራቸው መልካምነቱ ሊመሳጠር የሚገባው ከዚህ አንጻር ነው። ይህ ብሄራዊ ስሜት ብቻ ነው የምህረት መሰላል። ይሄንን ማድመጥ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ልብ ከሸፈተ መሰብሰብ አይቻልም። ዶር. አብይ አህመድም ራሳቸውን ከፈጣሪ በታች መጠበቅ ይገባቸዋል። ለሚሊዮኖች ድምጽ ሲሉ። በአቶ ለማ መንፈስ በዙም ስጋት የለብኝም፤ በተወሰነ ደረጃ የባለቤታቸው ነፍስ ጥግ ይሆናቸዋል ብዬ አስባለሁ። ይህንንም እንደመልካም አጋጣሚ ማዬቱ ይበጀናል።

የዶር አብይ አህመድ ጉዳይ እንኳንስ የወያኔ ሃርነት ትግራይ እና አቶ በረከት ስምዖን ጋዜጠኛ ማስረሻ አለሙ እኮ ያንገበገበው፤ የለበለበው ጨጓራውን የጠበሰው „የለማውያን“ አጀንዳ መሆን ነው። በዚህ ስሌት ማዕቀፉ ቡቃያ የማዬት ሳይሆን ተቀብሮ ወይንም ተሰናክሎ የማዬት ህልም ተለምዷል። እዚህ ውጪ ሀገር መፈናፈኛ የሌለውም ለዚህ ነው። ሃሳብ እንዳሻው የማይንሸራሸርው ማደግም ያልቻልነው። የሃሳብ እድገት እኮ የለም ከዚህ። ዝም ብሎ በዕምቅ ገድጓድ መማቀቅ። … የማይድን ምርቅዘት።

 • እርገት።

የኢትዮጵያ ሙሁራኑ ድምጽ 40 ዓመት ያልተደፈረውን ዕውነት አንድ ለአራት ሰሞኑን ሞግተው። ዕውነቱንም አፍልቀውታል። አዬዋ ወያኔ ዛሬስ ጆሮ አለህን? ግዴለህም አድምጠው። የምታውቀውን ብቻ ነው የምታውቀው። ጭካኔ። መክፈል። አጋ መለዬት። መግደልና ማሰር። ግን አሁንም ኢትዮጵያ በትግሬ የበላይነት ቅዝፈት ውስጥ ሰምጣ ሌሎቹ 79ኙ አቤት እያሉ ነው? ኤሉሄ እያሉ ነው። ትናንት ኢትዮጵያ የብሄረሰቦች እስር ቤት በማንፌስቶ ነበር። ዛሬ ግን 27 ዓመት ተኖረበት። ካድሬ ዕውነት አይደለም። መኖር ነው እውነት። የመኖርን እውነት ተቀበሉት ይሏችኋል። አራቱ ቅኖች ፈራ ተባ እያሉ በተመጠነችው የነፃነት ልክ። አንዱ ደግሞ አቶ አሰማህኝ አስረስ ለዛውም „የጋዜጠኝነት ተጋብቦት መምህር“ የጠጡትን መርዝ ያገሳሉ። አዝናለሁ የጋዜጠኛ መምህር ካድሬ¡ ያሳፍራል ጋዜጠኛ ተሁኖ ካድሬነትን መምረጥ፤ ሞት በስንት ጣዕሙ። መፍትሄውን ሳይሆን ገደሉን ነው እዬማሱት ያለው አቶ አሰማህኝ አስረስ። ማፈሪያ¡ አይኔን ግንባር ያድርገው፤ አልሰማሁም፤ አላዬሁም ይላሉ ሎሌነቱ ሆነ ግርድናው ተመችቷቸው። ይህ ለወያኔ ሃርነት ትግራይም አያድነውም። የሆነ ሆኖ የዶር አብይ አህመድ መሰረታዊ የተልዕኮ አቅም „ሰውን“ ማዕከል ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ የመፍትሄ አደራዳሪ ብቻ ሳይሆን መፍትሄ ነው በራሱ። ሰውነት የድል መባቻ ነው። ሰዋዊነት የብሥራት ዓዋጅ ነው። በራስ ላይ ዘምቶ መለወጥ ትውልድነት ነው። ከነስንክሳሩ ሳይሆን ከራስ በሚጀምር የውስጥነት የማጽዳት ዘመቻ ብቻ ነገ ይገኛል። አይዋ ወያኔ አንተም እምልህን ስማ፤ ይሄ የቃላት ካብ የድቡሽት ቤት ነው – እሺ የሰሞኑ መግለጫህ ድርቆሽ።

https://etzena.com/amharic/archives/43961

ወቅታዊ ውይይት -በአማራ ቴሌቪዥን።

„ማናችንም አድገን አልጨረስንም!“

(ከወ/ሮ ጽዮን ተክሉ ዓለም ዐቀፍ ድንቅ የምናብ ሰብል የተወሰደ።)

ኢትዮጵያዊነት ከመፈጠሩ ቀድሞ ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጢር!

በማጠቃልያው እስክመለስ ድርስ እግዚአብሄር ይስጥልኝ፤ መሸቢያ ጊዜ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.