መግለጫው ሲፈተሽ! (ኆኅተብርሃን ጌጡ)

ከኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ብዙ ባይጠበቅም፤ እንደዚህ የወረደ መግለጫ ይሆናል ተብሎ ግን አልተጠበቀም። በብዙ አንቀጾች (ዓረፍተ ነገሮች) ለሀገሪቱ ሕዝብ መግለጽ የፈለገው፤ ለሩብ ምዕተ ዓመታት ስለዘለቀው የመልካም አስተዳደር ግንባታ፤ የዲሞክራሲና የሰላም በሀገሪቱ መስፈንና ይህንኑ የማይናቅ ድል ጠብቆ ስለመጉዋዝ ነው።

በጥልቅ የመታደስ እንቅስቃሴው ዓላማ “ሀገሪቱ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ እየገሰገሰች ስለምትገኝ በዚህ እንቅስቃሴያችን የጎመጁ የውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን የሚሸርቡብንን ሴራ ተረባርበን ማክሸፍ እና ከምንጊዜውም በበለጠ የአራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች አመራሮች በመካከላችን የአስተሳሰብ አንድነት በመፍጠር ወደፊት መጉዋዝ ያለብን” መሆኑ በጣም አስፈላጊ እንሆነ ታምኖበታል ይለናል። በአደባባይ በአራቱ ድርቶች መካከልም የእርስ በርስ መጠራጠር መኖሩንና  አለመተማመን እየገነነ መምጣቱንም ሳይሸሽግ ለመናገር ሞክሯል። ከዚሁ ጋር አያይዞም በሀገሪቱ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  የእርስ በርስ ግጭት በሀገሪቱ በየትኛውም አቅጣጫ እየተባባሰ መምጣቱን እና የሰው ሕይወት ማለፉንም የአደባባይ ምስጢር ስለሆነ ደብቆ ማለፍ አልፈለገም።

ለዚህም ድርጊት ተጠያቂው መንግሥትና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መሆኑንም አምኗል። በየክልሉ ለጠፋው የሰው ሕይወትም መንግሥት ይቅርታ መጠየቁንም በይፋ ተናግሯል። ነገ እንዳለፉት ዓመታት የሰው ሕይወት አላግባብ እንዳይጠፋ የሚያደርግ ሕግ ግን የለውም። የገባውም ቃል የለም። ዋስትናም አይሰጥም። የሚወሰደው እርምጃ ግን ከሥልጣን መውረድ ጋር  የሚያያዝና  የፈጸመው ግፍም እዚያ የሚያደርስ አይደለም። ጥልቅ ተሐድሶው ለ 25 ዓመታት እስገኘሁዋቸው የሚላቸውን ድሎች ጠብቆ መጉዋዝና በሚታየው ሕዝባዊ አመፅ ለአገዛዙ ሳይመቹ የተገኙትን እንዳስፈላጊነቱና እንደሁኔታው ወቅት ጠብቆ መምንጠር ነው። በዚህ የመግለጫ ይዘትም ሰይፍ ሊመዘዝላቸው የተዘጋጁ “የውስጥ አብዮተኛች” መኖራቸውን መካድ አይቻልም። ባንድ ቃልም በሂደት እርምጃ ሊወሰድባቸው የታሰቡ ግለሰቦችን “ሕዝበኞች” (populist) ሲል ይገልጻቸዋል። ይህ ቃል በአማርኛ አዲስ አጠቃቀም በመሆኑ በግሌ ወድጄዋለሁ። “ሕዝበኞች” አጉል “እወደድ-ባዮች ሲል የሚገልጸውን አባባል ማለቴ ነው። የመግለጫው ትርጉዋሜ “ሕዝበኞች” የሚላቸው “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው”  እያሉ በአደባባይ መልክት ያስተላለፉትን እነ ለማ መገርሳን እና እነ ዶ/ዓቢይ አህመድን ለማመልከት እንደሆነ የሚጠራጠር ያለ አይመስለኝም። በሂደትም ለእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ቢላዋ እየተሳለላቸው መሆኑን ግድ ይሏል። ለሞቱት ይቅርታ መጠየቅና በሕይወት ያሉትን ለመግደል መዘጋጀት ግድያና ይቅርታ አብረው የማይጉዋዙ የእብሪተኝነት ባሕርያት ናቸው።
ኢሕአዴግ ለሠራዊቱ ያለውን አክብሮት መግለጹም ግድያን ማበረታት መሆኑ ሊታበል አይገባውም። የውጭ ጠላትን መክቶ ለሚመልስ ሠራዊት አክብሮት ብቻ ሳይሆን የሚቸረው፤ ሜዳልያም በአንገቱ ሊጠልቅለት ይገባል። የጀግንነት የዘውድ አክሊልም በእራሱ ላይ ቢጫንለት ሲያንሰው እንጂ፤ የሚበዛበት አይደለም። ወገኑን ተኩሶ ለሚገል ግን አክብሮት ሳይሆን፤ በፍርድ አደባባይ ፍርደኛ ሊሆን ነው የሚገባው።

መግለጫው በማብራሪያውና በማጠቃለያው “ለሩብ ምዕተ ዓመታት የተገኘውን የዲሞክራሲና የኢኮኖሚ ዕድገት ድል ለመጠበቅ፤ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ትንሳዔ ለማፋጠን ለማንኛውም ፈተና ባለመንበርከክ ለዘላቂው ድል ወደፊት መግፈት አስፈላጊ መሆኑ አስመሮበት ለማለፍ ሞክሯል። ተሳስቶ አንድ ዓረፍተ ነገር እንኩዋ አላግባብ የታሰሩ የፓለቲካ እስረኞች ስለሚፈቱበት ሁኔታ አንድም ቃል ለማለት አልፈለገም። አሁንም የእብሪቱ ጎማ ገና አልተነፈሰም። የተወጠረው ትእቢቱ ገና አላላም። ለሚደርሰው ችግር በአፋጣኝና በአስተማማኝ መንገድ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ በዛቻ መልክ መልክቱን ለማስተላለፍ ከመሞከር ባሻገር መሠረታዊ ለውጥ በሀገሪቱ ሊመጣ ስለሚችልበት መንገድ አንዳችም ነገር አልተነፈሰም።
ለምን?

1ኛ. በኦሮሚያና በአማራ ክልል እየተካሄዱ የሚገኙት ሕዝባዊ አመጾች ለማገዝ ለለውጡ የወሳኝነት ሚና ያለው የአዲስ አበባ ኗሪ መነሳት አልቻለም። በ1997 የቅንጅት እንቅስቃሴ የአዲስ አበባ ሕዝብ አምጾ የገጠሩ ሕዝብ ደግሞ ድምጹ አይሰማም ነበር። ግን የሀገሪቱ ብሎም የአፍሪካ መዲና የሆነችው የአዲስ አበባ ኗሪ አልገዛም ብሎ በነቂስ በመነሳቱ ( የሚያዝያ 27 ን የአዲስ አበባ 3 ሚሊዮን ሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ያስታውሷል) መንግሥት መፈናፈኛ በማጣቱ “የጥምር መንግሥት” እስከማቁዋቁዋም የሚደርስ ሀሳብ ለማቅረብ ተሞክሮ ነበር። ሴረኞቹ በረቀቀ ተንኮላቸው አከሸፉት።

2ኛ. ይህን የዚያን ጊዜውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በባለቤትነት የሚመራው እንደ አማራጭ ተቃዋሚ የፓለቲካ ድርጅት (ቅንጅት) ነበረ።
3ኛ. አሁን እንቅስቃሴውን የሚመራው በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ አፈንግጠው ይወጣሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ኦፒዲኦና ብአዴን ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች ተቃዋሚ ኃይል ሆነው ለመውጣት ምን ያህል አቅም አላቸው? በመግለጫው እንደጠቀሰው “ሕዝበኞች” አጉል እወደድ ባዮች ብሎ ፈርጆ ለመምታት ሰይፉን እየመዘዘላቸው የሚገኙ ናቸው። እነሱን ብቻ ተስፋ ካደረገ የትግል እስትራቴጂ በተለየና በተቀናጀ ሕዝባዊ አመጹ መመራት መቻል ይኖርበታል።

4ኛ. ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ላለፉት ዓመታት ለተሰሩ ግፎች እነኝህ ድርጅቶች  አብረው ተጠያቂዎች ናቸው። እናም በውጤቱ “ቁስል ያለበት ውሻ እንደ ልቡ” የመጮህ ችግር አለበት። የአኖሌን የጡት ቆረጣ ሐውልት ያቆመው ኦፒዲኦ ከደሙ ንጹህ የመሆን ታሪክ ሊኖረው አይችልም። እናም ወያኔ ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ሰበብ ፈልጎ እነኝህን ድርጅቶች ለማጥፋት ማጣፊያው አያጥርበትም። መግለጫው ጥቆማ ሰጥቶ እንዳለፈው፤

– የእርስ በርስ መጠራጠር መኖር፤
– አለመተማመን እየገነነ መምጣት፤
– ለደም አፋሳሽ ግጭቶች ድርጅቶቹ ተጠያቂ መሆናቸው፤
– በአባል ድርጅቶች መካከል “መርህ አልባ” ግንኙነት እየታየ መምጣቱ፤
– ባጭሩ የእርስ በእርስ መጠራጠር

በመካከላችን በመንገሱ ወዘተ… የመሳሰሉት አገላለጾች “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ዥግራ ናት” ይሏታል የሚለው አገላለጽ ለኢሕአዴግ አገዛዝ ያልተመቹ የአባል ድርጅት አመራሮችን ለመምታት መታሰቡን አቅጣጫ አመላካች መግለጫ መሆኑን ልናስተውለው ግድ ይለናል።

ከመግለጫው ውጭ አንድ የተገኝ ትልቅ ድል ግን ላለፉት ዓመታት እሳትና ጭድ ሆነው እርስ በርስ በመጠፋፋት የፓለቲካ ረድፍ ተሰልፈው የገዥውን ፓርቲ (ሕወሓት-ኢሕአዴግን) የሥልጣን ዕድሜ እንዲያራዝሙ መሣሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ የተፈረደባቸው አንጋፋ ብሔሮች በመካከላቸው የሰላም አየር እየነፈሰ መሆኑ ሌላው የሀገሪቱ ትልቅ የምሥራችና የአብሮነት ድላችን ነው። ቢያንስ በዚህ እንጽናና።

ሌሌች ድረ ገጾችን ብቻ ኮፒ ከማድረግ እንዳቅሚቲ መግለጫውን በዚህ መንገድ ተመልክቼዋለሁ ለማለት እንጂ፤ ሌላ ቁምነገር ይዤ አይደለም። ጊዜያችሁን በመሻመቴ ይቅርታ።

በዚሁ አጋጣሚም 2018 ያሰብነውን ሁሉ የሚሳካበት፤ ሀገራዊም ሆነ ግላዊ ራዕያችን ዕውን የሚሆንበት ዓመት እንዲሆንልን ልባዊ ምኞቴን ልገልጽላችሁ እወዳለሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.