እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የቂሊንጦ እስር ቤት ኃላፊን በዘር ማጥፋት ወንጀል እንደሚጠይቋቸው ገለፁ (በጌታቸው ሺፈራው)

እነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የቂሊንጦ እስር ቤት ኃላፊን በዘር ማጥፋት ወንጀል እንደሚጠይቋቸው ገለፁ

(በጌታቸው ሺፈራው)

መቶአለቃ ማስረሻ ሰጤ

በእነ ማስረሻ ሰጤ ክስ መዝገብ ስር የተከሰሱ እስረኞች የቂሊንጦ እስር ቤት ኃላፊን በዘር ማጥፋት ወንጀል እንደሚጠይቋቸው ገልፀዋል። ዛሬ ታህሳስ 24/2010 ዓም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በተከሳሾቹ ላይ የዐቃቤ ሕግ 83ኛ ምስክር ሆነው የቀረቡት የቂሊንጦ እስር ቤት ደህንነትና ጥበቃ ኃላፊ ዋና ኦፊሰር ገብረማርያም ወልዳይ ኣብርሃ ሊመሰክሩ በቀረቡበት ወቅት ከእስረኞቹ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

ተከሳሾቹ ዋና ኦፊሰር ገብረማርያም በቂሊንጦ ቃጠሎ ወቅት እስረኞችን በመግደልና በማስገደል እንዲሁም አስከሬናቸውን በእሳት በማቃጠል ተጠያቂ ናቸው ብለዋል። 1ኛ ተከሳሽ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ምስክር ሆነው የቀረቡትን ዋና ኦፊሰር ገብረማርያም ወልዳይ በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚጠይቋቸው በመሆኑ መመስከር እንደሌለባቸው ገልፆአል። 5ኛ ተከሳሽ አግባው ሰጠኝ ምስክሩ በቂሊንጦ ቃጠሎ ወቅት ሰው ገድለው እሳት ውስጥ በመጨመር ወንጀል እንደፈፀሙ ለችሎቱ ገልፆአል። በተመሳሳይ 4ኛ ተከሳሽ አበበ ኡርጌሳ ምስክሩ ለችሎቱ ጠቁመው ባሳዩት ወቅት “ያውቀኛል። ሲገድልና ሲያስገድል የነበረ ሰው ነው። በዘር ማጥፋት ሊጠየቅ የሚገባው ሰው ነው” ብሏል። 33ኛ ተከሳሽ ሸምሱ ሰኢድ “ገድሎ ማዕረግ የተሰጠው፣ ዞን 5 የተባለ የድሃ ልጅ የሚሰቃይበት እስር ቤት ያሰራ ሰው ነው።” ሲል ዋና ኦፊሰሩ እንዳይመሰክሩ ተቃውሟል። በተጨማሪም 31ኛ ተከሳሽ ጌታቸር እሸቴ “ምስክሩ ህሊናቸውን የሸጡ ናቸው። እንደሳቸው ህሊናቸውን የሸጡ አሉ። መንግስት ጨፍጭፌያለሁ ብሎ ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ እንኳን ከስህተታቸው አልተማሩም” ብሏል።

ተከሳሾቹ ዋና ኦፊሰር ገብረማርያም ወልዳይ እንዳይመሰክሩባቸው ተቃውሞ ካሰሙ በኋላ፣ 18ኛ ተከሳሽ አንጋው ተገኘ “እኛ ፍትህ እናገኛለን ብለን ሳይሆን ለታሪክ እንዲመዘገብ ስለምንፈልግ ይመስክር” ብሏል። ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ዋና ኦፊሰር ገብረማርያም ወልዳይ እንዲመሰክሩ ተከሳሾቹን ካግባቡ በኋላ ተከሳሾች ምስክርነቱ እንዲቀጥል ተስማምተዋል።

——————-////———————

እነ ጌታሁን በየነ ተፈረደባቸው

(በጌታቸው ሺፈራው)

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ጌታሁን በየነ ክስ መዝገብ በግንቦት 7 የተከሰሱት 9 ግለሰቦች ላይ የፍርድ ውሳኔ ሰጥቷል። 1ኛ ተከሳሽ ጌታሁን በየነ 9ኛ አመት ሲፈረድበት፣ 2ኛ ተከሳሽ ዶ/ር አስናቀ አባይነህ እና 5ኛ ተከሳሽ አለማየሁ ንጉሴ 16 አመት ከ6ወር፣ 4ኛ ተከሳሽ ብራዚል እንግዳ 15 አመት ተፈርዶባቸዋል። 2ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ በዝቅተኛ ደረጃ ተይዞ እንደተፈረደባቸው ፍርድ ቤቱ ተገልፆአል።

በተጨማሪም 7ኛ ተከሳሽ ያምላክነህ ገዛኸኝ፣ 8ኛ ተከሳሽ አብዱ ሙሳ እና 14ኛ ተከሳሽ ደመላሽ ቦጋለ እያንዳንዳቸው በ5አመት፣ 12ኛ ተከሳሽ መቶ አለቃ ፍቅሬ እሸቱ 4 አመት ከአራት ወር እንዲሁም 13ኛ ተከሳሽ ባንተወሰን አበበ 3አመት ከ10 ወር ተፈርዶባቸዋል።

ተከሳሾቹ የተላለፈባቸውን ውሳኔ የተቃወሙ ሲሆን “የታገልነው የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ነው፣ እናንተ ዳኞች ከእነ ሳሞራና አባይ ፀኃዬ በላይ ትጠየቃላችሁ፣ ወያኔ አንድ አመት አይቆይም…የጫካ ውላችሁ አይሳካም፣ እኛ የታገልነው ለመቶ ሚሊዮን ህዝብ ነው፣ ህወሓት ይቀበራል፣ነፃ እንወጣለን… ” ሲሉ ተሰምተዋል። በተጨማሪም የተሰጠባቸውን ውሳኔ በመቃወም ችሎትና ዳኞቹን ዘልፈዋል።

—————————–////———————-

የዋልድባ መነኮሳት በእስር ቤት የደረሰባቸው ስቃይ

(ከቂሊንጦ እስር ቤት የተላከ)

መነኮሳቱ ዋልድባ ገዳም መታረስ የለበትም፣ የእግዚያብሔር ቤት ነው በማለት ከ2004 ዓም ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ድረስ በመሄድ ለእምነታቸው ሲታገሉ ቆይተዋል። ከ4ቱ የገዳሙ ተወካይ መነኮሳት አንዱ የሆኑት አባ ገ/ እየሱስ ኪ/ማርያም ይህን ጥያቄ በሕጋዊ መንገድ በመጠየቃቸው ለእስር ተዳርገዋል። ከአባ ገ/ እየሱስ ኪ/ማርያም በተጨማሪ አባ ገ/ስላሴ ወልደ ሀይማኖትም ያለ ምንም ማስረጃ በሀሰት ተከሰው በስቃይ ላይ ይገኛሉ።

የዋልድባ ገዳም መፍረስ የለበትም በማለታቸው ብቻ የግንቦት 7 አባል ናችሁ ተብለው በ”ሽብር” ተከሰዋል። ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ መነኮሳት በ”ሽብር” የተከሰሱበት ወቅት ነው።

ያለ በቂ መረጃ እና ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የታሰሩት መነኮሳቱ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በምርመራ ወቅት ከፍተኛ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል። አሁን ደግሞ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ዞን 5 በሚባል ጨለማ ቤት ተወርውረዋል። የምንኩስና ልብሳቸውን እና ቆባቸውን አውልቁ፣ ካላወለቃችሁ ፍርድ ቤት አንወስዳችሁም ተብለዋል። በየጊዜው ድብደባ እየተፈፀመባቸው ታፍነው ይገኛሉ።

መነኮሳቱ ልብሳችን የእምነታችን መገለጫ ስለሆነ አናወልቅም፣ እምነታችን የሚያዘንን እንጅ ሌላ አናደርግም፣ የቃል ኪዳን ልብሳችን ነው በማለት በፅናት እየታገሉ ይገኛሉ።

በፆምና በፀሎት የደከሙትን መነኮሳት ሜዳ ላይ እያንከባለሉ ስለደበደቧቸው ለህመም ተዳርገዋል። የታሰሩበት ጨለማ ቤት በመሆኑ የተነሳ አይናቸው ተጎድቷል። ህክምና ማግኘት ስላልቻሉ በተለይ አባ ገ/እየሱስ ኪ/ማርያም በከፍተኛ ስቃይ ላይ ይገኛሉ። በእስር ላይ ያሉትን መነኮሳት ለመጠየቅ ከዋልድባ ገዳም የሚመጡ አባቶች በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው ነው።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.