ሀገርና ወገን ለማዳን አዉሬዉን ማስራብ (ሺፈራዉ አበበ)

ላለፉት ሁለት አመታት የትዉልድ አገራችን በጣም አሳሳቢ በሆነ የፖለቲካና የሰላም ቀዉስ ዉስጥ ትገኛለች። በሺህዎች ሞተዉ፣ ባስር ሺህዎች ታስረዉ፣ በመቶ ሺህዎች ከቤት ከቀያቸዉ ተፈናቅለዉ ያሉበት ወቅት ላይ ነን። መንስኤዉ ግልጽና ቀጥተኛ ነዉ፤ ባንድ በኩል፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ስድስት ፐርሰንት ብቻ የሚወክሉ፣ ግን ያገሪቱን የመከላከያ፣ የደህንነት፣ የመንግስት ተቋማትና፣ ቁልፍ የኢኮኖሚ አዉታሮች ለ27 ዓመታት ተቆጣጥረዉ የዘለቁ፣ ለስልጣን ጥማቸዉና ለንዋይ ፍቅራቸዉ ዳርቻ የሌለዉ፣ እንደአገር መሪ ሳይሆን እንደመንደር ወሮበላ የሚያስቡና የሚሰሩ፣ ጸረ-ሀገር ህወሃት-ወያኔዎች አሉ።

በተቃራኒ ጎን ህገ-መንግስታዊና ሰብአዊ መብቶቼ ይከበሩልኝ ብሎ የተነሳ፣ እንደቀድሞዉ ላርፋጃ መፈክር አሰምቶ ወደቤቱ የሚመለስ ሳይሆን፣ በቁርጠኝነቱ እየጸና፣ በሚያነሳቸዉ ጥያቄዎች አንድነቱን እያረጋገጠ የሄደ “ወያኔ-ህወሃት በቃኝ!” “ህወሃት-ወያኔ በቃዉ!” ብሎ የተነሳ ህዝብ አለ። ይህ ባብዛኛዉ በወጣቶች የሚመራና በኦሮሚያና አማራ ክፍለ ሃገሮች የተማከለ አመጽ ባሁኑ ሰአት አገዛዙን ከስሩ መንግሎ የሚጥልበት ስፋት ላይ ያልደረሰ ቢመስልም፣ በመላዉ አገሪቱ ብሶቱንና ቁስለቱን በሆዱ አምቆ ይዞ፣ በቋፍ ያለዉ ህዝብ የተቀላቀለዉ እለት የወያኔ-ህወሃት አገዛዝ ፍጻሜ እንደሚያገኝ መጠራጠር አያስፈልግም።

ላለፉት ሁለት አመታት የቀጠለዉ  ህዝባዊ አመጽ ህወሃት-ወያኔዎችን ስጋት ዉስጥ እንደከተታቸዉ ግልጽ ነዉ፤ ይሁንና የህዝቡ ጥያቄ ለመመለስ ይሉንታም አቅምም ስለሌላቸዉ በማያቋርጥ ስብሰባ ከተጠመዱ ወራት አልፈዋል። በመቀሌ እንደህወሃት-ወያኔ ለሁለት ወራት ከተሰበሰቡና እርባና ቢስ ሹም-ሽር ካደረጉ በኋላ፣ ወደአዲስ አበባ በመምጣት፣ ከእጅ ስራዎቻቸዉ ጋር ሌላ ስብሰባ ሲያካሂዱ ቆይተዋል። የዚህ የኋለኛዉ ዝግ ስብሰባ ዓላማ ነብስ አግብተዉና አፈርጥመዉ የቆዩዋቸዉን የእጅ ስራዎች ቢያንስ አንዳንዶቹን በማባበልና በማስፈራራት መልሰዉ ከጫማቸዉ ስር ካደረጉ በኋላ በቀጣይ የተነሳዉን ሰፍ ህዝባዊ አመጽ ለመጨፍለቅ መሞከር ነዉ።  የህወሃትም ሆነ የኢህአድግ የዉስጥ ፍጭት ዉጤት ምንም ይሁን ምን፣ የተበደለዉና የተገፋዉ፣ የ27 አመት የባርነት ህይወትና ችጋር ያንገፈገፈዉ ኢትዮጵያዊ በዘላቂ ወደቤቱ ይመለሳል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነዉ።  በመሰረቱ ባለፈዉ አመት፣ ሁለት አመት ያየነዉ የኦህዲድም ሆነ የብአዴን ጡንቻ ማፈርጠምና ህወሃት-ወያኔን መገዳደር የኦሮሞዉና የአማራዉ ህዝብ ትግል ዉጤት እንጂ የነዚህ ድርጅት መሪዎች በግል የፈጠሩት ክስተት አልነበረም።

ያም ሆነ ይህ፣ የዚህ ጽሁፍ አትኩሮት አንድ አገዛዝ በሚያጋጥመዉ የፖለቲካ ተግዳሮት ብቻ ከስልጣን እንደማይወድቅ ማስመርና የህወሃት-ወያኔን አገዛዝ ከስልጣን ለማስወገድi የኢኮኖሚያዊ ትግል ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ማስገንዘብ ነዉ። የኢኮኖሚ መሰረቱ ያልተናጋ  አገዛዝ፣ በፖለቲካዉ በኩል የሚደርሱበትን ችግሮች የማለፍ እድሉ ከፍተኛ ነዉ። ባንጻሩ በኢኮኖሚ የኮሰመኑ አገዛዞች፣ የፖለቲካ ኃይላቸዉም ይመነምናል፣ ብሎም የስልጣን እድሜያቸዉ ያጥራል። ከጥቂት አመታት በፊት በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛዉ ምስራቅ  ከስልጣን የተባረሩ አምባ-ገነናዊ አገዛዞች፣ የፖለቲካ ስልጣናቸዉ ከማጣታቸዉ በፊት፣ የኢኮኖሚ መሽመድመድ ዉስጥ ገብተዉ ነበር።  ከዚያም ቀደም ብሎ፣ ባፍሪካ፣ የእኛን አገር ጨምሮ፣ በእስያ፣ በላቲን አሜሪካና በምስራቅ አዉሮፓ በአመጽ ከስልጣን የተባረሩ አምባገነኖች ሁሉ፣ ከፖለቲካዊና፣ ወታደራዊ ዉድቀታቸዉ በፊት ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ ዉስጥ ተዘፍቀዉ እንደነበር የሚታወስ ነዉ።

ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ ያገዛዞቹን የበጀት አቅም በማቀጨጭ፣ አንደኛ በህዝቦች ዘንድ ታላቅ ተቃዉሞ ያስነሳል፤ ሁለተኛ ፖለቲካዊና፣ ወታደራዊ አመጾችን ለመጨፍለቅ የሚጠቀሙባቸዉን የጦርና ሌሎች መሳሪያዎች የመግዛት አቅማቸዉን ያደክማል፤ ሶስተኛ የስለላ መረቦችን ለመዘርጋት፣ ሆድ አደር ባለሟሎችን ለመግዛትና አፋኝ ኃይሎችን በጉርሻና በድለላ ለመያዝ የሚችሉበትን የገንዘብ አቅም  ያመነምናል፤ ብሎም ዉድቀታቸዉንም ያፋጥናል።

ወያኔ-ህወሃት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ፣ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንቱ ከዉጭ የሚያገኘዉ ገንዘብ ነዉ። ያለዚህ የገንዘብ ድጋፍ ይህ ሰዉ በላ ስርአት እስካሁን በህይወት ሊዘልቅ አይችልም ነበር።  ከዉጭ የሚያገኘዉ ገንዘብ ምንጩ የተለያዬ ነዉ፦

 • ለጋሽ  አገሮችና አለም አቀፍ ድርጅቶች የሚሰጡት እርዳታ፣
 • አገዛዙ ካበዳሪ ድርጅቶች በወለድ የሚወስደዉ ብድር፣
 • ከዉጭ የሚገባ ኢንቨስትመንትና፣
 • ዘመድ ለመርዳት በዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የሚልኩት ገንዘብ (ሃዋላ)

ይሁንና ባለፉት 27 አመታት ከዉጭ የሚገባዉ ገንዘብ፣ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚጠቅም የምርት ተግባር ላይ ባለመዋሉ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንዳመዘነ ምንም ጥርጥር ሊኖር አይገባም።

አንደኛ ፣ ባንድም በሌላም ከዉጭ የሚገባዉ ገንዘብ ዋና ተጠቃሚ የራሱ ህወሃት-ወያኔ ንብረት የሆኑትና የዉጭ ንግዱን ጨምሮ ቁልፍ የሚባሉትን ያገሪቱን የኢኮኖሚ መስኮች የሚቆጣጠሩትኤፈርትና መሰል ኮርፖሬሽኖችና አገዛዙን አቅፈዉና ደግፈዉ የያዙ፣ አሁን ሳዉዲ እስር ቤት የሚገኘዉን ሼክ ጨምሮ ጥቂት ባለሃብቶች  መሆናቸዉ መታወቅ አለበት። ለሰፊዉ የአገሪቱ ህዝብ የተረፈዉ ነገር ቢኖር፣ በሚገባዉ የዉጭ ገንዘብ መጠን አገዛዙ የሚያትመዉ ብር ያስከተለዉ የዋጋ ንረት፣ የኑሮ ዉድነት ነዉ።

ሁለተኛ ፣ ከዉጭ ከሚገባዉ ገንዘብ (የዉጭ ምንዛሬ) ዉስጥ ከፊሉ በህወሃት-ወያኔዎች፣ በኩባንያዎቻቸዉና ባለሟሎቻቸዉ አማካኝነት በድብቅ ካገር የሚሸሽ ነዉ። በዚህ ረገድ ስዉርና ህገወጥ በሆነ መነገድ ከፍተኛ ሃብት ካገር ከሚሸሽባቸዉ አገሮች ዉስጥ ኢትዮጵያ ባፍሪካ አንደኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።  እንደ ግሎባል ፋይናንሽያል ኢንተግሪቲ ጥናት ከ2005 እስከ 2014 ድረስ በድምሩ ወደ$30 ቢሊየን[i] የሚደርስ ሃብት ከኢትዮጵያ  በድብቅ ወጥቷል። የሃብት ሽሽቱ በየአመቱ እያደገ መጥቶ በ2014 ብቻ በመካከለኛ ግምት $4.6 ቢሊየን[ii] ደርሷል።

ሶስተኛ፣ አገዛዙ ያግበሰበሰዉና በ2015 መጨረሻ $21.7 ቢሊየን[iii]  ደርሶ የነበረዉና ባሁኑ ወቅት ወደ $30 ቢሊየን እንደተጠጋ የሚገመተዉ የዊጭ እዳ ለወደፊቱ ትዉልድ ታላቅ የኢኮኖሚ ሸክም ትቶ የሚያልፍ ነዉ። የወያኔ-ህወሃት መሪዎች ራሳቸዉ ያልተማሩ፣ የባለሙያ ምክር የማይሰሙ፣ ግትርና ሃላፊነት የጎደላቸዉ፣ ኢኮኖሚያዊ ዉሳኔዎችን በፖለቲካና ወገናዊ ስሌት የሚወስኑ፣ ይልቁንም ላገርና ወገን እድገት ግድ የማይላቸዉ ስለሆኑ፣ ለእዳ መክፈያ የሚሆን ጠንካራ ኢኮኖሚ መስርተዉ እንደማያልፉ እሙን ነዉ።

አራተኛ፣ ህወሃት-ወያኔዎች ከዉጭ የሚገባዉን ገንዘብ የስልጣን ዘመናቸዉን ለማራዘም በስፋት ይጠቀሙበታል፦

 • ለጭቆናና ለግድያ የሚጠቀሙባቸዉን የጦር፣ የስለላና ሌሎች መሳሪያዎች ከዉጭ ለመግዣ፣
 • ባለም ዙሪያ ካምሳ በማያንሱ ታላላቅ ከተሞች ዉድ ቢሮዎች ተከራይተዉ ያገዛዙን ፕሮፓጋንዳ ለሚነዙ አምባሳደሮቻቸዉና፣ በኤምባሲዎች ዉስጥ ተሸጉጠዉ ዉጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን ላይ የስለላ ስራ ከማቀናጀት እስከ ተራ የእግረኛነት ስራ ለሚሰሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ክፍያ፣
 • ያሜሪካንና የአዉሮፓን ቁልፍ ፖለቲከኞች ለማግኘትና፣ የድለላ ስራ ለሚሰሩ የሎቢ ድርጅቶች ወይም ግለሰቦችን ለመቅጠሪያ – ለምሳሌ በ ጃንዋሪ 2017, በአሜሪካ የወያኔ-ህወሃት አምባሳደር SGR Government Relations የተሰኘ የሎቢ ድርጅት በወር $150,000  ወይም ባመት $1.8 ሚሊየን[iv] ዶላር ቀጥሯል።
 • እንደ ኢሳት አይነት የዜና ምንጮችን የስርጭት ሞገድ ለማገድ፣ የግለሰቦችንና የድርጅቶች ኮምፒዉተሮችን ሃክ ለማድረግ ቴክኖሎጂዎችና ባለሙያዎችን ለመግዣ፣
 • በተለይ በአሜሪካና በአዉሮፓ አገዛዙን ተግተዉ በሚቃወሙና በሚያጋልጡ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያንና እንደኢሳት አይነት ድርጅቶች ላይ ርባና ቢስ ክስ ለመመስረት የህግ ባለያዎችንመቅጠሪያ፤

የወያኔ-ህወሃትን የኢኮኖሚ አጣብቂኝ ማባባስ የወቅቱ የዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያን ዋና የትግል መስክ ነዉ!!

የህወሃት-ወያኔ አገዛዝ ባሁኑ ወቅት ወሳኝ የሆነ የፖለቲካ ቀዉስ ዉስጥ ያለ ብቻ ሳይሆን፣ ቀስፎ የያዘዉ የኢኮኖሚ አጣብቂኝ ዉስጥ የሚገኝበት ጊዜ ነዉ። ይህን ደግሞ አገዛዙ ሳይቀር ያመነዉ ሃቅሲሆን፣ የብሄራዊ ባንኩ ገዢ አገዛዙ ከ$26 ቢልየን ዶላር በላይ ባፋጣኝካላገኘ የአገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ቀጥ እንደሚል ለህወሃት-ወያኔ ፓርላማ በኖቬንበር መጀመሪያ ላይ ማሳሰቡ የሚታወስ ነዉ።

የኢኮኖሚ ቀዉሱ አንዱ መገለጫ የዉጭ ገንዘብ (ምንዛሬ) አቅርቦቱ በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆሉ ሲሆን ለዚህም፦

 • አንደኛ አገሪቱ ከኤክስፖርት የምታገኘዉ የዉጭ ምንዛሬ አገዛዙ አቅዶት በነበረዉ መጠን ማደጉ ቀርቶ እንዲያዉም ከድሮዉ መቀነሱና ከአገሪቱ ኢምፖርት ጋር ሲነጻጸር በ2016በ$13.6[v] ቢሊየን ማነሱ፣
 • ሁለተኛ በአገሪቱ ዙሪያ፣ በተለይም በኦሮሞና አማራ ክፍለ-አገራት በተፈጠረዉ እምቢተኛነትና አገዛዙ በወሰደዉ ጨካኝ ርምጃ የተደናገጡ የዉጭ ኢንቨስተሮች ገንዘባቸዉን መሰብሰባቸዉ[vi]፣
 • ሶስተኛ አገዛዙ ከዉጭና ካገር ዉስጥ እስካሁን ያግበሰበሰዉ በድምሩ ከ$40 ቢሊየን[vii] በላይ የደረሰዉ እዳ፣ አለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶችን[viii] ያሰጋ መሆኑና ተጨማሪ የመበደር አቅሙን ዉስን ማድረጉና፣
 • ለጋሽ አገሮች በራሳቸዉ ኢኮኖሚ መድከም የተነሳ ለድሃ አገሮች  የሚሰጡት እርዳታ ባጠቃላይ በመቀነሱና ይልቁንም ሊሸፈን ያልቻለዉ የህወሃት-ወያኔ የሰብአዊ መብት ረገጣ ትኩረት እየሳበ በመምጣቱ ምክንያት ላገዛዙ የሚሰጡት ጉርሻ መኮስመኑ በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸዉ።

የህወሃት-ወያኔ አገዛዝ የተፈጠረበትን የዉጭ ገንዘብ እጥረት በተወሰነ ደረጃ ያቃልልኛል ብሎ ተስፋ ያደረገበት ምንጭ በትዉልድ አገራቸዉ በሰላም መኖር ስላልቻሉ ወይም የስራ እድልም ተስፋም ባለማየታቸዉ፣ ኑሮአቸዉንና ስራቸዉን በሰዉ አገር ያደረጉ ኢትዮጵያዉያንን ነዉ። እንደሚታወቀዉ፣ እንዲህ እንዳሁኑ ቀዉስ ዉስጥ ሳይገቡ፣ ህወሃት-ወያኔዎች በጠላትነት ፈርጀዉ ስሙን በየጊዜዉ ሲብጠለጥሉት እንዲያዉም፣ የተገላቢጦሽ፣ ኢትዮጵያዊነቱን እየካዱ ባገሪቱ ጉዳይ ዉስጥ አያገባዉም እያሉ ሲከሱት የኖሩት የህብረተሰብ ክፍል በዉጭ የሚኖረዉን  ኢትዮጵያዊ እንደነበር የሚታወቅ ነዉ። ድያስፖራ የሚለዉን ቃል ራሱ እንደመጥፎ መገለጫ ይጠቀሙበት እንዳልነበረ ዛሬ ችግር ዉስጥ ሲገቡ ያለይሉኝታ ዋና ወዳጃቸዉ ሊያደርጉት ሲዳዱ ማዬት ከትዝብት አልፎ በሁላችንም ዘንድ  ቁጣን ሊጭር የሚገባዉ ጉዳይ ነዉ።

በርግጥም የሌሎቹ የዉጭ ገንዘብ ምንጮች እየደረቁ ባሉበት ባሁኑ ወቅት ላገዛዙ ከፍተኛ ቀዳዳ እየሸፈነለት ያለዉ የዉጭ ምንዛሬ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያን ለዘመዶቻችን የምንልከዉ ገንዘብ ነዉ። የዚህ ገንዘብ መጠን ባሁኑ ወቅት በአመት ከ$4 ቢሊየን በላይ[ix] እንደደረሰ ይገመታል።  በሚቀጥሉት ወራት ደግሞ ዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያን ገንዘባቸዉን በገፍ ወደአገር እንዲያስገቡ በተለያዩ ተስፋዎችና ጥቅሞች ለማማለልና በእጁ ዉስጥ ለማስገባት አገዛዙ እንደሚልመጠመጥ መገመት ያቻላል። ካገራችን ህዝብ ቀምቶ የሚቸበችበዉን መሬትና ሌሎች የቢዝነስ ተስፋዎችን እንደጉቦ እንደሚያቀርብም መጠበቅ ይቻላል።

ይሁንና እልፍ አእላፍ ኢትዮጵያዉያን ህይወታቸዉን ላደጋ አጋልጠዉ አገዛዙን በእምቢተኝነት ትግል ወጥረዉ በያዙበት ባሁኑ ሰአትና አገዛዙ በሚያጣጥርበት የመጨረሻ ሰአት፣ ዲያስፖራኢትዮጵያዉያን የዚህ ትግል አጋር መሆን ሞራላዊ ግዴታችን ነዉ። አገዛዙን ልናንበረክክ  ከምንችልባቸዉ የትግል መስኮች፣ በጣም ቀላሉና ቀጥተኛዉ የዉጭ ምንዛሬ እጥረቱን ማባባስ ስለሆን፣ ይህን በእጃችን ዉስጥ ያለ፣ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ፍሬ ሊያስገኝ የሚችልን ሃይል መጠቀም ቀን የማይሰጠዉ ጉዳይ ነዉ።

በሌላ አገላለጽ አዉሬዉን ማስራብ ያገራችንንና የወገናችንን የነጻነት ቀን ማፋጠን ነዉ!

ለዚህም በቅርቡ አለምአቀፍ የኢትዮጵያዉያን የጋራ ግንብረሃይል ባደረገዉ ጥሪ መሰረት፥

 • አንደኛ– አገር ቤት ያሉ ዘመዶቻችንና ወዳጆቻችን ለመርዳት የምንልከዉ ገንዘብ ወያኔ-ህወሃት እጅ ዉስጥ እንዳይገባ የምንችለዉን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። ይህም ማለት እንደዌስተርን ዩኒዬናና መኒ ግራም አይነት መደበኛ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችን መጠቀም ማቆምና፣ ገንዘብ መላካችን የግድ ከሆነ፣ ግብረ-ሃይሉ የጠቆማቸዉን ሌሎች መስመሮችንና ዘዴዎችን መጠቀም ማለት ነዉ።
 • ሁለተኛ – ይህ አገዛዝ ተወግዶ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አገሩንና መብቱን በእጁ እስኪያስገባ ድረስ፣ ምንም ዓይነት ኢንቨስትመንት አገር ቤት አለማድረግን ነዉ።

ከላይ እንደተመለከተዉ የወያኔ-ህወሃት አገዛዝ ከዉጭ የሚያገኘዉ የዉጭ ምንዛሬ ቢደርቅ፣ በስልጣን መሰንበት አይችልም። ይህም ማለት ዲያስፖራ ኢትዮጵያዉያን ፣ አገዛዙን ለማሽመድመድ፣ ብሎም እድሜዉ ለማሰጠር ቀላል የማይባል አቅም በእጃችን ዉስጥ አለ። ለዉድ አገራችንና ለደጉ ህዝባችን ስንል እንጠቀምበት!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.