የሚፈቱት ዳግም ስላለመታሰራቸው ማስተማመኛ የለም #ግርማ_ካሳ

የኢሕአዴግ የሥራ ሳፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ ነው ተብሎ ካነበብነው፣ ከሁሉም ማእዘናት ወገዛና ተቃዉሞን ካስከተለው ፍሬከርስኪ መግለጫ በኋላ ፣ በመግለጫው ላይ ያለውን በመደገፍ ሳይሆን፣ መግለጫው ላይ ካለው መንፈስ ፍጹም የተለየ ጋዜጣዊ መግለጫ የአራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መሪዎች ሰጥተዋል። አመራሮች ወደ ስብሰባው ሲገቡ እርስ በርስ ችግር እንደነበረባቸው ገልጸው ከስብሰባው በኋላ ግን የአገርን ችግር ለመፍታት መስማማታቸውን ነው የገለጹት። አሥራ ሰባት ቀናት ያደረጉት ስብሰባ የአገርን ችግር ለመፍታት ያስችል ዘንድ መሰረታዊ ዉሳኒዎች እንደወሰኑም ገልጸዋል።

ከዉስኒዎች መካከል አንደኛ የሕሊና እስረኞችን መፍታት፣ ሁለተኛ የቶርቸር አዳራሽ የሆነው፣ በደርግ ጊዜ ከነበረው አሥር እጥፍ ላለፉት 25 አመታት ፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ዜጎች በነጌታቸው አሰፋ ቀጥተኛ ትእዛዝ የተሰቃዩበትና ማእከላዊ ተብሎ የሚታወቀው የስቃይ ቤትን መዝጋት፣ ሶስተኛ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትና መድበለ ፓርቲ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዲጎለበት ማድረግ የመሳሰሉ ይገኙበታል።

ኢሕአዴግ ወደዚህ ዉሳኔ እንዲመጣ ብዙዎች ለአመታት ስንጠይቅና ስንጎተጉት ነበር። ቢረፈድም ለዚህ ዉሳኔ እንደ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ ድጋፌን ነው የምሰጠው። ለራሳቸው ሲሉ ትክክለኛ እርምጃ ነው የወሰዱት።

ወደዚህ ዉሳኔ የመጡት በቀላሉ አይደለም። በሕዝብ ትግል ነው። የሕዝብ ትግል በተለይም በብአዴንና በኦህዴድ አመራሮች ውስጥ ከፍተኛ ጫና ለማሳደር ችሏል። በኦሮሚያ የተደረገው እንቅስቃሴ በኦህዴድ ውስጥ እነ ለማ መገርሳ ወደ አመራር እንዲመጡ አደርጓል። እነ ለማ ትልቅ ድፍረት በተሞላበት ሁኔታ የኦፎኮ አመራሮችን ጨመሮ የኦሮሞ እስረኞች እንዲፈቱ በይፋ ግፊት ሲያደረጉ ነበር።

የአማራው ክልል አስተዳዳሪና የብአዴን ም/ሊቀመንበር አቶ ገዱ አንዳግራቸው በስራ አስፈጻሚው ስብሰባ ላይ የሕዝቡን ብሶት አጠንክረ ነው የገለጹት። አቶ ገዱ “ በምንም ዉስጥ የሌሉበት ተራ ገበሬወች ታፍነዉ ለወራት የት እንደገቡ ሳይታወቅ ህጻን ልጆችና ቤተሰብ እያለቀሱ ነግረዉኛል፡፡ ቢሮየ ድረስ ህጻናት ልጆች ይዘዉ ቤተሰብ ይመጣሉ፡፡ ማጣራት ሳይደረግና እኛን በወጉ ሳታናግሩ የፈለጋችሁትን ታደርጋላችሁ፡፡ አማራ ክልል ላይ ለተነሳዉ ነገር በዋነኛነት እናንተ ብትሆኑም እኔን ተጠያቂ አድርጋችኋል፡፡ ባልሰማንበት ሁኔታ ከሽሬ በመጡ የደህንነት ሰዎች እንዲሁም አየር ማረፊያን ይጠብቃሉ የተባሉ ከ 15 በላይ ፌዴራሎች በመጠቀም ሰዉ ለማፈን በተደረገዉ እንቅስቃሴ ይሄ ሁሉ ምስቅልቅል ተነስቷል” የሚል አቤቱታ እንዳቀረቡ ዘገባዎች ይጠቁማሉ።

የመከላከያውና የደህንነት መዋዋቅሩን በመቆጣጠር ከሕግ ውጭ ህዝባችንን ሲያሸበሩና ሲያምሱ የነበሩት ሕወሃቶች ምንም ምርጫ አልነበረባቸው። በሰብሰባዎቹ ጅማሬ ለማስፈራራት፣ ነባር አመራር ያሏቸውን በማስጠራት ለማባበልና ለማማለል ሞክረዋል። ሆኖም እነ ገዱና ለማ ጠንካር አሉባቸው። ሕወቶች እየገደሉ፣ እያሰሩ፣ እያሰቃዩ፣ እያስፈራሩ መቀጠል እንደማይችሉ፣ ለነለማና ገዱ ጥያቄዎች በተወሰነ መልኩም አዎንታዊ ምላሽ ካልሰጡ የኢሕአዴግ መፍረስ እንደሆነ በሚገባ ተረድተዉታል። ለዚህም ነው አሁን የሕሊና እስረኞችን መፍታትን ጨመሮ አንዳንድ አዎንታዊ እርምጃዎችን ለመዉስድ የተስማሙት። በለለማና ገዱ ግፊት። የነለማና ገዱ መነሳት ደግሞ የሕዝብ ትግል ዉጤት ነው።

ይሄን ብዬ መረሳት የሌለባቸው ነጥቦች ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡

አንደኛ – እስረኞቹ ገና አልይተፈቱም። ምን አልባት የኦሮሞ እስረኞችን ብቻ በመፍታት በብአዴንና በኦህዴድ መካከል ችግር እንዲፈጠር ሊያደረጉም ይችላሉ። ዶር መራራ ጉዲናና አቶ በቀለ ገርባ ከሚፈቱት ውስጥ እንደሚኖሩ ሪፖተር ጋዜጣ ቢዘግብም እነ አንድዋለም አራጌ ያሉ አንጋፋ ፖለቲከኞች፣ በጎንደር አስደማሚው ሰልፍ ከፍ ብሎ ስሙ ሲጠራ የነበረው ኮሎኔል ደመቀ ዘዉዱ፣ የጎንደሩ ሰልፍ ልእልት፣ ንግስት ይርጋ የመሳሰሉት ካልተፈቱ የአገዛዙ ዉሳኔ የተንኮል ዉሳኔ ነው ማለት ነው። ሰዎቹ ደግሞ ተንኮል በማሰብና በማድረግ የተካኑ በመሆናቸው ይሄንን ብንጠረጠር አይፈረድብንም

ሁለተኛ – የእስረኞች መፈታት አስደሳች ቢሆንም በራሱ የአገር ችግር ስለመፈታቱ በጭራሽ አመላካች አይደለም። ከምርጫ 97 በኋላ የታሰሩ የቅንጅት መሪዎች ከሁለት አመታት በኋላ ተፈተው ነበር። ሆኖም አሁን ያለው የእስረኛ ቁጥር በዘጠና ሰባት ከነበረው መቶ እጥፍ ነው። ያኔ ታስረው የተፈቱ አሁን የታሰሩ እስረኞች ብዙ ናቸው። አንዱዋለም አራጌ፣ እስክንደር ነጋ ያኔ ታስረው ተፈተው ነበር። አሁን ግን እስር ቤት ናቸው። በመሆኑም አሁን የታሰሩ ቢፈቱም፣ ነገ ተመልሰው ስላለመታሰራቸው ምንም ማስተማመኛ የለም። እነዚህ ዜጎች መጀመሪያዉኑ መታሰር አልነበረባቸው። የታሰሩት አገራቸውንና ሕዝባቸውን በመዉደዳቸው ነው። ምስክሮችን በማስጠናት የዉሸት ማስረጃ እየቀረበ፣ ለዳኞች ከደህንነት ክፍሉ መመሪያ እየተሰጠ፣ ዜጎች የማሰርና የማሰቃየት አሰራር ከስር መሰረቱ ካልተነቀለ፣ በትክክል የሕግ ስርዓት ካልተዘረጋ ፣ እስረኞችን ፈታሁ ማለት ለጊዜው የፖለቲካ ትኩሳቱን ለማብረድ ከማሰብ ዉጭ ምንም ፋይዳ አይኖረውም።

ሶስተኛ – የፖለቲክ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ ስራ እንደሚሰራ ተነግሮናል። መልክም ነው። ግን በዋናነት የደህንነትና የመከላከያ መዋቅሩ ካልተቀየረ በቀር ዜጎች በነጻነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ያዳግታቸዋል። በአሁኑ ወቅት ሕወሃት የመከላከያዉንና የደህንነቱን መዋቅር አፍኖ ይዟል። በዚህ ረገድ ከኢሕአዴግ ግንባር ድርጅት አመራሮች የሰማነው ነገር የለም። እነ ሃይለማሪያም በሚኒስተሮች ምክር ቤት፣ እነ ለማና ገዱ በክልል መንግስታት ምክር ቤት የሚወስኑትን ዉሳኔዎች፣ ጌታቸው አሰፋ ከነ ስብሀት ነጋ ጋር ሆኖ በጎን መመሪያ እየሰጠ የሚሽር ከሆነ፣ የሃይለማሪያም በቴሌቭዥን ቀርቦ መግለጫ መስጠት የተለመደ ድራማ ከመሆን ውጭ ሌላ ሊባል አይችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አቶ ሃይለማሪያም እመራዋለሁ ከሚሉት መንግስት ጎን ለጎን የሚሰራ፣ አቶ ሃይለማሪያምን የሚያዘው፣ በአገሪቷ የፈለገው የሚነቅለንና የሚተክል ፣ ሕወሃቶች ብቻ ያሉበት፣ ኤርሚያ ለገሰ፣ የካስንሺስ መንግስት የሚለው መፍረስ አለበት።

ያ እስካልሆነ ድረስ፣ እነ ሃይለማሪያም በሰጡት መግለጫ መደሰታችን ተገቢ ቢሆንም ብዙ ጮቤ ባንረግጥ ጥሩ ነው። እዚህ ደረጃ የተደረሰው በትግል ነው። ሕወሃቶች አዘናግተው፣ አፈር ልሰው እንደገና የበለጠ ጠንካራ ሆነው ከመውጣታቸው በፊት ትግሉን የበለጠ ማጠናከር አስፈላጊ ነው። በጭራሽ መዘናጋት አያስፈለግም። ሰላማዊ በሆነ መንገድ ትግሉ መቀጠል አለበት።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.