የጠቅላይ ሚኒስተሩን ንግግር መርዝን በማር ጠቅልሎ የሚያጎርስ ነው

የአቶ ሀይለማሪያ ደሳለኝን መግለጫ የህወሓት መሪዎች ከገቡበት አጣብቅኝ ወጥተው እንደገና እስከሚጠናከሩ ድረስ ጊዜ ለመግዛት፣ የጋለ የህዝቡን ዓመፅ ለማቀዝቀዝ ፣ የዓለም ማሕበረሰብን ቀልብ ለመቀየርና እርስ በራሳችን ጥርጣሬ ውስጥ እንድንገባ ለማድረግ ሲባል ሆን ተብሎ ወደ ሕብረተሰቡ የተወረወረ የማዘናጊያ አጀንዳና የቤት ስራ ነው::

ከባርናባስ ገብረማሪያ

Bega2260@comcast.net

የህወሓት/ኢሕአዴግ መሪዎች የህዝብ ዓመፅና የውጭ ዓለም ጫና በበረታባቸው ቁጥር ከገቡበት አጣብቅኝና ከተጣሉበት አዘቅት ለመውጣት ሁሉ ጊዜ የሚጠቀሙበት ስልት አሳሳች የሆነ መግለጫ ይፋ ማድረግ ወይም አደናጋሪ ወሬ ማናፈስ የተለመደ የማጭበርበሪያ ተግባራቸው መሆኑን ያዳባባይ ሚስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል:: ይህን ዓይነቱ የማታሊያ ዘዴ ደግሞ ይቅርና ኢትዮ}ያውያን ቀርቶ የዓለም ማሕበረሰብም ጭምር ነቅቶባቿል:: እውነት ለሀገራቸውና ለወገናቸው የሚያስቡ ቢሆን ኖሮ አሁን ላለው የሀገሪቱንና የህዝቡን አንድነት ፣ ድህንነትና ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ቀውስ መፍትሄ ሊሆን የሚችል ፓሊሲ ይዘው በመጡ ነበር:: ነገር ግን አልተቻለም:: ከእባብ እንቁላል እርግብ ይወለዳል ብሎ መጠበቅ እንደማይቻል ሁሉ በቅርቡ በደረሰባቸው የፓለቲካ ኪሳራን መካካሻና ማታሊያ ሊሆን ይችላል ብለው ያወጡትን የጭንቀት መግለጫ ሳይበቃ ዛሬም አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝና መሰሎቻቸው የሰጡትን አሳሳች ንግግር አዲስ ሳይሆን የተለመደ ጭኾት ነው:: ለምሳሌ አቶ ሀይለማሪያም ራሳቸው ባለፉት ቅርብ ዓመታት ምን ይሉ እንደነበር እንመልከት:-

  1. በአዲስ አበባ አካባቢ ያለውን መሬት በከተማዋ ስር ለማካለል በወጣው መመሪያ ሳቢያ በኦሮሚያ ምድር በተነሳው የህዝብ ዓመፅ በመቶዎች የሚቆጠር ህይወት ከጠፋና ስንቱን ንብረት ከወደመ በሗላ ሁኔታው ከቁጥጥራቸው ውጭ እየሆነ ሲሄድ “ስህተቱ የመንግስት ነው የህዝቡ አይደለም:: ስለዚህ በመንግስት ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ:: ለደረሰው ጉዳትም እርምጃ እንወስዳለን::” በማለት ተናግረው እንደነበር ይታወሳል:: ይሁን እንጂ በተግባር የታየው በይፋ የተናገሩትን ቃል ሳይሆን በተቃራኒው የመድረክ አባል ድርጅቶች አመራርን ጨምሮ  በሽዎች የሚቆጠሩት ሰፊ አባላቶቻቸው ከያሉበት እየመነጠሩ ማጉሪያና ማጥቂያ አድርገው ነው የተጠቀሙበት እንጂ አንዳች የመፍትሄ እርምጃ አልወሰዱም::

 

  1. ከዚያም በሗላ በጎንደር በጎጃምና በወሎ አካባቢዎች ተክስቶ በነበረበት የህዝብ ዓመፅም የተከተሉት አካሄድ ተመሳሳይ ነው:: የዓመፁን ወላፈኑ ወደነሱ እንዳይጠጋ የተጠቀሙበት ስልት በስተጀርባ ሆነው አቅጣጫውን በመቀየር እርስ በርስ እንዲሆን በማድረግ የስንቱን ህይወት ካጠፉ በሗላ:: ጠቅላይ ሚኒስተር ሀይለማሪያምም በተለመደው አንደቤታቸው “ለደረሰው የህይወትና የንብረት ጉዳት እናዝናለን:: ይቅርታም እንጠይቃለን:: ችግሩን ለመፍታት ደግሞ ስብሰባ አድርገን ጥልቅ ተሃድሶ እናደርጋለን:: የመንግስት ስልጣን እየተጠቀሙ የግል ሃብታቸውን በሚደልቡ ባለስልጣናት ላይም ምሕረት የለሽ እርምጃ እንወስዳለን” ብለው እንደነበር ይታወሳል:: ነገር ግን አንዳች እርምጃ አልተወሰደም:: በዚያን ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስተሩን ንግግር ተከትሎ የተካሄደው የህወሓት/ኢሕአዴግ ማእከላይ ኮሚቴ ስብሰባ መግለጫ ተብሎ የወጣው ፅሑፍም ጥልቅ ተሃድሶ ሳይሆን የአቶ ሀይለማሪያምን ሃሳብ በመሰረቱ የሚፃረር እንደነበር እናስታውሳለን::

 

  1. አሁንም በተመሳሳይ መልኩ ህዝቡና ወጣቱ በጋራ ሆነው የህወሓትን ዓፋኝ አገዛዝ በቃኝ ብለው ለአንዴና ለመጨረሻ ከጫንቃቸው አውርዶው ለመጣል በሀገር ውስጥም ሆነ በዲያስፓራ ትልቅ ሀገራዊ ንቅናቄና መነሳሳት ተፋፍሞ የዓመፁን ነበልባል ደጃፋቸውን ማንኳኳት ሲጀምር በመደናገጥ የነብስ አድን መግለጫ ማውጣታቸው የሚገርም አይደለም:: ችግሩ የፓለቲካ እስረኞችን እንፈታለን ብለው በመናገራቸው አይደለም:: ካደረጉትማ እሰየው ነው:: ነገር ግን እኛ እያልን ያለነው ከባህሪያቸውና ከልምዳቸው እንዳየነው የተቃውሞ ማስታገሻ ካልሆነ በስተቀር የተናገሩትን ተግባር ላይ አይውልም ነው:: ቀበሮ የበግ ለምድ ለብሶ ቢመጣ ማንንም ማታለል አይችልም ምክንያቱም ተግባሩን ያገልጧልና:: የሰው ልጅ ህይወት የዶሮን ያህል ክብር የማይሰጡ፣ ዓይናቸውን በፍቅረ ንዋይና በስልጣን ጥም የታወሩ፣ የወገን ፍቅር የሌላቸውና ሕግ የማይገዛቸው መሪዎች ለሰብኣዊ መብት ይቆማሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም::

 

  1. ትናንት የፓለቲካ እስረኛ የሚባል ፈፅሞ የለንም ብለው ሲክዱ ቆይተው ዛሬ በሀገሪትዋ ውስጥ በእስር ቤት ታጉረው የሚገኙትን የፓለቲካ እስረኞ እንፈታለን ብለው ሲናገሩ በአንድ በኩል ስርዓቱ ምን ያህል ነውረኛና ውሸተኛ መሆኑን የሚገልፅ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የህዝቡን ዓመፅና ባጠቃላይ የታጋይ ሀይሉን ድምር እንቅስቃሴ ሃያልነትንና ተፅዕኖ ፈጣሪ እየሆነ መምጣቱን አማላካች ነው:: ስለሆነም እነሱ የፈለጉትን ይናገሩ በምንም መልኩ ላንድ አፍታ እንኳን ቢሆን ሳንዘናጋ ነቅተን በመከታተል በየጊዜው የሚፈጠሩትን አዳዲስ ሁኔታዎችን ወደ ራሳችን የትግል መስመር በመቀየርና ማጠናከሪያ አድርገን በመጠቀም እንቅስቃሲያችንን በበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት:: ሁሉ ጊዜ የምንከበረውና ጫና መፍጠር የምንችለው ስንተባበርና ጉልበት ሲኖረን ብቻ ነው:: ስለዚህ ትግላችን ፍሬ እያወጣ ነው:: ዛሬ ቀባሪ ያጣውና አንድ ሐሙስ የቀረውን የበሰበሰ ስርዓት የፈለገውን መግለጫ ያውጣ በምንም መልኩ እንደገና ተጠናክሮ እንዲወጣና በየተራ ሲቀጠቅጠን እንዲኖር ዕድል መሰጠት የለበትም::

 

  1. የህወሓት/ኢሕአዴግ የዓፈና መርበቦችና ተቋማት ሳይቀየሩ እንደተበተቡ ባሉበት ሁኔታ፣ የመርፌን ቀዳዳ ያህል የጠበበው የፓለቲካ ምሕዳ እንደተዘጋ ባለበትና እንዲሁም የመከላኪያ አፈ ሙዝ የአንድ ሞኖፓላዊ ፓርቲ መገልገያ መሳሪያ በማድረግ ጭቁኖችን እየገደሉና እያሳደዱ ባለበት ሁኔታ ላይ ሆነው ዛሬ የፓለቲካ እስረኞችን እንፈታሉን ቢሉ የሚያምናቸው የለም:: ዛሬ እስረኞችን እንፈታለን ቢሉም ለዓፈናና ለእስር ምክንያት የሆነውን ፓሊሲ ሳይቀየር ነገ ሰበብ አስባብ እየተፈለገ በሽዎች የሚቆጠሩትን ዜጎች መታጎራቸው የማይቀር ነው::

ስለሆነም መፍትሄው በፒያሳ ላይ ያለውን አረጌው እስር ቤት በሌላ አዲስ እስር ቤት መተካት አይደለም:: ነገር ግን መሰረታዊ መፍትሄው ለሁሉም ችግሮች መንሲኤ የሆነውን የህወሓት አረሜናዊ ስርዓትን ማስወገድ ነው:: ችግሩ በፒያሳ ያለው እስር ቤት ሳይሆን በአራት ኪሎ በቤተ መንግስቱ ዙሪያ የተሰገሰጉ መሪዎች ናቸው:: መሰረታዊ መፍትሄው ለጥላቻ ፣ ለመናቆር ፣ ለግድያ ፣ ለዝርፊያ ፣ ለስደት ፣ ለእስርና ለዓፈና ምንጭ የሆነውን የህወሓት ስርዓት በተባበረ ክንድ ከነግሳንግሱ ጠራርጎ ማስወገዱ ላይ ነው:: ከዚህ ሌላ አማራጭ የለንም:: “ ጆሮዋን ቆርጠው የሰጧትን ውሻ ስጋ የጧት ይመስላታል ” እንዲሉ ህዝባችንን በዘር ፣ በሀይማኖት ፣ በክልል ፣ በቋንቋ እየከፋፈሉና ብሎም ሀገራችንን እያፈረሱና ሉዓላዊ ክብራችንን እያስደፈሩ ነፃ እናወጣችሗለን ቢሉን እንደለመዱት ለማሞኘት ከመሞኮር አልፎ ሌላ ትርጉም አይኖረው::

በማጠቃለል የህወሓት መሪዎች እነሱንም ጭምር ነፃ የሚያወጣ የፓሊሲ ለውጥ ለማድረግ ያልደፈሩ ሰዎች ዛሬ ለስልጣናችን አደጋ ናቸው ብለው ያሰሯቸውን እስረኞችን ለመፍታት የሞራል ግዴታና ሃላፊነት ተሰምቷቸው በተግባር ይፈፅማሉ ብዬ አላምንም:: ምናልባት ለይስሙላ ጥቂት ሰዎችን ይፈቱና ሌሎች በሽዎች የሚቆጠሩትን እናጣራለን እያሉ ከማሸትና ከማሰቃየት በስተቀር አፋጣኝ እርምጃ ይወስዳሉ ብለን አንጠብቅም:: ነፃ የብዙሃን መገናኛ ፣ ነፃ የፍትሕና የዳኝነት ተቋማት እስከሌሉ ድርስ የተኛው እስረኛ የት እንዳለና በህይወት ይኑር አይኑር የማይታወቅ፣ በየቦታው የታጎሩትን የህሊና እስረኞች ስንት እንደሆኑም የሚያጣራ ገለልተኛ አካል በሌለበት ሁኔታ የወጣውን መግለጫ ለይስሙላ ለፕሮፓጋንዳቸው ጠቀሜታ ከመሆን አልፎ ፋይዳ አይኖረውም::

 

በቸር ይግጠመን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.