የቴዲ አፍሮ የባህርዳር ኮንሰርት በአንድ ቀን ተራዘመ

ከቴዲ አፍሮ የተሰጠ መግለጫ

ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር ! ጥር 13 ይካሄዳል

በቅድሚያ በባሕር ዳር ከተማ በታላቁ ብሔራዊ ስታድየም ” ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር ” በሚል ጉዞ የሙዚቃ ዝግጅቴን እንደማቀርብ ካሳወኩበት ጊዜ ጀምሮ በመላው አለም የምትገኙ አድናቂዎቼ ላሳያችሁኝ ፍቅርና ላደረሳችሁኝ የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክቶቻችሁ የከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ቀደም ብለን የሙዚቃ ድግሳችንን ልናቀርብ ያቀድንበት ጥር 12 ቀን በጥምቀት ማግስት በታላቅ ሐይማኖታዊና ባሕላዊ ድምቀት ከሚከበረው የቃና ዘገሊላ ክብረ በአል ጋር በመገጣጠሙ ፥ ራቅ ካሉ ከተሞች ወደ ባሕር ዳር ለምትመጡት አድናቂዎቼ አስቸጋሪ እንደሚሆንባችሁ በተለይም የታሪካዊቷ ጎንደር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች በደብዳቤ፣ በስልክና በኦፊሻላዊው የፌስ ቡክ ገፄ ገልፃችሁልኛል ።

እኔም እጅግ ከምወደውና ከማከብረው የጎንደር ሕዝብ እንዲሁም ከተለያዩ የሃገራችን ከተሞች ከሚኖሩ አክባሪዎቼና አድናቂዎቼ የቀረበልኝን ይህን የቀን ይቀየርልን ጥያቄ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የሙዚቃ ድግሳችንን በቃና ዘገሊላ ማግስት ዕሁድ ጥር 13 ቀን በታላቁ ብሔራዊ ስታድየም ለማካሄድ መወሰናችንን ከአክብሮት ጋር እያሳወቅሁ ፤ ኑና ስለ ፍቅር፣ ስለ ሰላምና ስለ አንድነት አብረን እንዘምር እላለሁ ።

ከምንም በላይ ደግሞ ይህ የሙዚቃ ኮንሰርት ኢትዮጵያዊነት የሚደምቅበትና ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ የሚታይበት ምሽት ይሆናልና በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች የምትገኙ ወዳጆቻችን መጥታችሁ እንድምትደሰቱ እርግጠኞች ነን ።

ሃገራችን ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !
ፍቅር ያሸንፋል !
ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.