የዛሬው ኢሳት አጫጭች ዜናዎች

1) (ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2010) በኢትዮጵያ የተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ የህወሃትን አገዛዝ ለተፋጠነ ውድቀት ሊዳርገው እንደሚችል ተገለጸ። ኢሳት ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉት የፖለቲካ አለመረጋጋት እየናጠው ያለው አገዛዝ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ መግባቱ ውድቀቱን እያፋጠነው ነው። ሀገሪቱ የገጠማት የኢኮኖሚ አደጋ አሁን በስልጣን ላይ ባለው አገዛዝ አቅም የሚፈታ ባለመሆኑ ህዝባዊ አመጾች ሚነሱበት እድል ሰፊ ነው ሲሉ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። የአገዛዙ ደጋፊ መገናኛ ብዙሃንም የኢኮኖሚ ቀውሱን በመጥቀስ ከፍተኛ አደጋ እየመጣ ነው ሲሉ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው። ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ ነው የሚለው ድምጽ እየጎላ የመጣው ከብዙ አቅጣጫ ነው። በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ኢኮኖሚውን አንኮታክቶታል የሚለው አስተያየት ተጠናክሮ መሰማቱን ቀጥሏል። የውጭ ምንዛሪ ክምችት በአስደንጋጭ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። ሀገሪቱ ያላት የውጭ የምንዛሪ ክምችት ከ1ቢለየን ዶላር በታች 700ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች ኢኮኖሚው ሙሉ በሙሉ ቀጥ ብሎ ከሚቆምበት ምዕራፍ ተጠግቷል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ። ለመድሃኒት መግዣ በሚል የሚፈቀደው የውጭ ምንዛሪ ከአንድ ወር በላይ የማያዛልቅ መሆኑ አደጋውን የበለጠ ያሰፋዋል ብለዋል። ኢሳት ያነጋገራቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ቀድሞውኑም የተበላሸው የኢኮኖሚ ገጽታ በፖለቲካው ትርምስ ምክንያት ቀና ከማይልበት ደረጃ ላይ ይገኛል። በሀገሪቱ በየአቅጣጫው የተነሳው የህዝብ አመጽ በዋናነት የኢኮኖሚ ጥያቄ ማጠንጠኛ መሆኑን የሚጠቅሱት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የአገዛዙ ውድቀት ከሚጠበቀው በላይ በፍጥነት ሊሆን እንደሚችል ምልክቶቹ በሚገባ እየታዩ ነው ሲሉ ይገልጻሉ። አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እንዳሉት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ፍጥነት ወደቀውስ እየገባች ነው። ኢኮኖሚው ወድቋል። አገዛዙ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ ተስኖታል። አንድ ሊፈራርስ የተቃረበ ስርዓት የሚታዩብት ምልክቶች አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጠው በመታየት ላይ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። ለአገዛዙ ቅርበት ያለው ሪፖርተር ጋዜጣ በጉዳዩ ላይ ጠንከር ያለ ዘገባ ያወጣው ህወሃት የገጠመው የኢኮኖሚ ቀውስ መደበቅ ከማይቻልበት ጊዜ ላይ በመድረሱ ነው ሲሉ ታዛቢዎች ይገልጻሉ። እንደሪፖርተር ዘገባ ከሆነ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንደበረዶ እየቀለጠ ነው። የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ መቀነስ ታይቶበታል። የንግድ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዟል። የግብይት ስርዓት ትርምስ ውስጥ ገብቷል። የቱሪዝም ፍሰቱ አደጋ ውስጥ ወድቋል። የዋጋ ግሽበቱ ወደሁለት አሃዝ ሲገባ የብር የመግዛት አቅም መቀነሱ ይበልጥ ኢኮኖሚውን አሽመድምዶታል። በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ሀገሪቱ እጅና እግሯ ተሳስሯል ሲል ቀውሱን በዝርዝር የገለጸው ሪፖርተር ጋዜጣ ይህ ሁኔታ በፍጥነት ካልተቀየረ አደጋው ከባድ ነው ሲል አስጠንቅቋል። የሪፖርተር ስጋት የአገዛዙ መውደቅ መሆኑ በግልጽ ያሳያሉ የሚሉ ታዛቢዎች ሊደበቅ የማይችለውን ቀውስ በአገዛዙ መገናኛ ብዙሃን ማስተንፈስ እንደአንድ ስልት ሊወሰድ ይችላል ሲሉም ግምታቸውን ገልጸዋል። በአሜሪካ ቨርጂኒያ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶክተር ዘላለም ተክሉ እንደሚሉት የፖለቲካውና የኢኮኖሚው ቀውሶች በአንድ ጊዜ ጎን ለጎን መከሰታቸው የህወሀትን አገዛዝ ውድቀት አይቀሬ አድርጎታል።


Inline image 1
 
2) (ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2010) የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ/ሕወሃት/ መንግስት ከእንግዲህ በማናቸውም ጥገናዊ ለውጥ ሊነሳ የማይችል ያበቃለት ቡድን መሆኑን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ገለጹ። አዲስአበባ ድረስ ታንክና መድፍ ይዘን የገባነው ለሁለቱ ህዝቦች ዘላቂ ጥቅም ስንል ነበር ሲሉም ተደምጠዋል። የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ትላንት በኤርትራ ቴሌቪዥን በተላለፈው ቃለ ምልልሳቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ በህወሃት አደፍራሽነት 25 አመታት የገጠማቸውን ኪሳራ የሚያስመልሱበት ግዜ ሩቅ እንዳልሆነም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን ቀውስ በተመለከተ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የወደፊቱን ለማየት ያለፈውን መቃኘት ያስፈልጋል በሚል የችግሩ መነሻ ነው ያሉትን ዘርዝረዋል። ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ በኢትዮጵያ ውስጥ የበላይ ሆኖ ለመቆየት ሕዝቡን በመከፋፈል መንቀሳቀሱና አንቀጽ 39ኝን በህገ መንግስቱ ውስጥ ማካተቱ ችግር መሆኑን ገልጸዋል። ከመነሻው ይህ መንገድ ትክክል እንዳልነበር ነግረናቸዋል ያሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከጤናማ አዕምሮ የማይመነጭ አፍራሽ ሃሳብ በግዜ ሂደት ሀገሪቱን እንዲህ ያለ ቀውስ ውስጥ እንደከተታትም አመልክተዋል። የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በአንድ ብሔር መያዝን ጨምሮ ለቀውሱ መባባስ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ከመነሻው እንደማያዋጣ በኤርትራ በኩል እንደተነገራቸው አስታውሰዋል። የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ቡድን ከእንግዲህ አብቅቶለታል ያሉት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝብ ዘላቂ ስትራቴጂካዊ ወዳጅነት ስንል የሕወሃትን መንግስት የሚቃወሙትን መደገፋችን ትክክል ነው ብለዋል። ቀደም ሲል ለሕወሃት የሰጡትና አዲስ አበባ ድረስ ያደረጉት ድጋፍ ለሁለቱ ህዝብ ይጠቅማል በሚል ነው ሲሉ ሁኔታውን ይገልጻሉ። “ታንኮቻችንንና መድፎቻችንን ይዘን አዲስ አበባ ድረስ ዘልቀን የገባነው ለጉራና ለዝና ሳይሆን ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝብ የወደፊት እድል ዋስትና ለመስጠት ነበር”ሲሉ ተናግረዋል።
Inline image 2
 
3)

ሱዳን ተጨማሪ ወታደሮቿን ወደ ኤርትራ ድንበር አስጠጋች

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2010)

Inline image 4

ከግብጽ ጋር ውዝግብ ውስጥ የገባችው ሱዳን ተጨማሪ ወታደሮቿን ወደ ኤርትራ ድንበር ከሰላ ማስጠጋቷን የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ትላንት በሱዳን ካርቱም የተገናኙት የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዱር ርምጃውን የወሰድነው በደረሰን መረጃ ላይ ተመስርተን ነው ብለዋል።

በወሩ መጀመሪያ ላይ ከኤርትራ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ሙሉ በሙሉ የዘጋችው ሱዳን ቀደም ሲል በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ ኤርትራ ድንበር ማስጠጋቷ ይታወሳል።

ሱዳን ወታደሮቿን ወደ ኤርትራ ድንበር ያስጠጋችው የግብጽ ወታደሮች ኤርትራ መግባታቸውን ተከትሎ እንደሆነም ይታወሳል።

ግብጽ ወታደሮቿን ወደ ኤርትራ የላከችበትና ከሱዳን ጋር ውዝግቡ የተካረረበት ሁኔታ የተከተለው ሱዳን ከቱርክ ጋር ባደረገችው ስምምነት ምክንያት እንደነበርም አልጀዚራ በዘገባው አስታውሷል።

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በታህሳስ በካርቱም ከሱዳን ፕሬዝዳት ጄኔራል ኦማር አልበሽር ጋር ያደረጉት ስምምነት ግብጽን አስቆጥቷል።

ሱዳን ሱአኪን የተባለውን ደሴቷን ለቱርክ አሳልፋ መስጠቷና ይህም ቱርክ በቦታው ወታደራዊ ሰፈር ልትገነባ ነው የሚል ጥርጣሬ መከተሉ ካይሮና ካርቱምን ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ አስገብቷል።

በሕጋዊ መንገድ በግብጽ ሕዝብ ምርጫ ወደ ስልጣን የወጡት ፕሬዝዳንት መሀመድ ሙርሲ በጄኔራል አልሲሲ መፈንቅለ መንግስት መባረራቸውን ቱርክ ተቃውማለች።

በዚህም በግብጽና በቱርክ መካከል ጤናማ ግንኙነት አለመኖሩ አሁን ለተፈጠረው ቀውስ በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች አንዱ ሆኗል።

ቱርክ በሱዳን የጦር ሰፈር ማግኘቷን ተከትሎ ግብጽ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ወደ ኤርትራ በመላክ በሱዳን ድንበር በኩል አስፍራለች።

ሱዳንም በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን ወደ ኤርትራ ድንበር ከማስጠጋቷም ባሻገር ከኤርትራ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ሙሉ በሙሉ ዘግታለች።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዱር ተጨማሪ የሱዳን ወታደሮች ከኤርትራ ጋር በሚዋሰኑበት ከሰላ ማስጠጋታቸውን ትላንት ይፋ አድርገዋል።

ርምጃውም የተደቀነውን ስጋት ለመከላከል እንደሆነም ጠቁመዋል።

የሱዳንና የግብጽ ውዝግብ ኢትዮጵያና ኤርትራንም በተዘዋዋሪ እያሳተፈ ይገኛል።

የኤርትራው ፕሬዝዳት ኢሳያስ አፈወርቂ ባለፈው ሳምንት ወደ ካይሮ ሲሄዱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ትላንት ካርቱም ገብተዋል።

የሱዳን ጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም ባለፈው ሳምንት አዲስአበባ መሄዳቸው ሲታወስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ ዛሬ ካይሮ ይገባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ባልታወቀ ምክንያት ጉዞው ወደ ረቡዕ መሻገሩ ተሰምቷል።

የግብጽ ወታደሮች ኤርትራ ገብተዋል በሚል አልጀዚራ የዘገበው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፈጠራ ዜና ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

4)አራት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተገደሉ 10 ቆሰሉ

Inline image 3

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2010)

የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ታጣቂዎች አራት የመከላከያ ሰራዊት አባላትን መግደላቸውንና 10 ማቁሰላቸው ተገለጸ።

ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በ14 የፖለቲካ እስረኞች ላይ የጥፋተኝነት ብይን ተሰቷል።

በችሎቱ እንደተገለጸውም የንቅናቄው ታጣቂዎች በ2007 በሁመራ በኩል በመግባት በሰነዘሩት ጥቃት የመንግስት ወታደሮች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉም ውሳኔ አሳልፏል።

በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከሰኔ 25 እስከ ሰኔ 28 2007 የተደረገው ውጊያ ነው ዛሬ በፍርድ ቤት ክስ ሆኖ የተነበበውና ብያኔ የተሰጠው።

ከክሱ መረዳት እንደተቻለው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ታጣቂዎች በቃፍታ ሁመራ በኩል ሰርገው በመግባት ከትግራይ ክልል ሚሊሺያ፣ ልዩ ሃይልና ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ውጊያ ይገጥማሉ።

ለአራት ቀናት ውጊያ መደረጉን በወቅቱ በኢሳትና በሌሎች የዜና ምንጮች የተገለጸ ሲሆን በወቅቱ መረጃውን ሀሰት በማለት የህወሀት አገዛዝ መገናኛ ብዙሃን ማጣጣላቸው የሚታወስ ነው።

ነገር ግን ውጊያ መደረጉንና በዚህም ውጊያ አራት የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮች ተገድለዋል ሲል በክስ መዝገቡ ላይ ተብራርቷል።

ሌሎች 10 የሰራዊቱ አባላትም በውጊያው እንደቆሰሉ ተጠቅሷል።

በአንድ መዝገብ የተከሰሱትና በስም የተዘረዘሩት የንቅናቄው ታጣቂዎች ገብሬ ንጉሴ፣ አገናኝ ካሱ፣ ስማቸው አምበሉ፣ ባባዬ አዛናው፣ አስቻለው ክፍሌ፣ ደሴ ክንዴ፣ ክብረት አያሌው፣ ብርሃን ዳርጌ፣ አወቀ መኮንን፣አበረ ፋንታሁን፣ሻንቆ ብርሃኑ፣ ጌትነት ዘሌ፣ ተሻገር መስፍን እና ሰጤ ጎባለ ናቸው።

በክስ መዝገቡ ላይ እንደተብራራው የንቅናቄው ታጣቂዎች በትግራይ ክልል ልዩ ሃይልና ሚሊሺያ እንዲሁም በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ከባድ ጉዳት አድርሰዋል።

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ሆኖ ስላገኛቸው እንዲከላከሉ ሲል ብይን መስጠቱን ለማወቅ ተችሏል።

ከተከሳሾቹ 9ኙ አንከላከልም በማለታቸው የመጨረሻ ብይን ሊሰጣቸው ለጥር 17 ቀጠሮ መሰጠቱ ተገልጿል።

እንከላከላለን ያሉት ቀሪዎቹ ተከሳሾች ምስክር እንዲያቀርቡ ለየካቲት 8 2010 መቀጠሩም ተመልክቷል።

አርበኞች ግንቦት ሰባት በተደጋጋሚ በመንግስት የተለያዩ የጸጥታና የመከላከያ ተቋማት ላይ ጥቃት እንደሚያደርስ ሲገልጽ ቢቆይም የህወሃት አገዛዝ ሲያስተባብልና ሲያጣጥል እንደነበረ የሚታወስ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የፍርድ ቤት ችሎቶች ላይ አርበኞች ግንቦት ሰባት አደረስኩ የሚላቸው ጥቃቶች ማረጋገጫ እየተሰጣቸው ነው።

ከአንድ ወር በፊት በህወሃት ንብረት በሆነው ሰላም ባስ ዋና ጋራዥ ጥቃት መሰንዘሩን በፍርድ ቤት በቀረበ ክስ መረጋገጡ ይታወሳል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሰሞኑን አደረስኩ ባለው ጥቃት ድል እንደቀናው አስታውቋል።

ንቅናቄው ለኢሳት በላከው መግለጫ ላይ እንደተመለከተው በሰሜን ጎንደር ዞን በለሳ አርባያ ወረዳ ጣና ኢየሱስ በተባለ ስፍራ የንቅናቄው ታጣቂዎች በፈጸሙት ድንገተኛ ጥቃት የወረዳው የጸጥታ ምክትል ሃላፊ አቶ በላቸው ፍቃዴ ሲገደል ሌላ የመንግስት ታጣቂ ጉዳት ደርሶበታል።

ይህን ጥቃት በተመለከተ ከህወሀት አገዛዝ በኩል ማስተባበያም ማረጋገጫም አልተሰጠም።

5)

የ528 ሰዎች ክስ ተቋረጠ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2010)

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የፖለቲካ እስረኞችን እፈታለሁ ያለው የሕወሃት አገዛዝ የ528 ሰዎችን ክስ ማቋረጡን ገለጸ።

ከነዚሁ መካከል 413 ክሶች የተቋረጡት ከደቡብ ክልል በጌዲዮና ኮንሶ ዞኖች ሲሆን ቀሪዎቹ 115ቱ ደግሞ ከፌደራል ናቸው።

ከሌሎቹም ክልሎች ጉዳያቸው ተጣርቶ ሲመጣ ክሳቸው ተቋርጦ የሚለቀቁ እንደሚኖሩ ተገልጿል።

የፌደራል ዋና አቃቢ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ከእስር ክሳቸው ተቋርጦ የሚለቀቁት ሕገ መንግስታዊ ስርአቱን በመናድ እንቅስቃሴ ያልተሳተፉና ሌሎችንም መስፈርቶች ያሟሉ ናቸው።

ዋና አቃቢ ሕጉ ጌታቸው አምባዬ ክሳቸው ስለተቋረጠ የፖለቲካ እስረኞች ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁም መግለጫ የሚፈቱና የማይፈቱ በሚል በአገዛዙ የተቀመጡ መስፈርቶችን ይፋ አድርገዋል።

አቶ ጌታቸው እንዳሉት ሕገመንግስቱን በሃይል ለመናድ የተንቀሳቀሱ የፖለቲካ እስረኞች አይፈቱም።

በዚሁም መሰረት ሕዝቡ ይፈታሉ ብሎ የጠበቃቸው የተወሰኑ የፖለቲካ እስረኞች ላይፈቱ እንደሚችሉ የአቶ ጌታቸው አምባዬ መግለጫ አመላክቷል።

ሕገመንግስት በሃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል፣መፈንቅለ መንግስት ለማድረግም ሞክረዋል ተብለው የተፈረጁና የታሰሩት ጂኔራል ተፈራ ማሞ፣ጄኔራል አሳምነው ጽጌና የመሳሰሉት እንደነበሩ ይታወሳል።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም በዚሁ ክስ ተፈርጀው ሞት የተፈረደባቸውና አሁንም ከየመን ታፍነው በእስር ላይ የሚገኙ ናቸው።

በዋና አቃቤሕጉ መግለጫ መሰረት በጸረ ሽብር ሕጉ ተከሰው መስፈርቱን የሚያሟሉ ሰዎች ግን በ2 ወር ጊዜ ውስጥ ተጣርቶ በይቅርታና በምህረት ሊፈቱ የሚችሉበት ሁኔታ ይኖራል።

እናም በጸረ ሽብር ሕግ ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት አንዱአለም አራጌ፣እስክንድር ነጋና ውብሸት ታዬን የመሳሰሉት የፖለቲካ እስረኞች ሊፈቱ እንደሚችሉ መግለጫው አመላክቷል።

በአቶ ጌታቸው አምባዬ መግለጫ መሰረት የወጡትን መስፈርቶች አሟልተው የሚገኙ እስረኞች ከሁለት ቀናት ስልጠና በኋላ ይፈታሉ።

ከነዚሁም መካከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈሃል ተብለው የተከሰሱት ዶክተር መረራ ጉዲና እንዲሁም በልዩ ልዩ ወንጀል የተከሰሱት አቶ በቀለ ገርባና የኦፌኮ አመራሮች ክሳቸው መቋረጡን በሀገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ናቸው።

በዋና አቃቤ ህጉ መስፈርት መሰረት ክሳቸው አይቋረጥም ወይንም አይፈቱም ከተባሉት መካከል በኢኮኖሚ አውታሮች ላይ ጉዳት ያደረሱ፣የሰው ሕይወት ያጠፉና የአካል ጉዳት ያደረሱ እንዲሁም በስርአቱ ተጠቃሚ ሆነው በሌሎች ገፋፊነት ወደ አመጽ የገቡ የሚሉትም ይገኙበታል።

የወልቃይት ማንነት ጥያቄ በማንሳት ወንጀል ሰርተዋል ተብለው የተከሰሱት እነ ኮለኔል ደመቀ ዘውዱ በምን መልኩ እንደሚፈረጁ ገና ግልጽ አልሆነም።

በይቅርታና በምህረት ደረጃውን ጠብቀው በ2 ወራት ውስጥ ይፈታሉ የተባሉ እስረኞች እነማን እንደሚሆኑም በዝርዝር የታወቀ ነገር የለም።

ሒደቱ ግን በ3 ዙሮች የሚከናወን መሆኑን ዋና አቃቢ ሕጉ አቶ ጌታቸው አንባዬ ገልጸዋል።

6)

አቶ አዲሱ ለገሰ ሕዝብን የመከፋፈል ሴራቸውን ቀጥለዋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 4/2010)

አቶ አዲሱ ለገሰ በቅማንት ጉዳይ ላይ የጀመሩትን ሕዝብን የመከፋፈል ሴራ መቀጠላቸው ተነገረ ።

የሕወሃትን ጉዳይ በማስፈጸም የሚታወቁት አቶ አዲሱ ለገሰ በጎንደር በተገኙበት ስብሰባ በብአዴን አባላት ሳይቀር ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

ሕዝቡም ቁጣውን በመግለፅ አቶ አዲሱ የተገኙበትን ስብሰባ ረግጦ ወጥቷል ፡፡

አቶ አዲሱ ለገሰ ጥር 2/2010 ምሽት በነበረው በረራ ጎንደር በመግባት “የቅማንት ኮሚቴ ” ነን በማለት በህወሃት የተቋቋሙ ግለሰቦችን አነጋግረዋል።

በዚህ ወቅት እነዚህ ኮሚቴዎች በብአዴን በኩል እየቀረበ ያለውን የሀብት ክፍፍል፣አይከል ከተማን በተመለከተ ግማሹ ቀበሌ የአማራ ነው የሚባለውን ሀሳብ እንደሚቃወሙ ነግረዋቸዋል።

አመራሮችን በመሾም በኩል ብአዴን ለእኛ ሊሾምልን አይገባም፣ብአዴን የኛ ጠላት ነው፣ ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችና ሀሳቦች ቀርበው እንደነበረም ነው የተገለጸው።

አቶ አዲሱ ለገሰም ይህን ሀሳብ በመያዝ እና ጉዳዩን ለማስፈፀም ወደ ህዝብ ሲገባ በብአዴን አባላት ሳይቀር ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል።

በወቅቱ ከ11 ቀበሌዎች የተመረጡ ነዋሪዎች ሳይቀር አቶ አዲሱ የተገኙበትን ስብሰባ ረግጠው ወጥተዋል ነው የተባለው ፡፡

ጥር 3/2010 በነበረው ጊዜም አድርባዬችን በመምረጥ ስብሰባው ለዛሬ መቀጠሩም ታወቋል።

በስብሰባው ዋና ተዋናይ የሆኑት አቶ አዲሱ ለገሰ፣ አቶ ሙሌ ታረቀኝ፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣አቶ አለምነው መኮነን እንዲሁም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አመራሮችና የመከላከያ አመራሮች ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ የህዝቦች መተባበር፣ መፈቃቀር ብሎም ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ እየወጣ መምጣቱ ህወሓትንና ጉዳይ አስፈጻሚዎቹን እጅግ እያስደነገጣቸው ይገኛል ፡፡

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.