ለውጤታማ የፍቅር ግንኙነት 10 ወሳኝ ነጥቦች!

A couple in love in the sunset on the beach

የታይታኒኮቹ ጃክና ሮዝ ምንም እንኳ የፍቅር ጊዜያቸው አጭር ቢሆንም እንደ ማር የጣፈጠ ነበር፡፡ ፊልሙን ስንመለከት የእነሱ ፍቅር የእኛን ልብ ጭምር ስልብ ያደርግ ነበር፡፡ ሁላችንም የምንመኘው አይነት ፍቅር ነበራቸው፡፡ ለመሆኑ ጣፋጭ ፍቅር እንዲኖረን የሚስችሉ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

“ናትናኤል ብራንደን እና ሮበርት ስተርንበርግ” የተባሉ በፍቅር ዙሪያ ጥናት ያደረጉ የስነ- አዕምሮ ጠበብቶች የፍቅር ግንኙነትን ለመመስረትም ሆነ በፍቅር ግንኙነት ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሰናክሎችን በተመለከ የተለያዩ ፅሁፎችን አዘጋጅተዋል፡፡ ጥናታቸው እንደሚጠቁመው ጥንዶች ውጤታማና ዘላቂነት ያለው ፍቅር እንዲኖራቸው የሚከተሉትን ወሳኘ ነጥቦች ተግባራዊ ቢያደርጉ ይመክራል። ለሚወዱት ሰው ሼር ያድርጉት

1.የፍቅር አጋርዎን እንደሚያፈቅሩት/ሯት በየጊዜው ይግለፁ

በተለምዶ ድርጊት ከቃላት ይልቅ ጮክ ብሎ ይናገራል ‘actions speak louder than words’ ቢባልም ቀላል በማይባሉ አጋጣሚዎች ቃላት ከድርጊት በተሻለ ሲናገር ማስተዋል እንግዳ አይደለም። ለፍቅር አጋራችን ሁሌም ከጎኑ እንደሆንን ለማሳየት ከቃላት የተሻለ ነገር መጠቀም አዳጋች ነው። በመሆኑም “እወድሃለሁ” ፣ “እወድሻለሁ”የሚሉት ቃላት ምን ያህል ግዙፍና አፍቃሪነትን እንዲሁም አለኝታነትን አመላካች መሆናቸውን መገንዘብ ያሻል።

2.የፍቅር ስሜታችንን እና ፍቅርን እናጋራ፣

ቀላል የሆኑና ብዙ ጊዜ የማናጤናቸውን ነገሮች ሁሉ አጠቃሎ የያዘ ጉዳይ ነው። አብረን የእግር ጉዞ ስናደርግ፣ ሲኒማ ቤትፊልም ስንመለከት ፣ ሶፋ ላይ ቁጭ ብለን እያለና በመሰል አጋጣሚዎች ሁሉ የፍቅር አጋራችንን እጅ መያዝ ፣ እጃችንን ትከሻውላይ ጣል ማድረግ ፣ ወገብ ማቀፍ እናየመሳሰሉትንም መፈፀም ይመከራሉ።ለፍቅር አጋራችን ያለንን ስሜትም በግልፅ ማጋራትም ወሳኝ ነው።

3. የአድናቆት ቃላትን ያዘውትሩ፣

በቋሚነት የፍቅር ጓደኛችንን ጥንካሬ አጉልተን ልንገልፅ ይገባል፣ የትኛውን ጥንካሬውን ይበልጥ እንደምናደንቅና እንደምንኮራበት ጭምር መግለፃችንም በፍቅር አጋራችን እና በእኛ መካከል የበለጠ መተማመን እንዲጎለብት የማድረግ አቅሙ ከፍተኛ ነው።
ደካማ ጎኖች ስናስተውልም እንዴት በቀላሉ ሊያሻሽላቸውና ሊቀርፋቸው እንደሚችል ቀለልባለ ሁኔታ መንገር እንጂ፣ እንዲሸማቀቅበትና አብሮት የተፈጠረ አድርጎ እንዲያስብ እድል መስጠት አይገባም።

4.በፍፁም ሀሳብዎን ከማጋራት አይቆጠቡ፣

ምን እንደምንወድ እና እንደምንጠላ፣ህልማችን እና ውጥናችን ምን እንደሆነ ለፍቅረኛችን ማጋራትን ፣ ምን ማድረግ በቀላሉ እንደሚሳካልን እና የትኛውስ ደግሞ እንደሚፈትነን፣ ስህተታችንን ሳይቀር ለሌላ ጓደኛ ወይም ወዳጃችን ከመንገር ይልቅ ለፍቅር አጋራችን መንገር ግንኙነታችን በተሻለ መተማመን ላይ እንድንገነባው የሚያስችለን ቁልፍ መሳሪያ ነው።

5.በችግር ጊዜ ደራሽነታችንን ማረጋገጥ፣

ፍቅረኛችን በሚገጥመው ከባባድ ፈተናዎችም ሆነ የህይወት ውጣ ውረዶች ወቅት ከጎኑ መቆም እንደሚገባን የታወቀ ነው።ይሁንና ብዙዎቻችን ብዙም ቁብ በማንሰጣቸው የህይወት መሰናክሎች ጊዜ አፍቃሪያችን ጎን መቆማችን እጅግ ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ የስራ ጫና፣ የራስ ምታት ችግር በሚከሰትበት ወቅት፣ በተለይ ሴቶች የወር አበባ በሚያዩበት ጊዜ፣ ከስራ ሃላፊ ጋር በሃሳብ በሚጋጩበት ሰዓት እና የመሳሰሉት ችግሮች በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ ፍቅረኛችንን ልንቀርበው እና ከችግር እንዲወጣ መፍትሄ ልናቀብለው ይገባል።

6.ስጦታ መስጠት፣

ስጦታ በመሰረቱ ለጥፋት ይቅርታ መጠየቂያ ስልት ሳይሆን ፍቅረኛችን ምን ያህል በልባችን ቦታ እንዳለው ለማሳየት ከልብ የምናደርገው መተሳሰብ ነው። የስጦታ ትንሽ የለውም ስለሆነም ስለምንገዛው ስጦታ ውድነት እና ብርቅዬነት በመጨነቅ ጊዜ ከማጥፋት ይልቅ ፍቅረኛችን ምን ይወዳል? የሚለውን ከግምት ማስገባት እና ሳያስበው ይሄንን ማድረግ (ሰርፕራይዝ )ማድረግ ይመረጣል።

7.ለፍቅር አጋርዎ ጊዜ ይስጡ፣

የስራ ባህሪያች የቱንም ያህል በስራ እንድንወጠር ቢያደርግም እንኳን ከፍቅረኛችን ጋር የምናጣጥመው ጊዜን ልንመድብ ይገባል። ቢያንስ ቢያንስ በሳምንት አንዴ አልያም ሁለትጊዜ ከስራ በኋላ ለመገናኘት መቀጣጣር ተመራጭ ነው። በዚህ ጊዜ የልብ የልባችንን የምናወጋበት፣ያጋጠሙንን ችግሮች እና ድሎች የምንለዋወጥበት እና በመፍትሄዎቹ ዙሪያም ሃሳብ የምንለዋወጥበት እንዲሁም ስለቀጣይ የፍቅር ህይወታችን የምንመካከርበት ውድ ጊዜ በመሆኑ ፣ከተጣማሪያች ውጪ ማንም መኖር የለበትም።

8.መልካምን ነገር የምናደርገው አፀፋውን በመጠበቅ መንፈስ መሆን የለበትም፣

ማድረግ ያለብንን ጥሩ ነገር ሁሉ ያደረግነው ከፍቅር የተነሳ እንጂ ከፍቅረኛችን የተሻለ አፀፋዊ ምላሽን በመጠበቅ መንፈስ ወይም “motive” ፈፅሞ መሆን የለበትም። በዚህ አረዳድ የምናደርገውን ሁሉ ማድረጋችን በፍቅረኛችን ዘንድ ይበልጥ ተወዳጅ፣ተቀባይ፣ ተደማጭ እንድንሆን ከማገዙም ባለፈ የፍቅር ህይወታችን ውብ እና የጣፈጠ እንዲሆን ያግዛል።

9.ለፍቅረኛችን ክብር ይኑረን፣

እኛ ሲደረግብን የማንወደው ነገር በተመሳሳይ የፍቅር አጋራችንን ውስጥ ይበልጥ ሊጎዳ እና ሊያሳምም እንደሚችል አስቀድመን እንገምት።በፍፁም ፍቅረኛችንን በበታችነት አይን ወይም ስሜት አንመልከት ይልቁን ለእኛ ያልታየን እና ያልገባን ነገር ለፍቅረኛችን ቀላል ሆኖ ተገኝቶለት ሊሆን ስለሚችል በጥሞና እናድምጠው።

10. ጥሩ ተናጋሪ ከመሆን፣ ጥሩ አዳማጭ እንሁን፣

በመሰረቱ ማዳመጥ የመናገርን ያህል እኩል ሚና እንዳለው ሊሰመርበት ይገባል። በተጣማሪዎች መካካል ሲሆን ደግሞ የማመጥ ጥቅም ከምንገምተው በላይ ከፍያለ ነው። በቀላሉ በመነጋገር የምንፈታውን ችግር እንኳን መፍታተ የምንችለው ቢያንስ አንዳችን ለማዳመጥ ያለን ረሃብ ከፍተኛ መሆን ሲችል ነው፣ በመሆኑም ከመናገር ይልቅ ለማድመጥ የበለጠ ቦታ እንስጥ። ፈጣሪስ አንድ ምላስ ሁለት ጆሮ የሰጠን ጥቂት እንድናወራ እና ብዙ እንድናደምጥ አይመስላችሁም?

ለሚወዱት ሰው ሼር ያድርጉት
………

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.