ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለአለም ጤና ድርጅት ራስ ምታት ሆነዋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 8/2010)

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለአለም ጤና ድርጅት ራስ ምታት ሆነው መቀጠላቸውን ዘገባዎች አመለከቱ።

የቀድሞውን የዚምባቡዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤን የአለም ጤና ድርጅት የበጎ ፈቃድ አምባሳደር በሚል በመሾማቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸው ውሳኔውን መሰረዛቸው ይታወሳል።

አሁን ደግሞ ምንም እውቅናና ችሎታ የሌላቸውን ሩሲያዊ ባለስልጣን የአለም ጤና ድርጅት የሳምባ በሽታ ፕሮግራምን እንዲመሩ በመወሰናቸው ከቀድሞው በባሰ እየተብጠለጠሉ መሆኑ ታውቋል።

 

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ለአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ከፍተኛ ስልጣን ሲታጩ ለቦታው አይመጥኑም በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር።

ለተቃውሞው ምክንያት የነበረው ደግሞ አቅመ ቢስ ናቸው፣በሕወሃት ስራ አስፈጻሚ አባልነታቸው ጊዜም በርካታ ወንጀሎችን ሰርተዋል የሚል ነው።

እንደተባለውም ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም በእነ ቢልጌት ድጋፍ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከተሾሙ በኋላ የሚይዙትን የሚጨብጡትን አተዋል።

ጤናን በሁሉም የአለም ዙሪያ ተደራሽ አደርጋለሁ፣በተለይ ደግሞ ሴቶችን በሚል የምርጫ ዘመቻ ያደረጉት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም “ጽድቁ ቀርቶ በወጉ በተኮነኑ”የሚያሰኝ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።

ገና በተሾሙ በ7 ወር ጊዜያቸው የቀድሞውን የዚምባቡዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርገው ሲሾሙ ከየአቅጣጫው የትችት ናዳ ዘንቦባቸዋል።

“አምባገነን መሪ እንዴት ለመሾም በቃህ?ይህ የሆነውም በአፍሪካ ህብረት ላገኘህው ድጋፍ ምስጋና ማቅረቢያ የተሰጠ ማካካሻ ነው” ተብለው ነበር።

የምዕራብ ሀገራትና አለመቀፍ ለጋሾች ባሰሙት ጩህትና ተቃውሞ ሹመቱን የተውትና ይቅርታ የጠየቁት ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ዛሬ ደግሞ ሌላ ጣጣ መቶባቸዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ሃላፊነት የሚጠይቀውን የሳምባ ነቀርሳ ፕሮግራም ሃላፊነትን አንድ እዚህ ግባ ለማይባሉ የሩሲያ ባለስልጣን በመስጠታቸው ነው።

ፖለቲኮ እንደዘገበው ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም አሁንም የአለም ጤና ድርጅት ራስ ምታት መሆናቸውን ቀጥለዋል።

እንደ ዘገባው ሰውየው ከሩሲያው መሪ ቭላድሜር ፑቲን ጋር ከአንድ ወር በፊት በሞስኮ ከተገናኙ በኋላ አቅም የሌላቸውን ባለስልጣን ለሳምባ ነቀርሳ ፕሮግራሙ ሃላፊነት ሾመዋል።

እናም ከድርጅቱ ሃላፊዎችና የአለም ጤና ከሚያሳስባቸው ታዋቂ ባለሙያዎች የአሁኑ ሹመት ከሮበርት ሙጋቤው በላይ የባሰ አቅመ ቢስነት ያሳዩበት ሹመት ሲሉ አጣጥለዋል።

እንደ ባለሙያዎቹ አባባል ከፍተኛ ልምድና ብቃት የሚፈልገው የሳምባ ነቀርሳ በሽታ ፕሮግራም ባልሆነ ሰው መመራት የለበትም።

ይህ ብቻ አይደለም ሩሲያ በሳምባ በሽታ መከላከል ምንም ልምድ ሳይኖራት ሃላፊነቱ ለሀገሪቱ ዜጋ መሰጠቱም አስቂኝ ነው ሲሉ ገልጸውታል።

ሩሲያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 ኤች አይቪንና የሳምባ ነቀርሳን ለመከላከል 127 ሚሊየን ዶላር እርዳታ ተጠይቃ ፈቃደኛ አለመሆኗም ይህን ሹመት ለመውሰድ አያበቃትም ነው የተባለው።

እናም የዶክተር ቴድሮስ ውሳኔ ሙያን መሰረት ከማድረግ ይልቅ ፖለቲካን መሰረት ያደረገና ሃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ነው በሚል ተብጠልጥለዋል።

በዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ላይ ትችቶች ቢዘንቡም ሩሲያዊቷ ተሿሚ ለውጥ ያመጣሉ ከማለት ውጭ ሹመቱን ለማንሳት እስካሁን ያሉት ነገር እንደሌለም ለማወቅ ተችሏል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.