የሁለት ታዛዦች ወግ! (ገዱ አንዳርጋቸው Vs ኮማንደር አማረ ጎሹ) – (ጌታቸው ሽፈራው)

 

ስለ ወልድያው ጭፍጨፋ ትናንት ማታ ሁለት “አመራሮች” የተለያየ ጉዳይ አውርተዋል። የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አማረ ጎሹ ድንበር ጥሶ ከውጭ የመጣ ጠላትን የገደለ ያህል በሚያሳብቅበት ሁኔታ ስለ ሟቾቹ ያለ ርህራሄ “የተለየ ፖለቲካ አላማ ያላቸው………” እያለ ለገዳዮች ምክንያት ሰጥቷል። ይባስ ብሎ “ታግሰናቸዋል” ሲል ተደምጧል። “ጦር እየተጨመረልን ነው፣ ነገ እናረጋጋዋለን” ብሏል ሀፍረተ ቢሱ ኮማንደር! ጦር ከየት ሊመጣለት እንደሚችልም መገመት አያዳግትም። ለተገደሉት ምንም አይነት ፀፀት አላደረበትም። በእርግጥ ከንግግሩ ማንን ወክሎ እንደሚናገርም ግልፅ ነው!

ሁለቱም “አመራሮች” ያሉት ወልዲያ ነው። በጭፍጨፋው ዙሪያ እንደሚያወሩ ግልፅ ነው። ሌላው ቀርቶ ለሚዲያ ምን አይነት መግለጫ እንደሚሰጡ መነጋገራቸው አይቀርም። ኮማንደሩ ለሟቾች ቅንጣት ርህራሄ ሳያሳይ፣ ማስመሰል እንኳ ሳይችል በሚዲያ ሲገልፅ እነ ገዱ ያሉበት ስብሰባ አዳራሽ ላይ ምን ሊል እንደሚችል ለመገመት አይከብድም።
በሌላ በኩል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ወልዲያ ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ “ጥፋት” ሲል ገልፆታል። ጉዳዩ እንደሚጠራም አክሏል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር “የተፈፀመው ጥፋት ነው” እያለ የአንድ ዞን ፖሊስ አዛዥ “ያጠፋነው አጥፊዎችን ነው፣ አሁንም እናጠፋቸዋለን” አይነት መግለጫ ይሰጣል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር “ከሕዝብ ጋር ተወያይተናል፣ ችግሮችን በየደረጃው እንፈታለን” ሲል የአንድ ዞን ፖሊስ አዛዥ “ጦር እየተጨመረልን ነው፣ አሁንም እንገድላቸዋለን” አይነት መግለጫ ይሰጣል። አቶ ገዱ የጭፍጨፋው ምክንያት ባሻገር ሕዝብ በርካታ ችግር እንዳለበት፣ እሱም በየደረጃው መፈታት እንደሚገባው ገልፀአል። ለኮማንደሩ ደግሞ የችግሩ ምንጭ የፖለቲካ አላማ ያላቸው አካላት ናቸው። እንደ ኮማንደሩ አባባል መፍትሄው “መደምሰስ” ነው።

ይህ የአቋም ልዩነት የክልሉን የፀጥታ ኃይል ጨምሮ ክልሉን እመራለሁ በሚልና በአንድ ዞን ፖሊስ አዛዥ መካከል የተፈጠረ ነው። ገዱ እንወያያለን እንጅ ጦር እንጨምራለን አላለም። ገዱ የሕዝብን ብሶት ሲያወራ፣ ኮማንደሩ የተለየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው አካላት እያለ ሲወቅስ ተደምጧል። ገዱ ጦር ባይልክለትም የሚልክለት አያጣም። ገዱ የተከማቸ የሕዝብ ችግር መፈታት አለበት ሲል ኮማንደሩ አሁንም መግደልን ነው መፍትሄ ያደረገው። እነዚህ ሁለት አመራሮች ከተናገሩት አንዱ አዛዥ፣ አንደኛው ታዛዥ አይመስሉም። በዚህ ጉዳይ ተቃዋሚና ገዥ ካልሆነ በስተቀር ርዕሰ መስተዳድር እና የዞን ፖሊስ ሊለያይ አይችልም።

አቶ ገዱ ሲናገር የነበረው ሳግ እየተናነቀው በሚመስል መልኩ ነበር። የአንድ ዞን ፖሊስ አዛዥን የማይመራ ሰው ይህ ሁኔታው ከማስመሰል ያለፈ ሊሆን አይችልም። እነ ኮማንደር አማረ ለተጨፈጨፈው ርህራሄ ሳያሳዩ፣ ሕዝብ እየፈረጁና በቀጣይም እንጨርሰዋለን አይነት መግለጫ የሚያሳየው የዞን ፖሊስ አዛዥ ሳይቀር ከባህርዳር ሳይሆን ከሌላ ዋና ከተማ እየታዘዘ፣ ጦርም እየመጣለት በወኪልነት ህዝብን እያስጨረሰ እንደሚገኝ ነው። አሊያም እነ ገዱም በትዕዛዝ ሕዝብን እያስጨረሱ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ብቻ በድርጊቱ ያዘኑ እያስመሰሉ እንደሆነ ብቻ ነው!

  (ጌታቸው ሽፈራው)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.