በቆቦ ከተማ ተቃውሞ፣ሞት፣ግጭትና ቃጠሎ _ ጽዮን ግርማ (VOA)

በቆቦ ከተማ ለሁለት ቀናት በተደረገ ተቃውሞና ግጭት እስካሁን ሰባት ሰዎች መሞታቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል። ከተቃውሞው በኋላ በርካታ ንብረቶች በቃጠሎ መውደማቸንና በአሁኑ ሰዓት ከተማው በመከላከያ ሠራዊት በቁጥጥር ስር መዋሉን ነግረውናል።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ግጭቱ የተቀሰቀሰው፤ “በወልዲያ ከተማ ንጹኃንን የገደሉ የመንግሥት ታጣቂዎች ለፍርድ ይቅረቡ” እንዲሁም “በቆቦ ከተማ የታሰሩ ወጣቶች ይፈቱ” የሚሉ መፈክሮችን የሚያሰሙ የከተማው ነዋሪዎች ለተቃውሞ አደባባይ በመውጣታቸው ነው ብለውናል።

ሁኔታውን በቅርብ ሲከታተል እንደነበር የገለፀለን ወጣት እንደተናገረው፤ “እስካሁን እነርሱ ሰባት ገድለዋል። አንድ መከላከያም ሞቷል። እስካሁን በሄሊኮፕተር ነው ሲያሸብሩን የዋሉት።” በማለት ከተማው ውስጥ የመንግሥት ታጣቂ ሰራዊት መስፈሩን ይናገራል።

አያይዞም የከተማው ሕዝብ ከወልድያው ግድያ በተጨማሪ በከተማው ከኮማንድ ፖስቱ ጊዜ ጀምሮ የታሰሩ ወጣቶችን ጉዳይ ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ማቅናቱን ይናገራል። “እነሱ ይፈቱልኝ ብሎ ጥያቄ አቀረበ። ይባስ ብለው የከተማውን ሕዝብ ይደበድቡ ነበር። በዚህ ግዜ ሕዝቡ በነቂስ ወጣ የታሰሩትን ካስፈታ በኋላ መረጃ እየሰጡ ሲያስደበድቡን ነበር ያሉትን ሰዎች ቤት ንብረትና የመንግሥት ተቋማትን ማቃተል ጀመረ” ሲል የቆቦ ከተማውን ውሎ ይናገራል።

ተቃውሞው ወደ ግጭት ተቀይሮ ፤ የመንግሥት ተቋማትና መኪኖች፣ የእርሻ ልማት ድርጅቶች፣ የፓርቲ ጽቤት፣ የባለሃብቶች ንብረት፣ ዘንርን መሰርት ያደረገ ቤትና ንብረት መቃጠሉን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።

የመንግሥት ታጣቂዎች ለተቃውሞ በወጣው ሕዝብ ላይ በምድርና በአየር ጥቃት እንደፈፀሙባቸውና ሄሊኮፕተሮቹ አሁን ከመሸም በኋላ በከተማው አናት ላይ እየተዘዋወሩ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ መረጃ ለማግኘት የክልሉን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁና ሌሎች ባለሥልጣናትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ስልካቸው ስለማይነሳ አልተሳካልንም።

የዘገባውን ሙሉ ዝርዝር ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።

[jwplayer mediaid=”46538″]

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.