በህዝባዊ ተቃውሞ የተነሳ የኔትዎርክ መቋረጥ መከሰቱ ተጠቆመ

ጉዳያችን

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ፣ የኔትዎርክ አገልግሎት መቋረጥ መከሰቱን መረጃዎች ጠቆሙ፡፡

በተለይ ካለፈው ሳምንት ወዲህ ዳግም ያገረሸውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ፤ ሆን ተብሎ የተፈጠረ የኔትዎርክ መቋረጥ ችግር እንደገጠማቸው እማኞች ተናግረዋል፡፡

እማኝነታቸውን ለቢቢኤን የሰጡ የችግሩ ሰለባዎች፣ በተለይ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ ተቃውሞ እያስተናገዱ ባሉ ከተሞች የኔትዎርክ አገልግሎት በቀላሉ ማግኘት አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል ወልድያ፣ ራያ እና ቆቦ እንዲሁም በሌሎች የክልሉ ከተሞች የኢንተርኔት መቆራረጥ ችግር እየተከሰተ እንደሚገኝ የጠቆሙት መረጃዎች፤ ችግሩ ይበልጥ ጎልቶ የታየው ካለፉት አምስት ቀናት ወዲህ መሆኑንም መረጃዎቹ ያክላሉ፡፡

የኔትዎርክ መቆራረጡ ገባ ወጣ የማለት ባህሪ የሚታይበት ሲሆን፤ ዘለግ ላለ ጊዜ ጠፍቶ ይቆይና፣ ደሞ ተመልሶ እንደሚመጣ የመረጃው ምንጮች ይገልጻሉ፡፡

እንደዚሁም በኦሮሚያ ክልል የተወሰኑ ከተሞች ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ከመረጃዎች ገለጻ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ችግሩ ተቃውሞዎች ረገብ በሚሉባቸው ጊዜዎች ጭምር እንደሚከሰት የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች፤ ይበልጥ ጎልቶ የሚወጣው ግን ህዝባዊ ተቃውሞዉ ዳግም ሲያገረሽ እንደሆነም የአስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ ያስረዳል፡፡

እንደ መረጃዎች ጠቋሚነት ከሆነ፤ ሰው ሰራሹ የኔትዎርክ መቋረጥ እንዲፈጠር የሚደረገው፡- ህዝባዊ ተቃውሞዎች እና ተቃውሞዎቹን ተከትሎ የሚወሰዱ የኃይል እርምጃዎች ይፋ እንዳይወጡ ተብሎ ነው፡፡

ስርዓቱ፣ የሚገጥሙትን ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተከትሎ የተለያዩ የኃይል እርምጃዎችን እንደሚወስድ ይታወቃል፡፡

አገዛዙ፣ ከግድያ፣ ድብደባ እና እስራት በተጨማሪም የኔትዎርክ እና የስልክ አገልግሎቶችን ሆን ብሎ በማቋረጥ፣ ህዝባዊ ትግሉን የተመለከቱ መረጃዎች ተደፍቀው ወይም ታፍነው እንዲቀሩ የማድረግ ስራ ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ሆኖም፤ ዘመኑ የተለያዩ አማራጮችን ይዞ ብቅ በማለቱ፣ ስርዓቱ ኔትዎርክ በማፈን የሚፈጽመው መረጃ የማድበስበስ ሴራ ሙሉ በሙሉ የተሳካ እንዳይሆን አድርጎታል ይላሉ-ታዛቢዎች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.