በቆቦ ህዝባዊ አመጹ እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 18/2010)

በሰሜን ወሎ ቆቦ የተጀመረው ህዝባዊ አመጽ ለሶስተኛ ቀን መቀጠሉ ተገለጸ።

የአጋዚ ወታደሮች ከተማዋን በማጥለቅለቅ ህዝቡ ላይ ጥቃቱን አጠናክረው ቀጥለዋል።

የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ወድመዋል።

ዛሬም በቆቦ ሰማይ ሄሊኮፕተር ሲመላለስ እንደነበር ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በሆስፒታል አድራሻቸው ያልታወቀ አስከሬኖች እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል።

በቆቦ አቅራቢያ በምትገኘው ሮቢትም የህዝብ አመጽ መነሳቱ ታውቋል።

የመከላከያ ሰራዊትን ግስጋሴ ለመግታት መንገዶች ተዘግተዋል።

ህዝቡ በመንግስት ተቋማትና በአገዛዙ ደጋፊና የደህንነት አባል በሆኑ ግለሰቦች ንብረቶች ላይ ጥቃቱን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በርካታ ቤቶች፣መጋዘኖች ዛሬም መቃጠላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ቅኝት የሚያደርጉ ሄሊኮፕተሮች በቆቦ ከተማ ላይ በማንዣበብ ህዝቡ ላይ የስነልቦና ሽብር ለመፍጠር እየሞከሩ መሆናቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የአጋዚ ወታደሮች ቤት ለቤት በመሄድ ድብደባ በመፈጸም ላይ ሲሆኑ ከህዝቡ በተሰነዘረ ጥቃት ዛሬም አንድ የአጋዚ ወታደር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

በሆስፒታል ማንነታቸው ያልታወቁ አስከሬኖች እንዳሉም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ትላንት ምሽት የሀበሻ ቢራ የቀጠናው ዋና አከፋፋይ ህንጻ ከ178 ማቀዝቀዣዎቹ ጋር በእሳት እንዲወድም መደረጉም ታውቋል። በቆቦ ያለው ውጥረት በርትቷል።

በቆቦ አቅራቢያ በምትገኘው ሮቢት ከተማም ከፍተኛ የህዝብ አመጽ ተቀስቅሷል።

3 ኦራል ተሽከርካሪዎች የአጋዚ ሰራዊት ጭነው ትላንት ሮቢት ከተማ ገብተዋል።

ህዝብና የአገዛዙ ታጣቂዎች ተፋጠዋል። ከመሀል ሀገር በወልዲያ አድርገው ወደ መቀሌ የሚያመሩ ተሽከርካሪዎች በሮቢት ህዝብ መንገድ በመዘጋቱ ወደ ኋላ መመለሳቸው ታውቋል።

ከተማዋን የወረሯት የአጋዚ ወታደሮች ህዝቡን ከመንገዶች ላይ እንዲበተን ለማድረግ ጥይት ወደ ሰማይ በመተኮስ እያስፈራሩ ቢሆንም ህዝቡ እዚያው ከጎዳና ላይ ተፋጦ እንደሚገኝ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ዘግይተው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ወደ ቆቦና ሮቢት ከመሀል ሀገር የሚጓዙ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የጫኑ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ወደፊት መግፋት አልቻሉም።

በተለያዩ ቦታዎች መንገዶች በመዘጋታቸው የሰራዊቱ ግስጋሴ መገታቱና በአማራጭ ወታደሮቹ በሄሊኮፕተር እየተወሰዱ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

በሌላ በኩል የትግራይ ተወላጆች ከቆቦ፣ ወልዲያና ሌሎች አካባቢዎች ተፈናቅለዋል የሚል የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ለመክፈት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።

ከቆቦ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ዲቃላ ወንዝ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የትግራይ ተወላጆችን በማሰባሰብ ድራማ ለመስራት መታቀዱንም ለማወቅ ተችሏል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.