ፌስቡክ የማህበራዊ ሚዲያ በአዕምሮ ጤና ላይ ስጋት መፍጠሩን አመነ

የማህበራዊ ትስስር ድረ ገፅ ኩባንያው በሰዎች አዕምሮ እና በማህበረሰቡ መልካም እሴቶች ላይ አሉታዊ ጫና እያሳረፈ ነው በሚል በርካታ ጊዜ ትችት ይቀርብበታል።

አሁን ላይ ኩባንያው ራሱ የማህበራዊ ትስስር ገፁን በተለይም አብዝቶ መጠቀም በሰዎች ስሜት እና አዕምሯዊ ጤንነት ላይ ችግር እየፈጠረ ነው የሚለው አስተያየት እውነት ነው ብሏል።

ሰዎች በፌስቡክ አማካይነት መረጃዎችን እያዩ ወይም እያነበቡ ያለምንም የመልዕክት ልውውጥ ወይም እረፍት ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉ ከሆነ፥ ለከፋ የስሜት ድብርት እንደሚዳረጉ በሰራሁት ምርምር አረጋግጫለሁ ነው ያለው።

ከዚህም ውጭ ሰዎች በፌስቡክ አማካይነት ከሌሎች ጋር የሚያወሩ እና መልዕክት የሚለዋወጡ ከሆነ አዕምሯዊ ደህንነታቸው እንደሚሻሻል ጠቁሟል።

የፌስቡክ ተመራማሪዎች ሌሎች ሰዎች በኢንተርኔት የሚያጋሩትን መረጃ ማንበባቸው አሉታዊ የማህበራዊ ግንኙነት እንደሚፈጥርባቸው መላምት ማስቀመጣቸውን የኩባንያው የምርምር ዳይሬክተር ዴቪድ ፊንስበርግ ተናግረዋል።

የኩባንያው መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ፥ ሰዎች በማህበራዊ የትስስር ገፁ ተጠቃሚ ሲሆኑ ጊዜያቸውን የተሻለ ማህበራዊ ግንኙነት እንዲፈጥሩበት እና ጠቃሚ መረጃዎችን እንዲለጣወጡበት ነው ብለዋል።

ሆኖም በተቋሙ እና ቤሎች የምርምር ድርጅቶች የተሰሩ ጥናቶች፥ ያልተገባ የፌስቡክ አጠቃቀም መኖሩን አረጋግጠዋል፤ ይህም ለሰዎች ስሜት መረበሽ እና የጤና ስጋት መፍጠር ምክንያት መሆኑን ነው ያነሱት።

ለአብነትም ታዳጊዎች ብዙ ጊዜ በማህበራዊ የትስስር ገፅ ላይ ብዙውን ጊዜያቸውን በማሳለፋቸው ለከፋ ድብርት እየተዳረጉ መሆኑ ተነግሯል።

በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ በተሰራ ጥናት ለ10 ደቂቃ ፌስቡክን ያለማቋረጥ እና ያለምንም የመልዕክት ልውውጥ እንዲያነቡ የተደረጉ ተማሪዎች በቀኑ መጨረሻ ስሜታቸው ተረብሾ እና ለጭንቀት ተዳርገው ተገኝተዋል።

በአንፃሩ በማህበራዊ የትስስር ገፁ ለ10 ደቂቃ ከሌሎች ሰዎች ወይም ከጓደኞቻቸው ጋር መልዕክት የተለዋወጡ ተማሪዎች ደግም ንቁ እና ደስተኛ ሆነው ነው የተገኙት።

ከዚህ ውጭ በፌስቡክ አማካይነት መልዕክት መላክ እና መቀበል ወይም በጓደኛ የመረጃ ዝርዝሮች ማስቀመጫ ላይ አስተያየትን ማስፈር ስነልቦናዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተጠቁሟል።

ፌስቡክ የቀረበበትን ቅሬታ ተከትሎ አሁን ላይ በገፁ “Snooze” የሚል ቁልፍ የጨመረ ሲሆን፥ ተጠቃሚዎቹ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ጓደኛቸው፣ የፌስቡክ ገጾች ወይም ቡድኖችን መርጠው ከ24 ሰዓት እስከ 30 ቀን ድረስ ጓደኝነታቸውን በጊዜያዊነት ማቆም የሚያስችል አሰራር ዘርግቷል።

ይህም የሚሆነው ተጠቃሚዎቹ unfriend ወይም unfollow የሚሉትን ቁልፎች መጫን ሳይጠበቅባቸው ነው።

ከዚህ በተጨማሪ “Take a Break” የሚለውን ቁልፍ በመጠቀም አዕምሯዊ ስጋት ከሚፈጥሩባቸው ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጥ ይችላሉም ነው የተባለው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.