ኢትዮጵያና ጅቡቲ፣ በኤርትራ መንግስት ላይ ማዕቀቡ እንዲቀጥል ጠየቁ

የመን እንደ ሶማሊያ መታመሷ፣ ለኤርትራ መንግስት አመቺ ይሆናል

4ba5137ddf717ec1b0abb55f86153b6c_XLኤርትራ መንግስት አካባቢውን እየበጠበጠ ስለሆነ በጋራ እንመክተዋለን ያሉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጅቡቲ ፕሬዚዳንት፤ በኤርትራ መንግስት ላይ የተጣለው አለማቀፍ ማዕቀብ እንዲቀጥል
የጠየቁ ሲሆን፤ የኤርትራው ፕሬዚደንት በበኩላቸው ውንጀላውን አስተባበሉ፡፡ሰሞኑን  በጅቡቲ የሶስት ቀናት ጉብኝት ያደረጉት ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ፤ የኤርትራ መንግስት ለአካባቢው አገራት ፀጥታ ስጋት ስለሆነ ኢትዮጵያና ጅቡቲ በጋራ እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡ የኤርትራ መንግስት የጅቡቲን ጨምሮ የአካባቢውን አገራት ፀጥታ እያወከ ነው ያሉት ፕሬዚደንት ኦማር ጊሌ፤ ኤርትራ ላይ የየተጣለው ማዕቀብ እንዲቀጥል ከጠ/ሚ ኃይለማርያም ጋር መስማማታቸውን ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ድንበራቸውን በጋራ ለመጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን የገለፁት ጠ/ሚ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ የኤርትራ መንግስት አካባቢውን ከመበጥበጥ ስላልተቆጠበ ስድስት አመት ያስቆጠረው አለማቀፍ ማዕቀብ እንዲቀጥልና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድበት ንጠይቃለን ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ህብረት፣ ከዚያም በተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ምክር ቤት አማካኝነት ኤርትራ ላይ ማዕቀብ የተጣለው፣ የሶማሊያ አሸባሪዎችን በመደገፍና በማስታጠቅ አካባቢውን ይበጠብጣል በሚል ምክንያት እንደሆነ ይታወሳል፡፡ የኤርትራ መንግስት የሶማሊያ አሸባሪዎችን እንዲሁም በየአገሩ አማፂ ቡድኖችን ያስታጥቃል በሚል ከፍተኛ ስጋት ያደረባቸው አገራት በተለይም ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከየመን ጋር ትብብር በመፍጠር ጫና ለማሳደር ሲጥሩ የነበረ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የየመን ቀውስ እየተባባሰ መንግስት አልባ መሆኗ ለሁለቱ አገራት ይበልጥ አሳሳቢ ሆኖባቸዋል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው፤ ከኢትዮጵያ የሚሰነዘረውን ውንጀላ በማስተባበል፤ በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እየላላ ስለመጣና ማዕቀቡ ይነሳል የሚል ስጋት ስላደረባቸው ነው ውንጀላውን የሚደጋግሙት ብለዋል፡፡

የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባሰራጨው ተመሳሳይ ምላሽ፣ ኢትዮጵያ የድንበር ዳኝነትን  ባለማክበር አካባቢውን ትበጠብጣለች በማለት የወነጀለ ሲሆን፤ ከጅቡቲ ጋር በኳታር ሸምጋይነት ድርድር ከተጀመረ በኋላ የጅቡቲ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ማበሩ አሳዝኖናል ብሏል፡፡ የኤርትራ መንግስት የሶማሊያ አሸባሪዎችን በማስታጠቅ፣ የጎረቤት አገራትን ፀጥታ ያውካል  በሚል በቀረበ ክስ፣ በ2001 የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ ላይ ማዕቀብ ሲጥል፤ ከቻይና እና ከራሺያ የተአቅቦ ድምፅ በስተቀር የምክር ቤቱን ይሁንታ በማግኘት ያለፈ ውሳኔ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ የተለያዩ ሰነዶችን በማስረጃነት ያቀረበች ሲሆን የኤርትራ መንግስት ጐረቤት አገራትን የሚበጠብጠው በመከላከያ ሚኒስትሩ ጀነራል ኤፍሬም ስብሀት አስተባባሪነት እንደሆነና፤ የአየር ሀይል እና የባህር ሀይል አዛዞችን ጨምሮ 12 ጀነራሎች የእንቅስቃሴው መሪዎች እንደሆኑ በሰነዶቹ ተዘርዝሯል፡፡

የኤርትራ የባህር ሀይል ዋና አዛዥ ሜ/ጀ ሁመድ ካሪካሬ፣  ባለፈው አመት የሞቱት  ሜ/ጀ ገብረ እግዚአብሄር አንደማርያም፣ ሜ/ጀ ሀይለ ሳሙኤል፣ የኤርትራ ብሄራዊ ደህንነት አዛዥ ብ/ጄ አብርሀ ካሳ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲን ፀረ ሰላም ሀይሎች በማስተባበር ያሰማራሉ ተብለው በስም ተጠቅሰው ነበር፡፡

ምንጭ – አዲስ አድማስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.