ዮዲት ማናት? (አበበ ሀረገወይን ዶ/ር)

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደ ዮዲት የተወገዘና የተጠላ ሌላ ፍጡር የለም። ድንገት ግራኝ ሞሐመድ ይወዳደራት ይሆናል። ይህም ስለሆነ ለዮዲት ብዙ ከዚህ ጋር የሚሄድ ቅጽል ወቶላታል። በጣም የታወቁት ዮዲት ጉዲትና እሳቲት ናቸው።

ዮዲት የአክሱም መንግስት መዳከም በጀመረበት በ9ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ብዙ ሰራዊት አስከትላ ከፍተኛ ወረራ አካሂዳ አክሱምን በቁጥጥሯ ስታደርግ የጊዜው የአክሱም ንጉስ አምበሳ ውድምና ተከታዮቹ አምልጠው ወደ ሸዋ መንዝ ተራሮች ተሰደው ተደብቀዋል። ዮዲት የአክሱምን ንጉስ ኤዛና ያሰሩትን የማርያስ ጽዮን ቤተ ክርስቲያንና እዚያ የሚገኙት ሌሎችም ጨምራ በእሳት እንዲነዱ ማድረጓ ታሪክ ያረጋግጣል። መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ዮዲት የክርስትናን ሀይማኖት ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ሰፊ ዘመቻ አድርጋ ከሷ በኋላ ግራኝ መሀመድ እንኳን ሊደርስበት ያልቺለውን ደብረ ዳሞን ጨምራ እንዳቃጠለች ታሪክ ይነግረናል። ከዚህም ጋር በማያያዝ ቀሳውስትንና ካህናትን ሊቋቋሙ የሞከሯትን ሁሉ አውድማለች። ብዙዎች ካህናት እሷ ከመምጣቷ በፊት ታቦታቸውንና ንዋየ ቅዱሳታቸውን ጠቅልለው ወደ ደቡብ በመሰደድ ሃይማኖታቸውን ሊያድኑ ችለዋል።

ዮዲት ኢትዮጵያን በጠቅላላው 40 አመት ገዝታለች።

ዮዲት ግን ማን ነች!

ዮዲት በተለምዶ በ4ኛው ክፍለ ዘመን ክርስትና ከገባ በኋላ ከዚያ በፊት የነበረው የአይሁድ እምነት ተከታዮች ክርስትናን አንቀበልም ስላሉ ከአክሱም ተባረው በሰሜን ኢትዮጵያ በየተራራውና ጎራው ተደብቀው ይኖሩ የነበሩት ንግስት ሆና የተነሳችው በሃይማኖት ቁጭት ነው የሚሉ አሉ። ብዙ መረጃ ባይኖረውም እነዚህ የአይሁድ እምነት ተከታዮች አገዎች ነበሩ ይባላል። አንዳንድ ተራኪዎች እንደሚሉት ካክሱም ከተባረሩ በኋላ ንጉስ ጌዲዎን የሚባል ንጉስ እንደነበራቸውና ዮዲትም የሱ ትውልድ እንደነበረች ይገልጻሉ።

የላይኛው ታሪክ በብዙው ተቀባይነት ያለው ቢሆንም ፣ ሌሎች ደሞ ዮዲት ባነሳሷም ሆነ በድርጊቷ ከሰሜን ሳይሆን ከደቡብ የተነሳች የሲዳማ ንግስት ነበረች ይላሉ። ይሄንን የሚሉትም በዚያን ዘመን ሀይለኛና በሴቶች ይገዛ የነበረ መንግስት የሲዳማ ስለ ነበረ ነው ይላሉ። አንዳንዶች እንደጻፉት የዮዲት ባል ንጉስ ዜኖቢስ አይሁድ ስለነበረ የአይሁድና የሲዳማ ባህላዊ እምነት የቀላቀለ እምነት ተከታይ ነበሩ ይላታል። የሲዳማ ባህላዊ ተራኪዎች እንደሙሉት ደሞ እንደሚሉት ትክክለኛ ስሟ ፉራ የምትባለው የሀቪላ ጋዲሬ ከሚባለው ዘር ነች ይላሉ።

ሱማሌዎችም ደሞ ሐርላ ከሚባለው ቦታ የነገሰች ባዲት የምትባል የሐረር ሱማሌ የኛ ናት ይሏታል።

ዮዲት 40 አመት ስትገዛ ኢትዮጵያን በውጭ ሀይል አላስደፈረችም። ነገር ግን እልኸኛ ስለነበረች ስልጣኗን ካረጋገጠችና ሀይሏን ካጠናከረች በኋላ በመንዝ ተራሮች የተደበቁትን አምበሳ ውድምንና ተከታይቹን ካላወደመች የመሰረተችው መንግስት ዘላቂ እንደማይሆን ስለገመተች ያለ የሌለ ሰራዊቷን ይዛ ወደ መንዝ ተራሮች ረጅምና አድካሚ ዘመቻ ጀመረች። ነገር ግን መንዝ ሰራዊቷን የገጠመው ከፍተኛ ሰራዊት ሳይሆን የድንጋይ ናዳ ነው። በዚያን ዘመን የመንዝ ህዝብ አገሩን ላለማስነካት በየመወጣጫውና በየበርበሩ የድንጋይ ናዳ ከምሮ ጠላቱን ይጠባበቅ ነበር። ለይዲትም የጠበቃት ይህ የናዳ ጦርና ሌላው ደሞ ፣ የመንዝ ሕዝብ ጠላትን የሚያጠቃው ሰብሉን ካቃጠለ በኋላ እህሉንና ከብቱን ይዞ የማይደረስበት ዋሻዎች ይደበቅና ጠላቱን ያስርብ ነበር። የዮዱት ጦርም ይሄን ሊቋቋም ባለመቻሉ ብዙ ሰው አለቀባት ፣ ከዚያ ተርፎ የተዳከመውን ጦሯን ሌሎች በየመንገዱ እያጠቁ አመናምነውባት እሷም አክሱም ሳትደርስ አዲ ቃዊ የሚባል ቦታ ሞታ ተቀብራለች ይባላል።

የዮዲት ታሪክ በደምብ የተዘገበ አይደለም። አብዛኛው ቃረሞሽና የመላምት ግጥምጥም ነው። አሁንም ቢሆን ብዙ አስተማማኝ የሚሆን በቂ ጭብጥ በጽሁፍ አልተገኘም። ዮዲት መኖሯ ግን ጥርጥር የለውም። ይህም ስለ ሆነ በታሪካችን ዮዲት 56ኛዋ ንግስት ነበረች መባል ይኖርበታል።

(አበበ ሀረገወይን ዶ/ር)

ዮዲት ጉዲት (Yodit Gudit) ማን ናት?

1 COMMENT

  1. Selam Dr. Abebe Haregwoin,
    It is alway pleasant and very interesting to read your articles short and long. I appreciated you marvel history on Yodit. You have reported the traditional knowledge about Yodit. You left out a few important segments of history, which I would like to add. I will do that in the form of a small article. For now, what you wrote suffices for general knowledge.
    Yours Zewge Fanta, Of negede Zagwe.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.