ሁል ጊዜ ለምን ድካም ይሰማናል?

“ሁል ጊዜ ለምን ድካም ይሰማኛል” ብለው ራስዎን ጠይቀው ያውቃሉ?

ይህ ፅሑፍ ለእርስዎ ድካም መሰማት ምክንያት የሆኑትን አንዳንድ የተለመዱ ምክንያቶችን እና ከዚህ የድካም ስሜት ለመውጣት ምን ማድረግ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ምክሮችን ያነሳል።

እንደ አሜሪካ የበሽታ ቁጥጥር እና መከላከል ማዕከል ገለፃ ከሆነ፥ በአሜሪካ 15 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና 10 ነጥብ 1 በመቶ ወንዶች በተደጋጋሚ የድካም ስሜት ስሜት ውስጥ ይኖራሉ ይላል።

ተመራማሪዎች ለዚህ ድካም መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ያሉዋቸውና እና የመውጫ መፍትሄዎችን እንደሚከተለው አስፍረዋል።

1. የእንቅልፍ እጦት

በቂ ወይም ተመጣጣኝ እንቅልፍ ማጣት የድካም ስሜት እንዲሰማን መነሻ ሊሆን ይችላል።

ስለዚህ የአሜሪካ የእንቅልፍ ህክምና እና ጥናት አካዳሚ እንደጠቆመው፥ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 60 ዓመት የሆኑ ሰዎች በየቀኑ ለ7 ወይም ከዚያ በላይ ሰዓታት ተመጣጣኝ እንቅልፍ ጤናቸውን ለማሳደግ ይረዳቸዋል።

በአንፃሩ ከተጠቀሰው ሰአት በታች እንቅልፍ ማግኘት ከስራ አፈፃፀም ማነስ እና ለአደጋዎች ከመጋለጥ ባሻገር የጤና እክል እንደሚያስከትልም ተገልጿል።

ይህም ውፍረት፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ የመንፈስ ጭንቀት፣ የልብ ሕመም፣ ሰትሮክ እና ለሞት የመጋለጥ ዕድል ያካትታል ነው የተባለው።

በቂ የ7 ሰዓት እንቅልፍ ለማግኘትም ከፈለጉ፥ ቋሚ የእንቅልፍ ሰዓት ልማድ ይኑርዎት፤ መኝታ ቤትዎ ፀጥ ያለ፣ ጨለማ እና ምቹ የሆነ ሙቀት እንዳለው ያረጋግጡ፤ ከመተኛትዎ በፊት ትንባሆ እና አልኮል ያስወግዱ ሲሉ ባለሙያዎች መክረዋል።

ከላይ የተጠቀሱትን የእንቅልፍ ልምዶች እየተገበሩ እያሉ አሁንም ድካም ከተሰማዎት፥ በአቅራቢዎ ከሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ድረስ በመሄድ መወያየቱ ጥሩ ነው ተብሏል።

2. የአመጋገብ ችግር

አትክልት.

ድካም ለማቆም ቀላሉ መንገድ በአመጋገብዎ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ነው።

ለዚህም ጤናማ እና የተመጣጠነ አመጋገብ መኖሩ እርስዎ ያለዎትን የድካም ስሜት ሊያስተካክል ይችላል።

ጤንነትዎን ለማሻሻል እና የሚያስፈልጎትን ንጥረ ነገሮች በሙሉ ለማሟላት እንዲሁም ድካምን ለማስወገድ ደግሞ፥ ፍራፍሬዎች፣ አትክልቶች፣ ጥራጥሬዎች፣ ገንቢ ምግቦች እና ወተት መመገብ አስፈላጊ ነው።

3. በአንድ ቦታ ለብዙ ጊዜ ቁጭ ማለት

ድካም ሲኖር ሶፋ ላይ ቁጭ ብሎ እና ዘና ማለት ብቸኛው የድካም መፍትሄ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ከተቀመጡበት በመነሳት መንቀሳቀስ ድካምዎን ለማጥፋት ሊያደርጉት ከሚችሉት ተግባራት አንዱ ነው ተብሏል።

ለዚህም በአንድ ጊዜ ቢያንስ ለ20 ደቂቃዎች ቀላል እንቅስቃሴ ማድረግ የድካም ስሜትዎ ለማስወገድ አንድ ምክንያት ነው።

በተጨማሪም ጥናቱ እንደሚያመላክተው ለአዋቂዎች በሳምንት በአማካይ ሁለት ሰዓት ከ30 ደቂቃ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ነው የተባለው።

ይህን ማድረግ የማይችሉ ከሆነ በየቀኑ የ10 ደቂቃ የእግር ጉዞ ማድረግ ያስፈልጋል።

ለዚህም ብስክሌት መንዳት፣ ቴኒስ መጫወት እና ወዘተ የሚሉት መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ የድካም ስሜትዎ መቀነስ ይችላሉ።

4. ከልክ ያለፈ ውጥረት

ሥራ፣ የገንዘብ ችግር፣ የግንኙነት ጉዳዮች፣ የሕይወት ክስተቶች፣ ስራ አጥነት እና አለመግባባት የመሳሰሉ ብዙ ሁኔታዎች ውጥረት ያስከትላሉ።

እነዚህን ችግሮች በማስወገድ የድካም ስሜት መቀነስም የሚቻል ሲሆን፥ ይህም የጭንቀት ምንጭ ምን እንደሆነ መለየት እና መቆጣጠር፣ ከሚያስጨንቋችሁ ሰዎች መራቅ፣ ሁኔታዎችን ይበልጥ አዎንታዊ በሆነ መንገድ መመልከት እና ይቅር ማለት መማር ከመፍትሄዎች ተጠቃሶች ናቸው።

5. የጤና ሁኔታ

በአካላዊ እንቅስቃሴዎ፣ በአመጋገብዎ፣ በጭንቀትዎ ደረጃ እና በእንቅልፍዎ ላይ ለውጦች ቢያደርጉም ከሁልጊዜ የድካም ስሜት ላይገላገሉ ይችላሉ።

ይህም ህክምና የሚያስፈልገው የጤና ሁኔታ ሊሆን ስለሚችል፥ ከምልክቶቹ በጣም የተለመዱት ሁኔታዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ።

ይህም የደም ማነስ፣ የስኳር በሽታ፣ ጭንቀት፣ ድብርት፣ ሥር የሰደደ የድካም በሽታ፣ የሽንት አካላት በሽታ፣ የምግብ አለመስማማት፣ የልብ ህመም፣ ትኩሳት፣ እርግዝና፣ የቫይታሚን እና የማዕድን እጥረት የሚሉት ናቸው።

ስለዚህ ድካም እንዲሰማዎት የሚያደርግ የጤና ችግር ካለብዎት በአቅራቢዎ ከሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ለመወያየት ቀጠሮ መያዝ እና በፍጥነት መታከም ያስፈልጋል።

ምንጭ፦ www.medicalnewstoday.com

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.