በበርካታ ሙት መንፈሶች! (ጌታቸው ሽፈራው)

ሌኒን ሶቭየትን አንድ አደርጋለሁ ብሎ አዲስ መዝሙር፣ ምልክት፣ ሰንደቅ አስተዋውቋል። ቀይ ቀለም አብዮት፣ አምስቱ ኮከብም የአብዮቱ፣የአርሶ አደር፣ የሰርቶ አደርና የወታደር ምልክት ነው ተባለ። ይህን ምልክት ሕዝብ የእኔ ነው ብሎ እንዲጠቀምበት ለፈፈ። ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱ እነመለስ ሌኒን ሀገር አንድ ለማድረግ የተጠቀሙበትን ምልክት ሁሉ ተጠቀሙበት፣ ሶሻሊዝም ካለቀለት፣ ሌኒንና አስተሳሰቡ በሩሲያ ሳይቀር ከሞቱ በኋላ ምልክት እንዳደረጉት ቀጠሉ። የእነ ሌኒን አስተምሮት እነ ፑቲን እንኳ አፈራርሰውታል፣ አይረባም አይጠቅምም ብለው ጥለውታል እነ መለስ ሕዝብን በውድም በግድም አስተማሩት፣ ለፈፉ!

መለስና ጓደኞቹ ሌኒኒዝምን እያሰመሩ ሲያበቡ በነበረበት ወቅት ያበጠሩትን የ”አብዮት” ጉፈሬ ላጭተውታል፣ ወይም ተመልጠዋል። የአብዮተኛ የሚሉትን ልብሰ ከእነ ቅጫሙ ወርውረው የ”ምዕራቡ አለም” ዘመናዊ ሱፍ እየለበሱ ነው። የሌኒን ሕዝብ ቀይ ኮከብና ቀለም አሽቀንጥሮ በጣለበት እነ መለስ በስማ በለው ሲሰብኩት የነበረውን ሕዝብ ግን አሁንም የሌኒንን ኮከብ ያለብሱታል።

ይህ ሕዝብ ከኮከቡ በፊት ለበርካታ ሀገራት ተምሳሌት የሆነውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ያውቃል። ተጠቅሞበታል! ለብሶትም ነበር! የአፍሪካ ሀገራት ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ወስደዋል፣ የአክሱም አካባቢ ሰዎች ሳይቀሩ ግን ረዥሙን ታሪክ አውልቀው የ40 አመት የትህነግን ታሪክ የሚያሳይ ቀይ ኮከብ ምልክት እንዲያደርጉ ሆነዋል! ተሰብከዋል!

እድሜ ለትህነግና ሩሲያ የተወችውን ኢትዮጵያውያን ከፖለቲካ መቀስቀሻነት አልፎ እንደ ባህል ልብስ እየለበሱት ነው፣ በሰርግ እየለበሱት ነው! ህዝብ ሸማን አውልቆ የሌኒንን ምልክት በጥበብና ጥልፍ ኮከብን ተክቶ “አምሮብኛል” እንዲል ተደርጓል። ከባህላዊ ልብሰ አንፃር ፔስታል ያለበሷቸው ያህል ይሰማኛል፣ ከታሪክ አንፃር ታሪክ እንደነሷቸው ግልፅ ነው፣ ከሀገር አንፃር ትህነግ ካፈራረሳት ኢትዮጵያ ይልቅ ለፈረሰችው ሶቭየት በሌለችበት እንዲቀርቡ አድርገዋቸዋል!

ሕዝብ እየኖረ ያለው በሙታን መንፈስ ነው። ቀይና ቀይ ኮከብን ምልክት ባደረገው መንፈስ፣ ቀይ ቀለምና ኮከብ ምልክቱ በነበረው ሶሻሊዝም፣ ይህን ሶቭየት ምልክት ለሕዝብ አሸክሞ ውድ ሱፍ ለብሶ በሞተው መለስ ዜናዊ! በርካታ ሙት መንፈሶች!

ትህነግ ይህን ሁሉ የሙት መንፈስ ሕዝብ ላይ ሲያሰርፅ:_

1) የንጉሱ ስርዓት ፊውዳላዊ ነው፣ መሳርያው ደግሞ ኃይማኖት ነው፣ ኃየማኖት ማደንዘዣ ነው፣ እያለ ኃይማኖትን መሰረት ባደረጉት የአረብ ሀገራት እርዳታ ይታጠቅ ነበር

2) ምዕራባዊያን ካፒታሊስት ናቸው፣ ካፒታሊዝም ደግሞ ጠላታችን ነው፣ ካፒታሊዝም ይውደም! እያለ በካፒታሊስቱ ሲ አይ ኤ ሙሉ ድጋፍ ወደ ስልጣን ዘለቀ

3) “የዓለም ሰራተኞች ተባበሩ” የሚለውን የእነ ማርክስ መርህ እያነበነበ “ከትግራይ ሰራተኛ ውጭ” ያለው ተባበረ አልተባበረ አያገባኝም አለ። እንዲያውም ጨቋኝ ነው ብሎ በማርክሲዝም ሌኒኒዝም ተነግሮ የማያውቅ ቀልድን ሲሰብክ ኖሯል።

4)ሶቭየት አንድ እንድትሆን የለፋው ሌኒን ያነገባቸውን ተሸክሞ፣ መገንጠልን አላማው አደረገእነዚህ ስልጣን ላይ ሳይወጣ ይወናበድባቸው የነበሩት ናቸው። ማሳያዎች! ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ያለፈባቸው የተጣረሱ “አስተሳሰቦች” እጅግ ብዙ ናቸው። ምልክቱ፣ ሰንደቅ አላማውም ግን ያው ነው! ፖለቲከኞቹ የተውትን ሁሉ ሕዝብን ያስለብሳል! የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ቀን እያከበረ፣ ከጭፈራ መልሰ የሚያስለብሱት፣ የሚያስፎክሩበት፣ ወይ ንቅንቅ፣ እናንቃችኋለን የሚያሰኙት በሞተው ሌኒን ምልከት ነው፣ በተቀበረው ርዕዮት ምልክት ነው፣ እነ ፑቲን በሚያወግዙት የድሮ ሶቭየት አብዮታዊ ባህል ነው፣ መለስና ጓደኞቹ አምጥተው ባወለቁት አስተሳሰብ ነው፣ የተቀበረውና የቀሩት “ራዕዩ ተቀብሯል” በሚሉት መለስ ያመጣው፣ ያወለቀው፣ የሙት መንፈስ ነው! በርካታ የሙት መንፈሶች!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.