በጉዲፈቻ የተወሰዱ ሰባት ሺ ህጻናት የት እንደደረሱ አይታወቅም ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 29/2018)

በጉዲፈቻ ከኢትዮጵያ ወደ ወጭ የተወሰዱ ሰባት ሺ ህጻናት የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

 

ሚኒስትሯ ወይዘሮ ደሚቱ ሃምቢሳ ወደ ውጭ በጉዲፈቻ የሚሰጡ ህጻናት በተገቢው ህጋዊ አሰራር እየተፈፀመ አለመሆኑን ለፓርላማ ገልፀዋል፡፡

የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ደሚቱ ሃምቢሳ እንደገለጹት በኢትዮጵያ ያሉ ደላሎች ወላጆችን በማታለልና ከሌሎች አካላት ጋር በመመሳጠር በህገወጥ መንገድ ህፃናትን ወደ ተለያዩ ሀገራት ልከዋል፡፡

በደላሎች ተታለው ልጆቻቸውን ልከው ያሉበትን ያላወቁ ወላጆችም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ልጆቻቸውን እንዲያገናኛቸው እየተማፀኑ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

ህጻናቱ ለአሳዳጊዎቹ ሲሰጡ በቂ መረጃ እና አድራሻ ያልተያዘ በመሆኑ ፍለጋው አዳጋች እንደሆነም ሚንስትሯ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ግን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው መፍትሄ እያፈላለገ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ህጻናቱ ሊገኙ ይችላሉ ተብሎ በሚታሰብባቸው ስፔን፣ ጣሊያን እና አሜሪካ ከሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት መካሄዱንና ጥረቱ መቀጠሉንም ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ እንዲጎለብት እየሰራ መሆኑንና ወላጆችም በሀገር ውስጥ ልጆቻቸው የሚያድጉበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ፓርላማ በቅርቡ በጉዲፈቻ ሕጻናትን ወደ ወጭ መውሰድን የሚከለክል ሕግ ማጽደቁ ይታወቃል።

ሕጉ የጸደቀው በጉዲፈቻ ስም በውጭ ዜጎች ከኢትዮጵያ የሚወሰዱ ሕጻናት ለበርካታ ጊዜያት በአሳዳጊዎቻቸው ከፍተኛ በደል እንደሚደርስባቸው በመታወቁ ነው ተብሏል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በጉዲፈቻ መልክ ከኢትዮጵያ የሚወሰዱ ሕጻናት ብዙዎቹ ደብዛቸው ሲጠፋ አንዳንዶቹ ደግሞ እስከመገደል ደርሰዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1999 ወዲህ ብቻ 15 ሺ ሕጻናት በጉዲፈቻ መልክ ወደ አሜሪካ ተወስደዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 ሁለት አሜሪካውያን ባልና ሚስቶች አንዲት ኢትዮጵያዊ ለማሳደግ ከወሰዱ በኋላ ገድለዋት በመገኘታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳዩ ሲያነጋግር እንደነበር አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.