ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ከሃላፊነት ሊነሱ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 30/2010)

በሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ሕወሃት/ውስጥ የተፈጠረውን ቀውስ ተከትሎ በአሸናፊነት የወጣውና በአቶ ስብሃት ነጋ የሚደገፈው ቡድን ጄኔራል ሳሞራ የኑስን ከሃላፊነት እንዲነሱ መወሰኑን ምንጮች ገለጹ።

የሕወሃትን የበላይነት ባስጠበቀ ሆኖም በሀገሪቱ የተከሰተውን ውጥረት በሚያረግብ መልኩ እየተከናወነ ነው የተባለው የሰራዊቱ አመራር ብወዛ፣በክፍለ ጦር አዛዦችና በተዋረድ ባሉ መዋቅሮች ላይ ምንም አይነት መሰረታዊ ለውጥ ሳያመጣ የሕወሃት ታጋዮች በአመራሩ ስፍራ እንደሚቀጥሉም ተመልክቷል።

የሃገሪቱን አራት የእዝ አዛዥነት ቦታዎች በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ የተያዙት የትግራይ ተወላጆች በሆኑት የሕወሃት ታጋዮች ነው።

ይህም የሃላፊነት ቦታ ሳይነካ እንደሚቀጥልና ሰሞኑን የጄኔራልነት ማዕረግ ካገኙት አንዱ እዞቹን የማስተባበር ሃላፊነትን እንዲወስዱ ይደረጋል ተብሏል።

ሌላው የጄኔራልነት ማዕረግ ያገኙት ደግሞ “ፕሪንስፓል” ስታፍ አስተባባሪ ማለትም የመከላከያ  መምሪያዎችን በበላይነት እንዲያስተባብሩ መታቀዱንም ምንጮች ገልጸዋል።

ይህንን መዋቅር ተግባራዊ ለማድረግ የሀገሪቱን የሰራዊት ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል ለፓርላማው የማሻሻያ አዋጅ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

አሁን እየተሰራበት ባለው የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ ቁጥር 809/2006 የምክትል ኢታማጆር ሹምነት መዋቅር ባለመኖሩ ይህንን ጨምሮ በአዋጁ ላይ ማሻሻያ የማድረግ ስራ እየተሰራበት ይገኛል።

ከ1993 ግንቦት ወር ጀምሮ የመከላከያ ሰራዊቱ ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ሆነው የቆዩት ሳሞራ የኑስ በጡረታ እንደሚሰናበቱና በምትካቸው የህወሃቱ ሰዓረ መኮንን ይተካሉ ተብሎ በመጠበቅ ላይ ነው።

ነገር ግን ሌሎች የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ግን ሳሞራ የኑስን የሚተኳቸው ጄኔራል አብርሃ ወልደማርያም የተባሉት የሕወሃት ታጋይ ሊሆኑ ይችላሉ።

በዚህ ጉድይ ላይ የሕወሃት መሪዎች ያሳልፋሉ የሚባለው የመጨረሻ ውሳኔ በመጠበቅ ላይ ነው።

ከጄኔራል ሳሞራ ጋር የተወሰኑ የጦር አዛዦችም በጡረታ እንደሚገለሉ ተመልክቷል።

የአየር ሃይል አዛዥ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት የብአዴኑ አደም መሀመድ የሙሉ ጄኔራልነት ማዕረግ ማግኘታቸውን ተከትሎ ከአየር ሃይል አዛዥነት እንዲነሱ ተወስኗል።

በምትካቸውም የቀድሞው የአየር ሃይል አዛዥ የህወሃቱ ሞላ ሃይለማርያም በሌተናል ጄኔራልነት ማዕረግ መልሰው የአየር ሃይል አዛዥነቱን ስፍራ ይይዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለመከላከያ ሰራዊት አዛዦች በተሰጠ ከፍተኛ ወታደራዊ ሹመት 4 ሙሉ ጄኔራልነትን ጨምሮ 61 መኮንኖች የጄኔራል መኮንንነት ማዕረግ ማግኘታቸው ይታወሳል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.