አቶ አባይ ወልዱ የህወሃት ክንፍ እንዲፈጠር ከሳሞራ ጋር አሲረዋል በሚል ተገመገሙ

ኢሳት ዜና

Samor &Abay wolduየካቲት ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቤተመንግስት ትንሹ አዳራሽ ውስጥ የተካሄደውን የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ግምገማ የሚቃኘው መረጃ እንደሚያሳየው የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አባይ ወልዱ የህወሃት ክንፍ እንዲፈጠር ከመከላከያ ኢታማጆር ሹም ሳሞራ የኑስ ጋር ማሴራቸው በሌሎች የኢህአዴግ አባላት ሂስ ቀርቦባቸዋል። አቶ አባይ ወልዱ የቀረበባቸውን ሂስ በደፈናው ተቀብያለሁ፣ አርማለሁ በማለት መመለሳቸውን ሰነዱ ያስረዳል።

አቶ አባይ ግለሂሳቸውን እንዲያወርዱ ሲጠየቁ የስራ ሰአት የማክበር ችግር እንዳለባቸው፣ ከአሉባልታ ወሬ ጋር በተያያዘ ችግር እንዳለባቸውና በ1 ለ5 አደረጃጃት እንደማይሳተፉ ተናግረዋል።

በምክር  ቤቱ  የተሰበሰቡት ባልደረቦቻቸው  በበኩላቸው ” አስተያየት የመቀበል ችግር አለብህ፣ በረባ ባልረባው ከስራ ገበታህ ትቀራለህ፣ ችግሮችን በውይይት የመፍታት እጥረት አለብህ፣ የሰራሃውን ስራ በጊዜ የማምጣት ችግር አለብህ፣ ህጎችን የማክበር ችግር ይታይብሃል” በማለት ገምግመዋቸዋል። አቶ አባይ በአጠቃላይ ግምገማየ ” ቢ” ውጤት ማግኘታቸውም በሰነዱ ተመልክቷል።

የጠ/ሚኒስትሩ የጸጥታ አማካሪ የሆኑት የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕ/ት ጸጋየ በርሄ ደግሞ ” የማሳቀድ ውስንነት አለብኝ፣ በንባብ ራስን የማብቃት እጥረት አለብኝ፣ በጥራት የማሰራት እጥረት አለብኝ” በማለት ግለ-ሂሳቸውን ሲያወርዱ ወይም ራሳቸውን ሲገመግሙ፣ ጓደኞቻቸው ደግሞ ” ሞጋች የሆኑ ነገሮችን ያለመንካት ችግር አለብህ፣ አስተባብሮ የመስራት እጥረት አለብህ፣ ሌሎችን አሳቅዶ የመስራት እጥረት አለብህ፣ ሰአት አታከብርም፣ ውሳኔ የመስጠት ችግር አለብህ፣ የክትትልና ቁጥጥር እጥረት ይታይብሃል” በሚል ሂስ ሰጥተዋቸዋል።

አቶ ጸጋየ ለቀረበባቸው አስተያየት ተቀብየዋለሁ ያሉ ሲሆን በስራቸውም “ቢ” ተሰጥቷቸዋል።

ዶ/ር ካሱ ኢላላ በበኩላቸው የማንበብ እጥረት አለብኝ በማለት ራሳቸውን የገመገሙ ሲሆን፣ ሎሎች ባልደረቦቻቸው ደግሞ ” የስልክ አጠቃቀም ችግር አለብህ፣ ወሬ የመስማት፣ የማኩረፍ ችግር አለብህ፣ የቢሮ ስነምግባር አለማክበር ይታይብሃል፣ ፈሪ ነህ፣ ግንባር ቀደም አይደለህም፣ ሰርቶ የማሰራት እና የመምራት ችግር አለብህ፣ ለተተኪዎች አይንህ ደስተኛ አይደለም” በሚል ተገምግመዋል፤፡ ዶ/ር ካሱ ኢላላ ሂሱን መቀበላቸውን ገልጸው ፣ ሲ ውጤት ተሰጥቷቸዋል።

አቶ አርከበ እቁባይ ደግሞ በቁጭትና በእልህ የመስራት እጥረት አለብኝ፣ ስራን አድምቶ የመስራት እጥረት አለብኝ፣ ሰአት ማክበር፣ በቡድን መስራት ላይ ውስንነቶች አሉብኝ በማለት ራሳቸውን የገመገሙ ሲሆን፣ ሌሎች ጓደኞቻቸው ደግሞ ስራን የማዘግየት ችግር አለብህ፣ ከስራ ባልደረቦች ጋር ተግባብቶ የመስራት ችግር አለበት፣ ነገሮችን አግዝፎ የማየት፣ ቂመኛነት አለበት፣ ለችግሮች መፍትሄ የመሻት እጥረት አለብህ፣ ግጭትን ያለማርገብ ችግር አለብህ” በሚል ተገምግሟል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳ አቅዶ የመስራት ክፍተት አለብኝ፣ ራስን በማያቋርጥ የንባብ ባህል የማብቃት እጥረት አለብኝ በማለት ራሳቸውን የገመገሙ ሲሆን፣ ባልደረቦቻቸው ደግሞ ” በንባብ ራስን የማብቃት ችግር አለብህ፣ አሳምኖ የማሰራት እጥረት አለብህ፣ ለሌሎች ሀሳብ የመስጠት ቁጥብነት አለብህ፣ ያለህን እውቀት ለሌሎች የማጋራት እጥረት አለብህ፣ ሳሞራን ትፈራዋለህ፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤትህ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ደካማ ነው” በሚል ተተችተዋል።

አቶ ሲራጅ መከላከያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ደካማ መሆኑን ፣ ችግሩ በመስሪያ ቤቱ ብቻ ሳይሆን በጦሩም እንደሚታይ ገልጸው፣ አደረጃጀት ለመፍጠር ቢሞክሩም የሚተባበራቸው አመራር ማጣታቸውን፣ ከሳሞራ ጀምሮ ሃይለማርያምም እንደሚያውቅ ” ተናግረው፣ ሌሎች የተነሱት ሃሳቦች ገንቢ ናቸው፣ ተቀብያቸዋለሁ ብለዋል።

የኦሮምያ ም/ል ፕ/ት የሆኑት ወ/ሮ አስቴር ማሞ በበኩላቸው “የስራ ሰአት እሸራርፋለሁ፣ ስሜታዊነት አለብኝ፣ በአንድ ለአምስት ላይ ክፍተት አለብኝ” በማለት ራሳቸውን የገመገሙ ሲሆን፣ ሌሎች የምክር ቤት አባላት ደግሞ ” ተግባብቶ የመስራት እጥረት አለብሽ፣ ከስራ ማርፈድ ፣ መቅረት አለብሽ፣ የቢሮ ሰአት አታከብሪም፣ ትሸራርፊያለሽ፣ ከባልደረቦችሽ ጋር ትጋጫለሽ፣ በቢሮው ውስጥ ሶስት የአካባቢሽን ልጆች አዲስ አበባ በአጠቃላይ ዘጠኝ የሚደርሱ በሚኒስትር ቢሮዎች በሹመት እንዲመጡ አድርገሻል ” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

ወ/ሮ አስቴር ሰዎቹ የመጡት በእርሳቸው ትእዛዝ መሆኑን፣ ነገር ግን ሰዎቹ ከአቅም በታች ናቸው ማለት እንደማይቻልና፣ ሁላችንም በተመሳሳይ መንገድ በችሎታቸው ያመጣናቸው አሉ ሲሉ ተከላክለዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ ሶፍያን አህመድ ደግሞ ስራን በፍጥነት የመፈጸም እጥረት አለብኝ ብለው ራሳቸውን ሲገመግሙ፣ ሌሎች ባልደረቦቻቸው ደግሞ “ከደባል ሱስ የጸዳህ ብትሆን፣ ስራ ያዘገያል፣ ስራን ለነገ ባትል፣ ራስህን ከሌሎች ማራቅህ ብተተው” በሚል ገምግመዋቸዋል።

የሴቶችና የወጣቶች ሚኒስትር ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ በበኩላቸው የስራ ሰአት መሸራረፍ አለብኝ፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የታቀደውን ያህል አልሰራሁም በሚል ስለድክመታቸው ሲናገሩ፣ ሌሎች የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው ” ለኢህአዴግ ተልእኮ አስፈላጊ ነገሮችን ጠይቆ ማሟላት ላይ እጥረት አለብሽ፣ ይሉንታ ያጠቃሻል፣ ሴቶች ተሳትፎ ስራው ላይ እንዲሻሻል የጎላ ድርሻ አልተወጣሽም ፣ ክፍት ሚኒስቴር ነው ማለት ይቻላል፣ የሃሰት አፈጻጸም እና ሪፖርት ታቀርቢያለሽ” በሚል ገምግመዋታል። ወ/ሮ ዘነቡ “የተሰጠኝ አስተያየት ገምቢ ነው ወደ ፊት አየዋለሁ፣ ሂሱን ወስጀዋለሁ” ብለዋል።

ሽፈራው ሽጉጤ ደግሞ “የስራ ሰአት አለማክበር ብቻ ሳይሆን ትቀራለህ፣ ስብሰባ ላይ አትገኝም፣ አማራን ባስወጣህበት የደቡብ ክልል መስተዳደር ጊዜህ ለክልሉ ነዋሪዎች ነፍጠኛ ከኛ ይወገዳል ብለህ ተናግረሃል” በሚል ከብአዴን ተወላጆች አስተያየት ቢሰጥም፣ አቶ ሽፈራው ” ከጠ/ሚኒስትሩ የተሰጠኝን ተልእኮ ነው በአግባቡ የተወጣሁት፣ ሌላ አልጨመርኩም አላስወጣሁም” ብለው መልሰዋል።

የአማራ ክልል ም/ል ፕሬዚዳንት እና የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አለምነው መኮንን ” የመለስን ቦታ የመተካት ህልም አለህ፣ የስልጣን ጥመኝነት አለብህ፣ የድርጅቱን ህልውና አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ ተንቀሳቅሰሃል፣ ከመለስ ውጭ ሌላው የሞተ ነው ብለህ ተናግረሃል፣ ሆን ብለህ ለኢሳት መረጃ እንዲደርስ ታደርጋለህ፣ የብሄሮችን እኩልነት አትቀበልም፣ የስልጣን ሰንሰለት በጎጠኝነት መስርተሃል፣ አጉል ጀብደኝነት አለብህ” ተብለው ሲገመገሙ፣ እርሳቸው ግን ከተሰጠኝ ተልእኮ ውጭ አልተንቀሳቀስኩም፣ ነገሩን አጣመው የሚያቀርቡ ሰዎች አሉ በማለት በብሄር እኩልነት አታምንም በተባሉት ላይ ከረር ያለ መልስ ሰጥተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ደግሞ “በእቅድ ላይ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ላይ ስኬታማ አይደለሁም፣ የስራ ሰአት አከባበር ችግር አለብኝ” ብለው ራሳቸውን የገመገሙ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ” ስራን የማዘግየት ችግር አለበት፣ በማህበራዊ ሚዲያ የግለሰቦችን ታሪክ ለራሱ ገጽታ ግንባታ አውላል፣ ለአብነትም ከአረብ አገራት የተመለሱ ሰዎችን፣ ከተሰጠው ተልእኮ ውጭ ይንቀሳቀሳል” ብለዋቸዋል። ዶ/ር ቴዎድሮስ ሂሱን እንደማይቀበሉት የቃለ ጉባኤ ሰነዱ ያሳያል።

የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት እስማኤል አሊ ሴሮ ” የንባብ ባህል እጥረት አለብኝ” ብለው ራሳቸውን ሲሄሱ፣ ሌሎች ደግሞ አርፍዶ የመግባት፣ ፈጥኖ የመውጣት ነገር ይታይበታል፣ እቅድ እና ቅድመ ዝግጅት ላይ እጥረት አለበት፣ ሰአት አለማክበር ይታይበታል” ብለዋቸዋል።
ደግሞ “ጥራት ያለው ስራ መስራት ላይ እጥረት አለብኝ፣ የንባብ ባህል ችግር አለብኝ፣  አንድ ለአምስት ላይ ብዙም ንቁ ተሳትፎ አላደረኩም ” ብለው ራሳቸውን የገመገሙ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ በክልሉ ውስጥ ችግር ሲከሰት ለመፍታት አትሞክርም፣ አሉባልተኝነት ላይ ራስህን በደንብ ብታይ ” ተብለዋል።

የፌደራል ሚኒስትሩ ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው ” ጥራት ያለው  ስራ እሰራለሁ ብየ አላስብም፣ የንባብ ባህል ላይ ችግር አለብኝ፣ ሰአት እሸራርፋለሁ” ብለው ሰለራሳቸው ድክመት ከተናገሩ በሁዋላ፣ ሌሎች ደግሞ ” ስራ ሲታዘዝ እገሌ ሳይሰራ የማለት ባህሪ አለው ቢያስተካክል፣” ብለው ሲገመግሙዋቸው . ዶ/ር ሽፈራው አልቀበለውም ብለዋል። ጉዳዩ እንደገና ይታይ የሚል ከቤቱ አስተያየት በመቅረቡ ” ሌሎች እንደገና ” የባህሪ ቁጡነት ይታይብሃል፣ አንድ ለአምስት አዘውትረህ አትሳተፍም፣ ይሉንታ አለብህ፣ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ ያለውን አክራሪነት መቆጣጠር አልቻልክም” የሚል ሂስ አቅርበዋል። ዶ/ር ሽፈራው ” ማህበረ ቅዱሳንን መንካት መሞት መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን፣ ከሱ ውጭ ያለውን ግን እየሰራሁ ነው።” ብለው መልስ ሰጥተዋል። አንዳንድ ሂሶችን መቀበላቸውን ተናግራል።

ሩድዋን ሁሴን በኮሚኒኬሽን ስራ ተቃዋሚዎች እንዲበልጡን አስደርግሃል የሚሉና ሌሎች በርካታ ትችቶች ሲቀርቡባቸው፣ አባ ዱላ ገመዳ ደግሞ ከስራቸው እና በኦሮምያ ከሚታየው ችግር ጋር ተያይዞ ትችት ቀርቦባቸዋል።