ቁም ነገር መፅሄት ልዩ ዘገባ – ሃናና ሀበሻ ‹ፕራንክ› – ከሄርሜላ እስከ ካሚላት ከአበራሽ እስከ ፍሬህይወት- ከሃና እስከ ?

ቁም ነገር ቅጽ 13 ቁጥር 192 ህዳር 2007
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን /ኢቲቪ3/ እና በኢቢኤስ ቲቪ ላይ ከሚቀርቡ የመዝናኛ ፕሮግራሞች መሀከል ‹ጨዋታ› ሐበሻ ፕራንክ ፕሮግራም አንዱ ነው፡፡ በኮንታክት መልቲ ሚዲያ ተዘጋጅቶ የሚቀርበው በዚህ ፕሮግራም ላይ ‹የካሜራ ትኩረት› የተሰኘ የመዝናኛ ትርኢት ይቀርባል፡፡ ከውጪ ሀገር የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ተኮርጆ በሀገር ውስጥ ድንገቴ ትወና በመስራት በስውር ካሜራ ተቀርፆ የሚቀርበው ዝግጅት በማናቸውም ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የህብረተሰባችንን የአስተሳሰብ ደረጃ የት ድረስ እንደሆነ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ፕሮግራም ነው፡፡ ፕሮግራሙን ላልተመለከታችሁና ላላያችሁ ሰዎች ይህ አጭር መግለጫ የፕሮግራሙን ምንነት ያሳያል፡፡
አንድ
በቅድሚያ ሁለት ወጣቶች/አንድ ወንድና ሴት/ በካሜራው ፊት ይሆኑና ‹አሁን እኔ መንገድ ላይ እቆምና እሷ ዩኒፎርም ለብሳ ከትምህርት ቤት ስትመጣ አስቆማትና አታልፊም ከእኔ ጋር ካልሄድሽ እላታለሁ፡፡ በዚህ ጊዜ በአካባቢው የሚያልፉ ሰዎች ሁኔታውን ተመልክተው ምን እንደሚያደርጉ አብረን እንመለከታለን› በማለት ወደ ትወናቸው ይገባሉ፡፡ ይህን ጊዜ አንድ ስውር ካሜራ ድምፃቸውንና ምስላቸውን በመኪና ውስጥ ሆኖ ይቀርፃል፡፡ ወጣቱ ፀጉሩን አንጨባሮ ዩኒፎርም ለብሳ ደብተሯን ሸጉጣ ከትምህርት ቤት የምትመጣውን ወጣት መንገድ ላይ በማስቆም ‹ዛሬ ከእኔ ጋር ነው የምትውይው› ይላታል ጮክ ብሎ፡፡ ልጅቱም አስቀድማ በተዘጋጀችበት መልኩ መተወን ትጀምራለች፡፡‹ወደ ቤቴ መሄድ አለብኝ፤ አሳልፈኝ እባክህ› እያለች አላፊ አግዳሚውን እየተመለከተች ትናገራለች፡፡ ወጣቱ ግን በአካባቢው ሰዎች ማለፍ ሲጀምሩ‹ሳልፈቅድልሽ ከዚህ

ቦታ እንዳትንቀሳቀሺ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር አብረን ሄደን ጫት እንቅማለን፤ ከእኔ ጋር ነው የምትውይው › ይላታል፡፡ ልጅቱ አሁንም እየተነጫነጨች ‹እባክህ ልቀቀኝ ? ወደቤቴ መግባት አለብኝ› ትላለች፡፡ በአካባቢው የሚያልፉ ሰዎች የልጅቱንና የወጣቱን ጭቅጭቅ ቢሰሙም ገልመጥ ብለው ያልፋሉ፡፡ በዛች አጭር የትወና ደቂቃ በአካባቢው ከሚያልፉ አስር ሰዎች ስምንቱ ወጣቱ የልጅቷን እጅ ይዞ ከእኔ ጋር ካልሄድሽ ሲላት ‹ተው እንጂ› የሚል የለም ተገላምጦ አይቶ ከማለፍ ውጪ፡፡ ምናልባት አንድ ሁለቱ ቆም ብለው ጭቅጭቁን ከተመለከቱ በኋላ‹ ምንድነው ያለፍላጎቷ የምታደርጋት?› ለማለት ሲከጅሉ ይታያል፡፡ ነገር ግን ልጁ ጠጋ ብሎ ‹ምንድነው?› ብሎ ሲያፈጥባቸው አንገታቸውን ጠምዝዘው ሲሄዱ ይታያል፡፡ ከብዙ የምንቸገረኝ ትዕይንት በኋላ ግን ‹ሆን ተብሎ የሚሰራ ድንገቴ ትወና በመሆኑ ወጣቶቹ ተቃቅፈው አንድ ላይ ሲሄዱ ይታያል፡፡
ሁለት
እነዚሁ ወጣቶች ልብስ ቀይረው በመንገድ ላይ ይጓዛሉ፡፡ ወጣቱ ድንገት ወደ ወጣቷ ሄዶ ‹ሞባይልሽን አምጪ!› ብሎ ይቀበላትና ‹ከእዚህ አካባቢ ጥፊ› ይላታል፡፡ ልጅቷ ግን እየተከተለችው ‹ሞባይሌን መልስልኝ እንጂ?› እያለች በአካባቢው የሚያልፉ ሰዎች እንዲሰሙ ጮክ ብላ ትለምነዋለች፡፡ ወጣቱ ግን ወደ ኋላ ተመልሶ ልጅቷን እንደ መማታት እየዛተባት ‹አልሰጥሽም ሂጂ ከዚህ አካባቢ› ይላታል፡፡ በአካባቢው ወጣቱ ሞባይሏን ሲነጥቃት የተመለከቱም ሆኑ ‹ሞባይሌን መልስልኝ› የሚለውን የልጅቱን ጥያቄ ያዳመጡ ሰዎች ‹ ለምንድነው ሞባይሏን የምትሰጣት?› ሲሉ በስውር ካሜራው አይታዩም፡፡ ቆም ብለው ጭቅጭቃቸውን ከሰሙና ከተመለከቱ በኋላ መንገዳቸውን ነው የሚቀጥሉት፡፡ በመጨረሻ ወጣቶቹ በስውር ካሜራ ፊት የሚተውኑ ተዋንያን መሆናቸውን አሳውቀው ተቃቅፈው እስከሚሄዱ ድረስ የዚህ አይነት ትዕይንት በተደጋጋሚ ይታያል፡፡
ይህ ለመዝናኛነት ተብሎ የሚሰራ ትወና የማህበረሰባችንን የ‹ያገነባኛል›ን የሀላፊነት ደረጃ› ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ሴቶችን በመንገድ ላይ ማንም ጎረምሳ ‹አታልፊም ›ብሎ ሲያስቆማትና ሲጎትታቸው ‹ለምን?› ብሎ የሚጠይቅ ሰው የለም፡፡ ከሴቶች ጥቃት አንፃር ብቻ ሳይሆን ከልዩ ልዩ ማህበራዊ ችግሮቻችን አንፃር በዚሁ ‹ሀበሻ ፕራንክ/ጨዋታ› በተሰኘው ፕሮግራም ላይ ቀርቦ ተመልክተናል፡፡ አስፋልት ላይ ቆሞ የሚሸና… የመንገድ አካፋይ ብረት ለመሸጥ የሚነቅል … ከመንገድ ዳር የኔ ብጤ ላይ ሳንቲም የሚነጥቅ… ወዘተ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ የተለያዩ ህብረተሰብን የሚጎዱ ተግባራት ሲፈፅሙ ‹ለምን?› ብለው የሚጠይቁና መደበኛ ሥራቸውን ትተው ለሌላው መብት የሚታገሉ ሰዎች የሉም፡፡ ወይም ቁጥራቸው እጅግ ሲበዛ አነስተኛ ነው፡፡
የዚህ አይነት ለማህበረሰቡ ጠቃሚ የሆኑ መልዕክቶች የሚተላለፉበት ፕሮግራም በስፖንሰር እጦት ሲንገታገት መመልከት ደግሞ ሌላው የማህበረሰባችንን የአስተሳሰብ ‹ልምሻ› ማሳያ ነው፡፡ 
***********
የሃና ላላንጎ ጥቃት
ሰሞኑን የማህበራዊ ድረ ገፆችንና የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንን አጨናንቆት የከረመው ወሬ የ16 ዓመቷ ታዳጊ ልጃገረድ ሃና ላላንጎ ላይ የተፈፀመው ጥቃትና ከዚሁ ጥቃት ጋር በተያያዘ የደረሰባት ሞት ነው፡፡ዓመታትና ወራትን እያለፈ ከመከሰቱ በቀር የሃና ጉዳይ ቀደም ሲል በሀበሻ ፕራንክ ፕሮግራም ላይ የተመለከትነው የህብረተሰባችን ቸልተኝነት ውጤት አንድ ማሳያ ነው፡፡ የዚህ አይነት አስከፊና የማህበረሰባችንን የሞራል ደንብ የሚጥስ ተግባር ሲፈፀም የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ ከመሆን ያልዘለሉ የተለያዩ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን እናስታውሳለን፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለን ባለፉት ዓመታት የተከሰቱና የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ያገኙ የጥቃት ሰለባ ሴቶችን ታሪክ ስንመለከት ተመሳሳይ ድርጊቶችን እናስተውላለን፡፡
***********
የሄርሜላ ታሪክ
የዛሬ 15 ዓመታት ገደማ ሄርሜላ የምትባል ወጣት ‹አፈቀርኩሽ› በሚል ሰበብ አንድ ጎረምሳ መግቢያ መውጫ ያሳጣታል፡፡ ልጅቱ ትምህርቷን እንኳ መከታታል የማትችልበት ደረጃ ላይ ስትደርስ ለቤተሰቦቿ ጉዳዩን ታሳውቃለች፡፡ ቤተሰቦቿም የችግሩ ፈጣሪ የተባለውን አፍቃሪ ወጣት አግኝተው ለማነጋገር ይሞክራሉ፡፡ ከነእርሱ አቅም በላይ ሲሆን ለፖሊስ ያመለክታሉ፡፡ ፖሊስ ወጣቱን ይዞ ቢመረምርም በፍቅር ሳቢያ የሆነ መሆኑን በመገንዘብ ‹አጠገቧ እንዳትደርስ› በማለት በምክር ይለቀዋል፡፡ ወጣቱ ግን ከስህተቱ ከመታረም ይልቅ ሄርሜላን በሀይል የራሱ ለማድረግ ቆርጦ ይነሳል፡፡ በሁለቱ መሀከል የገቡ ቤተሰቦቿንም በገጀራ በማስፈራራት ልጅቱን ሌላ ስጋት ላይ ይጥላታል፡፡ጉዳዩ በኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ቢያዝም መፍትሔ አላመጣም፡፡ ለዓመታት የተፈጠረው ችግር በመገናኛ ብዙሃን ላይ ከቀረበ በኋላ ልጁ ተይዞ ክስ ይመሰረትበታል፡፡ ፍርድ ቤት ቀርቦም ከተፈረደበት በኋላ ‹ሊያመልጥ ሲል › በሚል ምክንያት እዛው ፍርድ ቤት ደጃፍ ላይ በጥይት ይገደላል፡፡ ምንም እንኳ አርቲስት ሰማከኝ በለው ‹አላበድኩም ያዢኝ› የተሰኘ ነጠላ ዜማ ከማውጣቱና ታሪኩ ዳይሬክተር ዮናስ ብርሃነ መዋ ‹ሄርሜላ› የተሰኘ ፊልም ለመስራቱ ምክንያት ከመሆኑ በቀር ጉዳዩ መሰረታዊ የሴትና የወንድ ልጅን የፍቅር ግንኙነት ማስተማሪያ ሆኖ በማህብረሰቡ ውስጥ አልተስተዋለም፡፡ በመሆኑም ሌሎች ዘግኛኝ የሴት ልጅ ጥቃት ዜናዎች መሰማታቸው ቀጠለ፡፡
***********
የካሚላት ታሪክ
ካሚላት መህዲ በ1999 ዓ.ም የገና ዋዜማ ከታላቅ እህቷ ጋር ከምትሰራበት ሱቅ አምሽታ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ ወደ ቤቷ ስትሄድ አንድ

ሰው ወደ አጠገባቸው መጥቶ አሲድ ፊቷ ላይ ደፍቶ ይሰወራል፡፡ ካሚላት በወቅቱ በደረሰባት የፊት መቃጠል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባት ሲሆን በሀያት እና በየካቲት 12 ሆስፒታል ህክምና ቢደረግላትም የፊቷ ቆዳ ከ96 ከመቶ በላይ መቃጠሉ በሀኪሞች ይረጋገጣል፡፡ ይህ አስከፊ አደጋ በአዲስ አበባ ብዙሃን መገናኛ ኢቲቪ 2 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እስከሚቀርብ ድረስ የካሚላት ጉዳት ሚስጥር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ጉዳዩ በመገናኛ ብዙሃን ቀርቦ የአደጋው አስከፊነት ድንጋጤ ከፈጠረ በኋላ በተለያዩ ወገኖች አስተያየቶች መሰጠት ጀመሩ፡፡ ጉዳዩን ፈፅሞታል ተብሎ በካሚላት የተገለፀው ደምሰው ዘርይሁን ከነግብረ አበሮቹ ተይዞ ምርምራ እየተካሄደ መሆኑን ፖሊስ ይፋ አደረገ፡፡
ድርጊቱን ፈፅሞታል የተባለውን ወጣት በተመከለተም ብዙዎች ስሜታዊ ሆነው ‹አውሬ ነው፤ ሊሰቀል ይገባል› ብለው በመገናኛ ብዙሃን ላይ ሳይቀር ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የሴቶች ጉዳይ ማህበራትና አመራሮችም ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ በህግ አስፈፃሚ አካላት ላይ ተፅእኖ ለመፍጠርና ከበድ ያለ ቅጣት እንዲፈረድበት ጠየቁ፡፡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ያለው ወጣት ‹እኔ ድርጊቱን አልፈፀምኩም፤ እንደውም ፍቅረኛዬ ነች› ብሎ የፎቶግራፍ ማስረጃዎችን ይፋ እስከሚያደርግ ድረስ (ቁም ነገር መፅሔት 6ኛ ዓመት ቁጥር 62፤ መጋቢት 1999ዓ.ም) በተፈጠረው ድርጊት ዙሪያ ግራና ቀኝ ለማየትና የችግሩን መሰረት ለመመርመር ፍላጎት ያለው አካል አልነበረም ለማለት ይቻላል ጉዳዩ ውሎ ሲያድር ቀደም ሲል የነበረው ስሜታዊነት በጠፋበት በዓመቱ ድርጊቱን ፈፅመውታል የተባሉት ሁለት ወጣቶች የዕድሜ ልክ እስራትና የሃያ ዓመት ፍርድ ተበየነባቸው፡፡ ወጣቶቹ ይግባኝ ጠይቀው የዕድሜ ልክ እስራቱ ወደ ሃያ ዓመት የሃያ ዓመቱ በነፃ እስከሚቀየር ድረስ የካሚላት ጉዳይ አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል፡፡
***********
የአበራሽ ታሪክ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ /ሆስተስ/ የሆነችው ወ/ሮ አበራሽ ሀይላይ መስከረም 2 ቀን 2004 ዓ.ም ገርጂ በሚገኘው ኮንዶሚኒየም ኪራይ ቤቷ በማግስቱ ወደ ደቡብ ሱዳን ጁባ ለምታደርገው በረራ ልብሶቿን እያስተካከለች ነው፡፡ ከትዳሯ ከተፋታች ገና አራት ወር እንኳን ያልሞላት አበራሽ በተከራየችው ኮንደሚኒየም ቤቷ ይህ ነው የሚባል የቤት ቁሳቁስ ገና አላሟላችም፡፡ ሁሌም በረራ ላይ ጊዜዋን የምታሳልፈው አበራሽ የቤት ሰራተኛ ለመቅጠር ገና አላሰበችም ነበር፡፡ በመሆኑም በዕለቱ ከምሽቱ 11 ሰዓት ገደማ ወደ ቤቷ ገብታ በማግስቱ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ላለባት በረራ ቅድመ ዝግጅት ላይ ናት፡፡ ከምሽቱ 4 ሰዓት ገደማ ከቤቷ ደጃፍ አንድ ሰው ደጋግሞ በሯን ይቆረቁራል፤ ግለሰቡ ከደቂቃዎች በፊት ከአጎቷ ቤት የተለየችው የቀድሞ ባለቤቷ አቶ ፍስሀ ታደሰ ነበር፡፡ ከአጎቷ ቤት የተለየችው ግለሰብ ዳግመኛ ቤት ድረስ መምጣቱ ቢያስገርማትም ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላ አስቀድሞ ባቀደውና በተዘጋጀበት መሰረት በያዘው ጩቤ ሁለት ዓይኖቿን ለማውጣት የሚያደርስ ችካኔ ይፈፅማል ብላ ግን ፈፅሞ አልገመተችም ነበር (ቁም ነገር መፅሔት 10ኛ ዓመት ቁጥር 116፤ መስከረም 2004ዓ.ም)፡፡
ፖሊስ ማረፊያ ቤት አስቀምጦ ምርምራ ከጀመረ በኋላ ወሬው እንደተለመደው መገናኛ ብዙሃን ጆሮ ይደርሳል፡፡ ወሬውን የሰሙ ሁሉ የደርጊቱን ፈፃሚ ‹አውሬ፤ ሊሰቀል ይገባል!› ማለት ጀመሩ፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሴቶቹ ማህበራትና አደረጃጀቶች ሁለት የስብሰባ ፕሮግራሞችን በዳግማዊ ምንሊክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትና በሸራተን አዲስ አዘጋጁ፡፡ በመድረኮቹ ላይ ድርጊቱ ለምን ተፈፀመ?› በሚል መወያየት ላይ ያተኮረ ሳይሆን ይህንን የጭካኔ ደርጊት የፈፀመው ግለሰብ ሊሰቀል ይገባል በሚል የበቀል አስተያየት ላይ ያተኮረ ነበር (ቁም ነገር መፅሔት 10ኛ ዓመት ቁጥር 116፤ መስከረም 2004ዓ.ም)፡፡በሸራተን አዲስ የተዘጋጀው መድረክ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ሰራተኞችን ያሳተፈ ስለነበር ሊወሰድ በታሰበው የፍርድ ቤት ውሎ ላይ የራሱ የሆነ ተፅእኖ ለማሳለፍ የታለመበት ነበር ለማለት ይቻላል፡፡
***********
የፍሬህይወት ታሪክ
ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 ገደማ ከካሳንቺስ ኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ወደ ኦሎምፒያ የሚወስደው መንገድ እንደወትሮው የትራፊክ እንቅስቃሴ አጨናንቆታል፡፡ በተጨናነቀው በዚህ መንገድ ላይ ግን አንድ ሃችፓክ መኪና በአየር ላይ የሚበር በሚመስል ሁኔታ ይከንፋል፡፡ ከፊት ለፊቱ ባሉ መኪናዎች መንገድ የተዘጋበት የዚህ መኪና አሽከርካሪ ልክ ዮርዳኖስ ሆቴል ደጃፍ ጋር ሲደርስ ‹‹በአሳልፉኝ›› ምልክት በክላክስ አካባቢውን ያውከዋል፡፡
የክላክስ ድምፁ በተደጋጋሚ የተነፋላት ከፊት ለፊቱ ያለችው በተለምዶ ወያኔ ዲኤክስ መኪና አሽከርካሪ ክላክሱ ለእሷ የተነፋ አልመሰላትም ነበር፡፡ ወላጅ እናቷን ጭና ወደ ኦሎምፒያ አቅጣጫ መብራቱን ለመሻገር ጥረት ታደርግ የነበረችው አሽከርካሪ ከኋላዋ ያለውን ሰው ማንነት ለማረጋገጥ በመኪናዋ የጎን መስታወት /ስፖኪዮ/ ስትመለከት በፍ/ቤት በፍቺ ወረቀት የተለየችው የሁለት ልጆቿ አባት መሆኑን ተመልክታለች፡፡
የቀድሞው ባለቤቷ የክላክስ ጩኸትና በተደጋጋሚ በእጅ ምልክት እንድትቆም የሚያሳያት ዛቻ ያላማራት ሚስት የመንገዱን መብራት በፍጥነት አቋርጣ ወደ ኦሎምፒያ ደንበል አቅጣጫ ሽቅብ መንዳት ትጀምራለች፡፡ ከኋላዋ እየተከታተላት ያለው አሽከርካሪም የመጨረሻ ፍጥነቱን ጨምሮ ይከተላታል፡፡ አጠገቧ ያሉት እናት ወ/ሮ ተናኜ ሀ/ማርያም ባሏ ምን እንደፈለገ ቆማ እንድታናግረው አለበለዚያም የፀጥታ ሀይሎች ወዳሉበት እንድትነዳ ሲጠይቋት የሁኔታውን አስፈሪነት በመረዳት ሁለተኛውን አማራጭ ነበር የመረጠችው፡፡ እናም

ወደ ደንበል የሚወስደውን መንገድ በፍጥነት ነድታ አዲስ እየተሰራ ያለው አደባባይ ጋር ስትደርስ በአይኗ ግራና ቀኝ ፖሊሶችን ፍለጋ አማተረች፡፡
በወቅቱ በአካባቢው ላይ የትራፊክ ፖሊሶችና ሌሎች የፌደራል ፖሊስ የፀጥታ ሠራተኞች ነበሩ፡፡ ሚስት አደባባዩን እንደተሻገረች ላፓራዚያን ካፌ ፊት ለፊት ከመድረሷ በፊት ከኋላ የሚከተላት የባሏ መኪና ሲጋልብ አጠገቧ ይደርሳል፡፡ አመጣጡ ያላማራት ሚስት መኪናዋን ካርቱም ሬስቶራንት ፊት ለፊት ባለበት ሁኔታ አቁማ በመውረድ ወደ ፀጥታ ሠራተኞች ለመሮጥ በመወሰን መኪናዋን ታቆማለች፡፡
የአደጋ መከላከያ ቀበቶዋን በፍጥነት ፈትታ ልትወርድ ስትል ግን መኪናው በበሯ አጠገብ ሲጢጥ ብሎ በማቆም አሽከርካሪው ወደ እሷ መጣ፡፡ በሯ በመኪናው መዘጋቱን የተመለከተችው ሚስት በሌላኛው የፊት በር በፍጥነት ወጥታ ለማምለጥ ጥረት እያደረገች ሳለ ረዥም ክላሺንኮቭ ጠመንጃውን እያቀባበለ ወደ እሷ የተጠጋው አሽከርካሪ በቀጥታ በመተኮስ በ18 ጥይት የሁለት ልጆቹን እናት ባለችበት ጣላት፡፡ ከተኮሳቸው ጥይቶች መሀከል ወላጅ እናቷን ሶስት ጥይት አግኝቷቸዋል፡፡ ሁኔታውን በስፍራው ሆነው ሲከታተሉ የነበሩ የአይን እማኞች እንደገለፁት ከሆነ ያለምንም ንግግር ይህንን አስከፊ ድርጊት የፈፀመው ሰው በቀረው ጥይት ራሱን ለማጥፋት ወደርሱ ለመተኮስ ቢሞክርም ጠመንጃው ጥይቱን ጨርሶ ስለነበር መሞት አልቻለም፡፡ ይህ ከሁለት እስከ ሶስት ደቂቃ የፈጀውን ትዕይንት ለማስቆም ጊዜ ያጡት በአካባቢው የነበሩት የፀጥታ ሠራተኞች የድርጊቱን ፈፃሚ ዋና ተዋናይ በቁጥጥር ስር አድርገው ተጎጂዎቹን ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ ወዲያ ወዲህ ቢሉም ሚስት ወ/ሮ ፍሬህይወት ታደሠ ሰውነቷ ላይ ባረፉት 18 ጥይቶች ሳቢያ እስከወዲያኛው ያሸለበችው እዚያው መኪና ውስጥ ነበር(ቁም ነገር መፅሔት 6ኛ ዓመት ቁጥር 62፤ መጋቢት

1999ዓ.ም)፡፡ ፍሬህይውት ታደሰ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነበረች፡፡ ከባለለቤቷ ወንድወሰን ይልማ ጋር የተዋወቀችው ቦሌ ብራስ ሆስፒታል አካባቢ ባለ አንድ መ/ቤት ሊፍት ውስጥ በአጋጣሚ ሲሆን ብዙም ሳይቆዩ በከተማችን ለየት ባለ ባህላዊ ጋብቻ ነበር የተጋቡት፡፡ ወንድወሰን የሁለት ልጆቹን እናት በዚህ ሁኔታ ከገደለ በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ለሰሚ ግራ የሆነው ይህ ጭካኔ የተሞላበት ዜና እንደተሰማ አሁንም በመገናኛ ብዙሃኑ ላይ እንደወጣ ተመሳሳይ ድምጾች ወጡ፡፡ ‹ሊሰቀል ይገባል! › ተባለ፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ከአንድ ዓመት ከሶስት ወራት በኋላ የዕድሜ ልክ እስራት ፈርዶበት ወደ ማረሚያ ቤት ተላከ፡፡
*******
የቤተል ታሪክ
የ25 ዓመቷ ቤተል ሀዲስ ሀምሌ 3 ቀን 2003 ዓ.ም ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን የመጀመሪያ ዲግሪዋን የተቀበለች ወጣት ናት፡፡ ከልጅነቷ ጀምሮ ለትምህርቷ ያላትን ፍቅርና ትጋት የሚያውቁት ቤተሰቦቿ ዲግሪዋን ይዛ ወደ ምትኖርበት ወደ ምዕራብ ወለጋ መንዲዳ ስትመጣ በደስታ ነበር የተቀበሏት፡፡ በአካባቢው ልጃገረዶች እንደ አርአያ መታየት የጀመረችው ቤተል በተማረችው ትምህርት ራሷን ለመቻልና ሀገሯን ለማገልገል ወደ ሥራ ፍለጋ የተሰማራችው በማግስቱ ነበር፤ አዲስ አበባ መጥታ ሥራ ለማግኘት ቁርጥ ሀሳብ ላይ የደረሰችው ቤተል አዲስ ዓመትን ከቤተሰቦቿ ጋር አሳልፋ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ጀመረች፡፡
መስከረም 4 ቀን 2004 ዓ.ም ማለዳ ወደ አዲስ አበባ ታላቅ እህቷ ለምለም ሀዲስ ጋር ለመሄድ በማሰብ በዋዜማው ልብሶቿን ስታጣጥብ በትዳር አብረን ካልኖርን እያለ የሚያስቸግራት ግለሰብ ቤቷ ድረስ በመምጣት ‹‹ወደ አዲስ አበባ
መሄድ ብሎ ነገር የለም›› በማለት ዝቶባት ይሄዳል፡፡ ማታ በጠዋት ለመነሳት በጊዜ ወደ አልጋዋ ላይ የወጣችው ቤተል ከምሽቱ 3 ሰዓት ተኩል ገደማ ከእንቅልፏ የሚቀሰቅሳት ሰው መምጣቱና በር ላይ መቆሙ ይነገራታል፡፡ አይኗን እያሻሸች ወደ ደጅ ብቅ ያለችው ቤተል የጋብቻ ጥያቄውን በሀይል እንድትቀበል የሚጎተጉታት ሰው መሆኑን ብትረዳም ከደቂቃዎች በኋላ በእጁ የያዘውን ጄሪካን ሙሉ ሰልፈሪክ አሲድ መላ ሰውነቷ ላይ ይደፋብኛል ብላ አላሰበችም፡፡
******
የትእግስት ታሪክ
የ3 ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ ትእግስት መኮንን ከባለቤቷ ከአቶ ምናለ አቻሞ ጋር እንደ ማንኛውም ባልና ሚስት ተደጋጋሚ የቤት ውስጥ ፀብ ነበረባቸው፡፡ ሚያዝያ 30 ቀን 2003 ዓ.ም ግን ቤሰቦቿን ለመጠየቅ ወደ ቤታቸው ካመራችበት በስልክ ወደ ቤቷ እንድትመለስ ትጠራለች፡፡ አባት ሁሌም ቤት ውስጥ ሲመጣ ልጆቹን የማስቸገር ልማድ እንዳለው የምታውቀው ወ/ሮ ትእግስት ባሏ ወደ ቤት መምጣቱን ስትሰማ ልጆቿን እንዳይረብሽባት በሚል ወደ ቤቷ ትመለሳለች፡፡ ወትሮም የተለመደ የባልና ሚስት ፀብ ይኖራል ብላ የገመተችው ወ/ሮ ትእግስት ቤቷ ስትገባ የጠበቃት የባሏ ዱላ ነበር፡፡ ትእግስት ራሷን የመከላከል አቅሟን ካዳከመና ምንም ማድረግ እንደማትችል ካረጋገጠ በኋላ መላ ሰውነቷ ላይ አሲድ ደፍቶ ይሰወራል፡፡ በጉዳቱ መላ ሰውነቷ የተቃጠለባት ወ/ሮ ትዕግስት ለህክምና ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ብትወሰድም ጉዳቱ ከባድ ስለነበር ከቀናት የሕክምና እርዳታ በኋላ ሰኔ 1 ቀን 2003 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች፡፡
******
የጊዜሽ ወርቅ ታሪክ
ወ/ሮ ጊዜሽወርቅ ዓለሙ ከአቶ ጌቱ ቶሎሳ ጋር ወዳጅ ዘመድ በተገኘበት ተጋብተው ሲኖሩ ስድስት ልጆችን ወልደዋል፡፡ ግልፍተኛ ስሜት የሚታይበት አቶ ጌቱ ሁለተኛ ልጃቸውን ከእኔ እንዳልወለድሽው ‹‹በራዕይ ታይቶኛል በሚል ከባለቤቱ ጋር ነጋ ጠባ ጠብ ውስጥ ይገባል፡፡ የምታደርገው ነገር የጠፋት ወ/ሮ ጊዜሽወርቅ የዘር ማንነት ምርመራ (DNA) ልጃቸው እንዲመረመር ተደርጎ ልጃቸው እንደሆነ በህክምና ባለሙያ ይረጋገጣል፡፡
ነገር ግን ታይቶኛል ያለው ራዕይ ከቀድሞው እውነታ በቀር ሌላ ነገር እንዳይቀበል አድርጎታልና ፈፅሞ DNA

ምርመራውን መቀበል አልቻለም፡፡ ሰኔ 2 ቀን 2003 ዓ.ም አድብቶ ከሥራ ወደ ቤት ይመለሳል፡፡ የቤት ሰራተኛቸውን ወደ ሱቅ እቃ ገዝታ እንድትመጣ ከላካት በኋላ የ6 ልጆች አባት ያደረገችውን ሚስቱን በጥይት ደብድቦ በመግደል እጁን ለፖሊስ ይሰጣል፡፡ ፖሊስም ምርመራውን አጠናቆ ለአቃቤ ህግ አቅርቦ መዝገቡ የቀረበለት ከፍተኛ ፍ/ቤት የ13 ዓመት ፅኑ እስራት ፈረደበት፡፡
*****
የእመቤት ታሪክ
አቶ ከበደ ተሰማና ወ/ሮ እመቤት ጌታቸው ከሚያዚያ 1999 ዓ.ም ጀምሮ በትዳር ሲኖሩ እንደ ማንኛውም ባልና ሚስት ጊዜያዊ ግጭት በመሀከላቸው መፈጠሩ አልቀረም፡፡ መጋቢት 12 ቀን 2003 ዓ.ም በመሀከላቸው የተፈጠረው አለመግባባት ግን ከሀይለ ቃል አልፎ ወደ ላዱላ አመራ፡፡ ባል አቶ ከበደ ለዓመታት አብራው የኖረች ባለቤቱን ጭንቅላቷን በዱላ ደጋግሞ በመምታት የቀን ጎዶሎ እንዲሉ ፓራላይዝድ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ አቶ ከበደ በሚስቱ ላይ ባደረሰው ከባድ የአካል ጉዳትን የተመለከተው ፍ/ቤት በአቶ ከበደ ላይ የወሰነው የ4 ዓመት ከ6 ወር እስራት ብቻ ነው፡፡
*****
የሳራ ታሪክ
የሐረር ከተማ ነዋሪ ሣራ መሀመድ በንግድ ሥራ የምትተዳደር የ24 ዓመት ወጣት ናት፡፡ ሣራ ከተጠርጣሪ ባለቤቷ አቶ አብዱልናስር ዑመር ጋር ቀለበት አስራ በአንድ ጎጆ ውስጥ በጋራ መኖር ከመጀመራቸው በፊት ተጠርጣሪ ሌላ ሚስት ነበረችው፡፡ ከዚህችው ማለቱም 3 ልጆች የወለደ ሲሆን ሳራ ጋር ሆኖ ተቆራጭ ያደርግላቸዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ሐረር የሚሰራ ሚኒባስ ታክሲ ያለው ግለሰቡ ቀኑን የሚያሳልፈው መኪናውን ለሹፌር ሰጥቶ ቤት ውስጥ ነው፡፡
ሣራ መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም ከንግድ ስራዋ ላይ የምትጥለው እቁብ ደርሷት ስለነበር ለቀድሞ ባለቤቱና ለልጆቹ የ5 ሺህ ብር ልብሶች ገዝታ እንድትሰጥለት ይጠይቃታል፡፡ እሷም ገዝታ ሰጥታለች፤ ምን ያደርጋል ልብስ የገዛችበትን ብር ነገ ዛሬ እሰጥሻለሁ እያለ ካቆያት በኋላ መስከረም 6 ቀን 2004 ግን ቀደም ብሎ እቤት ተዘጋጅቶ በመጠበቅ ከሥራ ቶሎ ብላ እንድትወጣ በስልክ ይጠራታል፡፡ ሀገር አማን ነው ብላ ሥራዋን ቶሎ ጨርሳ ወደ ቤቷ የገባችው ሣራ ቀደም ሲል ግዥ ባላት ልብስና በገንዘቡ ዙሪያ ይጨቃጨቃሉ፡፡ ሁኔታው አላምር ያላት ሣራ ከሳሎን ወደ መኝታ ቤት ገብታ ስልክ ለታናሽ ወንድሟ ደውላ ‹‹የድረስልኝ›› መልእክቷን ታስተላልፋች፡፡ ይህንን የሰማው ተጠርጣሪው አስቀድሞ ባዘጋጀው ሽጉጥ ሁለቴ አከታትሎ ደረቷን፤ ሁለት ጊዜ ደግሞ ጡቷን ከዚያም በሁለት ጥይት እጆቿን በመምታት ገድሎ ቤት ውስጥ ያስቀመጠችውን የእቁብ ብር ይዞ ይሰወራል፡፡ ተጠርጣሪ በወቅቱ ኮንትራት ታክሲ ተከራይቶ ወደ አዋሳ ከተማ መሄዱ የታወቀ ሲሆን እስካሁን ድረስ በሀረር ፖሊሶች እጅ እንዳልገባ ታውቋል፡፡
*****
የዮዲት ታሪክ
ወ/ሮ ዮዲት አሰፋ ከተጠርጣሪ ባለቤቷ የፌደራል ፖሊስ ባልደረባ ኮማንደር ግርማ ሞገስ ጋር ትዳር የመሰረተችው በ1995 ዓ.ም ነው፡፡ በትዳራቸውም አንድ ሴት ልጅ ያፈሩ ሲሆን ነጋ ጠባ ጠብ ያልተለየው ትዳር በመሆኑ ገና በተጋቡ በስድስት ወራቸው ይጣሉ ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ ድግሪ ያገኘችው ዮዲት በትዳሯ ውስጥ ሁሌም ያለው ጭቅጭቅና አለመግባባት ሲያይል ቤቷን ትታ ከ4 ዓመት በፊት አባቷ ቤት ተቀምጣ ነበር፡፡ ጉዳዩ በሽማግሌዎች ተይዞ እንዲለያዩ ቢወሰንም በእሱ ጠያቂነት ታርቀው በአንድ ቤት መኖር ጀምረው ነበር፡፡ ደግሞ ፍቅራቸው ብዙም ሳይዘልቅ ወዲያው ተጣልተው በፍ/ቤት ፍቺ ይፈፅማሉ፡፡ በፍቺው መሠረት ለልጃቸው ተቆራጭ እያደረገ ዮዲት ማሳደግ ብትጀምርም በተደጋጋሚ እየመጣ ልጁን ልውሰደው እያለ ማስፈራራቱ አልቀረም፡፡ ዛቻና ማስፈራራቱ ደግሞ መንግስት ለደህንነት ብሎ ባስታጠቀው መሳሪያ የታጀበ ሲሆን በተደጋጋሚ ያደረገውን ዛቻ ‹‹ለህይወቴ ያሰጋኛል›› በማለት ዮዲት ለፖሊስ በማሳወቋ በፖሊስ ይያዛል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን በ1000 ብር ቅጣት ይለቀቃል፡፡ በዚህ ቂም የያዘው ተጠርጣሪው ሰኔ 18 ቀን 2003 ዓ.ም ሱማሌ ተራ ከሚገኘው የአባቷ ቤት የዘጠኝ ዓመት ልጇን ወደ ት/ቤት ለማድረስና በዚያው ወደ መ/ቤቷ ለመሄድ የወጣችውን ዮዲትን መከታተል ይጀምራል፡፡ ልጇን ት/ቤት ልካ ወደ መ/ቤቷ ለመሄድ ተክለሃይማኖት አደባባይ ጋር ታክሲ ቆማ ስትጠብቅ ተጠርጣሪው በያዘው የመንግስት መሳሪያ ተኩሶ ጭንቅላቷን በመምታት ገሏታል፡፡ ተጠርጣሪ ተይዞ ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን ለጥቅምት 23 ቀን 2004 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡
የሃናስ ታሪክ
ሃና ላላንጉ የ16 ዓመት ወጣትና የኢን ኢንተርናሽናል ት/ቤት ተማሪ ነች፡፡ ባለፈው ዓመት የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ሆና ት/ቤቱን የተቀላቀለችው ሃና ዘንድሮ የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን መከታተል ከጀመረች ገና አንድ ወር እንዳልሞላት ቤተሰቦቿ ይገልፃሉ፡፡ በሃና ላይ የደረሰውን ጥቃት መንስኤ በተለመከተ ሁለት አይነት መግለጫዎች ሲነገሩ ከርሟል፡፡ አንዳንዶች ‹ሃና የተደፈረችው ሺሻ ቤት ነው › ሲሉ ሌሎች ደግሞ በታክሲ በሀይል ታፍና ተወስዳ ነው ይላሉ፡፡
መስከረም 21 ቀን 2007 ዓ.ም በተለመደው አኳኋን ወደ ት/ቤት ያመራችው ሃና እስከ ቀኑ 9 ሰዓት ተኩል ድረስ እንደማንኛውም ተማሪ ትምህርቷን ስትከታተል ቆይታ ነው ወደቤቷ ለመሄድ የወጣችው፡፡ አየር ጤና አካባቢ ከሚገኘው ትምህርት ቤቷ ወደ ጦር ኋይሎች ለመጓዝ ታክሲ የተሳፈረችው ሃና ከፊት ለፊቷ መጥቶ የቆመው ሚኒባስ ታክስ ሾፌሩን ጨምሮ አምስት ሰዎችን ያሳፈረ ነበር፡፡ በታክሲ ውስጥ ስለተሳፈሩት ሰዎችም ምንም ግንዛቤ ያልነበራት ሃና መውረጃዋ ጦር ኋይሎች ጋር ስትደርስ ግን ‹ወራጅ አለ› ስትል የተሰጣት ምላሽ ጩቤ በማውጣት ማስፈራራት ነበር፡፡ በታክሲ ውስጥ የተሳፈሩት አምስት ጎረምሶች ሃናን አስፈራርተው ወደ አንደኛው ተሳፋሪ መኖሪያ ቤት በመውሰድ ለተከታታይ አምስት ቀናት እየተፈራረቁ እንደደፈሯት ነው ሪፖርተር ጋዜጣ የፖሊስ ሪፖርት ጠቅሶ የዘገበው፡፡
በዕለቱ ወደ ቤት በተለመደው ሰዓት ያለመምጣቷን የተረዱት ቤተሰቦቿ ጉዳዩን ያውቃሉ ወደተባሉ ጓደኞቿ ሄዱ፡፡ ማንም እናውቃለን ያለ አልነበረም፡፡ ጉዳዩን ለፖሊስ ካሳወቁ በኋላ ፖሊስ ትምህርት ቤቷ ድረስ በመሄድ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል የተባሉ ሶስት ተማሪዎችን የፍርድ ቤት ማዘዣ በማውጣት ወደ ጣቢያ በመውሰድ ምርምራ አደረገ፡፡በዚህ መሀል ልክ በአስራ አንደኛው ቀን ሃና ጦር ኋይሎች ሙሉ ወንጌል ቤተክርሲቲያን አካባቢ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባት ተጥላ መገኘቷን አባቷ አቶ ላላንጎ ይነገራሉ፡፡ቤተሰቦቿም ልጃቸውን ከወደቀችበት አንስተው መጀመሪያ ወደ አለርት ከዚያም ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል በመውስድ ህክምና እንድታገኝ፡፡
ሃና በቤት ውስጥ ታግታ ያ ሁሉ ግፍ ሲፈፀምባት ከደፋሪዎቹ በአንዱ ስልክ ለጓደኛዋ ደውላ ስለነበር ጓደኛዋ የሞባይል ስልክ ቁጥሩን ለፖሊስ በመስጠት የመጀመሪያ ተጠርጣሪና ግብረ አበሮቹ የሚኒ ባስ ሾፌሩን ጨምሮ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ይደረጋል፡፡ሃና በህክምና ላይ እያለችም ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን ሆስፒታል ድረስ በመውስድ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች መሀል አድርጎ በማሳየት እንድትለያቸው መደረጉን አባቷ አቶ ላላንጎ አየይሶ ለቁም ነገር መፅሔት በሰጡት ቃለ ምልልስ ገልፀዋል፡፡ ሃና የደረሰባት ጉዳት ግን ከባድ ስለነበር በ18ኛው ቀን ላይ ከዚህ ዓለም በሞት ትለያለች፡፡ ሀና ጥቃቱ ከተፈፀመባት በኃላ ቤተሰቦቿ በየሆስፒታሉ ቢንከራተቱም ህክምና ያገኘችው ከአራት ቀናት በኋላ መሆኑ ለሞቷ መፋጠን አስተዋፅኦ እንደነበረው አቶ ላላንጎ ተናግረዋል(ቃለ ምልልሱን በገፅ 8 ላይ ይመልከቱ)፡፡ መንግሰት አጥፊዎችን ህግ ፊት ለማቅረብ ሃላፊነት እንዳለበት ሁሉ የህክምና ተቋሞቻችንን የአገልግሎት አሰጣጥ ሊፈትሽ እንደሚገባ ሁኔታው ያመለክታል፡፡
አሁንም ጉዳዩ ወደ መገናኛ ብዙሃን ሲወጣ ድርጊቱን ለማውገዝ የዘገየ የለም፡፡ በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ የዚህን ድርጊት ፈፃሚዎች እንደተለመደው ‹አውሬዎች› መባሉ አልቀረም፡፡ በተለመደው ሁኔታም በራስ ሆቴል ሃናን መነሻ ያደረገ አንድ የምክክር ስብሰባ ባለፈው ሰኞ ተካሂዷል፡፡ በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይም በተለይም ህዳር 13 ቀን 2007 ዓ.ም ሃና የምትታሰብት ቀን እንዲሆንና ‹ፍትሕ ለሃና› በሚል መርህ የፀረ ሴት ልጅ ጥቃት ዘመቻ በአንዳንድ ተቆርቋሪዎች አስተባባሪነት ተካሂዷል፡፡
በሃና ላይ ያንን የመሰለ ግፍ የፈፀሙት ተጠርጣሪዎች ከሳምንት በፊት ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅትም ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሰው በፍርድ ቤቱ ደጃፍ ተገኝቶ ቁጣውን በወጣቶቹ ላይ ገልፆአል፡፡ፖሊስ ምርምራዬን አላጠናቀቅሁም በማለቱም ተጨማሪ የ10 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡
ከቀደሙት ጥቃቶችና ከልምዳችን ተነስተን ነገሩን ስንፈትሽ የሃና ጉዳይም ከቀናት በኋላ ይረሳና መደበኛው ህይወት ይቀጥላል፡፡ የሴት ልጅ ጥቃት ጉዳይ በመገናኛ ብዘሃንም ሆነ በማህበራዊ ድረ ገጾች

ላይ ትኩረት ተሠጥቶት የሚዘገበው ጥቃቶች ሲደርሱ ነው፡፡ ከእንደዚህ አይነት ዘግናኝ ጥቃቶች በኋላ ለድርጊቱ መፈፀም መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ ስለሚባሉ ስነ ልቦናዊም ሆነ ማህበራዊ ችግሮች መድረክ ተከፍቶ ወጣቶች ከእንደዚህ አይነት የሀይል ተግባራት ራሳቸውን እንዴት ገትተው በውይይትና በንግግር መፍታት እንደሚችሉ ውይይት አይደረግም፡፡
በተለይም አብዛኛዎቹ ጥቃቶች የሚፈፀሙት በፍቅር ግንኙነትና በትዳር ውስጥ መሆኑን ስንመለከት በዚህ ዙሪያ ሰፊ የቤት ስራ ይጠብቀናል፡፡ እንደ መንግስትም እንደማህበረሰብም በፍቅር ግንኙነት መሀል የሚኖሩ አለመግባባቶች እንዴት እንደሚፈቱ ወይም እንዴት መፈታት እንዳለባቸው በማህበረሰብ ሳይንስና በሥነ ልቦና ባለሙያዎች የታገዘ ተደጋጋሚ የውይይት መድረክ እንደሚያስፈልግ ቁም ነገር መፅሔት በተደጋጋሚ አሳስባለች፡፡ በተለይም የፍቅር ግንኙነት የሚጠነሰሰውና የሚያድገው ከትምህርት ቤት ጀምሮ በመሆኑ ተማሪዎች ከዕድሜ እኩዮቻቸውና ከከንፈር ወዳጆቻቸው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እንዴት ሰላማዊና ጤናማ መሆን እንዳለበት ስልጠና መሰጠት እንዳለበት እናምናለን፡፡
የሴቶች ማህበራት ሚና
የሃና ጉዳይ ሰሞኑን መነጋገሪያ ከሆነ በኋላ በየማህበራዊ ድረ ገፆችም ሆነ በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደመጠው ነገር በድርጊቱ ፈፃሚዎች ላይ መወሰድ ስላለበት የፍርድ ሂደት ነው፡፡ መንግስት አጥፊዎችን የሚቀጣበት የተፃፈ ህግ ያለው በመሆኑ ከፍርድ በፊት አስተያየት መስጠት ጣልቃ እንደመግባት ሊያስቆጥር ይችላል፡፡ ነገር ግን የዚህ አይነት አስከፊ ጥቃቶች ዳግመኛ በሴት እህቶቻችን፤ልጆቻችንና እናቶቻችን ላይ እንዳይደገም ሰፊና መሰረታዊ ሊባል የሚችል ትምህርት መስጠት መጀመር አለብን፡፡
የኢትጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የነበረችው የአበራሽ ጥቃት አደባባይ በወጣበት ወቅት በሸራተን አዲስ ሆቴል በሴቶች ማህበራት ቅንጅት አንድ ህዝባዊ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚያ ስበሰባ ላይ የአቋም መግለጫ ወጥቶ የነበረ ሲሆን በዛ የአቋም መግለጫ ላይ ‹መንግስት ለሴት የጥቃት ሰብሰባዎች ፈንድ እንዲያቋቁምና እንዲረዱ ሊደረግ ይገባል› የሚል ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጥያቄ ቀርቧል፡፡
ቁም ነገር መፅሄት በወቅቱ ይህንን ሀሳብ ኮንናለች፡፡ የሴቶች ጥቃት ቋሚና በየጊዜው የሚከሰት እንደሆነ በማሰብ ፈንድ ይቋቋም ማለት የጥቃቱን ቀጣይነት አምኖ እንደመቀበል ይቆጠራል፡፡ የሴቶች ጥቃት በትምህርትና በግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች የሚቀየር መሆኑን መርሳት ተገቢ አይደለም፡፡ መንግስት ለተጠቂ ሴቶች እንዲመድብ የሚጠየቀውን ፈንድ ለግንዛቤ ማስጨበጫ ቢውል በቀጣይነት የሴት ተጠቂዎች ቁጥር አይኖርም ወይም በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል፡፡ይህ ሃሳብ ዓመታትን ቆጥሮ ባለፈው ሰኞ በራስ ሆቴል ለሃና በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ድጋሚ የአቋም መግለጫ ሆኖ ወጥቷል፡፡ ጥያቄውንም ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንደሚላክም ተጠቁሟል፡፡አቶ ኃ/ማርያም ጥያቄውን ከአቶ መለስ በተለየ መንገድ ይመለከቱታል ወይ የሚለውን ጥያቄ ወደ ጎን ትተን የሴቶች ማህበራት አሁንም በአስተሳሰብ ለውጥ ላይ አተኩረው መስራታቸውን እንደዋነኛ ግብ አድርገው ሊወስዱት እንደሚገባ የዘነጉት ይመስላልና ሁኔታውን ከዚህ አንፃር መመልከት ያስፈልጋል እንላለን፡፡
የመገናኛ ብዙሃን ሚና
መገናኛ ብዙሃን ቋሚና ተከታታይ ስራን በሴቶች ና በወንዶች የፍቅር ግንኙነት ዙሪያ ከመስራት ይልቅ ጥቃት በደረሰ ጊዜ ለአየር ሰዓት መሙያ ብቻ የሚጠቀሙበት እየሆነ መጥቷል፡፡ ሰሞኑን ከሃና የሃይል ጥቃት ጋር በተያያዘም የታየው ነገር ተመሳሳይ ነው፡፡የሃና አባት አቶ ላላንጎም አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በልጃችን ሞት የደረሰብን ሀዘን ገና ሳያጠግግ እኛ ያላልነውን ነገር ለህዝብ እያስተላለፉ ሌላ መከራ ውስጥ ከተውናል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
የሴት ልጅ ጥቃት የአንድ ወቅት ዜና ከመሆን ባለፈ መልኩ መሰረታዊ ችግሩ ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞች ሲቀርቡ አይታይም፡፡ከዚህ አንፃር ለአውሮፖ እግር ኳስ ከተመደበው አየር ጊዜ ሲሶውን እንኳ በመመደብ ስለ ጤናማ የፍቅር ግንኙነት፤ ስለ ጤናማ ቤተሰብ ምስረታ፤ አለመግባባትን በፍቅረኞች መሀል እንዴት መፍታት እንደሚቻል ወዘተ ማቅረብ የነገውን ትውልድ መታደግ እንደሆነ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡
ህብረተሰቡም በየአካባቢው የሚመለከተውን የሴት ልጅ ጥቃት በምን ያገባኛል ስሜት ሳይመለከት በጋራና በተናጠል መዋጋት አለበት፡፡ ዛሬ መንገድ ላይ አንዲት ሴትን ሲጎትት የምንመለከተው ጎረምሳን አይተን እንዳለየ ፊታችንን ካዞርን ነገ የምትጎተተው የራሳችን ልጅ ወይም እህት እንደሆነች መዘንጋት አይገባም፡፡ ሃናን እየጎተቱ ወደ ቤት ሲያስገቧትና እየተፈራረቁ ሲደፍሯት አይተው እንዳላየ የሆኑ ጎረቤቶች ስለመኖራቸው አባቷ አቶ ላላንጎ እንባ እየተናነቃቸው የተናገሩትን መዘንጋት አይገባም፡፡ ይህ እስካልተጀመረ ጊዜ ድረስ ግን ሌላ ሄርሜላ፤ ሌላ ካሚላት፤ ሌላ አበራሽ፤ሌላ ፍሬህይወትና ሌላ ሃናን ማጣታችን አይቀርም…

Receive Ethiopian News and Videos by email. Sign up for Email alerts ትኩስ እና ሰበር ዜና፣ በብዛት የታዩ ቪድዮዎችን፣ ድራማዎችን፣ሙዚቃዎችን፣ ጠቃሚ ምክሮችን እና አስገራሚ ታሪኮችን በኢሜል አድራሻዎ እንልካለን። ኢሜሎን ያስመዘግቡ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.