ኢትዮጵያ ለዘላለም እንድትኖር! (በተክሉ አባተ)

በተክሉ አባተ (ዶ/ር)

መግቢያ ኢትዮጵያዊያን እጅግ የተቀናጀ፣ ያመረረና ቀጣይነትም ያለው ተቃውሞ በመንግስት ላይ እያካሄዱ ይገኛሉ። ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ እንደ ሰደድ እሳት ተቀጣጥሏል። መሠረታዊ የሆኑ የመብትና የነጻነት እንዲሁም የፍትህ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። ይህንም ተከትሎ ቁጥራቸው በግልጽ ያልታወቀ ኢትዮጵያውያኖች በመንግስት ታጣቂዎች ተገለዋል፣ ቆስለዋል፣ ታስረዋል። ይህም ሁሉ መከራ ወርዶ ሕዝቡ ለበለጠ ትግል ተነሳስቷል። እስካሁን የተከናወኑት ክስተቶች እንዲሁም ሕዝቡ የሚያስተጋባቸው መፈክሮች በግልጽ እንደሚያሳዩት መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከምን ጊዜውም በላይ ተቀባይነትን አጥቷል። የጉልበት አገዛዝ ጊዜው አልፎበታል። ይህንም መንግስት ራሱ በደንብ የተገነዘበ ይመስላል። የፖለቲካ እስረኞች መፈታትም የዚሁ አካል እንደሆነ መገመት የሚያሻማ አይመስልም። ይሁንና ሕዝባዊ ትግሉ የመጨረሻ ዓላማውን እስኪመታ ድረስ ተቀናጅቶ መቀጠል ይኖርበታል።

የትግሉ ዓላማና መርሆች

መንግስት እውነተኛ ለውጥ እንዲያመጣ 27 ዓመታት ያህል ተጠብቋል። ሆኖም ችግሮች እየተባባሱ እንጂ እየቀነሱ አልሄዱም። ከዚህ በላይ መንግስት ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠው ዘንድ አግባብ እንዳልሆነ ሕዝቡ እየተናገረ ነው። እንዲህ ከሆነ በመካሄድ ላይ ያለው የሕዝብ ትግል ዓላማው ምን መሆን ይኖርበታል? ውድ ኢትዮጵያዊያን መስዋዕት የሆኑለት ዓላማ የላቀ ነው። አጠቃላይ መሠረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ በግልጽ ታይቷል።

ሕዝቡ እያስተጋባው ካለው መፈክር በመነሳት ትግሉ መቆም ያለበት ፍጹም ዘለቄታ ያለው ፍትህና ነጻነት ሲረጋገጥ ብቻ ነው። ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያለምንም መሸማቀቅ አስበው ተናግረው ሠርተው የሚኖሩባት የሚኮሩባት አገር ይናፍቃሉ። ማንኛውም ዜጋና የመንግስት አካል እኩል ከሕግ በታች የሚሆንባት አገር ትመሰረታለች። ይህን መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ግን ትግሉ በመርሆች ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት። ለምሳሌ ያህል ቀጥለው የተዘረዘሩትን መርሆች ግምት ውስጥ ያስገባ ትግል በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ያስፈልጋል።

• የትግሉ ዓላማ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ዘላቂ ፍትህና ነጻነት ባጠቃላይም የሕዝብ መስተዳድር ለማምጣት እንጅ የመንግስት ባለሥልጣናትንና አጋሮቻቸውን ለማሳደድ አይደለም። እንዲያውም የሚተባበሩ ከሆነ የመንግስት ባለሥልጣናትና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ደጋፊዎቻቸው የትግሉ ውጤት ተጠቃሚ ይሆናሉ። ዳሩ ግን ግፍ የፈጸሙ ታላላቅ ባለሥልጣናት ሕዝብን ከልብ በመነጨ ይቅርታ ጠይቀው ቀሪ ዘመናቸውን በንስሃ ሊያሳልፉ ይገባል። ተመልሰው ወደሥልጣን እንዳይመጡም ማእቀብ ቢደረግባቸው ፍትህ እንጅ ማግለል አይሆንም
• ኢትዮጵያዊያንን ለማሸማቀቅና ለማፈን የወጡ ሕጎች ተቀባይነት የላቸውም
• ትግሉ የሕዝብ ስለሆነ በአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሊመራ አይችልም። ይልቁንስ ሁሉንም የኀብረተሰብ ክፍል የወከለ ታማኝና አስተዋይ ግለሰቦችን ያካተተ ልዩ ብሄራዊ ግብረ ሓይል ይመሰረታል
• በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የትግሉ አካል መሆን አለበት
• በትግሉ ወቅት የመንግስትም ሆነ የመንግስት ደጋፊ ግለሰብ ንብረት ከሚወድም ይልቅ ለትግሉ መፋፋም ሊያግዝ ይችላል
• ትግሉን ለማኮላሸት የሚጥሩ ካሉ በምክር እንዲመለሱ ይደረጋል። ይህም ካልሆነ ከማንኛውም የማኅበረሰብ ሱታፌዎች ይገለላሉ
• የሃይማኖት ተቋማት በአንድም በሌላም መንገድ ትግሉን ከማቀዝቀዝ መታቀብ አለባቸው
• ትግሉ ፍጹም ሰላማዊ ነው። ዳሩ ግን መንግስት እርምጃ የሚወስድ ከሆነ ማናቸውም አዋጭ የትግል ስልቶች ሥራ ላይ መዋል ይችላሉ
• ሕዝባዊ ትግሉን ለሚያስተባብሩ ወገኖች ሕዝቡ የደኀንነት ጥበቃ ያደርጋል
• በትግሉ ወቅት የወደቁና የሚወድቁ ውድ ኢትዮጵያውያን የሰማዕትነት ክብር ይሰጣቸዋል
• ትግሉ የኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን በመሆኑ የምዕራቡ ዓለም አገሮች ላይ ጥገኛ አይሆንም

ባለድርሻ አካላት

ከላይ የተዘረዘሩትን ዓላማዎች በተሳካ ሁኔታ ለመምታት የተለያዩ አካላት ልዩ ሱታፌ ማድረግ አለባቸው። በታሪካችን ከዚህ በፊት የተካሄዱት የለውጥ ሙከራዎች ዘለቄታዊነት ያለው ውጤት ያላመጡት በብዙ ምክንያቶች የተነሳ ቢሆንም ዋናው ግን ባለድርሻ አካላት እንደሚገባቸው ባለመሥራታቸው ነው። ከዚህ በፊት የለውጡ መሪ አንድ ፓርቲ ወይም ወታደሩ ስለነበር የፈለግነውን ውጤት አላገኘንም። ደም መላሽ መንግስታትን ስናስተናግድ ኖረናል። ከዚህ ተመሳሳይ አዙሪት ለመዳንና ኢትዮጵያውያን ወደማያዳግም ዘርፈ ብዙ ለውጥ እንዲሸጋገሩ ከተፈለገ ትግሉ ሁሉን አሳታፊና አቃፊ መሆን ያስፈልገዋል። በመሆኑም መንግስትና ደጋፊዎቹ፣ ትግሉን በማካሄድ ላይ ያለው ሰፊው ሕዝብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማትና የመገናኛ ብዙኅን ልዩና ላቅ ያለ አስተዋጽዖ ማድረግ ያስፈልጋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ከልምዳቸው በመነሳት ለትግሉ የሚጠቅሙ ስልቶችንና ግብአቶችን ሊያቀርቡ ይችላሉ። ዳሩ ግን ትግሉን ለሥልጣን ሲሉ ብቻ ለመቆጣጠር የሚሞክሩ እንዳይኖሩ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የሃይማኖት ተቋማት ለእውነት መቆምና አማኞቻቸውም መንግስትን የመቃወም መብት እንዳላቸው መቀበል አለባቸው። ኢትዮጵያም በውጭውም ዓለማት ያሉ የመገናኛ ብዙኅንም እየሆነ ያለውን እውነታ በወቅቱ መዘገብ እንዲሁም ሕዝብን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ዝግጅቶችን ከማቅረብ መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል። እንዲያውም አንድነትን፣ ፍትህንና ነጻነትን የሚሰብኩ ሥራዎችን ማቅረብ አለባቸው። ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የመንግስትና የደጋፊዎቹ ድርሻንና አስፈላጊነት ሰፋ አድርጌ ለማሳየት ልሞክር።

መንግስትና ደጋፊዎቹ

ምንም እንኳን በሕግ እንደሚታወቀው መንግስትና ገዥ ፓርቲ የተለያዩ ቢሆኑም በነባራዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ሁለቱ አንድ ናቸው። ኢሕአዴግ ፓርቲም መንግስትም ነው። ኢሕአዴግ የሆነ ሁሉ ግን እኩል መብትና አቅም የለውም። ሕወሓት የመንግስት መሥራች፣ ሿሚና ሻሪም ነው። ሌሎች ኦሮሞውን፣ አማራውንና ደቡቡን እንወክላለን የሚሉ ፓርቲዎች የሕወሓት ተባባሪዎች ናቸው ቢባል አይጋነንም። የሆነው ሆኖ መንግስት የለውጡ አካል መሆን አለበት ስል ሕወሓትን፣ ብአዴንንም፣ ኦሕዴድንም እንዲሁም ደሕዴድንም ይመለከታል። ይህ መንግስት የሚቆጣጠራቸውን የስለላ ተቋሙን ወታደሩን ፖሊሱንና ሚሊሻውንም ይመለከታል። የመንግስት ደጋፊዎች ስል ደግሞ በቢዝነስም ይሁን በርዕዮተ ዓለም መንግስትን የሚደግፉና ከሱም ጋር በሽርክና የሚሠሩትን ኢትዮጵያ ውስጥና በውጭው ዓለም ያሉትን ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ያካትታል።

ከዚህ በፊት የተካሄዱት አብዮቶች በጥሎ ማለፍና በጥቃትና በበቀል ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ደርግ የጃንሆይን መንግስት የለውጡ አካል ለማድረግ ጥቂት ሞከረና ወደ እብሪት ተሸጋገረ። በደመ ነፍስ ንጹሐን ኢትዮጵያውያንን ሳይቀር በጅምላ ረሸነ። የደርግን ጥሩነት ለማሳየት የጃንሆይ የነበሩትን ሁሉንም ሥራዎች ማውገዝን ተያያዘው። በዚያም የተነሳ ቀላል የማይባል የሕዝብ ድጋፍ አጣ። አይወድቁ አወዳደቅ ወደቀ። ያሁኑ መንግስትም 27 ዓመት ሙሉ ደርግን በማውገዝ የራሱን ንጽህናና ልማታዊነት ለማሳየት ይጥራል። ከዚያም አልፎ ስህተቱን የሚነግሩትን ወገኖች ነፍጠኛና ያለፈው ሥርዓት ናፋቂ በማለት ያሸማቅቃል። ባጠቃላይ በዚህ መንግስት ዐይን ሲታይ የደርግ የነበረው ሁሉና ስለኢትዮጵያ የሚናገር የተወገዘ ነው። የደርግ ደጋፊዎች የነበሩም እንደ ዜጋ አይቆጠሩም። ይህ አስተሳሰብ ግን ለመንግስት ኪሳራ እንጅ ትርፍ አላስገኘለትም።

ያሁኑ ሕዝባዊ ትግል ግን ፍጹም የተለየ መሆን አለበት። ዘላቂ ሰላም፣ እውነተኛ ዴሞክራሲና ነጻነት ለማምጣት ሰላም፣ እውነተኛ ዴሞክራሲና ነጻነት እንዳይኖር የጣረውና የሚጥረው መንግስትና ደጋፊዎቹም መካተት አለባቸው። ይህም የታሰበው ስለአራት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው። አንደኛ በመንግስት መዋቅርና በሽርክና የሚሠሩ፣ በሀሳብና በሞራልም የሚደግፉ ምናልባትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ። እነሱም የለውጡ አካል ቢሆኑ ትግሉ ዓላማውን በቶሎ ያሳካል። ሁለተኛ መንግስትና ደጋፊዎቹም ቢሆኑ እውነተኛ ነጻነት ፈላጊዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሦስተኛ በብድርና በእርዳታ እስከ አፍንጫው ድረስ የታጠቀውን መንግስትን የለውጡ አካል ማድረግ የይቅርታና የርህራሄ መንፈስን ስለሚያንጸባርቅ ትግሉ ሰላማዊ ይሆናል። አላስፈላጊ የሕይወት መስዋዕትነትንና የንብረት ውድመትን ያስቀራል። አራተኛ መንግስትንና ደጋፊዎችን የለውጡ አካል ማድረግ ለነገው ትውልድ የማይረሳ ትምህርትን ይሰጣል። ለውጥ የሚመጣው በማጥቃትና በማግለል ሳይሆን በዳይንም ተበዳይንም በማሳተፍ እንደሆነ ትውልዱ ይረዳል። እንደ ባህልም ይይዘዋል።

ዳሩ ግን መንግስትና ደጋፊዎቹ የለወጡ አካል ሊሆኑ የሚችሉት ለሥልጣን ከመስገብገብና ከስሜት ወጥተው ለምስኪኑ ዜጋ ይልቁንስ ለራሳቸውም ማሰብ ሲጀምሩ ነው። የተገነቡ ሕንፃዎችንና መንገዶችን እንዲሁም የተመሰረቱ ብሄር ተኮር ፓርቲዎችን ብቻ እያነሳሱ መመፃደቅ የትም እንደማያደርስ መታወቅ ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ያለባትን የገንዘብ እዳ፣ የህዝቡን ተጨባጭ የዕለት ተዕለት ሕይወት፣ የእስር ቤቶችንና የታሳሪዎችን ብዛት፣ የተሰደዱትንና በሂደቱም የሞቱትን ወዘተ በማስታወስ የማዘንና የመጸጸት

ከዚያም ለውጥ ለማምጣት የማመን አዝማሚያ መታየት አለበት። ጊዜው የፈለጉትን ገሎና ዘርፎ ውጭ አገር በሰላም መኖር የሚቻልበት እንዳልሆነ ማሰብም ይጠቅማል። መንግስትና ደጋፊዎቹ በዚህ ወሳኝ የለውጥ ሂደት ቢሳተፉ ታሪክና ልጆቻቸው በበጎ እንደሚያነሷቸው እስካሁንም ለተሠሩ ስህተቶችና ግፎች ማርከሻ ወይም ንስሃ እንደሚሆን ማወቅ አለባቸው። ዛሬና ነገ እውነተኛና ዘላቂ ለውጥ ለማድረግ ያሰበን አካል ሕዝቡ በትናንት በደሉ ሊፈልገው አይችልምና! ስለዚህ ባለቀ ሰዓት መንግስት የማይረሳ እንቁ ታሪክ የመሥራት እድሉ አለው።

መንግስት ተሳትፎውን በልዩ ልዩ መንገዶች መግለጽ መጀመር ይችላል። ለውጡን የሚያስተባብር ልዩ ብሄራዊ ግብረ ኃይል ቶሎ እንዲቋቋም መፍቀድ በሱም መሳተፍ፣ ለሰልፍ የሚወጡት ላይ ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰድ፣ ለችግሮችም መፍትሔ እንደሚሰጥ ማሳወቅ፣ በትግሉ ምክንያት የታሰሩትን ያለቅድመ ሁኔታ መፍታት፣ የመንግስት መገናኛ ብዙኅን ከአጉል ቀስቃሽ ፕሮፓጋንዳ እንዲታቀቡ ማድረግ፣ ባጠቃላይ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የሕግ ከለላ ማድረግ የሚቋቋመው ግብረ ኃይል ዝግጅት ሲጨርስ ሥልጣንን በሰላም ማስረከብ ወዘተ ሊሆን ይችላል።

ልዩ ብሄራዊ ግብረ ኃይል

ከላይ እንደተገለጸው አስተማማኝና ዘለቄታ ያለው ለውጥ ለማምጣት መንግስት አቅምም ፍላጎትም እንዳለው ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ አላሳየም። አሁን ተነስቶ ይህን ለማድረግ ቃል ቢገባ እንኳን ማንም አይቀበለውም። መንግስት ከኦርቶዶክሱ፣ ከሙስሊሙ፣ ከአማራው፣ ከኦሮሞው፣ ከጋምቤላው፣ ከአፋሩ፣ ከሶማሌው፣ ከጉራጌው፣ ወዘተ በደንብ ተለያይቷል። በአንጻሩም ይህን ትግል በተሳካ ሁኔታ ሊመራ የሚችል የፖለቲካ ፓርቲ እንዳይኖር ላለፉት በርካታ ዓመታት በዘመቻ ተሠርቷል። ትግሉን ሕዝቡ እንደጀመረ ሕዝቡ ይጨርስ ማለት ደግሞ አይቻልም። ሕዝቡ የትግሉ ባለቤትና ኦዲተር ሆኖ አሥፈጻሚ አካል ወይም ልዩ ብሄራዊ ኮሚቴ ያስፈልገዋል። ይህን ልዩ አካል መምረጥ ያለበት ሕዝቡ ራሱ ነው። ኮሚቴው ለምንና እንዴት መመረጥ እንዳለበት ለመነሻ ያህል ጥቂት ነጥቦችን ላንሳ። • የዚህ አካል ዋና ዓላማ ፍጹም ግለሰባዊና ቡድናዊ ነጻነት፣ ፍትህና ዴሞክራሲ የሚገዛው መንግስት ለመመስረት የሚያስችሉ ጉዳዮችን መለየትና ተግባራዊ ማድረግ ነው

• ሥራውንም ለዚሁ ተብሎ በሚዘጋጀው መንገድ ለሕዝብ በየጊዜው ያሳውቃል
• ዝርዝር የሥራውን ጠባይና አይነት ከባለቤቱ ከሕዝቡ ያገኛል
• አሥፈጻሚው አካል ወይም ልዩ ኮሚቴው በብሄራዊ ደረጃ መዋቀር አለበት። ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ግለሰቦች መካተት ይኖርባቸዋል። ዳሩ ግን በዘር ላይ የተመሰረተ ውክልና እንዳይኖር ጥንቃቄ ያስፈልገዋል
• የሚመረጡት ግለሰቦች ከሙስና፣ ከዘረኝነትና ከድንቁርናና ነጻ የሆኑና የሥልጣን ጥም ያላገኛቸው፣ ለእድገትና ለለውጥ ቀና አስተሳሰብ ያላቸው፣ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያፈቅሩ እንዲሁም ጥበበኞችና ተናግሮ አሳማኞች መሆን አለባቸው
• የሚመረጡት ግለሰቦች ኢትዮጵያ ውስጥ በውጭውም ዓለም ከሚኖሩት መሆን ይገባዋል
• የሚመረጡት ግለሰቦች በሰላማዊ መንገድና በትጥቅ ትግልም ከሚታገሉ ድርጅቶችም መመረጥ አለባቸው። በትጥቅ ትግል ካሉት ድርጅቶች ውክልና እንደተገኘ የትጥቅ ትግላቸውን ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ለጊዜው ማቆም ያስፈልጋል

ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት አንዱ የሌላውን ጭራ ወይም ጅራት ይዟል። አንዱ ቀድሞ ቢለቅ በሌላው ሊነከስ ይችላል። ያለው አማራጭ ሁለቱም አካላት እጆቻቸውን ከጨበጧቸው ጭራዎች ላይ በአንድ ጊዜ በማንሳት እጅ ለእጅ ለመያያዝ ፊታቸውን ማዞር ነው። እጅ ለእጅ ከተያያዙ መተያየት ይመጣል። ከተያዩ ደግሞ መነጋገር ይችላሉ። ከተነጋገሩ ደግሞ ወይ ወደጭራ መጨበጥ ለመመለስ ወይም ደግሞ ለመተቃቀፍ አለበለዚያም በመሃል ገላጋይ ለማስገባት ይችላሉ። በዚህ ጽሑፍ የተነሳው ዋና ሀሳብ የሚያተኩረው ጭራን ለቆ እጅ ለእጅ ለመጨባበጥ ዝግጅት ማድረግ ላይ ነው። ዝግጅቱ እየተካሄደ ወይም ካለቀ በኋላ ግን መጨባበጥ ከዚያም መተቃቀፍ ሊመጣ ይችላል። ካልሆነም አንደኛው ወገን ድል ይነሳል። መቼም መንግስት እንጅ ሕዝብ አይሸነፍ! እኔ የምመኘው ፍላጎትና የምር ለውጥ እስካለ ድረስ ትግሉ ማንንም ሳያገልና ሳይበላ በንጽህና ይካሄድ ዘንድ ነው! እንዲህ ከሆነ የኢትዮጵያን ዘላለማዊነትና ነጻነት እናረጋግጣለን ለመጪ ትውልዶችም ኩራትና መሠረት እንሆናቸዋለን! ይህን አይነት ለውጥ ለማምጣት ግን ከፍተኛ የሞራል ልዕልናና ዲሲፕሊን ከሁሉም ወገን ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

ገንቢ አስተያየት ካለዎት በ teklu.abate@gmail.com ይላኩልኝ!
ይህ ጽሑፍ በ2016 ታትሞ ነበር። የወቅቱን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት መጠነኛ መሻሻል ተደርጎለት እንደገና ወጥቷል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.